እስራኤል የሶሪያ የአየር ኃይል ጦር ሠፈር ላይ ጥቃት መፈጸሟን አሜሪካ አወገዘች

የፎቶው ባለመብት, Anadolu via Getty Images
እስራኤል በቱርክ ድንበር አቅራቢያ የሚገኝ የሶሪያ ወታደራዊ ጦር ሠፈር ላይ ጥቃት መፈጸሟ ከተሰማ በኋላ ዩናይትድ ስቴትስ ባልተለመደ መልኩ ተችታለች።
አሜሪካ በጦር ሠፈሩ ላይ የተፈጸመውን ድብደባ “አላስፈላጊ የሆነ ውጥረት” የሚፈጥር በማለት ያለምንም በቂ ምክንያት ሁኔታዎችን የሚያባበብስ ጥቃት መሆኑን ገልጻለች።
እስራኤል በአቡ ዱሁር የአየር ኃይል ጦር ሠፈር ላይ በፈጸመቻቸው ስምንት ድብደባዎች የአውሮፕላን መንደርደሪያዎችን እና መጋዘኖችን ማጥቃቷን የሶሪያ ቴሌቪዥን ዘግቧል።
በጥቃቱ በሰው ላይ የደረሰ ጉዳት ስለመኖሩ አልተገለፀም።
እስራኤል ስለፈጸመችው ጥቃት በቀጥታ አስተያየት ባትሰጥም፥ የቱርክ ወታደሮች የአየር ኃይል ጦር ሠፈሩን እንዲጠቀሙ በመፍቀድ የተደረሰውን የደህንነት መግባቢያ ለመጣስ “ጫፍ ደርሳ ነበር” ስትል ሶሪያን ወንጅላታለች።
ሶሪያ እና ቱርክ የእስራኤል ጦር ጥቃቶቹን መፈጸሙን በመግለጽ በቀጣናው ውጥረት እንዲባባስ ያደርጋል ሲሉ ገልጸዋል።
በሶሪያ እና ኢራቅ የዶናልድ ትራምፕ ልዩ ልዑክ ሆነው የተሾሙት እና በቱርክ የአሜሪካ አምባሳደር የሆኑት ቶም ባራክ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው በለጠፉት መልዕክት ጥቃቱን አውግዘዋል።
"በአቡ አል-ዱሁር የአውሮፕላን ማረፊያ ላይ የተፈጸሙትና የተረጋገጡት የእስራኤል ጥቃቶች፣ ለቀጣናዊ መረጋጋት አስተዋጽኦ የማያደርጉ እና አላስፈላጊ የሆነ ውጥረት የሚፈጥሩ ድርጊቶች በመሆናቸው ከፍተኛ ስጋት አለን" ሲሉ ባራክ በኤክስ ገጻቸው ላይ ጽፈዋል።
የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ቢሮ ባወጣው መግለጫ ደግሞ “እስራኤል እና ሶሪያ በደህንነት ጉዳዮች ላይ አሁን ያለውን ሁኔታ ለመጠበቅ ተስማምተዋል። ሶሪያ የቱርክ ወታደሮች ከአሌፖ አቅራቢያ በሚገኝ የአየር ማረፊያ እንዲሰፍሩ በመፍቀድ ይህንን ሁኔታ ለመጣስ ተቃርባ ነበር” ብሏል።
የሶሪያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ “ምክንያት ሊቀርብለት የማይችል የትንኮሳ ተግባር” በማለት “የቀጣናው ደህንነት እና መረጋጋትን” አደጋ ላይ የሚጥል ብሎታል።
ቱርክ ጦሯ ከድንበሩ በ70 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ወደሚገኘው ወደ አቡ ዱሁር የአየር ኃይል ጦር ሠፈር ስለመንቀሳቀሳቸው ምንም ማረጋገጫ አልሰጠችም።
ነገር ግን እስራኤል ስጋት ይደቅናል ስትል የሰጠችውን መግለጫ ውድቅ አድርጋለች።
የቱርክ የኮሚኒኬሽን ዳይሬክቶሬት፣ የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ያቀረባቸው ክሶች ሐሰተኛ እና እስራኤል በሶሪያ ላይ የምታደርሰውን ጥቃት ቅቡልነት ለመስጠት የተደረጉ መሆናቸውን ገልጿል።
ቱርክ ጥቃቶቹ የሶሪያን ሉዓላዊነት እና የግዛት መብት የሚጥሱ መሆናቸውን አስታውቃለች።















