ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታኒያሁ ከሊባኖስ ጋር ድርድር እንዲጀመር አዘዙ

የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ሠራዊታቸው ከባድ ጥቃት እየፈጸመ ካለባት ሊባኖስ ጋር ሚኒስትሮቻቸው ቀጥተኛ ንግግር እንዲጀምሩ ማዘዛቸውን አስታወቁ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኤክስ ገጻቸው ላይ በእብራይስጥ ቋንቋ ባሰፈሩት ጽሁፍ ከሊባኖስ በኩል ቀጥተኛ ድርድር እንዲደረግ ቀረበ ባሉት “ተደጋጋሚ ጥሪ” መሠረት ካቢኔያቸው ንግግሩን “በአስቸኳይ” እንዲጀምር መጠየቃቸውን ገልጸዋል።
ኔታኒያሁ ጨምረውም የሚደረገው ንግግር “ሄዝቦላህን ትጥቅ ማስፈታት እንዲሁም በሊባኖስ እና በእስራኤል መካከል ሰላማዊ ግንኙነት እንዲፈጠር ማድረግ” ላይ የሚያተኩር ይሆናል ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታኒያሁ ይህንን ከማሳወቃቸው ቀደም ብሎ የሊባኖስ ፕሬዝዳንት ጆሴፍ አዎንስ ብቸኛው መፍትሄ ሁለቱ አገራት ተኩስ አቁም አድርገው “ቀጥተኛ ድርድር” ማካሄድ ነው ሲሉ ተናግረው ነበረ።
ፕሬዝዳንቱ የሊባኖስ የፀጥታ ኃይሎች “በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥም ቢሆን” ሕግ የማስከበር ሥራቸውን ሙሉ ለሙሉ ሲያከናውኑ መቆየታቸውን ተናግረዋል።
እስራኤል የኢራን አጋር የሆነውን የሊባኖስ ታጣቂ ቡድን ሄዝቦላህን ዒላማ በማድረግ ከአንድ ወር በላይ ጥቃት እየፈጸመች ሲሆን፣ እግረኛ ወታደሮቿንም በደቡባዊ ሊባኖስ አሰማርታለች።
እስራኤል ባለፉት ሁለት ቀናት ዋና ከተማዋ ቤይሩት ውስጥ እና በሌሎች በርካታ የሊባኖስ አካባቢዎች በፈጸመቻቸው ጥቃት ከ200 በላይ ሰዎች ተገድለዋል። ከአንድ ሺህ በላይ ሰዎች ደግሞ ጉዳት ደርሶባቸዋል።


















