የእስራኤል ጦር ከኢራን ጋር ለሚኖር ሌላ ዙር ጦርነት እየተዘጋጀ መሆኑ ተዘገበ

የፎቶው ባለመብት, AFP
እስራኤል በቀጣይ በኢራን ላይ ሊፈጸም በሚችለው ጥቃት ውስጥ ሠራዊቷ ከአሜሪካ ጎን እንዲሳተፍ ለማድረግ እየተዘጋጀች መሆኑን የእስራኤል መገናኛ ብዙኃን ዘገበ።
ካን የተባለው ቴሌቪዥን ጣቢያ ስማቸው ያልተጠቀሰ የእስራኤል የደኅንነት ባለሥልጣንን ዋቢ አድርጎ እንደዘገበው፤ አሜሪካ በኢራን ላይ አዲስ ጥቃት ከጀመረች እስራኤል በዘመቻው ውስጥ በመሳተፍ የኢራንን “የኃይል ማመንጫ መሠረተ ልማቶችን” ዒላማ ታደርጋለች ብለዋል።
ይህ ዘገባ የተሰማው ፕሬዝዳንት ትራምፕ እና ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታኒያሁ እሑድ ዕለት በስልክ ከተወያዩ እንዲሁም የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ኢራን ከስምምነት ለመድረስ ያላት ጊዜ ወደ ማብቂያው እየተቃረበ መሆኑን ከገለጹ በኋላ ነው።
ካን ቴሌቪዥን እንደዘገበው በእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር እና በአሜሪካው ፕሬዝዳንት መካከል የተደረገው የስልክ ውይይት ከግማሽ ሰዓት በላይ የቆየ ሲሆን፣ ከኢራን ጋር ሌላ ዙር ጦርነት ሊከሰት በሚችልበት ሁኔታ ላይ ተነገግረዋል።
ሌላኛው የእስራኤል ቴሌቪዥን ቻናል 12 ደግሞ በሁለቱ መሪዎች መካከል የተደረገውን የስልክ ውይይት “ከኢራን ጋር ለሚደረግ አዲስ ጦርነት በሚደረግ ዝግጅት ጥላ ስር” መካሄዱን በመጥቀስ የእስራኤል ጦርም ለአዲስ ግጭት በሙሉ ተጠንቀቅ ላይ” መሆኑን ዘግቧል።
በተጨማሪም ቻናል 13 የተባለው የእስራኤል ቴሌቪዥን ጣቢያ በርካታ የጭነት አውሮፕላኖች የጦር መሳሪያዎችን ይዘው ወደ እስራኤል መግባታቸውን ዘግቧል።
ዘገባው ጨምሮም የጭነት አውሮፕላኖቹ ጀርመን ውስጥ ከሚገኙ የአሜሪካ ጦር ሰፈሮች ተነስተው ባለፉት 24 ሰዓተት ቴል አቪቭ ውስጥ አርፈዋል።


