የቬንዙዌላውን ፕሬዚዳንት ለመያዝ በተደረገው ዘመቻ አሁንም ምስጢር የሆኑ ጉዳዮች

የፎቶው ባለመብት, REALDONALDTRUMP
የቩንዙዌላውን ፕሬዝዳንት ኒኮላስ ማዱሮን በቁጥጥር ስር ለማዋል የተደረገው ዘመቻ አንድ ሳምንቱን ከደፈነ በኋላ ስለተደረገው ዘመቻ የሚወጡ ዝርዝሮች ግልፅ እየሆኑ ነው፤ ሆኖም አሁንም አንዳንድ ሚስጢራት የሆኑ ጉዳዮች አሉ።
የስለላ መረጃ
ተልዕኮው ሲታቀድ እና የደኅንነት መረጃን በመሰብሰብ ለወራት የዘለቀ ነበር።
ባለፈው ነሐሴ የአሜሪካው የስለላ ተቋም ሲአይኤ ምስጢራዊ ማንነት የተላበሱ ሰላዮችን ልኳል ተብሎ ይታመናል።
አሜሪካ በቬንዙዌላ የሚሰራ ኤምባሲ የላትም። እናም ይህ ቡድን የዲፕሎማሲያዊ ሽፋን የማይጠቀም እና በስለላው ዓለም "የተከለከለ አካባቢ" ተብሎ በሚጠራ ስፍራ እየተንቀሳቀሰ ነበር። አባላቱ ዒላማዎችን ለመለየት እና የሚረዷቸውን ሰዎች ለመመልመል ወደ አገሪቱ ገብተው ነበር።
የአሜሪካ ባለሥልጣናት ለተልዕኮው ወሳኝ የሆነው የማዱሮን እንቅስቃሴ በሚመለከት ዝርዝር የደኅንነት መረጃ የሚሰጥ አንድ ሁነኛ ምንጭ እንደነበር ተናግረዋል።
የእነዚህ ምንጮች ማንነት በጥብቅ ሚስጢር መጠበቅ በጣም የተለመደ ነው።
ወዲያውኑ ግን ፕሬዝዳንቱ ያሉበትን ስፍራ እና መቼ የሚለውን የሚያውቅ፣ ከማዱሮ ጋር የቅርብ ግንኙነት ያለው እና በዙሪያቸው ካሉ ታማኝ ሰዎች አንዱ እንደሚሆን ግልፅ በመሆኑ "መንግሥታዊ" ምንጭ እንደሚሆን ታመነ።
ይህም የምንጩን ማንነት እና ምን እንደገጠማቸው ለማወቅ መላምቶች በስፋት እንዲሰራጩ አድርጓል። ሆኖም ግን እስካሁን ድረስ ማንነቱ ይፋ አልሆነም።
መሬት ላይ ያሉ ከሰው የሚሰበሰቡ የደኅንነት መረጃዎች የካርታ እና የሳተላይት ምስሎች ከመሰሉ ቴክኒካል የደኅንነት መረጃዎች ጋር ተጣምረው ተልዕኮውን ለማቀድ ውለዋል።
ተልዕኮው
የተልዕኮው መጠን፣ ፍጥነት እና ውጤት የሚጠበቅ አይደለም።
"ያለ እንከን ነበር የተከናወነው። ይህ ብዙ ጊዜ አይሆንም" ይላሉ ከአሜሪካ ጦር ጋር ተልዕኮዎችን በማቀድ የሰሩት የሲአይኤ የቀድሞ የላቲን አሜሪካ የተልዕኮ አዛዥ ዴቪድ ፊትዝጀራልድ።
"የወታደራዊ ስልቱ አይደለም ተልዕኮውን የመራው፤ የደኅንነት መረጃው እንጂ" ይላሉ።
በዚህ ዘመቻ ቢያንስ 150 አውሮፕላኖች ተሳትፈዋል። ማዱሮ ቅጥር ግቢ አካባቢ ሂሊኮፕተሮች ከመሬት በመቶ ጫማ ብቻ ከፍ ብለው እየበረሩ ነበር።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ይሁን እንጂ አሁንም አንዳንድ ምስጢሮች አሉ። አንደኛው አሜሪካ ልዩ ኃይሏ ካራከስ ሰርጎ እንዲገባ የኤሌክትሪክ መብራቱን እንዴት እንዳጠፋች ነው።
ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ "የካራከስ መብራት ባለን ልዩ ሙያ ተጠቅመን በአብዛኛው ጠፍቶ ነበር። ጨለማ ነበር እና አደገኛ ነበር" ብለዋል።
በዚህ ተልዕኮ የአሜሪካ የሳይበር ዕዝ መመስገኑ ብቻ የአሜሪካ ጦር መረጃ መንታፊዎች ቬንዙዌላ ኔትወርክ ውስጥ አስቀድመው ገብተው በሁነኛ ሰዓት ማስተላለፊያውን ዘግተውታል ወደሚል መላምት መርቷል። ሆኖም ዝርዝር መረጃዎች የሉም።
የቻይና እና የሩሲያ የአየር መከላከያ ክፍተት እንዳለበትም አጋልጧል።
አሜሪካ ይህን ተልዕኮ ለመደገፍ ምን ዓይነት የአየር ኃይል ቴክኖሎጂን ብታሰማራ ነው የሚለው ጎልቶ ወጥቷል። ሳተላይቶችን የሚመራው የአሜሪካ የጠፈር ዕዝ ልዩ ኃይሉ ሳይታይ ሰርጎ እንዲገባ "መንገድ በመጥረግ" ምስጋና ተችሮታል።
ስውር ድሮኖችም በዚህ ተልዕኮ እንደተሰማሩ ይታመናል። ጥቅም ላይ የዋሉት ድሮኖች ትክክለኛ የአቅም ዝርዝር በምስጢር እንደሚያዝ ቢታወቅም፤ የአሜሪካ ባላንጣዎች ምን እንደተፈጠረ ለመረዳት ጥረታቸውን ማድረጋቸው አይቀሬ ነው።
ውጊያው
ውስብስብ ተልዕኮዎችን አቅደው የሚያውቁ ሰዎች ስኬት ብዙ ጊዜ እንደማይኖር በመጥቀስ የአሜሪካ ተልዕኮ በእቅዱ መሠረት መፈፀሙ አስደናቂ ነው ይላሉ። በዚህ ተልዕኮ አንድ ሂሊኮፕተር ቢመታም መብረር የቻለ ሲሆን፤ አንድም የአሜሪካ ኃይል አባል አልተገደለም።
በማዱሮ ቅጥር ግቢ፣ ፉርቱ ቲውና ስለተደረገው ውጊያ አሁንም ድረስ ጥቂት መረጃ ብቻ ነው ያለው።
የኩባ መንግሥት 32 ዜጎቹ በአሜሪካ ጦር መገደላቸውን አስታውቋል።
እነዚህ ሰዎች ከማዱሮ የቅርብ አጋር ኩባ ለግል ጥበቃቸው የተመደቡ ናቸው። የካሪቢያን አገር ኩባ ጠባቂዎችን ብቻ ሳይሆን ለማዱሮ አገዛዝ ሰፊ የደኅንነት ድጋፍ ታደርጋለች።
"ከማዱሮ በቅርብ በሚኖር የደኅንነት ክልል ውስጥ ምናልባትም ዜሮ የቬንዙዌላ የፀጥታ መኮንኖች እና ከደኅንነት ክልሉ ውጭ ደግሞ የሁለቱም ነበሩ" ይላሉ ዴቪድ ፊትዝጀራልድ።
በጣም ውጤታማ አለመሆናቸው ምናልባትም አንዳንድ የአገዛዙ ባለሥልጣናት ተልዕኮውን በሆነ መንገድ አሳልጠው ሊሆን ይችላል ወደሚል ጥያቄ የመራ ሆኗል።
የአሜሪካ ኃይል አባላት ማዱሮ ቤት ውስጥ በመግባት በብረት ከተሰራ ክፍል ገብተው በሩን ለመዝጋት ሲሞክሩ የነበሩትን ፕሬዚዳንት በሩን ከመዝጋታቸው በፊት መያዝ ችለዋል።
አስፈላጊ ከሆነ ተቀጣጣይ እና ፈንጂዎችን ተጠቅመው በሩን ለመክፈት ዝግጁ ነበሩ። ነገር ግን የተልዕኮው ፍጥነት የግቢውን አቀማመጥ በሚመለከት ጠንካራ እና በቂ አረዳድ እንደነበር የሚጠቁም ነው።

የፎቶው ባለመብት, CBS
ዕቅዱ
የአሜሪካ ብሔራዊ የደኅንነት መረጃ ኤጄንሲ ሲአይኤ ማዱሮ ሲወገዱ ምን ሊፈጠር ይችላል የሚለውን ለማጤን ምስጢራዊ ግምገማ አስቀድሞ አድርጓል።
ተንታኞች በርካታ አማራጮችን መመልከታቸውን እና እንደ አንዳንድ ሪፖርቶች ከሆነ ተሰደው ካሉ የአገሪቱ ተቃዋሚዎችን አምጥቶ ከመሾም ይልቅ ካለው የቬንዙዌላ አገዛዝ ጋር መስራት የተሻለ መረጋጋት ይፈጥራል የሚል እይታ ይዘዋል።
ይህም አሜሪካ ከምክትል ፕሬዝዳንት ዴልሲ ሮድሪገዝ ጋር እንድትሰራ ጠንካራ እገዛ አድርጓል።
ታዲያ ይህ ከማዱሮ አገዛዝ ባለሥልጣናት ጋር ስለ ተልዕኮው እና ውጤቱ እንደተጠበቀው ባይሆን ራሳቸውን እንዴት ማደራጀት እንዳለባቸው አስቀድሞ በምስጢር መነጋገራቸውን የሚጠቁም ጭምጭምታ አለ።
የእነዚህ ጉዳዮች ዝርዝር ምስጢራዊነታቸው የቀጠለ ነው። ነገር ግን ተልዕኮው ለምን እንደተከናወነ? ለምን ውጤታማ እንደሆነ እና ቀጣዩ ዕቅዱ ምን እንደሆነ ለማወቅ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደርጋል።














