ቀጥታ, የኢራን ከፍተኛ ባለሥልጣናት በታደሙበት የቀድሞው አያቶላህ የቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ ጠቅላይ መሪው ሳይገኙ ቀሩ

የቀድወው ኢራን አያቶላህ የቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ በርካታ የአገሪቱ አመራሮችን ጨምሮ በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ቢገኙም፤ ጠቅላይ መሪው ሞጅታባ ኻሜኒ የአባታቸው ሽኝት ላይ ሳይታዩ ቀርተዋል። እሁድ ዕለት በተካሄደው የጸሎት ሥነ-ሥርዓት ላይ የቀድሞው ጠቅላይ አሊ ኻሜኒ ሦስት ልጆች መስዑድ፣ ሙስጠፋ እና መይሰም ከፕሬዝዳንት መስዑድ ፔዜሽኪያን እና ከእስላማዊ አብዮታዊ ዘብ መሪ አህመድ ቫሂዲ ጋር ተገኝተዋል።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

የኢራን ከፍተኛ ባለሥልጣናት በታደሙበት የቀድሞው መሪ አያቶላህ የቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ ጠቅላይ መሪው ሳይገኙ ቀሩ

ትራምፕ ይገደሉ የሚል መፈክር የያዘች እና ሌሎች ሐዘንተኞች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የቀድሞው የኢራን ጠቅላይ መሪ አያቶላህ የቀብር ሥነ ስርዓት ላይ በርካታ የአገሪቱ አመራሮችን ጨምሮ በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ቢገኙም ጠቅላይ መሪው ሞጅታባ ኻሜኒ የአባታቸው ሽኝት ላይ ሳይታዩ ቀርተዋል።

እሁድ ዕለት በተካሄደው የጸሎት ሥነ-ሥርዓት ላይ የቀድሞው ጠቅላይ መሪ አሊ ኻሜኒ ሦስት ልጆች መስዑድ፣ ሙስጠፋ እና መይሰም ከፕሬዝዳንት መስዑድ ፔዜሽኪያን እና ከእስላማዊ አብዮታዊ ዘብ መሪ አህመድ ቫሂዲ ጋር ተገኝተዋል።

መጋቢት ላይ ወደ ሥልጣን ከመጡ አንስቶ ለሕዝብ ያልታዩት ሞጅታባ ኻሜኒን የጤና ሁኔታ በተመለከተ የተለያዩ መረጃዎች ይናፈሳሉ። አባታቸውን በገደለው የአየር ጥቃት እርሳቸውም እንደተጎዱ ይነገራል።

የቀድሞው ጠቅላይ መሪ ከአውሮፓውያኑ 1989 ጀምሮ እስከሞቱበት የካቲት ወር ድረስ እስላማዊቷን ሪፐብሊክ መርተዋል።

አርብ ዕለት የተጀመረው የአያቶላህ አሊ ኻሜኒ ይፋዊ የቀብር ሥነ ሥርዓት በዚህ ሳምንትም በተለያዩ የኢራን እና ኢራቅ አካባቢዎች መካሄድ ይቀጥላል።

የኢራን ባለሥልጣናት “የክፍለ ዘመኑ የቀብር ሥነ ሥርዓት” ሲሉ በገለጹት በዚህ የሽኝት ሥነ ሥርዓት ላይ ከ12 እስከ 20 ሚሊዮን ሰዎች ይገኛሉ ብለው እንደሚጠብቁ ተናግረዋል።

በአሁኑ ሰዓት የኻሜኒ አስከሬን ቴህራን ውስጥ በሚገኘው ግዙፉ መስጊድ ግራንድ ሞሳላ ውስጥ ተቀምጧል።

እሁድ ዕለት በመላው ኢራን ክብረ በዓል ሆኖ የታወጀ ሲሆን አስከሬኑ ከመስጊዱ እንደሚወጣ እና ዛሬ ሰኞ ሰልፍ እንደሚካሄድ ተገልጿል።

የቀብር ሥነ ሥርዓቱ በጥንቃቄ የተሰናዳ ነው። በሥነ ሥርዓቶቹ ላይ የሞጅታባ ኻሜኒ አለመገኘት የተስተዋለው እስራኤል ልትገድላቸው ትፈልግ ይሆናል የሚል ስጋት ባደረበት በዚህ ወቅት ነው።

ተፋላሚዎቹ አገራት በገቡበት ጠንካራ ያልሆነው ተኩስ አቁም ምክንያት ጦርነቱ ጋብ ብሎ ስምምነት ላይ ለመድረስ የሚደረገው ንግግር ቀጥሏል።

ይሁን እንጂ አሜሪካም ሆነ ኢራን ወታደራዊ እርምጃ ውስጥ በድጋሚ ለመግባት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የቀብር ሥነ ሥርዓቱ እስከሚጠናቀቅ ከኢራን ጋር የሚደረገው ንግግር እንዲቆም መደረጉን ለአሜሪካው የዜና ምንጭ አክሲዮስ ተናግረዋል።

አሜሪካ በቀብር ሥነ ሥርዓቱ ላይ የሚታደሙትን የኢራን ከፍተኛ አመራሮች “በአንድ ጥይት” ልትገድላቸው እንደምትችልም መናገራቸውን አክሲዮስ አስነብቧል። ። ነገር ግን "ይህንን አናደርግም፤ ምክንያቱም ከዚያ የምንደራደረው ሰው አይኖርም" ብለዋል።

ትራምፕ ሕዝቡ የቀድሞውን ጠቅላይ መሪ ይጠላቸዋል ብለው ያስቡ እንደነበር ገልጸው፤ የተወሰኑ ኢራናውያን ሲያለቅሱ በመመልከታቸው እንደተገረሙ ተናግረዋል።

በቴህራን በተደረገው ሽኝት ላይ ታዳሚዎች 'ሞት ለትራምፕ' ሲሉ እንደነበር እንዲሁም ሞሐማድ ረሱሊ የተባሉ ገጣሚ ከጸሎት ሥነ ሥርዓት በፊት “ትራምፕን መግደል የእኛ ኃላፊነት ነው” የሚል ግጥም ማቅረባቸውን አሶሺዬትድ ፕሬስ እና ዘ ጋርዲያን ዘግበዋል።