"እናቴ መርዝ ልታበላኝ ስትል ደረስኩባት…" ሁላችንም ትንሽ ትንሽ 'እያበድን' ይሆን?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ይህ በአንድ መለስተኛ ኮሌጅ ያስተምር የነበረ የአንድ ምስኪን መምህር እውነተኛ ታሪክ ነው። ስሙን እንሸሽጋለን፤ መምህር ገሬ ብለን እንጠራዋለን።
ገሬ ገራገር መምህር ነበር። በተማሪ እና በአስተማሪ እኩል የሚወደድ።
ከዕለታት አንድ ቀን ነገር ተቀየረ። 'ከዕለታት አንድ ቀን' ሳይሆን ቀስ በቀስ ነው ነገር የተቀየረው።
ገሬ ሁሉንም ሰው መጠራጠር ጀመረ። የገዛ ሚስቱን ጭምር።
አንድ ቀን፣ ሰርግ ላይ ታዳሚው ብፌ እያነሳ እሱ ድንገት መሀል ላይ ቆመ። ባለቤቱ ግራ ገብቷት፣ 'ገሬ! አንሳ እንጂ ምን ያፈዝሃል?' አለችው።
ሳህኑን መለሰና ከሰርጉ አዳራሽ ውልቅ ብሎ ወጣ። አልተመለሰም። ማታ ሚስቱ እሳት ለብሳ እሳት ጎርሳ ምን ነካህ አለችው። ብፌው ተመርዞ እንደነበር ነገራት።
ባለቤቱ ግራ ገባት። ከዚያን ቀን ጀምሮ ነገሮች እየባሰባቸው መጣ።
ለምሳሌ ቢራ ሲጠጣ ቆርኪውን አይጥለውም። በተጎነጨ ቁጥር ቶሎ ብሎ ጠርሙሱን ይከድንበታል። ለሽንት መጸዳጃ ቤት ሲሄድ ያጋመሰውን ቢራ ይዞት ይሄዳል።
'ባልደረቦቼ መርዝ ይጨምሩበታል' ይላል።
ገሬ የጀበና ቡና ነፍሱ ነው። ረከቦት ላይ የሚደረደሩት ነጫጭ ስኒዎቹን ግን ደመኞቹ ናቸው። አያምናቸውም። ጢኒኒጥ ሰይጣኖች እንደ ምልምል ወታደር ተሰልፈው ነው የሚታዩት። ስለዚህ የራሱን ስኒ በኪሶ ይዞ ይዞራል።
መምህር ገሬ ከሁሉም በላይ የሚጠራጠረው የኮሌጁን ዲን ነው። ዲኑ ትልቅ ሰው ናቸው። የተከበሩ ባለትዳር። ገሬ ግን አያምናቸውም።
'እኚህ እርኩስ ዲን ሚስቴን ያማግጧታል' ብሎ ይበግናል፤ ይንጨረጨራል።
ከማስተማር ይልቅ እሳቸውን በመከታተል ጊዜውን ያጠፋል።
ኮሌጁ ውስጥ የመምህራን መኖርያ ግቢ አለ። ገሬ ምሽት ላይ በዛፍ ሥር ተደብቆ ለሰዓታት ይጠብቃቸዋል። ዲኑ የሚኖሩበት ብሎክ ከሱ ቤት ፈንጠር ብሎ ይገኛል።
የዘውትር ህልሙ ሚስቱ እና እሳቸው 'መርፌና ክር' ሆነው እጅ ከፍንጅ መያዝና 'አብደሃል እኮ' የሚሉትን ባልደረቦቹን አፍ ማስያዝ ነው።
ዘወትር አስተምሮ ወደ ቤት ሲገባ የቤቱን እጀታ በመሀረብ ነው የሚይዘው፤ የኮሌጁ ዲን አሻራ እንዳይጠፋ።
ታሪኩን ረዥም ቢሆንም እናሳጥረው።
ትልቅ ችግር የተፈጠረው የመምህር ገሬ ሚስት ያረገዘች ጊዜ ነበር። ዘጠኝ ወር አብሯት አማጠ። እየገፋ ያለውን ሆዷን እያየ 'ህምምም' ይላል፤ ያልጎመጉማል። ''እንተያያታለና!'' ዓይነት።
ሴት ልጁ ከተወለደች በኋላ ገሬ ክርስትና ሳይሆን ፎቶ እንድትነሳ አደረገ።
ፎቶዋን አባዝቶ አሳተመው። ከዚያ እያዞረ ለባልደረቦቹ ያሳያል። በየቢሯቸው እየሄደ። አንዳንዶቹን ከሚያስተምሩበት ክፍል ጭምር እያስጠራ።
"ልጄ ማንን እንደምትመስል ተመልከቱ፤ አሁንስ አመናችሁኝ?" አያለ ከቢሮ ቢሮ ይሮጣል።
በመጨረሻ ዲኑን በደብዳቤ ጭምር ከሰሳቸው። ከገዛ ባለቤቴ ጋር ተኝተዋል፣ ሚስቴን አማግጠውብኛል ነው የሚለው።
የልጁን ፎቶ በማስረጃነት ከአባሪ ደብዳቤው ጋር አያይዞ ነው የከሰሰው።
''ሚስቴ ጥቁር ናት። የተወለደችው ልጅ ግን ቀይ ናት። እንዴት ይሄ ሊሆን ቻለ?'' እያለ ገሬ 'አበደ'።
አስገራሚው ነገር ዲኑ ጠይም፣ ገሬ ግን ቀይ መሆናቸው ነው። ይህ ግን ለእርሱ አይታየው።
በእነዚያ ሁሉ ዓመታት መምህር ገሬ ሕክምና አግኝቶ አያውቅም።
አሁን ላይ መምህር ገሬ ምን ደረጃ ላይ እንዳለም አይታወቅም።
ይህ ልቦለድ የመሰለ በስኪዞፍሪኒያ የተሰቃየ መምህር ታሪክ አሁን አሁን የብዙዎችን ቤት አያንኳኳ ይመስላል።
ሁላችንም ትንሽ ትንሽ እያበድን ይሆን?
'የማሪያምን ብቅል እየፈጩ መዋል'
ስኪዞፍሪኒያ የሚባል የአእምሮ ጤና መታወክ እንዴት ያለ ነው?
ፕሮፌሰር ሰለሞን ተፈራ ፒኤችዲ ሠርተውበታል።
ለ20 ዓመት ተመራምረውበታል። በስኪዞፍሬኒያ የሚሰቃዩ በርካታ ታካሚዎች ነበሯቸው፤ አሏቸው።
ፕሮፌሰሩ ነገርን በአጭር የማስረዳት ፀጋ አላቸው። ይህን የአእምሮ በሽታ እንዲህ ይገልጹታል።
"ነገሩ የማርያምን ብቅል ሲፈጩ መዋል ነው" ይሉታል።
ምን ማለታቸው ነው?
"ስምህ የተጠራ መስሎህ ዞር ብለህ አታውቅም? ታማትራለህ። ማነው የጠራኝ ትላለህ። በመጨረሻ 'የማርያምን ብቅል እየፈጨሁ ነው' ትላለህ፤ ያቺ ላንተ ቅፅበት ናት። ለታማሚው ግን የቀን ተቀን ሕይወቱ ናት።''
በሌላ አነጋገር ስኮዞፍሪኒያ የ'ማሪያምን ብቅል ሲፈጩ እና ሲያስፈጩ እንደመዋል ያለ' ነው።
ለታማሚው ብቻ የሚታዩ ፍጡሮች አሉ። ለታማሚው ብቻ የሚሰሙ ድምጾች አሉ።እንግዳ ነገር ነው።
የገሃዱ ዓለም ከቅዠት ዓለም ጋር ሲደበላለቅ፤ ሲምታታ፣ ሲቀዣበር ስኪዞፍሪኒያ ይባላል። የእውነታው ዓለም ቅጥያ ሲኖረው ስኪዞፍሪንያ ማለት ነው።
ታማሚውን የሚያወሩት እነዚህ ምናባዊ ሰዎች፣ ምናባዊ ድምጾች አንዳንዴ ቀጥታ ትዕዛዝ ሊሰጡት ይችላሉ።
አይበለውና ይህ ትዕዛዝ 'የገዛ ሚስትህን ግደል' የሚል ቢሆንስ?
ለዚህ ነው ቶሎ መታከም ያለበት።
ይህ ችግር ቤታቸውን ያንኳኳባቸው ሰዎች፣ ታማሚው 'ከመናፍስት ጋር ይገናኛል' እያሉ ያሙታል።ሌላ ምን ይበሉ?
ቢቢሲ ጉዳዩን ይበለጥል ለመረዳት ባለሙያዎችን አነጋግሯል።
ከፕሮፌሰር ሰለሞን ሌላ ዶክተር ግንባሩ ገብረማርያምን አነጋግሯል።
ዶ/ር ግንባሩ ለ30 ዓመታት በጦር ኃይሎች እና በአማኑኤል ሆስፒታሎች በሐኪምነት አገልግለዋል።በተለይ በጦር ኃይሎች ሆስፒታል የአእምሮ ሕክምና ክፍል ኃላፊም ነበሩ። አሁን በስማቸው የሚጠራ የአእምሮ ጤና ክሊኒክ (Dr. Ginbaru Psychiatry Specialty Clinic)ን ይመራሉ።
በ30 ዓመታት አገልግሎታቸው ያላዩት ዓይነት ታካሚ የለም።አንድ ሁለቱን ታካሚዎች እስከዛሬም አይረሷቸውም።
ስኪዞፍሬኒያን እንድንረዳ ምልክቶቻቸውን እንዲህ ያጋሩናል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የገዛ ፎቁን ያፈረሰው ታካሚ
ይህ የስኪዞፍሪኒያ ታካሚ ባለፀጋ ነው። ፎቅ እያስገነባ ሳለ ካሜራ መገጠሙን አመነ። ቤተሰቦቹን አማከረ። ምን ብሎ?
'በዚህ ጅምር ሕንጻ ውስጥ ካሜራ ተገጥሟል፤ ግን ላገኘው አልቻልኩም' አላቸው። ሊሰሙት አልቻሉም። እንዲያውም፣ 'ተው እንጂ! ምን ነካህ?' አሉት።
እሱ መልሶ አምባረቀ። 'ምን ነካችሁ? ለምን አታምኑኝም? ምንድነው ችግራችሁ?' አላቸው። 'ይልቅ የተገጠመውን ካሜራ ፈልጉ- ዳይ!' አላቸው።
ቤተሰቡ አጉረምርሞ በጊዜ ሂደት ቸል አለው።
እሱ ግን ነገሩን ቸል አላለውም።
'ተገጠመ' የሚለውን ካሜራ ሲፈልግ ሲፈልግ አጣው። የቀን ሠራተኛ አሰማርቶ እያስገነባ ያለውን ሦስት ፎቅ አስፈረሰና እፎይ አለ።
በዚህ ጊዜ ነበር ቤተሰቡ አፋፍሶ ይህን ሰው ወደ ዶክተር ግንባሩ ዘንድ ያመጡት፤ ለሕክምና።
"አንተ ሐኪም አይደለህም፤ ከጠላቶቼ ጋር ተመሳጥረህ እየሠራህ ነው" ይላቸው ነበር፤ እስኪሻለው ድረስ።
''ናሳ ቺፕስ ቀብሮብኛል''
ይቺ ታካሚያቸው ደግሞ ከአሜሪካ ነበር የመጣችው። ቤተሰቦቿ በአገር ፀበል ትድናለች ብለው ነው ያስመጧት።
የአሜሪካ መንግሥት በናሳ በኩል ጭንቅላቴ ውስጥ ቺፕሰ ቀብሮብኛል ትላለች። ኢትዯጵያ መጥታም በሳተላይት እየከታተሏት እንደሆነ በጽኑ ታምናለች።
"እኛ መድኃኒኑቱን እየወሰዱ እንደ እምነታቸው ፀበልም ምንም እንዲከታተሉ ነው የምንመክረው" ይላሉ ዶክተር ግንባሩ።
ከዚች ታካሚያቸው የማይረሱት ደጋግማ 'ራጅ እና ኤምአርአይ' እንድተነሳ ትወተውት እንደነበረ ነው። ምክንያቱም ናሳ ቀበረብኝ የምትለው ቺፕስ በኤክስሬይ ግልጥ ብሎ እንደሚታይ ታምን ስለነበረ ነው።
ዶክተር ግንባሩ ለቢቢሲ እንዳረጋገጡት በርካታ የስኪዞፍሬኒያ ታካሚዎች በተለይ ከአውሮፓ፣ ከካናዳና አሜሪካ እርሳቸው ዘንድ ይመጣሉ። የብዙዎቹ ታሪክ ደግሞ ተመሳሳይነት አለው።
'ቺፕስ ቀብረውብኛል፤ ሞሳድ እየተከታተለኝ ነው፣ ሳተላይት ተገጥሞብኛል' የሚሉ ይበዛሉ።
ወደ ፕሮፌሰር ሰለሞን እንመለስ። እርሳቸው ለ20 ዓመታት በስኮዞፍርኒያ ዙሪያ ተመራምረዋል፤ አክመዋል።
ከዚህ ቀደም ያከሟቸውን ታማሚዎች፣ ስም ሳይጠሩ፣ አእምሯቸው እንዴት ያስብ እንደነበረ ያስረዱናል።
'ከማርስ ጨረር እየተለቀቀብኝ ነው'
ይህ የፕሮፌሰር ሰለሞን ታማሚ ከስካንዲኒቪያን አገር ፊዚክስ በፒኤችዲ ደረጃ ተምሮ የመጣ ነው። የዩኒቨርስቲ ሌክቸረርም ነበር።
አየሩ ላይ ጎጂ ጨረሮች ተለቀዋል ብሎ ያምናል። በተለይ እሱን ዒላማ ያደረጉ ጨረሮች በስፋት እየተለቀቁ ነው።
ከዚህ የተነሳ ማንኛውንም ኤሌክትሮኒክስ አይጠቀምም። ስልክ የለውም። ቴሌቪዥን አያይም፤ ራዲዮ አይሰማም።
"የተገለጥኩ መጽሐፍ ነኝ"
ይህ ታማሚ አገር ምድሩ የጓዳ ምሥጢሩን የሰማ ያወቀ ይመስለዋል።
"'ዶክተርዬ አሁን የኔ ኑሮ፣ ኑሮ ነውን? ሰው ምሥጢሩ ገሃድ ከወጣ ምን ቀረው?' ይለኛል" ይላሉ ፕሮፌሰር ሰለሞን።
ይህ ታማሚ መንገድ ላይ ሲሄድ ማንኛውም ሰው እሱ የሚያስበውን የሚያውቅ ይመስለዋል።
በእሱ ዓለም ሁሉም ፍጡር ገመናውን ያውቃል። "እኔ እኮ ሰው አይደለሁም፤ ሰው ማለት ምሥጢር ያለው ነው፤እኔን ግን የተገለጥኩ መጽሐፍ ነኝ" ይላቸው ነበር፤ ደጋግሞ።
"ጥርሴ ውስጥ ቺፕስ ቀበሩብኝ"
ይህ ታካሚም በቅርብ ጊዜ ከውጭ የመጣ ነው።
ውጭ አገር ጥርሱን ታክሞ ነበር። ሐኪሞቹ በድብቅ 'ቺፕስ' ቀበሩበት። የእሱ አእምሮ የሚያምነው እንደዚያ ነው።
ይህ ታማሚ ሲአይኤ ቺፕሱን በመጠቀም ከሕዋ (ስፔስ) ላይ ፎቶ እያነሱት እንደሆነ በጽኑ ያምናል። በተደጋጋሚ ናሳን ተጠያቂ ያደርጋል።
ፕሮፌሰር ሰለሞን እንደሚሉት፣ ታማሚዎቹ በጣም የተማሩ ሲሆኑ የሚታያቸው ነገርም በዚያው መጠን ውስብስብ የመሆን ዕድል አለው።
የታሸገ ውሃና ብስኩት ብቻ
ይህ ታማሚ ደግሞ ምግቦች በሙሉ ተመርዘዋል ብሎ ያምናል። በረሃብ ላለመሞት የታሸገ ውሃ እና ብስኩት ብቻ ይጠቀማል። ቁርስ ምሳ እራቱ ይኸው ነው። የታሸገ ውሃ፣ የታሸገ ብስኩት ወይም ሌላ።
የቅጥያ ዓለም
ፕሮፌሰር ሰለሞንም ይሁን ዶክተር ግንባሩ እንደሚያስረዱት ታማሚዎቹ ሁልጊዜም በቅጥያ ዓለም ነው የሚኖሩት።
ለጤነኛው የማይሰሙ ድምጾችን ይሰማሉ። ቴሌቪዥኑ፣ ራዲዮው ስለነሱ እያወራ እንደሆነ ያስባሉ።
የሥራ ባልደረቦቼ ይዶልቱብኛል፣ ሞሳድ ይከታተለኛል፣ መንግሥት ሊያስገድለኝ ነው...የሚሉ ብዙ አሉ።
ይህ የሚሆነው ደግሞ ከእውነታው ዓለም የሚቀነጨብ የቅጥያ ዓለም በታማሚዎቹ አእምሮ ስለሚፈጠር ነው።
የሚወዷቸውን ሰዎች ደግሞ ተጠያቂ የማድረግ ዝንባሌ ያሳያሉ።
"አሁን በቅርብ የነበረች ታካሚዬ የምታስበው ነገር በሙሉ ከጨረቃ ላይ በተገጠመ ማይክሮፎን ለሕዝብ እየተሠራጨ እንደሆነ ታምናለች፤ ለዚህ ተጠያቂ የምታደርገው ደግሞ ቤተሰቦቿን ነው" ይላሉ ዶክተር ግንባሩ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ስኪዞፍሬኒያ እና ጫትን ምን ያገናኛቸዋል?
ጫት እና ስኪዞፍሬኒያ ምንና ምን ናቸው?
ፕሮፌሰር ሰለሞን የጫት እና የስኪዞፍሬኒያን ግንኙነት በስፋት አጥንተዋል። በስመ ጥር ጆርናልም አሳትመዋል።
"ስኪዞፍሬንያ በጫት ምክንያት አይመጣም" ይላሉ። ነገር ግን ካለ ይባባሳል።
ምን ማለት ነው?
ይህ የአእምሮ በሽታ በዘር የሚመጣ (Genetic) ነው። ተጋላጭነቱ በተፈጥሮ ያለ ነው። ከጊዜ በኋላ የሚመጣ አይደለም።
የዘር ነው ስንል ግን በዘሩ ባለ ሰው ላይ ይገለጣል ማለት አይደለም። ኖሮብን ነገር ግን አንዳችም ጉልህ ምልክት ሳናሳይ ኖረን ልናልፍ እንችላለን።
ጫት ጉድ የምትሠራን እዚህ ጋ ነው።
"አደገኛ ዕጽ የሚወስዱ፣ ጫት የሚቅሙ ከሆነ ፀጥ ብሎ የቆየው በሽታ ነፍስ ይዘራል።ያንሰራራል።"
ይህ ብቻ አይደለም። ፕሮፌሰር ሰለሞን እንደሚሉት፣ ጫት አዘውትረው በሚቅሙት ላይ መድኃኒቱ አይሠራም፤ ሕመማቸውም ይባባሳል።
ቢሻላቸውም ጫት ከቃሙ ያገረሻል። የመድኃኒቶቹን ውጤታማነት በእጅጉ ይቀንሰዋል። እንዲያውም ሕመሙ ጽኑ (Chronic) ይሆናል።
በአጭሩ ስኪዞፍሬኒያና ጫት እሳትና ጭድ ናቸው። ለዚያ ይሆናል በርካታ የስኪዞፍሪኒያ ታማሚዎችን ጫት በሚዘወተርባቸው አካባቢዎች የምናገኘው።
ዶክተር ግንባሩ በአጭሩ፣ ስኪዞፍሬኒያ ያለበት ሰው ጫት ከቃመ 'እሳት ላይ ቤንዚል አርከፈከፈ' ይላሉ።
እርኩስ መንፈስ ነው?
ዶክተር ሰለሞን ቡታጀራ በሚገኙ 320 የስኪዞፍሬኒያ ታማሚዎች ላይ ምርምር አድርገዋል። ታማሚዎቹን ለአምስት ዓመታት ሳያቋርጡ ተከታትለዋቸው ምርምር ሠርተዋል።
የጥናታቸው ውጤት ሁለት ነገር አሳይቷል።
አንደኛ ታማሚዎች ካልታመሙት በሁለት እጥፍ የመሞት ዕድል አላቸው።
ሁለተኛ ስኪዞፍሬኒያ ታመው መድኃኒት የሚወስዱ ረዘም ላለ ዕድሜ መኖር ቻሉ።
ጥናቱን በሠሩባቸው ዓመታት ውስጥ ብቻ በቡታጀራ 32 ወንዶችና 4 ሴቶች በድምሩ 38 የስኪዞፍሬኒያ ታማሚዎች ሞቱ።
እሱ አይደለም የሚገርመው። መድኃኒት የማይወስዱት መድኃኒት ከወሰዱት ጋር ሲነጻጸሩ የማይወስዱት በ20 ዓመት ቀድመው ይሞታሉ።
ጥናቱ ወስብስብ ጉዳዮችን ያነሳል። ለዚህ ዘገባ ሲጨመቅ ግን ይኸው ነው። መድኃኒት መውሰድ ምርጫ መሆን የለበትም።
እናቴ በመርዝ ልትገድለኝ ታስባለች
ፕሮፌሰር ሰለሞን በዓመታት ውስጥ ከነበሯቸው ታካሚዎች የማይዘነጓቸው አሉ።
አንዲት ወጣት ወላጅ እናቷ መርዝ ሊያበሏት እንደሆነ ታምናለች። ስለዚህ የእናቷን ምግብ አትበላም።
በተከታታይ አንድ ድምፅ በጆሮዋ ያንሾካሹካል። 'እናትሽ መርዝ ልታበላሽ ነው' የሚል።
"ታማሚዎች 100% የሚያዩትንና የሚሰሙትን ያምኑታል" ይላሉ ፕሮፌሰር።
"ሲሻላቸው ግን 'እንዴት እንደዚያ ላስብ ቻልኩ? እንዴት እናቴን ልጠራጠር ቻልኩ?' ይሉኛል።"
ውጤታማ ሕክምና ሲደረግ ወደቀልባቸው ይመለሳሉ።
መመለስ ብቻ ሳይሆን ምን ሆነው እንደነበር ሊረዱም ይችላሉ።ይህ አስገራሚ ነገር ነው። በእርግጥ ስኪዞፍሬኒያ የታመሙ ሲሻላቸው ታመው እንደነበረ ያውቃሉ?
''አዎ! በርካታ ሕመምተኞች አሉኝ። ሲያገግሙ የሚሉኝ እንደዚያ ነው። እኔም የሕክምናውን ውጤታማነት የምለካው በዚያ ነው" ሲሉ ፕሮፌሰር ሰለሞን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ይህ ብዙዎች እርኩስ መንፈስ የሚመስላቸው የአእምሮ ጤና እክል በፍፁም ያለ መድኃኒት ማከም አይቻልም።
ፀረ- ሳይኮቲክስ የሚባሉ መድኃኒቶች አሉ። ለስኪዞፍሬኒያ ፍቱኑ መድኃኒት እሱ ነው። ከዚያ ግን በቴራፒ ሊደገፍ ይችላል።
አደጋ ሊያደርሱ ይችላሉ?
ፕሮፌሰር ሰለሞን ይህን ጉዳይ ለማብራራት ባልተለመደ ሁኔታ ቁጥብ ይሆናሉ። ያለምክንያት አይደለም። መገለልን ያስከትላል ብለው ስለሰጉ ነው።
"በእኛ አገር እንኳ ቤተሰባቸውን የገደሉ ታማሚዎች እናውቃለን' ይሉና፣ ዝርዝር ነገር ከመናገር ይቆጠባሉ።
ታማሚዎቹ ያልታሰበ ከባድ አደጋ ሊያደርሱ የሚችሉት ግን ካልታከሙ ብቻ ነው።
አደጋ ቢያደርሱ እንኳ ተጠያቂ ሊደረጉ አይችሉም። በጤናማ አእምሮ ስላልፈጸሙት ሕጉ ''Not guilty by insanity'' ብሎ ነጻ ያደርጋቸዋል።
ባደጉ አገሮች የስኪዞፍሬኒያ ታማሚዎች ሕመማቸው ሲጸና ዕድሜ ልክ እየታከሙ የሚኖሩባቸው የሆስፒታል ማገገሚያዎች አሉ።
ለሕብረተሰቡ አደጋ ናቸው ሲባል ጥብቅ ማገገሚያ (Maximum Security Hospitals) እንዲገቡም ይደረጋል።
ይሄ ፎረንሲክ ሳይካትሪ ይባላል። ሐኪሙ ''በቃ ይህ ሰው አደጋ ሊያደርስ ስለሚችል ሆስፒታል ነው መኖር ያለበት'' ብሎ ሊበይን ይችላል።" ይላሉ ፕሮፌሰር ሰለሞን።
ዶክተር ግንባሩ ኅብረተሰቡ እግረ ሙቅ አድርጎ የደበቃቸው ታማሚዎችን ሲያስቡ ራሳቸው መልሰው ይታመማሉ።
ማኅበረሰባችን ከአእምሮ ጤና ጋር በተያያዘ ብዙ ይቀረዋል ባይ ናቸው።
ክርስቲያኑ 'መተት' ተሠርቶበት ነው ይልኻል፤ ሙስሊሙ 'ስህር' ተደርጎበት ነው ይላል። ችግር ነው ብቻ። ቶሎ ይዘዋቸው አይመጡም።በየቀኑ የማየው ነገር ያሳዝናል" ይላሉ።
የአእምሮ ሕመም ታማሚው አመመኝ የሚልበት አለመሆኑ ነው ሌላው ችግር።
"ሆድህን ቢቆርጥህ ሮጠህ ሐኪም ቤት ሄደህ 'ዶክተር እዚህ ጋ አመመኝ' ትለኛለህ፤ አእምሮውን የታመመ ሰው ግን መታመሙን አያውቅም። እየተሰቃየ ነው።ቤተሰብ ካላወቀለት ያ ሰው ስቃይ ላይ ነው።"
"እባካችሁ በየእምነታችሁ እያከማችኋቸውም ቢሆን ሐኪም ቤት አምጧቸው፤ ሁለቱ አይጣሉም" ሲሉ ዶ/ር ግንባሩ ይማጸናሉ።
የፕሮፌሰር ሰለሞንም ተማጽኖ ከዚህ አይለይም።















