
የፎቶው ባለመብት, Reuters
የምስሉ መግለጫ, በኢራን ዋና ከተማ ቴህራን ውስጥ ነዋሪዎች የሁለት ሳምንቱን የተኩስ አቁም በመደገፍ አደባባይ ወጥተዋልኢራን እና አሜሪካ የሆርሙዝ ወሽመጥ ተከፍቶ
መርከቦች እንዲያልፉ የሚያስችል የሁለት ሳምንት የተኩስ አቁም ለማድረግ ተስማሙ።
ሁለቱ አገራት እዚህ ስምምነት ላይ የደረሱት፤ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ኢራን ወሳኙን የባሕር መተላለፊያ ማክሰኞ ሌሊት ድረስ ማትከፍት ከሆነ “ዛሬ ማታ ሙሉ ሥልጣኔ ይወድማል” የሚል
ዛቻ ካሰሙ ከሰዓታት በኋላ ነው።
አገራቱን ሲያሸማግሉ የነበሩት የፓኪስታን ጠቅላይ
ሚኒስትር ሼህባዝ ሻሪፍ የተኩስ አቁሙ ወዲያውኑ ገቢራዊ መሆን እንደሚጀምር አስታውቀዋል።
ፕሬዝዳንት ትራምፕ፤ ቴህራን ከባሕረ ሰላጤው
የሚወጡ የነዳጅ እና ሌሎች ምርቶች መተላለፊያ የሆነውን የሆርሙዝ ወሽመጥ የምትከፍት ከሆነ “ሁለት ሳምንት ለሚሆን ጊዜ ኢራን ላይ
የሚፈጸመውን ድብደባ እና ጥቃት ለማቆም” መስማማታቸውን ገልጸዋል።
ትራምፕ በትሩዝ ሶሻል ማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው
ባሰፈሩት ጽሑፍ በዚህ ጊዜያዊ የተኩስ አቁም የተስማሙት “ሁሉንም ወታደራዊ ግብ ስላሳኩ እና ከዚያም በላይ” ስላገኙ እንደሆነ ጠቅሰዋል።
በዚህ ሁለት ሳምንት ውስጥ ኢራን ከወታደራዊ
ኃይሏ ጋር በመቀናጀት በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል መርከቦች እንዲያልፉ ትፈቅዳለች።
ኢራን በበኩሏ 10 ነጥቦች ያሉት እቅድ ይፋ
አድርጋለች። በእቅዱ ውስጥ ከተካተቱ ጉዳዮች አንዱ ኢራን፣ ኢራቅ፣ ሊባኖስ እና የመን ውስጥም ጥቃቶች መቆም አለባቸው የሚል ነው።
ኢራን ላይ የተጣሉ ማእቀቦችን ለማንሳት “ሙሉ ቁርጠኝነት” እንዲኖር ማድረግ፣ በአሜሪካ የተያዙ የኢራን ገንዘብ እና ሀብቶችን መልቀቅ
እንዲሁም በአገሪቱ ላይ የደረሰው ውድመት “መልሶ የሚገነባበትን ወጪ የሚሸፍን ሙሉ የካሳ ክፍያ” መፈጸሙም በእቅዱ ውስጥ ተጠቅሰዋል።
የአገሪቱ መንግሥት፤ “ኢራን ማንኛውም የኒውክሌር
መሣሪያ እንዲኖራት ላለመፈለግ ሙሉ ቁርጠኛ ይሆናል” ሲል ቃሉን ሰጥቷል።
የኢራን የብሔራዊ ደኅንነት ጠቅላይ ምክር ቤት
ባወጣው መግለጫ፤ ይህ ”የኢራን ድል በፖለቲካዊ ድርድር ላይም ይጸናል” ብሏል።
የፓኪስታን ጠቅላይ ሚኒስትር ሻሪፍ፤ የተኩስ
አቁሙ እስራኤል በኢራን የሚደገፈውን ሄዝቦላህ ላይ ዘመቻ ከፍቻለሁ ባለችበት ሊባኖስ ውስጥም ተግባራዊ እንደሚሆን ተናግረዋል።
የእስራኤል ባለሥልጣናት ግን በሄዝቦላህ የተጋረጠው
ስጋት እስከሚወገድ ድረስ ከሊባኖስ እንደማይወጡ ተናግረዋል።
የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔትያናሁ የተኩስ አቁሙ ይፋ ከተደረገ ከጥቂት ሰዓታት በኋላ ባወጡት መግለጫ፤ “ኢራን በአፋጣኝ ሆርሙዝ ወሽመጥን የምትከፍት እንዲሁም አሜሪካ፣ እስራኤል
እና ሌሎች የቀጣናው አገራት ላይ የምትፈጽመውን ጥቃት የምታቆም መሆኗን ተከትሎ የሚሰነዘርባት ጥቃት ለሁለት ሳምንት እንዲቆም ፕሬዝዳንት
ትራምፕ ያስተላለፉትን ውሳኔ እስራኤል ትደግፋለች” ብለዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ መግለጫ አክሎም “የተኩስ
አቁሙ ሊባኖስን አያካትትም” ሲሉ እስራኤል እግረኛ ወታደሮቿን ባሰማራችባት ጎረቤት አገር ተፈጻሚ እንደማይሆን ገልጿል።
ፕሬዝዳንት ትራምፕ በኢራን የተኩስ አቁም ለማድረግ ውሳኔ ባሳለፉበት ሂደት ውስጥ እስራኤል ምን ያህል ተሳትፎ እንደነበራት ግልጽ አይደለም።