የትራምፕ እርምጃ በዓለም ዙሪያ ላሉ አምባገነን ባለሥልጣናት ምን መልዕክት ያሰተላልፋል?

የፎቶው ባለመብት, EPA
የቬንዝዌላ መሪ ኒኮላስ ማዱሮ በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ተከትሎ፣ ዶናልድ ትራምፕ ከምንጊዜውም በላይ ጠንካራ መሆናቸውን፣ ጥንካሬያቸው ደግሞ ከአሜሪካ ወታደራዊ አቅም እንደሚመነጭ አሳይተዋል።
አሜሪካ ማዱሮን በፕሬዝዳንቱ ትዕዛዝ መሠረት ወደ ወህኒ የወረወረች ሲሆን፣ ቬንዙዌላን ደግሞ "አስተዳድራለሁ" ብላለች።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ይህንን በአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ላይ ከፍተኛ አንድምታ ያለውን ውሳኔ ያሳወቁት በፍሎሪዳ በሚገኘው የመኖሪያ ቤታቸው ነው።
ትራምፕ "ደኅንነቱ የተጠበቀ፣ ትክክለኛ እና ፍትሃዊ ሽግግር እስክናደርግ ድረስ" አሜሪካ ቬንዝዌላን ታስተዳድራለች ብለዋል።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ከቬንዝዌላ ምክትል ፕሬዝዳንት ዴልሲ ሮድሪጌዝ ጋር መነጋገራቸውን ገልጸዋል።
ምክትል ፕሬዝዳንቷ ከአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር በነበራቸው ውይይት "የምትፈልጉትን ሁሉ እናደርጋለን" ማለታቸውን ሩቢዮ ተናግረዋል።
አክለውም "...በጣም አመስጋኝ ነበረች ብዬ አስባለሁ፣ ግን ምንም ምርጫ የላትም" ብለዋል።
ትራምፕ በቬንዝዌላ ስለተካሄደው ወታደራዊ ዘመቻ ዝርዝር ጉዳዮችን ከመናገር ተቆጥበው "ማድረግ ካለብን ወደ አገሪቱ ወታደሮቻችንን ለማሰማራት አንፈራም" ብለዋል።
ፕሬዝዳንት ትራምፕ ቬንዝዌላን ከርቀት ሆኖ ማስተዳደር እንደሚቻል ያምኑ ይሆን? ለጊዜው ጥርት ያለ መልስ የለም።
ማርኮ ሩቢዮ እና የአሜሪካ የመከላከያ ሚኒስትር ፒት ሄግሴት በማር-አ-ላጎ ያወደሱት የአገራቸው ወታደራዊ እርምጃ የቬንዝዌላን መጻዒ ዕድል ለመቅረጽ እና የላቲን አሜሪካ መሪዎችን ወደ ታዛዥነት ለማሸጋገር በቂ ይሆናል? ፕሬዝዳንት ትራምፕ እንደዚያ የሚያምኑ ይመስላል።
ማስረጃው ግን ቀላል ወይም አልጋ በአልጋ እንደማይሆን ያሳያል።
ኢንተርናሽናል ክራይሲስ ግሩፕ በጥቅምት ወር የማዱሮ ውድቀት በቬንዝዌላ ውስጥ አመፅና አለመረጋጋት ሊያስከትል እንደሚችል አስጠንቅቋል።
ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ በዚሁ ወር ባወጣው ዘገባ፣ በመጀመሪያው የትራምፕ አስተዳደር ውስጥ የነበሩ የመከላከያ እና የዲፕሎማሲ ባለሥልጣናት ማዱሮ ከሥልጣን ቢወርዱ ምን ሊከሰት እንደሚችል ተንብየው ነበር።
መደምደሚያቸው የታጠቁ አንጃዎች ለሥልጣን ሲወዳደሩ ኃይለኛ ትርምስ እንደሚፈጠር ያሳያል።
የኒኮላስ ማዱሮ መወገድ እና መታሰር የአሜሪካን ወታደራዊ ኃይል አስደናቂ ብቃት ማረጋገጫ ነው።
አሜሪካ ግዙፍ የጦር መርከቦችን በቀጠናው በማሰማራት የኒኮላስ ማዱሮ ቤተ መንግሥትን ስታጠቃ የአንድም የአሜሪካ ወታደር ሕይወት አልጠፋም።

የፎቶው ባለመብት, @realdonaldtrump
ማዱሮ የቬንዝዌላ ሕዝብን ፍላጎት ችላ በማለት፣ የምርጫ ሽንፈታቸውን ወደ ጎን በመተው የሙጥኝ ካሉበት ሥልጣን መነሳታቸው በብዙ ዜጎቹ ዘንድ በበጎ ሊታይ ይችላል።
ነገር ግን የአሜሪካ እርምጃ አንድምታ ከቬንዝዌላ ድንበር ባሻገርም ይዛመታል።
በማር-አ-ላጎ የነበረው ጋዜጣዊ መግለጫ በድል አድራጊነት ስሜት የተሞላ ነበር። ለዚህ ምክንያቱ ዘመቻው የተመራው በአሜሪካ ልዩ ኃይል መሆኑ እና የተከናወነው ለሌሎች መማሪያ የሚሆን ነበር።
ወታደራዊ ዘመቻው የመጀመርያ እርምጃ ነው።
አሜሪካ ባለፉት 30 ዓመታት የመንግሥት ለውጥ ለማድረግ በተሳተፈችበት ሁሉ የተከሰተው ውድመት ነው።
ቀጥሎ የሚመጣው ፖለቲካዊ እርምጃ ሂደቱን ፍሬ እንዲያፈራ ወይንም እንዲከሽፍ ያደርጋል።
አሜሪካ እአአ በ2003 ኢራቅን ከወረረች በኋላ አገሪቱ ወደ ደም አፋሳሽ ግጭት አምርታለች።
በአፍጋኒስታን ሁለት አስርታት ዓመታት እና ቢሊዮን ዶላሮችን አፍስሳ እአአ በ2021 መውጣቷን ተከትሎ የአገር ግንባታው ውሃ በልቶታል።
እነዚህ ሁለቱም አገራት ከአሜሪካ በሺህ ኪሎ ሜትሮች ርቀት ላይ የሚገኙ ናቸው።
በቅርብ ርቀት በሚገኙት የላቲን አሜሪካ አገራት የምትወስዳቸው እርምጃዎች ግን ከስጋት ውጭ ተስፋ የሚፈነጥቁ አይደሉም።
ትራምፕ በ1823 ፕሬዝዳንት ጄምስ ሞንሮ ሌሎች ኃይሎች በአሜሪካ በምዕራቡ ዓለም ውስጥ ባለው የተፅዕኖ ክልል ውስጥ ጣልቃ እንዳይገቡ ለማስጠንቀቅ የሰጡትን መግለጫ 'የሞንሮ ዶክትሪን' በማለት ጠቅሰዋል።
"የሞንሮ ዶክትሪን ትልቅ ጉዳይ ነው፣ ግን በብዙ ነገር ተክተነዋል" ሲሉ ትራምፕ በማር-አ-ላጎ ተናግረዋል። "በአዲሱ የብሔራዊ ደኅንነት ስትራቴጂያችን መሠረት፣ በምዕራባዊው ንፍቀ ክበብ የአሜሪካ የበላይነት እንደገና ጥያቄ ውስጥ አይገባም።"
የኮሎምቢያ ፕሬዝዳንት ጉስታቮ ፔትሮ ትራምፕ "ቁጣቸውን መቆጣጠር አለባቸው" ብለዋል።
በኋላም ለፎክስ ኒውስ "ከሜክሲኮ ጋር አንድ ነገር መደረግ አለበት" ሲሉ ተናግረዋል።
ኩባም ያለምንም ጥርጥር በአሜሪካ አጀንዳ ውስጥ ትገኛለች፤ ወላጆቻቸው ከኩባ የሆኑት የአሜሪካው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሩቢዮ ጉዳዩን በበላይነት ይዘውታል።
አሜሪካ በላቲን አሜሪካ ውስጥ ለረጅም ጊዜ የዘለቀ የትጥቅ ጣልቃ ገብነት ታሪክ አላት።
ፕሬዝዳንት ቢል ክሊንተን እአአ በ1994 በሄይቲ የአገዛዝ ለውጥን ለማስፈጸም 25,000 ወታደሮችን እና ሁለት የአውሮፕላን ተሸካሚዎችን ላኩ።
ከዚያም የሄይቲ አገዛዝ ምንም ዓይነት ጥይት ሳይተኮስ ፈራረሰ።
ይህ የአሜሪካ እርምጃ የተሻለ ዕድልን ለሄይቲያውያን ከማምጣት ይልቅ ላለፉት 30 ዓመታት ሕዝቡ የማይቋረጥ መከራ ውስጥ ይገኛል። ሄይቲ አሁን በታጠቁ ወንበዴዎች የምትመራ የወደቀች አገር ነች።
ዶናልድ ትራምፕ ቬንዝዌላን ዳግም ታላቅ ስለማድረግ አንስተዋል። ነገር ግን ስለ ዲሞክራሲ ያሉት ነገር የለም።
የ2025 የሰላም ኖቤል ሽልማት ያሸነፈችው የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዋ ማሪያ ኮሪና ማቻዶ አገሪቱን ልትመራ ትችላለች የሚለውን ሃሳብ ውድቅ አድርገዋል።
"ለእርሷ መሪ መሆን ከባድ ይመስለኛል። ድጋፉ የላትም። ተገቢው ክብርም የላትም።"
ቬንዝዌላውያን እአአ በ2024 ባደረጉት ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ እንዳሸነፉ የሚነገርላቸው ኤድሙንዶ ጎንዛሌዝንም አላነሱም።
ከዚያ ይልቅ አሜሪካ በአሁኑ ወቅት ለቬንዝዌላ ምክትል ፕሬዝዳንት ድጋፏን የሰጠች ይመስላል።
ማዱሮን ከሥልጣን ለማስወገድ ከውስጥ ሆኖ መረጃ ያቀበለ ግለሰብ አለ የሚለው የውስጥ ፍጭት ቢፈጥርም በሁጎ ቻቬዝ የተመሠረተው መንግሥት አሁንም ባለበት እንደቀጠለ ነው።
የቬንዝዌላ ጦር የአሜሪካን ወታደራዊ ጥቃት የመገዳደር ፍላጎት እና አቅም ይኖረዋል ተብሎ አይታሰብም።
አሜሪካ በቬንዝዌላ ላይ የፈጸመችው ጥቃት ትራምፕ ዓለምን የሚመለከቱበት መነጽር ላይ ትኩረት እንዲደረግ አድርጓል።
ትራምፕ የሌሎች አገራት የማዕድን ሀብት ቀልባቸውን እንደሚስባቸው ሸሽገው አያውቁም።
አሜሪካ ለዩክሬን የሰጠችውን ወታደራዊ ድጋፍ ተገን አድርገው ዩክሬን ማዕድን ለማውጣት ተስማምተዋል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ትራምፕ የቬንዝዌላ የማዕድን ሀብትን መቆጣጠር እንደሚፈልጉ ሸሽገው አያውቁም። የአገሪቱ መንግሥ የነዳጅ ኢንዱስትሪውን ከውጭ ባለሃብቶች ነጥቆ በራሱ ቁጥጥር ሥር ሲያደርግ የአሜሪካ ኩባንያዎች ተዘርፈዋል ብለው ያስባሉ።
ይህ የአሜሪካ መንግሥት እርምጃ በግሪንላንድ እና ዴንማርክ ፍርሃት አንግሷል።
አሜሪካ ግሪንላንድን የመጠቅለል ፍላጎቷን አልተወችውም። ግሪን ላንድ ባላት የተፈጥሮ ሃብት እና በስትራቴጂክ ጠቃሚነቷ አሜሬካ ዐይኗን ጥላባታለች።
ማዱሮ ከሥልጣን የተወገዱበት መንገድ ዓለምን ለማስተዳደር ምርጡ መንገድ በዓለም አቀፍ ሕግ የተቀመጡ ደንቦችን መከተል የሚለውን እምነት ላይ ጥያቄ አስነስቷል።
ዶናልድ ትራምፕ በአሜሪካም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ የማይፈልጓቸውን ሕጎች ችላ እንደሚሉ በተደጋጋሚ አሳይተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ኪር ስታርመርን ጨምሮ በርካታ የአውሮፓ መሪዎች ትራምፕን ላለማስቆጣት ከፍተኛ ጥንቃቄ ሲያደርጉ ታይተዋል።
የማዱሮ ከሥልጣን መነሳት የተባበሩት መንግሥታትን ቻርተር በግልጽ የሚጥስ መሆኑን ሳያወግዙ የዓለም አቀፍ ሕግን እንደሚደግፉ ለመናገር ቃላት ሲመርጡ ተስተውሏል።
የአሜሪካ ወታደሮች የቬንዝዌላ ፕሬዝዳንት ከአደንዛዥ ዕፅ ዝውውር ጋር በተያያዘ በቁጥጥር ስር ማዋላቸውን ቢነገርም፣ ትራምፕ አሜሪካ አሁን አገሪቱን እና የነዳጅ ኢንዱስትሪዋን እንደምትቆጣጠር በመግለጻቸው ጉዳዩን ያከብደዋል።
ማዱሮ እና ባለቤታቸው በቁጥጥር ሥር ማዋላቸው ጥቂት ሰዓታት በፊት የቻይና ዲፕሎማቶችን በቤተ መንግሥታቸው አግኝተው አነጋግረው ነበር።
ቻይና የአሜሪካን እርምጃ አውግዛለች።
ዶናልድ ትራምፕ በአስተዳደራቸው ወቅት ለአሜሪካ የሚሠሩ መመሪያዎችን ደንቦችን ራሳቸው የሚጽፉ ነው የሚመስለው። ሌሎች ግን ይህንን የማድረግ ዕድል ያላቸው አይመስልም።
ትራምፕ የፈረንጆች አዲስ ዓመት ሲጀምር በቬንዝዌላ ላይ የወሰዱት እርምጃ ቀጣዮቹን 12 ወራት ሊንጥ ይችላል።















