ቬንዙዌላን የሚመራት ማነው? በቀጣይስ ምን ሊሆን ይችላል?

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images
የአሜሪካው ፕሬዝደንት ትራምፕ የቬንዙዌላው ፕሬዝደንት ኒኮላስ ማዱሮ በካራካስ ከተፈፀመ መጠነ ሰፊ ጥቃት በኋላ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን አስታውቀው "ትክክለኛ" ሽግግር እስኪመጣ ድረስ "ሀገሪተን ለመምራት" ቃል ገብተዋል።
የቬንዙዌላው ግራ-ዘመም መሪ እና ቀዳማዊ እመቤቷ በመኖሪያ ቤታቸው ሳሉ ነው ተይዘው ወደ ኒው ዮርክ የመጡት ከተወሰዱ በኋላ ብሩክሊን የሚገኝ እስር ቤት መግባታቸው ታውቋል።
የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት ማዱሮ ቅዳሜ ከመጡ በኋላ ኒው ዮርክ በሚገኘው የአሜሪካ የዕፅ ቁጥጥር ቢሮ (ዲኢኤ) በዕፅ ዝውውር እና የጦር መሣሪያ በመያዝ ክስ ተመስሮባቸዋል።
ማዱሮ ከዚህ ቀደም የዕፅ አዘዋዋሪ ቡድን ኃላፊ ናቸው መባላቸውን ማስተባበላቸው ይታወሳል።
ማዱሮ እና ሚስታቸው ኒው ዮርክ ፍርድ ቤት መቼ እንደሚቀርቡ አልታወቀም።
ማዱሮን የመያዝ ዘመቻው እንዴት ተፈፀመ?
የአሜሪካ ልዩ ኮማንዶዎች ወደ ቬንዙዌላ ዘልቀው በመግባት ጥቃት ፈጽመው ፕሬዝዳንት ኒኮላስ ማዱሮን በቁጥጥር ሥር በማዋል የወሰዱበትን ተልዕኮ በተመለከተ ጄነራል ዳን ኬይን ቅዳሜ ከሰዓት መግለጫ ሰጥተዋል።
በጄነራሉ ገለፃ መሠረት የአየር፣ የምድር፣ የህዋ፣ የባሕር እና የደኅንነት መረጃ ባለሙያዎች የተልዕኮውን ዕቅድ ሲያዘጋጁ እና ሲያቀናጁ ለወራት ቆይተዋል።
አርብ ምሽት 4 ሰዓት ከ46 ደቂቃ ላይ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ዘመቻው እንዲካሄድ ትዕዛዝ ካስተላለፉ በኋላ 'አብሶሉት ሪዞልቭ' የሚል ስያሜ የተሰጠው ተልዕኮ በምዕራቡ ንፍቀ ክበብ ከሚገኙ የተለያዩ 20 የአሜሪካ ጦር ሰፈሮች 150 አውሮፕላኖችን ወደ ቬንዙዌላ በማንቀሳቀስ ተጀመረ።
የምድር ኃይል እና ሄሊኮፕተሮችን ያካተተው ፕሬዝዳንቱን ነጥሎ የሚይዝ ኃይል ቅዳሜ ሌሊት ሰባት ሰዓት ላይ ፕሬዝዳንት ኒኮላስ ማዱሮ እና ሚስታቸው ወደሚኖሩበት ቅጥር ጊቢ አቀና።
ይህ ኃይል በበርካታ ዘመና ተዋጊ የጦር ጄቶች፣ ቦምብ ጣይ አውሮፕላኖች እና በድሮኖች ከፍተኛ ጥበቃ እየተደረገለት ነበር።
ሄሊኮፕተሮች ላይ ተኩስ ተከፍቶባቸው አንደኛው ቢመታም በዘመቻው ወቅት ግዳጁን ለመፈጸም ከመብረር ያገደው አልነበረም ሲሉ ዶናልድ ትራምፕ ተናግረዋል።
ፕሬዝዳንት ኒኮላስ ማዱሮ እና ባለቤታቸው ከመኖሪያቸው ተይዘው በሄሊኮፕተር ከቬንዙዌላ እንዲወጡ ከተደረገ በኋላ ከሌሊቱ 9 ሰዓት ከ39 ደቂቃ በአሜሪካዋ የጦር መርከብ ዩኤስኤስ አይዋ ጂማ ላይ እንዲርፉ ተደርጎ በቀጣይ ወደ ኒው ዮርክ ተወሰዱ።
በዘመቻው አንድም የአሜሪካ ወታደር እንዳልተገደለ ፕሬዝደንት ትራምፕ አሳውቀዋል።
አሁን ቬንዙዌላን የሚመራው ማነው?
ቬንዙዌላ ላይ ድንገተኛ የኮማንዶ ጥቃት በመፈጸም አገሪቱ መሪ በአሜሪካ እጅ መግባታቸውን በተመለከተ ፕሬዝንት ትራምፕ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ "አስተማማኝ፣ ተገቢ እና ሕጋዊ ሽግግር እስኪካሄድ ድረስ ቬንዙዌላን አሜሪካ ታስተዳድራለች" ሲሉ በኩራት ተናግረዋል።
በጋዜጣዊ መግለጫቸው ላይ ትራምፕ የአገሪቱን የነዳጅ ሀብት በተመለከተም ትላልቅ የአሜሪካ ኩባንያዎች ወደ ቬንዙዌላ በመግባት መሠረተ ልማቶቿን መልሶ በመጠገን "ለአገሪቱ ገቢ ማስገኘት ይጀምራሉ"ብለዋል።
አክለው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ማርኮ ሩቢዮ ከቬንዙዌላ ምክትል ፕሬዝደንት ዴልሲ ሮድሪጌዝ ጋር ውይይት ማድረጋቸውን አሳውቀዋል።
የቬንዙዌላ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዝደንት የሀገሪቱ ጊዜያዊ መሪ እንዲሆኑ ወስኗል። ትራምፕ እንዳሉት ዴልሲ "አሜሪካ ለሚያስፈልጋት ነገር በሙሉ" ድጋፍ ለመስጠት ፈቃደኛ ናቸው።
ነገር ግን ዴልሲ ከሹመታቸው በኋላ በሀገሪቱ ቴሌቪዥን ቀርበው ባሰሙት ንግግር በአሜሪካ ቁጥጥር ስር የዋሉት ኒኮላስ ማዱሮ የቬንዙዌላ ብቸኛው ፕሬዝደንት ናቸው ሲሉ ተናግረዋል።
ትራምፕ የቬንዙዌላ የወደፊት ፕሬዝደንት ሆነው ይመረጣሉ ተብለው የሚጠበቁት የኖቤል የሰላም ሽልማት አሸናፊዋ ማሪና ኮሪና ማቻዶ ሀገሪቱን ለመምራት "ድጋፍም የላትም ክብርም አይሰጣትም" ብለዋል።
ማቻዶ የተቃዋሚ ፓርቲያቸው አባል የሆኑት ኤድሙንዶ ጎንዛሌዝ ሥልጣን መያዝ አለባቸው ብለዋል። በ2024 በቬንዙዌላ በተደገው ምርጫ ማዱሮ አሸናፊ ተደርገው ቢሰየሙም የተቃዋሚ ፓርቲ ያሰባሰበው ድምፅ ጎንዛሌዝ በሰፊ ልዩነት እንዳሸነፉ ያሳያል።

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images
የቬንዙዌላ ዕጣ ፈንታ
የአሜሪካ ባለሥልጣናት በቬንዙዌላ ተጨማሪ ወታደራዊ እርምጃ እንደማይወስዱ ቢናገሩም ፕሬዝደንት ትራምፕ "ወታደር ለማሰማራት አንፈራም" ብለዋል።
የአሜሪካ የነዳጅ ኩባንያዎች ገብተው መሠረተ ልማቱን እንደሚያሻሽሉት እና "ለሀገሪቱ ገንዘብ ማምጣት እንደሚጀምሩም" ፕሬዝደንቱ ተናግረዋል።
"ከስፍራው ትልቅ ሀብት እንወስዳለን። ገንዘቡ ለቬንዙዌላዊያን እና ለአሜሪካ ይውላል" ያሉት ትራምፕ "ላወጣነው ወጪ ካሳ ይሆናል" የሚል ሐሳብ ሰጥተዋል።
አሜሪካ የቬንዙዌላን ነዳጅ ለሌሎች ሀገራት እንደምትሸጥም ጠቁመዋል።
የቬንዙዌላ መንግሥት ጥቃቱ "የቬንዙዌላን ስትራቴጂካዊ ሀብት በተለይ ደግሞ ነዳጅ እና ማዕድናትን ለመቆጣጠር የተቃጣ ነው" ሲል ኮንኗል።
ቬንዙዌላ በዓለማችን ትልቁ የነዳጅ ክምችት ያላት ሀገር ስትሆን ከነዳጅ ሽያጭ የሚገኘው ገቢ ከመንግሥት በጀት ግማሽ ያክሉን ይሸፍናል። ነገር ግን ወደ ውጭ የምትልከው ነዳጅ መጠን በማዕቀብ ምክንያት የተገደበ ነው።
ማዱሮ የቀረበባቸው ክስ
የአሜሪካ ዐቃቤ ሕግ ፓም ቦንዲ የቬንዙዌላው ፕሬዝደንት እና ቀዳማዊ እመቤቷ በኒው ዮርክ ደቡባቂ ቀጣናት ክስ እንደቀረበባቸው ተናግረዋል።
የዕፅ ሽብር ለመፈፀም በማሴር፣ ኮኬይን በማስገባት፣ የጦር መሣሪያ እና ሌሎች አጥፊ መሣሪያዎችን በመያዝ እንዲሁም በአሜሪካ ላይ ጥቃት ለመሰንዘር የጦር መሣሪያ እና ሌሎች አጥፊ መሣሪያዎችን ለመያዝ በማሴር ክስ ተመስርቶባቸዋል።
ሬዝዳንቱ እና ባለቤታቸው አሜሪካ ውስጥ "በአሜሪካ ምድር፣ በአሜሪካ ፍርድ ቤት የአሜሪካንን የፍትሕ አቅም ሙሉ ለሙሉ በቅርቡ ይጋፈጡታል" ሲሉም አክለዋል።

የፎቶው ባለመብት, Donald Trump
ማዱሮ ማናቸው? ለምንስ ተያዙ?
ኒኮላስ ማዱሮ ወደ ሥልጣን የመጡት በግራ ዘመሙ ፕሬዝደንት ሁጎ ቻቬዝ አመራር ወቅት ነበር። ማዱሮ የቻቬዝ የቬንዙዌላ ዩናይትድ ሶሻሊስት ፓርቲ መሪ ናቸው።
የቀድሞው የአውቶቡስ ሹፌር፤ ቻቬዝን ተክተው የቬንዙዌላ ፕሬዝደንት የሆኑት በአውሮፓውያኑ 2013 ነው።
ቻቬዝ እና ማዱሮ ቬንዙዌላን ላለፉት 26 ዓመታት መርተዋል። ፓርቲያቸው ብሔራዊውን ጉባዔ፣ አብዛኛውን ፍርድ ቤት እና የምርጫ ኮሚሽኑን ይቆጣጠራል።
ትራምፕ የቬንዙዌላው መሪ ወደ አሜሪካ ለሚመጡ በመቶ ሺዎች ለሚቆጠሩ ስደተኞች ተጠያቂ ናቸው ሲሉ ይወቅሳሉ።
በቬንዙዌላ ያለውን የምጣኔ ሀብት ቀውስ እና አፈና በመሸሽ ከ2013 በኋላ 8 ሚሊዮን የሚጠጉ ቬንዙላዊያን ከሀገራቸው እንደሸሹ ይገመታል።
ምንም እንኳ ትራምፕ ማስረጃ ባያቀርቡም ማዱሮ "እስር ቤት የአእምሮ በሽተኞች ማቆያዎች" ያሉ ግሰለቦች "ወደ አሜሪካ እንዲሸሹ አድርጓ" ሲሉ ይወቅሳሉ።
አክለው ወደ አሜሪካ የሚገቡ በተለይ ፌንታኒል እና ኮኬይን የተባሉ አደንዛዥ ዕፆች በቬንዙዌላ በኩል ነው የሚያልፉት ሲሉ ይሞግታሉ።
የአደገኛ ዕፅ ምሁራን እንደሚሉት ግን ቬንዙዌላ በዓለማችን የዕፅ ዝውውር ውስጥ ያላት ሚና ዝቅተኛ ሲሆን በሌሎች ሀገራት የሚመረቱ ዕፆች የሚተላለፉባት ሀገር ናት።
ማዱሮ በተደጋጋሚ የዕፅ አዘዋዋሪ ቡድን መሪ አለመሆናቸውን ተናገረው አሜሪካ "በዕፅ ላይ ከፈትኩት ያለችው ጦርነት" እሳቸውን ከሥልጣን ለማስወገድ እና የቬንዙዌላ የነዳጅ ክምችትን ለመቀራመት ያለመ እንደሆነ ይናገራሉ።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የዓለም መሪዎች ምን አሉ?
የዓለም ሀገራት መሪዎች የአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ የቬንዙዌላውን መሪ ስለመያዛቸው የሰጡት ምላሽ የተደበላለቀ ነው።
ትራምፕ መጠነ ሰፊ ባሉት ቅዳሜ በተደረገ ጥቃት ማዱሮ እና ሚስታቸው በአሜሪካ ኃይሎች ተይዘው ወደ አሜሪካ እንዲመጡ ተደርገዋል። ጥንዶቹ ኒው ዮርክ ውስጥ በዕፅ ዝውውር ወንጀል ተከሰዋል።
የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ኪር ስታርመር መንግሥታቸው ለማዱሮ አገዛዝ "እንባ እንደማያፈስ" ተናግረዋል። ስታርመር ጥቃቱን ዓለም አቀፍ ሕግን የጣሰ ነው ወይ በሚል የቀረበላቸውን ጥያቄ ሳይመልሱ ቀርተዋል።
የፈረንሳዩ ፕሬዝደንት ኢማኑኤል ማክሮን "የሽግግር ሒደቱ ሰላማዊ እና ዲሞክራሲያዊ ሊሆን ይገባል" ሲሉ በኤክስ ገፃቸው ፅፈዋል።
የቬንዙዌላ ጎረቤቶች ጥቃቱን ሲያወግዙት የማዱሮ የረዥም ጊዜ አጋር የሆኑት ቻይና እና ሩሲያም እርምጃውን ተቃውመዋል።
ቻይና በአንድ ሉዓላዊት ሀገር እና ፕሬዝደንቷ ላይ ጥቃት መድረሱን በተለመከተ "በጣም ደንግጠናል በፅኑም እንቃወማለን" የሚል አስተያየት ሰጥታለች።
ሩሲያ በበኩሏ አሜሪካ "የወረራ ድርጊት ፈፅማለች" ስትል ከሳለች። ከትራምፕ መንግሥት ጋር አለመግባባት ውስጥ የምትገኘው ኢራን ደግሞ ጥቃቱ "የሀገሪቱን ብሔራዊ ሉዓላዊነት የገፈፈ ነው" ብላለች።
የብራዚሉ ፕሬዝደንት ሉላ ዳ ሲልቫ በኤክስ ገፃቸው የአሜሪካ ድርጊት "የማይታለፍ መስመር የጣሰ ነው" ብለው የትራምፕ አስተዳደር "ዓለም አቀፍ ሕግን በጣሰ ሁኔታ ሀገራትን ዓለማችንን ማጥቃት ግጭት፣ ብጥብጥ እና አለመረጋጋት ውስጥ ይከታታል" ብለዋል።












