ትራምፕ በቬንዙዌላ ላይ የፈጸሙት ወረራ የፈጠረው ቀውስ እና ቻይና ላይ የደቀነው አደጋ

የቬንዙዌላው ፕሬዚዳንት ኒኮላስ ማዱሮ (በስተግራ) እና የቻይናው አቻቸው ዢ ጂንፒንግ (በስተቀኝ)

የፎቶው ባለመብት, Miraflores Palace via Reuters

የምስሉ መግለጫ, ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የቬንዙዌላው ፕሬዚዳንት ኒኮላስ ማዱሮ እና የቻይናው አቻቸው ዢ ጂንፒንግ ጠንካራ ግንኙነት መስርተው ነበር

ዶናልድ ትራምፕ ቻይና ለአስርት ዓመታት ስትገነባ የቆየችውን ግንኙነት ለማደፍረስ ጥቂት ሰዓታት ብቻ ፈጅቶባቸዋል።

የቬንዙዌላው ፕሬዝዳንት ኒኮላስ ማዱሮ በሌሊት በተፈጸመ ወረራ ከመያዛቸው ከጥቂት ሰዓታት በፊት ከከፍተኛ የቻይና ዲፕሎማት ጋር በቤተ መንግሥታቸው ውስጥ በነበራቸው ውይይት ላይ ዢ ጂንፒንግን "ታላቅ ወንድም" ሲሉ አወድሰዋቸው ነበር።

ቻይና በነዳጅ በበለፀገችው እና በደቡብ አሜሪካ ካሏት የቅርብ አጋሮች መካከል አንዷ በሆነችው ቬንዙዌላ ላይ ከፍተኛ መዋዕለ ነዋይ አፍስሳለች።

የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ያንን ለማረጋገጥ የፕሬዝዳንቱን እና የዲፕሎማቱን ስብሰባ ቪዲዮ አሳይተዋል።

ይህ ተንቀሳቃሽ ምሥል በፈገግታ የተሞሉት ዲፕሎማት እና ፕሬዝዳንቱ በሁለቱ አገራት መካከል ከተደረጉት 600 ስምምነቶች መካከል አንዳንዶቹን ሲገመግሙ ያሳያል።

ቀጥሎ ለዓለም ሕዝብ የታየው የማዱሮ ምሥል ግን በአሜሪካ የጦር መርከብ ላይ ዐይናቸው ተሸፍኖ፣ እጃቸው በካቴና ታስሮ ግራጫ የሌሊት ልብስ ለብሰው የተነሱት ነው።

ቻይና ዋሽንግተን በሉዓላዊት መንግሥት ላይ የወሰደችውን እርምጃ በማውገዝ በዓለም ዙሪያ ካሉ በርካታ አገራት ጋር ተቀላቅላለች።

አሜሪካን እንደ "የዓለም ዳኛ" እየሆነች ነው ብላ የከሰሰችው ቻይና፣ "የሁሉም አገራት ሉዓላዊነት እና ደኅንነት በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት ሙሉ በሙሉ መጠበቅ አለበት" ስትል ትናገራለች።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ከእነዚህን መራር ቃላት ጀርባ ቤይጂንግ በደቡብ አሜሪካ ያላትን ቦታ ለማረጋገጥ ብቻ ሳይሆን፣ ከትራምፕ ጋር ያለውን አስቸጋሪ ግንኙነት ለመቃኘት የተጠና እርምጃ መውሰዷ አይቀርም።

ከዚህም ባሻገር በቀጠናው በአሜሪካ እና በቻይና መካከል ያለው አዲስ ፉክክር ሙሉ በሙሉ ያልተጠበቀ ለውጥ በማምጣቱ የሚቀጥሉትን እርምጃዎቿን ለመወሰን ጥንቃቄ የተሞላበት ስሌት ታደርጋለች ተብሎ ይጠበቃል።

ብዙዎች ይህንን ለቻይና አምባገነን የኮሚኒስት ፓርቲ ገዥዎች እንደ ዕድል አድርገው ይመለከቱታል።

ነገር ግን ቤይጂንግ ለአስርት ዓመታት ስትገዛበት የኖረችውን ዓለም አቀፍ ደንብ አሜሪካ ከጣሰች በኋላ ምን ማድረግ እንዳለባት ያለማወቅ አደጋ፣ እርግጠኛ አለመሆን እና ብስጭት አለ።

የረዥም ጊዜ ወዳጅነትን መመሥረት የምትፈልገው ቤይጂንግ ትርምስን አትወድም።

በትራምፕ ሁለተኛ የሥልጣን ዘመን ደግሞ በተደጋጋሚ የሚታየው ትርምስ ፈላጊነታቸው ነው።

ፕሬዝዳንቱ በዓለም አገራት ላይ የጣሉት የንግድ ታሪፍን የተቋቋመችው ቻይና፤ ለአሜሪካ እና ለዓለም የማኑፋክቸሪንግ እና የቴክኖሎጂ ኩባንያዎቿ ምን ያህል ጠንካራ እንደሆኑ አሳይታለች።

አሁን ግን ቤይጂንግ አዲስ ፈተና ገጥሟታል።

ትራምፕ ለቬንዙዌላ ነዳጅ ሲሉ የወሰዱት እርምጃ ቻይና የአሜሪካ ፍላጎቶች ላይ ያላትን ጥልቅ ጥርጣሬ አጠናክሮታል። አሜሪካ የቻይናን ተጽዕኖ ለመቆጣጠር እስከ ምን ድረስ ትሄዳለች?

የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ እሁድ ዕለት ለኤንቢሲ ሲናገሩ "ይህ ምዕራቡ የዓለም ንፍቀ ክበብ ነው። የምንኖረው እዚህ ነው፤ እናም የምዕራቡ ዓለም ንፍቀ ክበብ የዩናይትድ ስቴትስ ተቃዋሚዎች፣ ተፎካካሪዎች እና ተቀናቃኞች መናኸሪያ እንዲሆን አንፈቅድም" ብለዋል።

ብዙም ያልተደበቀው እና ከደጃፋችን ዞር በሉ የሚለው መልዕክት ለቤይጂንግ ነበር።

እጃቸው በካቴና የታሰረው ኒኮላስ ማዱሮ በፌደራል የፀጥታ ኃይሎች ታጅበው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ኒኮላስ ማዱሮ በአሜሪካ የፌደራል የፀጥታ ኃይሎች ተይዘው ኒው ዮርክ ሲደርሱ

ቤይጂንግ ይህንን መስማት አትፈልግም። ነገር ግን ቀጥሎ የሚሆነውን ለማየት በትዕግሥት ትጠብቃለች።

አንዳንዶች ቻይና ራስ ገዝ በሆነችው ታይዋን ላይ ተመሳሳይ ነገር ማድረግ ትችል እንደሆነ ለማየት እየጠበቀች እና እየተከታተለች እንደሆነ ያስባሉ።

ዢ ታይዋን አንድ ቀን ከቻይና ጋር "እንደገና እንደምትዋሃድ" ቃል ገብተዋል፤ ይህንንም ለማሳካት ኃይል መጠቀምን ወደ ጎን አላሉም።

በቻይና ማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ ያሉ አንዳንድ ብሔርተኞች አሜሪካ በቬንዙዌላ ላይ በተናጠል እርምጃ መውሰድ ከቻለች ቤይጂንግ የታይዋን ፕሬዝዳንትን ለማንሳት የሚያግዳት ምንድን ነው? ሲሉ ይጠይቃሉ።

ቻይና የቬንዙዌላን ጉዳይ ከታይዋን ጋር በተመሳሳይ መንገድ ላታየው ትችላለች። ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ ታይዋንን እንደ ዓለም አቀፍ ሳይሆን እንደ ውስጣዊ ጉዳይ አድርጋ መቁጠሯ ነው።

ነገር ግን ከሁሉም በላይ አስፈላጊው ነገር፣ ዢ ደሴቲቱን ለመውረር ከወሰኑ አሜሪካ እርምጃ ስለወሰደች እንደማይሆን የውጭ ግንኙነት ምክር ቤት አባል የሆኑት ዴቪድ ሳክስ ተናግረዋል።

ቻይና "ተቀባይነት ባለው መንገድ ልታሳካ እንደምትችል በራስ መተማመን" እንደሌላት ጽፈዋል።

"ያ ቀን እስኪመጣ ድረስ ግን ቻይና የታይዋንን ሕዝብ ለማዳከም ጫና የመጠቀም ስልቷን ትቀጥልበታለች፤ ዓላማውም ታይዋንን ወደ ድርድር ጠረጴዛ ማምጣት ነው። አሜሪካ በቬንዙዌላ ላይ የሰነዘረችው ጥቃት ይህንን አይለውጠውም።"

ይልቁንስ ቻይና የደቡቡን ንፍቀ ክበብ ለማሸነፍ ያስቀመጠችውን የረዥም ጊዜ ዕቅድ አደጋ ላይ ይጥላል።

በቤይጂንግ እና በካራካስ መካከል ያለው ግንኙነት ዕድሜው ገና ለጋ ነው።

ቻይና ነዳጅ ዘይት የምትፈልግ ሲሆን፣ ቬንዙዌላ ደግሞ ገንዘብ ትሻለች።

ከአውሮፓውያኑ 2000 እስከ 2023 አካባቢ ቤይጂንግ ለቬንዙዌላ የባቡር ሐዲዶችን፣ የኃይል ማመንጫዎችን እና ሌሎች የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶችን ለመደገፍ ከ100 ቢሊዮን ዶላር በላይ ድጋፍ አድርጋለች።

በምላሹም ካራካስ እያደገ የመጣውን ኢኮኖሚዋን ለማነቃቃት የሚያስፈልገውን የነዳጅ ዘይት ለቤጂንግ ሰጥታለች።

ባለፈው ዓመት ወደ 80 በመቶ የሚሆነው የቬንዙዌላ ነዳጅ ዘይት ወደ ቻይና ተልኳል። ይህ አሁንም አገሪቱ ከምታስገባቸው የነዳጅ ምርቶች 4 በመቶ ብቻ ነው።

ስለዚህ በካራካስ የቻይናን የፋይናንስ አደጋዎች በተመለከተ "አንዳንድ ምልከታዎችን መጠበቅ አስፈላጊ ነው" ሲሉ የዘ ቻይና ግሎባል ሳውዝ ፕሮጀክት ዋና አዘጋጅ ኤሪክ ኦላንደር ተናግረዋል።

"እንደ ሲኤንፒሲ እና ሲኖፔክ ያሉ የቻይና ኩባንያዎች በቬንዙዌላ ካሉ ትልልቅ ተዋናዮች መካከል ናቸው፤ እናም እነዚያ ሀብቶች በቬንዙዌላውያን ሊወረሱ፣ በአሜሪካ አመራር ሠጪነት፣ ወይም በሌላ መልኩ በቀውሱ ውስጥ የመገለል አደጋ ተጋርጦባቸዋል።"

ቬንዙዌላ ከቻይና አበዳሪዎች የወሰደችው ወደ 10 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ውዝፍ ብድርም አለባት።

ነገር ግን ኦላንደር በአገሪቱ ውስጥ ያሉ ኢንቨስትመንቶች በአሁኑ ጊዜ አደጋ ላይ ናቸው ወይ? የሚለው ግልጽ ስላልሆነ ጥንቃቄ እንዲደርጉ አሳስበዋል።

ነገር ግን ለወደፊት መዋዕለ ነዋያቸውን ማፍሰስ ለሚፈልጉም ማስጠንቀቂያ አላቸው።

"የቻይና ኩባንያዎች በተለያዩ ፕሮጀክቶች ላይ መዋዕለ ነዋያቸውን ከማፍሰሳቸው በፊት የአሜሪካ ጣልቃ ገብነት አደጋዎችን እና መጠኑን ሙሉ በሙሉ መገምገም አለባቸው" ሲሉ የሬንሚን ዩኒቨርሲቲ የዓለም አቀፍ ግንኙነት ትምህርት ቤት ባልደረባ ኩይ ሹጁን ለቻይና የመንግሥት ሚዲያ ተናግረዋል።

ቤይጂንግ ከአሜሪካ ጋር የተፈራረመችውን የንግድ ስምምነት አደጋ ላይ መጣል አትፈልግም፤ ነገር ግን በላቲን አሜሪካም ያላትን ቦታ ማጣት አትፈልግም። በተለይም እንደ ትራምፕ ያልተጠበቀ ውሳኔ በሚወስን የዓለም መሪ ባለበት ያንን ሚዛን መጠበቅ ከባድ ይሆናል።

ለቻይና የሚያሳስበው ነገር በደቡብ አሜሪካ የሚገኙ ሌሎች አገራት "የአሜሪካን አላስፈላጊ ትኩረት ላለመሳብ በማሰብ" ከፍተኛ የቻይና ኢንቨስትመንቶች በሚመለከት ሁለቴ ማሰብ ሊጀምሩ ይችላሉ" ሲሉ ኦላንደር ተናግረዋል። "ይህ ቀጠና ለቻይና ወሳኝ የምግብ፣ የኃይል እና የተፈጥሮ ሀብቶች ምንጭ ሲሆን፣ የሁለትዮሽ ንግዱ አሁን ግማሽ ትሪሊዮን ዶላር ደርሷል።"

አሜሪካ የፓናማ መንግሥት ከፓናማ መተላለፊያ ጋር የተያያዙ የቻይና የወደብ ይዞታዎችን እና ኢንቨስትመንቶችን በሙሉ እንዲሰርዝ እንደምትፈልግ ግልጽ አድርጋለች፤ ይህም "ለቻይና በማያወላውል መልኩ አሳሳቢ" እንደሆነ አክለዋል።

ስለዚህ ቤይጂንግ በዋሽንግተን ደጃፍ የገጠማትን ጦርነት በሌሎች መንገዶች ማሸነፍ ሊኖርባት ይችላል።

ዢ እና ማዱሮ እአአ በ2013 ቤጂንግ በተገናኙበት ወቅት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ዢ እና ማዱሮ እአአ በ2013 ቤጂንግ በተገናኙበት ወቅት

ቻይና ደቡብ አሜሪካን በመማረክ ረገድ ትዕግሥት እና ጽናት አሳይታለች።

የደብቡ ንፍቀ ክበብ "የጋራ ዕጣ ፈንታ ያለው ማኅበረሰብ" መሆኑን በመስማማት "በአንድ ወገን የሚደርስ ጉልበተኝነትን" የሚቃወሙ አገራት ስብስብ ነው።

ይህ መልዕክት ከምዕራቡ ዓለም በተለይም በትራምፕ ዘመን ዋሽንግተንን በተመለከተ ስጋት ካለባቸው መንግሥታት አቋም ጋር ይስማማል።

ቻይና ከጅምሩ ከአጋሮቿ ምን እንደምትፈልግ በግልጽ አሳውቃለች።

አጋሮቿ የ"አንድ ቻይና" መርኅን ተቀብለው ታይዋን የቻይና "አካል" እንደሆነች ዕውቅና ይሰጣሉ።

ቤይጂንግ የላቲን አሜሪካ አገራት ከታይዋን ጋር ያላቸውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኘኙነት ወደ ቻይና እንዲቀይሩ በማሳመን ረገድ ከፍተኛ ስኬት አስመዝግባለች።

ኮስታሪካ፣ ፓናማ፣ ዶሚኒካን ሪፐብሊክ፣ ኤል ሳልቫዶር፣ ኒካራጓ እና ሆንዱራስ ባለፉት 20 ዓመታት ውስጥ የ19 ትሪሊዮን ዶላር ስትራቴጂካዊ አጋርነት ላይ ሲሠሩ ቆይተዋል።

ኦላንደር "ይህ በጣም ወሳኝ ነው፤ ምክንያቱም በቬንዙዌላ ያለው ሁኔታ በቀላሉ ወደ ቀውስ ሊያመራ ይችላል" ይላሉ።

አክለውም "በኢራቅ የሆነውን አንርሳ፤ አሜሪካ የአገሪቱ የነዳጅ ሀብት ምጣኔ ሀብቱን መልሶ ለመገንባት ይውላል ብላ ነበር። ያ ግን አልሆነም፤ አሁን የኢራቅ ድፍድፍ ነዳጅ ዘይትን በከፍተኛ መጠን የምትገዛው ቻይና ናት፤ በቬንዙዌላም ይኸው ሊከሰት ይችላል።"

በተቃራኒው ትራምፕ ከዋሽንግተን ጋር ያለው ግንኙነት ተለዋዋጭ ሊሆን እንደሚችል አሳይተዋል።

እናም ይህ ቻይና ራሷን ከመቼውም ጊዜ በበለጠ እንደ የተረጋጋ አገር ራሷን ለማስተዋወቅ ዕድል ሊሰጣት ይችላል።

ለዓመታት የአሜሪካ ኮንግረስ ቻይና በደቡብ አሜሪካ ያላት ተጽዕኖ ትኩረት እንዲሰጠው ግፊት ሲያደርጉ ነበር። እርምጃውን ወስዳለች ነገር ግን ማንም እርግጠኛ ያልሆነው ቀጥሎ የሚመጣውን ነው።

በቬንዙዌላ እንዲሁም በአጠቃላይ በላቲን አሜሪካ በአሜሪካ እና በቻይና መካከል ያለው ፉክክር ቁማር ነው። ቤይጂንግ ደግሞ በምንም መልኩ ቁማር መጫወትን ትጠላለች።