ፕሬዝዳንት ትራምፕ ድርድሩ ካልተሳካ ለጦርነት እየተዘጋጁ መሆናቸውን ተናገሩ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ከኢራን ጋር ፓኪስታን ውስጥ ቅዳሜ የሚጀመረው ድርድር የማይሳካ ከሆነ ለቀጣይ ጦርነት እየተዘጋጁ መሆናቸውን ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ተናገሩ።
ፕሬዝዳንቱ በሰጡት ቃለ ምልልስ ላይ የሰላም ንግግሩ የማይሳካ ከሆነ በሚል አሜሪካ የጦር መርከቦቿን “ምርጥ የተባሉ የጦር መሳሪያዎችን እያስታጠቀች ነው” ሲሉ አመልክተዋል።
ፕሬዝዳንቱ ኒው ዮርክ ፖስት ከተባለው ጋዜጣ በስልክ ባደረጉት ቃለ ምልልስ ላይ እንደተናገሩት የድርድሩን ውጤት “በ24 ሰዓታት ውስጥ የምናውቅ ይሆናል” ብለዋል።
“መርከቦቻችንን በታሪክ ውስጥ ከተሠሩት ሁሉ የላቁ የጦር መሳሪያዎችን እያስታጠቅን ነው፤ እንዲያውም ከዚህ በፊት ሙሉ ለሙሉ ለመደምሰስ ከተጠቀምበንት ኃይል በከፍተኛ ደረጃ የበለጠ ነው።
"እናም ከስምምነት ላይ ካልደረስን እነዚህን የጦር መሳሪያዎች በጣም ውጤታማ በመሆነ መንገድ እንጠቀማቸዋለን” ሲሉ ፕሬዝዳቱ አክለዋል።
ኢራናውያንን በተመለከተም “የሚናገሩት እውነታቸውን ይሁን አይሁን ማወቅ የሚቻሉ ሕዝቦች አይደሉም" በማለት ያላቸውን ጥርጣሬ ገልጸዋል።
ለሁለት ሳምንት የሚቆይ የተኩስ አቁም አሜሪካ እና ኢራን ከደረሱ በኋላ ፓኪስታን ውስጥ የመጀመሪያውን ድርድር ቅዳሜ ዕለት ይጀምራሉ ተብሎ እየተጠበቀ ነው።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ፕሬዝዳንቱ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ኢራናውያን ”ዓለም አቀፍ የባሕር መተላለፊያዎችን በኃይል በመዝጋት ለማስገደድ ካሆነ ሌላ አማራጭ የላቸውም" ሲሉ ጽፈዋል።
አሁንም "በሕይወት ለመቆየታቸው ብቸኛው ምክንያት ለመደራደር ነው” በማለት ከስምነምት ላይ ከመድረስ ውጪ ምንም ማድረግ አይችሉም ብለዋል።
የኢራን ፓርላማ አፈ ጉበኤ ግን እስራኤል በሊባኖስ ላይ የምታካሂደው ጥቃት ሳይቆም እና የታገዱ የኢራን ሀብቶች ሳይለቀቁ ድርድር አይኖርም የሚል ቅድመ ሁኔታ አቅርበዋል።


















