"እኔ የጦር እስረኛ ነኝ" - በድራማ የተሞላው የማዱሮ የችሎት ውሎ

ኒኮላስ ማዱሮ በአሜሪካ የፖሊስ መኮንኖች ተይዘው ወደ ፍርድ ቤት ሲወሰዱ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የቬንዙዌላው መሪ ኒኮላስ ማዱሮ ወደ ኒው ዮርክ ፍርድ ቤት ሲዘልቁ እግራቸው ላይ የታሰረው ሰንሰለት እያንቃጨለ ነበር።

ማዱሮ ችሎቱን ወደ ሞሉት ጋዜጠኞች እና ታዳሚዎች ዞር ብለው "በአፈና ነው የመጣሁት" ሲሉ ድምፃቸውን አሰሙ።

የቬንዙዌላው መሪ ወደ ፍርድ ቤቱ ከገቡ ከደቂቃዎች በኋላ የ92 ዓመቱ ዳኛ አልቪን ሄለርስታይን ማዱሮ ነዎት አይደል? ሲሉ ማንነታቸውን ጠየቋቸው።

"አዎ ነኝ ጌታዬ! እኔ የቬንዙዌላ ሪፐብሊክ ፕሬዝደንት ነኝ። ከጥር 3 ጀምሮ በአፈና ነው የመጣሁት" ሲሉ ረጋ ባለ ስፓኒሽ ተናገሩ። አስተርጓሚ ተቀጥሮላቸዋል። አክለው "ካራካስ ከሚገኘው ቤቴ ነው ተይዤ የመጣሁት" አሉ።

ዳኛው ማዱሮን አቋርጠው "ሌሎች ጉዳዮችን የምናወራበት ጊዜና ቦታ አለው" አሏቸው።

በኒው ዮርክ ሰዓት አቆጣጠር ሰኞ ከሰዓቱን የተከናወነው የማዱሮ የችሎት ውሎ 40 ደቂቃ የፈጀ ነበር። ማዱሮ እና ባለቤታቸው ሲሊያ ፍሎሬስ በቀረበባቸው ክስ "ጥፋተኛ አይደለንም" ሲሉ አስተባብለዋል።

ማዱሮ "እኔ ነፃ ነኝ። እኔ መልካም ሰው ነኝ" ሲሉ ባለቤታቸው ፍሎሬስ ደግሞ "እኔ ፍፁም ነፃ ነኝ" የሚል ምላሽ ሰጡ።

አሜሪካ ብዙዎች ባልጠበቁት ድንገተኛ ዘመቻ የቬንዙዌላው መሪ ኒኮላስ ማዱሮ እና ባለቤታቸውን በቁጥጥር ስር ያዋለቸው ባለፈው ቅዳሜ ነበር።

ሰማያዊ እና ብርቱካንማ ቀለም ያለው ካናቴራ እንዲሁም ካኪ ሱሪ ለብሰው ፍርድ ቤት የተገኙት ጥንዶቹ አስተርጓሚያቸውን ለመስማት እንዲያስችላቸው የጆሮ ማዳመጫ አድርገዋል። ጠበቃቸው መሐከላቸው ተቀምጧል።

ማዱሮ በቢጫ ማስታወሻ ደብተር ላይ የሚሰሙትና የሚያዩት በአንክሮ ይፅፋሉ። ችሎቱ ሲጠናቀቅ ደብተሩን ይዘው መሔድ ይፈቅድላቸው እንደሆን ዳኛውን ጠይቀው ተፈቅዶላቸዋል።

የቬንዙዌላው ፕሬዝደንት ኒኮላስ ማዱሮ በአሜሪካ ፖሊሶች ተይዘው ወደ ፍርድ ቤት ሲወሰዱ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, ማዱሮና ሚስታቸው ባፈለው ቅዳሜ ነው ከካራካስ ተይዘው ወደ ኒው ዮርክ የመጡት
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ይህ ፍርድ ቤት ከወራት በፊት ታዋቂው አሜሪካዊ የሙዚቃ ባለሙያ ሾን "ዲዲ" ኮምብስ ችሎቱን የተከታተለበት እና ፍርድ ያገኘበት ነው።

ማዱሮ ወደ ችሎቱ ከዘለቁ በኋላ አዳራሹን ለሞላው ታዳሚ ሰላምታ ሰጥተዋል። ፊታቸው ላይ ምንም ዓይነት ስሜት ማንበብ አይቻልም። እርጋታ ተላብሰዋል። ችሎቱ ሲጠናቀቅ ከታዳሚዎች መካከል አንዱ ብድግ ብሎ "ለወንጀልህ ዋጋ ትከፍላለህ" ብሎ ሲጮህ እንኳ በእርጋታ ነው የተመለከቱት።

"እኔ ፕሬዝደንት ነኝ። የጦር እስረኛ ነኝ" ሲሉ በስፓኒሽ ለግለሰቡ ምላሽ ሰጡ። እንባ የተናነቀው ግለሰብ ከእስር ቤቱ እንዲወጣ ተደረገ።

የችሎት ውሎው ለአብዛኛዎቹ ታዳሚዎች ስሜታዊ ነበር። ቬንዙላዊቷ ጋዜጠኛ ማይቦርት ፔቲት ችሎቱን ለመታደም ተገኝታለች። ለዓመታት የማዱሮን መንግሥትን ስራ ስትዘግብ ቆይታለች። አሜሪካ ማዱሮን በቁጥጥር ሥር ለማዋል ባደረሰችው ጥቃት ምክንያት ካራካስ የሚገኘው የቤተሰቦቿ ቤት ጉዳት ደርሶበታል።

የቀድሞው የሀገሯ መሪ የእስር ቤት ልብስ ለብሰው፤ እግራቸው በካቴና ታስሮ በአሜሪካ የፖሊስ መኮንኖች እየተመሩ ወደ ችሎቱ ሲገቡ ማየት የፈጠረባት ስሜት ከባድ ነበር።

የማዱሮ ባለቤት ፍሎሬስ ብዙም ድምፃቸው አልተሰማም። አይናቸው እና ግንባራቸው ላይ ፕላስተር ለጥፈዋል። ጠበቃዎቻቸው በቁጥጥር ሥር ሲውሉ የደረሰባቸው ጉዳት ነው ይላሉ።

ጠበቃዎቻቸው ትክክለኛው የሕክምና አገልግሎት ሊሰጣቸው ይገባል ሲሉ ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል። ምናልባትም የጎን አጥንታቸው ላይ ጉዳት ሳይደርስባቸው አይቀርም ብለዋል።

ማዱሮ እና ባለቤታቸው በዋስ እንዲለቀቁ ፍርድ ቤቱን አልጠየቁም። ነገር ግን ወደፊት ሊጠይቁ እንደሚችሉ ተናግረዋል። እስከዚያው ድረስ በፌዴራል ማረሚያ ቤት ይቆያሉ።

አሜሪካ ማዱሮን በዕፅ-ሽብርተኝነት ሴራ፣ ኮኬይን በማስመጣት እንዲሁም የጦር መሣሪያና በሌሎች አጥፊ መሣሪያዎች ሤራ ትከሳቸዋለች።

ፍርድ ቤቱ ቀጣይ የችሎት ውሎ ለመጋቢት 8/2018 ቀጠሮ ሰጥቷል።