ስዊድንን ጎረቤቶቿ ለምን ይሆን ያገለሏት?

የፎቶው ባለመብት, AFP
ስዊድን በኮቪድ-19 ላይ የተከተለችውን ፍልስፍና በዓለም ላይ የትኛውም አገር አልተከተለውም። ይህ የቫይረሱ የመጨረሻው ምዕራፍ ከሆነ እውነትም ስዊድን ፍልስፍናዋ ዋጋ ሳያስከፍላት አልቀረም።
ለምሳሌ ዴንማርክና ኖርዌይ ውድ ጎረቤቶቿ ናቸው። የብልጽግና ቁንጮ ተደርገው የሚታዩት እነዚህ ሦስቱ አገሮች እንደ ወንድምና እህት ያህል ይቀራረባሉ ማለት ይቻላል። በብዙ መንገድ መመሳሰል አላቸው።
በኮሮና ተህዋስ ዙርያ የተከተሉት መመርያ ግን ለየቅል ነው።
የወረርሽኙን መከሰት ተከትሎ ስዊድን እጅግ ልል የሆነ መመርያን ነው ለሕዝቧ ያስተላለፈችው።
ጎረቤቶቿ ወለም ዘለም የማይባልበትን ሁሉን አቀፍ የጉዞና የእንቅስቃሴ እቀባ ሲያደርጉ ስዊድን ግን "አዋቂ አይመከርም፤ አስፈላጊውን ጥንቃቄ እያደረጋችሁ ኑራችሁን ቀጥሉ" የሚል መልዕክት ነው ያስተላለፈችው ለሕዝቧ።
"ከዚህ ሌላ ትንሽም ቢሆን ሕመም ከተሰማችሁ ከቤት አትውጡ" ብላለች ዜጎቿን። ታመው ቤት የዋሉ ዜጎች ደመወዛቸው ሳይቀነስ ይከፈላቸዋል።
በስዊድን ከተሞች ለሚዘዋወር በዓለም ላይ እጅግ አደገኛ ወረርሸኝ ስለመከሰቱ እምብዛምም ላይሰማው ይችላል። የሰዎች እንቅስቃሴ ከወትሮው ብዙም አልተለየም ነበር።
ካፌዎችና ሬስቶራንቶች ሥራቸውን ቀጥለዋል። ሰዎች ርቀታቸውን ጠብቀው ይዝናናሉ። የሕዝብ ትራንስፖርት አልተቋረጠም። ይህ ሁኔታ ስዊድንን ጎድቷታል የሚሉ አሉ።
እነ ዴንማርክና ኖርዌይ ታዲያ ከሰሞኑ ድንበራቸውን ሲከፍቱ፤ ጎረቤታቸው ስዊድንን ገሸሽ ያደረጉበት አንዱ ምክንያትም ይኸው ነው።
እርግጥ ነው ስዊድን ከመጀመርያውም ቢሆን ከቤት እንዳትወጡ ብላ እንደ ሌሎች የአውሮፓ አገራት ዜጎቿን አላስጨነቀችም።
በጣሊያንና ስፔን ሰዎች እንደ ቅጠል ሲረግፉ ስዊድኖች በየካፌው ሰብሰብ ብለው ድራፍታቸውን ይጨልጡ ነበር።
ዶ/ር አንደርስ ተግኔል ከዚህ ልል ፍልስፍና ጀርባ ያለ ሰው ነው። በድርጊቱ መጠነኛ ጸጸት የተሰማው ይመስላል። ግን ደግሞ ተሳስተን ነበር ለማለትም ጊዜ ገና እንደሆነ ይናገራል።

"ከዚህ ልል የመከላከል ፍልስፍናችን የተነሳ ከፍ ያለ ቁጥር ያለው ዜጋ ሳይሞትብን አልቀረም" ብሏል ትናንት ከስዊድን ራዲዮ ጋር በነበረው ቆይታ።
ስዊድን እስከ ትናንት ድረስ 40 ሺህ 800 ሰዎች በኮሮና ተህዋስ ሲያዙባት፣ 4 ሺህ 542 ሰዎች ደግሞ ሞተውባታል። ይህ ከነጣሊያን፣ ስፔንና ዩናይትድ ኪንግደም ጋር ሲነጻጸር ትንሽ ቢመስልም ለስካንዲኒቪያን አገሮች ግን አስደንጋጭ ቁጥር ነው።
እነ ዴንማርክ፣ ፊንላንድና ኖርዌይ ጠበቅ ያለ መመርያን ለሕዝባቸው በማስተላለፋቸው ከዚህ በጣም ያነሰ የሟች ቁጥር ነው ያስመዘገቡት።
ለምሳሌ ዴንማርክ 580 ዜጎች ብቻ ናቸው የሞቱባት፤ ኖርዌይ በበኩሏ 237 ሰዎች ሞተውባታል። ፊንላንድ 321 ዜጎቿን አጥታለች።
10 ሚሊዮን ሕዝብ ያላት ስዊድን ከተጠቀሰው አሃዝ በተጨማሪ ትናንት ረቡዕ ተጨማሪ 74 ሰዎች ሞተውባታል።
ዶ/ር አንደርስ ተግነል በስዊድን የኅብረተሰብ ጤና ኃላፊና የኮቪድ-19 ጉዳዮች ዋናው ተጠሪ ናቸው። ባለፈው ሚያዚያ ከቢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ አገራቸው ስዊድን የምትከተለው ፍልስፍና ላላ ያለ መሆኑ ችግር እንዳላስከተለ ተናግረው ነበር።
ለጊዜው የሟቾች ቁጥር ከፍ ያለውም የአዛውንቶች ማረፊያ የሆኑ የእንክብካቤ ማዕከላት ቫይረሱን ለመመከት በመዘግየታቸው እንደሆነ ነበር የተናገሩት።
ትናንት ግን ዶ/ር ተግነል ለስዊድን የሕዝብ ራዲዮ እንዳመኑት "ከዚህ ወዲህ እንዲህ ዓይነት ወረርሽኝ ቢመጣ ምላሻችን እንዳሁኑ ይሆናል ብዬ አላምንም። ያኔ ፍልስፍናችን የሚሆነው አሁን እኛ በተከተልነውና ሌላው ዓለም በተከተለው ጥብቅ መመርያ መሀል የሚሆን ይመስለኛል" ብለዋል።
በተከተልነው ልል መመሪያ ምክንያት በርካታ ዜጎቻችንን በአጭር ጊዜ ውስጥ አጥተናል ማለት ይቻላል ወይ? ተብለው ሲጠየቁም "አዎ! ይህ ምንም ጥርጥሬ የለውም" ብለዋል።
ነገር ግን ስዊድን በትክክል ምን ማድረግ ነበረባት በሚለው ዙሪያ አሁንም ግልጽ ምላሽ አልሰጡም።
ትናንት ረቡዕ በነበረው ሌላ ጋዜጣዊ መግለጫ ለምሳሌ "ስዊድን ቫይረሱን ለመከላከል የተከተለችው ፍልስፍና ትክክል ነበር" ብለዋል።
"በመሠረተ ሐሳብ ደረጃ ስዊድን ትክክለኛውን የመከላከል ዘዴ ነው የተከተለችው ብለን ነው አሁንም የምናምነው" ሲሉ ተደምጠዋል ዶ/ር አንደርስ ተግነል።
"ልዩነታችን ሌሎች አገሮች በአንድ ጊዜ ድንበራቸውን ዘጋግተው ዜጎቻቸውን በቤታቸው ውስጥ ሲቆልፉ እኛ የተከተልነው ዘዴ ግን ቁጥጥሩን ቀስ በቀስ ማጥበቅ ላይ ነበር።"
"አሁንም ቢሆን የእኛ አካሄድ ችግር ነበረበት ለማለት ጊዜ ገና ነው" ብለዋል። "ከታሪክ እንደምንረዳው እንዲህ ያሉ ወረርሽኞች ዳግም ሲመጡ የከፋ ጉዳት ያደርሳሉ" ሲሉ ለድምዳሜ ጊዜው ገና እንደሆነ ጠቁመዋል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ልል የተባለው የስዊድን መመሪያ እንዴት ያለ ነበር?
በርካታ አገራት በሕዝባቸውን ላይ ጥብቅ የእንቅስቃሴ ገደብ ሲጥሉ ስዊድን ይህንን አላደረገችም።
እርግጥ ነው ስዊድን በሕዝቧ መልካም ፈቃድ ላይ የተመሰረተ የማኅበራዊ መራራቅን አበረታታለች። ከ50 ሰዎች በላይ በአንድ ቦታና ጊዜ መሰብሰብን ከልክላለች። ይህም ወደ በኋላ የሆነ ነው።
በእድሜ የገፉ ዜጎችን መጎብኘትንም ከልክላ ነበር።
ስዊድን እጅግ አስፈላጊ ካልሆነ በስተቀር ጉዞ ማድረግን አላበረታታችም።
ሆኖም ጥንቃቄ ባለው ሁኔታ ጉዞ ማድረግን ስዊድን አልከለከለችም።
ዘመድ ወዳጅ ጥየቃ በእድሜ የገፉ ሰዎች ጋር እስካልሆነ ድረስ ክልከላ አልነበረውም።
ዴንማርክና ኖርዌይ ይህ የስዊድን አካሄድ ብዙም ስሜት የሰጣቸው አይመስልም።
የኖርዌይ የኅብረተሰብ ጤና ኃላፊ ፍሮድ ፎርላንድ እንደተናገሩት ስዊድን በይበልጥ ትኩረት ያደረገችውና የተከተለችው ታሪካዊ የቫይረሶችን የሥርጭት ሞዴልን ነው። እኛ በአንጻሩ ጠርቅመን በራችን መዝጋት ነው የመረጥነው" ብለዋል።
የስዊድን የቀድሞው የኅብረተሰብ ጤና ኃላፊ አኒካ ሊንድ አገሪቱ የተከተለችው የመከላከል ፍልስፍና ትክክል እንዳልነበረ ፊት ለፊት ተናግረዋል።
በሦስት ነገሮች ላይ ልዩ ትኩረት መስጠት ሲገባ ይህ እንዳልተደረገ ነው ያብራሩት።
የቀድሞ የኅብረተሰብ ጤና ጉዳዮች ኃላፊ ይህ እንዳልተደረገ ጠቅሰው አገራቸው ስዊድን በተከተለችው ልል መመሪያ ምክንያት የደረሰውን ጥፋት ተችተዋል።
የስዊድን መገናኛ ብዙሃን እንደዘገቡት ከሆነ የዚህ ስዊድን የተከተለችው ልል ፍልስፍና አመንጪና መሪ ለሆኑት ዶ/ር አንደርስ ተግነል በቅርቡ ካልታወቁ ሰዎች የግድያ ዛቻ በኢሜይል ደርሷቸዋል።
ያም ሆኖ በስዊድን በመንግሥት፣ በሕዝብና በተቋማት መካከል ከፍተኛ መተማን እንዳለ ይነገራል። ዶ/ር ተግነል በቅርቡ ለአሜሪካ ዴይሊ ሾው አሰናጅ ትሪቨር ኖዋ እንደገለጹት የሕዝባቸው 70 እና 80 ከመቶው ስዊድን የተከተለችው ልል የመከላከል እርምጃ ተገቢ ነው ብሎ ያምናል።



















