ከሥልጣን የተነሱት የዩክሬን መከላከያ ሚኒስትር ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ እንዲካሄድ ጠየቁ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የቀድሞው የዩክሬን የመከላከያ ሚኒስትር ማይካኢሎ ፌዶሮቭ በጦርነት ጊዜ ምርጫ እንዲካሄድ ጥሪ አቀረቡ።
ሩሲያ ከአራት ዓመት ተኩል በፊት ዩክሬንን ሙሉ በሙሉ ከወረረች ወዲህ በአገሪቱ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ተካሄዶ አያውቅም።
ይህም ለቮሎዲሚር ዘሌንስኪ ፕሬዝዳንትነት ትልቁ ፈተና እንደሆነ በሰፊው ይታሰባል።
የ35 ዓመቱ ፌዶሮቭ ማክሰኞ ዕለት በዩቲዩብ ላይ ባጋሩት መልዕክት "ዲሞክራሲ በሩሲያ ታግቶ ሊያዝ አይችልም" ሲሉ ተናግረዋል። አክለውም ዩክሬን የምትታገለው "ነፃ የአውሮፓ መንግሥት ሆነን ለመቀጠል ስለምንፈልግ" ነው ብለዋል።
ጦርነቱ ከተጀመረበት ከ2022 ጀምሮ ዩክሬን በወታደራዊ ሕግ ሥር እየተዳደረች ትገኛለች። ይህም በአገሪቱ የሚደረግ ምርጫ ለጊዜው ታግዶ እንዲቆይ አድርጓል።
በመከላከያ ሚኒስትርነት በተሾሙ በስድስተኛ ወራቸው ከሥልጣናቸው የተባረሩት ፌዶሮቭ ባስተላለፉት የቪዲዮ መልዕክት ላይ የዜሌንስኪን ስም አልጠቀሱም።
ዜሌንስኪ የመከላከያ ሚኒስትሩን ከሥልጣን ባነሱበት ወቅት ከፍተኛ ተቃውሞ ገጥሟቸው የነበረ ሲሆን አሁን በቪዲዮው ላይ ስለተላለፈው መልዕክትም ምንም ያሉት ነገር የለም።
ፌዶሮቭ በሥልጣን ላይ ሳሉ በጣም ተወዳጅ የመከላከያ ሚኒስትር የነበሩ ሲሆን ሚኒስቴሩን በማነቃቃት፣ ሙስናን በመዋጋት እና በግንባር የሚካሄደውን የውጊያ አፈጻጸም ለመተንተን እና ለማሻሻል የሚያስችል መረጃን በመጠቀም ምስጋና ተችሯቸው ነበር።
ከሥልጣናቸው ለመባረራቸው ምክንያቱ በእርሳቸው እና በሠራዊቱ ዋና አዛዥ ኦሌክሳንድር ሲርስኪ መካከል ከተፈጠረ ውጥረት ጋር የተያያዘ እንደሆነ በሰፊው ተወርቷል።
በጥቂት ቀናት ውስጥ በአዲስ ሚኒስትር የተተኩት ፌዶሮቭን የዩክሬን ፕሬዚዳንት እንዲመልሷቸው የሚጠይቁ በርካታ ባለሥልጣናት ጫና ፈጥረው ነበር።
ፌዶሮቭ ቪዲዮውን ከማጋራታቸው ከሰዓታት ቀድም ብሎ ዘሌንስኪ የዬቭኒ ክማራን በመከላከያ ሚኒስትርነት መምረጣቸውን አስታውቀዋል።
ፌዶሮቭ በቪዲዮው ላይ በቀጣይ የፖለቲካ ሕይወታቸው ምን ሊመስል እንደሚችል ፍንጭ አልሰጡም።
















