ባህሬን “ከኢራን አብዮታዊ ዘብ ጋር ግንኙነት ያላቸው” 41 ሰዎችን አሰረች

የባህሬን የአገር ውስጥ ሚኒስቴር ከኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ ጋር “ግንኙነት ያላቸው” 41 ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን አስታወቀ። የባህሬን ዜና ወኪል ያወጣው የሚኒስቴሩ መግለጫ እንደሚያስረዳው ግለሰቦቹ የታሰሩት “የደኅንነት አካላት ባደረጉት ምርመራ እና ባጠናቀሩት የደኅንነት ሪፖርት” መሠረት ነው።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. ኢራን ከሰሞኑ አሜሪካ የፈጸመችው ጥቃት "ለዲፕሎማሲ ያላትን ፍላጎት ጥርጣሬ” ውስጥ ከትቷል አለች

    የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    አሜሪካ እና ኢራን አንዳቸው በሌላኛቸው ላይ ጥቃት በፈጸሙ በኋላ በትናትናው ዕለት ከቱርክ አቻቸው ጋር የተነጋገሩት የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ፤ ዋሽንግተን “የተኩስ አቁም ስምምነቱን በተደጋጋሚ መጣሷ” ለዲፕሎማሲያዊ መፍትሔ ያላትን “ቁርጠኝነት ጥርጣሬ ውስጥ መክተቱን” ተናገሩ።

    አራግቺ፤ ከቱርክ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሃካን ፊዳን ጋር ያደረጉት የስልክ ንግግር በዋነኛነት ትኩረት ያደረገው ቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ እንደነበር ባወጡት መግለጫ አስታውቀዋል።

    መግለጫው እንደሚያስረዳው፤ የኢራኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አሜሪካ ከሰሞኑ በፋርስ ባሕረ ሰላጤ አካባቢ “የጀብድ እንቅስቃሴ” ማድረጓን ጠቅሰዋል። “ከፍተኛ የአሜሪካ ባለሥልጣናት ጸያፍ እና ስድብ ንግግሮችን” ማድረጋቸውን በማንሳትም ከስሰዋል።

    አሜሪካ እና ኢራን ሐሙስ ምሽት አንዳቸው በሌላኛቸው ላይ ጥቃት ፈጽመዋል። ጥቃቱን ማን ቀድሞ እንደጀመረው አልተረጋገጠም።

    ኢራን ግን ወደ ሆርሙዝ ወሽመጥ እየተጠጉ የነበሩ ነዳጅ ጫኝ እና ሌላ መርከቧ በአሜሪካ ዒላማ እንደተደረጉባት ገልጻለች። በተለያዩ የባሕር ዳርቻ አካባቢዎች ላይ የአየር ጥቃት መፈጸሙን አስታውቃለች።

    አሜሪካ በበኩሏ ወሽመጡ ላይ በሰፈረው ሚሳዔል ተሸካሚ አውዳሚ መርከቧ ላይ ኢራን ለፈጸመችባት ጥቃት “የራስን መከላከል ጥቃቶችን” በማድረስ ምላሽ መስጠቷን ትናገራለች።

    የኢራኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፤ ከሰሞኑ የአሜሪካ ኃይሎች በፋርስ ባሕረ ሰላጤ “ውጥረት የማባባስ እና የተኩስ አቁም ስምምነቱን በተደጋጋሚ የመጣስ” ተግባራት ላይ መሰማራቸውን አንስተዋል።

    በዚህም ምክንያት “አሜሪካ ለዲፕሎማሲው መንገድ ስላላት ፍላጎት እና ቁርጠኝነት የተፈጠረው ጥርጣሬ ጨምሯል" እንዳሉ በመግለጫው ሰፍሯል።

    “የአሜሪካ አጥፊ አካሄድ የዲፕሎማሲውን ሂደት የሚጎዳ እና የኢራን ሕዝብ በአሜሪካ ዓላማ ላይ ያለውን ጥርጣሬ የሚያባብስ” እንደሆነም ተናግረዋል።

    የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ይህንን ወቀሳ ያሰሙ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አሜሪካ ላቀረበችው የስምምነት እቅድ የኢራንን ምላሽ እየጠበቁ መሆኑን በተናገሩ ማግሥት ነው። እስካሁን ድረስ ኢራን ምላሽ ስጥታ እንደሆነ አልተገለጸም።

    ትራምፕ ከሐሙስ ዕለቱ ጥቃት በኋላ በማኅበራዊ ደዲያ ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ፤ “ዛሬ በድጋሚ እንደዘረርናቸው ሁሉ፤ ስምምነታቸውን በፍጥነት ካልፈረሙ ወደፊት በበለጠ ጥንካሬ እና ከፍ ባለ ኃይል እንዘርራቸዋለን” በማለት ተናግረዋል።

  2. ባህሬን “ከኢራን አብዮታዊ ዘብ ጋር ግንኙነት ያላቸው” 41 ሰዎችን አሰረች

    የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ ወታደሮች

    የፎቶው ባለመብት, EPA

    የባህሬን የአገር ውስጥ ሚኒስቴር ከኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ ጋር “ግንኙነት ያላቸው” 41 ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን አስታወቀ።

    የባህሬን ዜና ወኪል ያወጣው የሚኒስቴሩ መግለጫ እንደሚያስረዳው ግለሰቦቹ የታሰሩት “የደኅንነት አካላት ባደረጉት ምርመራ እና ባጠናቀሩት የደኅንነት ሪፖርት” መሠረት ነው።

    በተደረገው ምርመራ “ከኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ እና ከዊላያት አል ፋቂህ ርዕዮተ ዓለም ጋር ግንኙነት ያለው ቡድን” መገኘቱን የባህሬን መንግሥት ገልጿል።

    የአሁኑ እርምጃ የአገሪቱ አቃቤ ሕግ ከዚህ ቀደም “ውጭ አካላት መሰለልን እና የኢራን ጥቃቶችን መደገፍን” በተመለከቱ ጉዳዮች ላይ ሲካሂድ ከነበረው ምርመራ ጋር የተያያዘ እንደሆነ በመግለጫው ተጠቅሷል።

    “41 የዋናው ቡድን አባላት በቁጥጥር ስር መዋላቸውን እና ሕጋዊ እርምጃ እየተወሰደባቸው መሆኑንም” እንዳስታወቀ የዜና ወኪሉ ዘግቧል።

    የባህሬን መንግሥት ከሁለት ሳምን በፊት "የኢራንን ጠበኛ እርምጃዎች በማድነቅ፣ በመደገፍ ወይም ከውጭ አካላት ጋር ግንኙነት በመፍጠር" የተከሰሱ 69 ግለሰቦችን ዜግነት መሠረዙን አሰስታውቆ ነበር።

    የካቲት ላይ በአሜሪካ እና እስራኤል ጦርነት የተከፈተባት ኢራን የአጸፋ እርምጃ የወሰደችው ባህሬን እና ሌሎች የባሕረ ሰላጤው አገራት ላይ ጥቃት በመፈጸም ነው።

  3. የኢራን ፓርላማ ጦርነቱ ከተጀመረ ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ በኦንላይን ሊሰበሰብ ነው

    የኢራን ፓርላማ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የኢራን ፓርላማ አሜሪካ እና እስራኤል ጦርነት ከከፈቱበት የካቲት ወዲህ የመጀመሪያ የሆነውን ስብሰባውን ነገ እሁድ ሊያካሂድ ነው።

    ከሦስት ወር ገደማ በኋላ የሚካሄደው ስብሰባ በቪዲዮ ኮንፈረንስ አማካኝነት እንደሚደረግ የፓርላማው የፕሬዝዳንት ቃል አቀባይ አባስ ጎደርዚ ተናግረዋል።

    የኢራን ፓርላማ የመጨረሻውን መደበኛ ስብሰባውን ያካሄደው ጦርነቱ ከመጀመሩ 11 ቀናትን አስቀድሞ የካቲት 20/2018 ዓ.ም. ነበር።

    ነገ የሚካሄደው ስብሰባ ከ82 ቀናት በኋላ የሚደረግ ነው። ፓርላማው ያወጣው መግለጫ እንደሚያስዳው፤ የነገው ስብሰባ ዋነኛ አጀንዳዎች "የገበያ አለመረጋጋት፣ የሕዝብ ስጋቶች እና ሰሞነኛ የዋጋ ንረት" ናቸው።

    የኢራን እስላማዊ ምክር ቤት ከጦርነቱ በፊት በነበረው የመጨረሻ ስብሰባው የተወያየው ስለ ዓመታዊ ረቂቅ የበጀት ማሻሻያ ነበር።

    ፓርላማው ለረጅም ጊዜ ስብሰባ ሳያካሂድ የቆየው "በደኅንነት ጉዳዮች" የተነሳ እንደሆነ ተገልጿል።

    ዘገባዎች እንደሚያመለክቱት፤ አሜሪካ እና ኢራን የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ከደረሱ በኋላ የኢራን ፕሬዝዳንት እና የካቢኔ አባላት አልፎ አልፎ በአካል በመገኘት ስብሰባዎችን ሲያካሂዱ ቆይተዋል።

    በመጀሪያው ቀን የአሜሪካ እና የእስራኤል ጥቃት የተገደሉትን አያቶላህ አሊ ኻሜኒ የሚተካ መሪ ለመምረጥ የተደረገው የሊቃውንት ጉባኤ ድምጽ የመስጠት ሂደት የተካሄደው በኦንላይን እንደነበር ይታወሳል።

  4. ፕሬዝዳንት ፑቲን፤ ዩክሬን "በመላው የኔቶ ጥምረት መሣሪያ የሚቀርብላት ጠብ ጫሪ ኃይል" ነች አሉ

    ሩሲያ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን

    የፎቶው ባለመብት, EPA/Shutterstock

    ሩሲያ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ዛሬ በሞስኮ በተከበረው የድል በዓል ላይ ባደረጉት ንግግር ዩክሬን ውስጥ የሚያካሂዱት ጦርነት ትክክለኛለት ገልጸው፤ የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳንን (ኔቶ) አወገዙ።

    በመቶዎች የሚቆጠሩ የጦር ኃይል አባላት እና ጥቂት የዓለም መሪዎች በተገኙበት ክብረ በዓል ላይ ንግግር ያደረጉት ፑቲን፤ ዩክሬን ውስጥ እየተዋጉ ያሉት “ፍትሐዊ” ጦርነት መሆኑን ገልጸዋል።

    ዩክሬንን "በመላው የኔቶ ጥምረት መሣሪያ የሚቀርብላት እና የምትደገፍ ጠብ ጫሪ ኃይል" እንደሆነች ሲናገሩም ተደምጠዋል።

    ፑቲን ንግግር ያደረጉበት በዓል፤ ሶቪየት ኅብረት ናዚ ጀርመንን ላይ የተቀዳጀችበት ድል የሚከበርበት የሩሲያ ትልቁ ብሔራዊ በዓል ነው። የዘንድሮው የበዓሉ አከባበው ከዚህ ቀደም ከነበረው አንጻር የቀዘቀዘ ነው።

    ቀኑ ከመድረሱ አስቀድሞ ሩሲያ እና ዩክሬን የሦስት ቀናት ተኩስ አቁም ለማድረግ መስማማታቸውን የአሜሪካ ዶናልድ ትራምፕ አርብ ዕለት አስታውቀዋል።

    ከበርካታ ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በዘንድሮው የሞስኮ የድል በዓል ሰልፍ ላይ መሣሪያ የጫኑ ተሽከርካሪዎች ወይም ባለስቲክ ሚሳዔሎች አልታዩም። የጦር ኃይል አባላት ግን በጥብቅ የደኅንነት ጥበቃ ሥር ሆነው በከተማዋ ቀይ አደባባይ አካባቢ ተሰልፈው አልፈዋል።

    ፑቲን በክብረ በዓል ንግግራቸው፤ የሩሲያ ወታደሮች “በመላው የኔቶ ጥምረት መሣሪያ የሚቀርብለት እና የሚደገፍን ጠብ ጫሪ ኃይል ላይ እየተጋፈጡ ነው። ይህ ሁሉ ሆኖም ጀግኖቻችን ወደ ፊት እየገሰገሱ ነው" ብለዋል።

    ወታደራዊ ሠልፍ

    የፎቶው ባለመብት, MAXIM SHIPENKOV/EPA/Shutterstock

    ፑቲን በመሪዎች መሃል

    የፎቶው ባለመብት, EPA/Shutterstock

    ተዋጊ ጄቶች

    የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images

  5. በኢራን ኻርግ ደሴት ነዳጅ ወደ ባሕር ፈስሶ ሊሆን እንደሚችል የሳተላይም ምሥሎች አሳዩ

    በኻርግ ደሴት ያጋጠመውን የነዳጅ መፍሰስ የሚያሳይ የሳተላይ ምስል

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    ኢራን ለውጭ ገበያ ከምታቀርበው የነዳጅ ምርት 90 በመቶ የሚሆነው በሚተላለፍበት ኻርግ ደሴት አቅራቢያ በርካታ ስኩዌር ኪሎ ሜትር ስፋት የሚሸፍን የነዳጅ መፍሰስ የሚመስል ክስተት ማጋጠሙን የሳተላይት ምሥሎች አሳዩ።

    የማሪታይም መረጃ ተቋም የሆነው ‘ዊንድዋርድ ኤአይ’ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አሚ ዳንኤል ለአሶሺዬትድ ፕሬስ እንደተናገሩት፤ ነዳጅ እንደሆነ የሚታመነው ፍሰት 71 ካሬ ኪሎ ሜትር ይሸፍናል። አሁንም ነዳጅ እየፈሰሰ መሆኑን ምሥሎቹ መጠቆማቸውንም ገልጸዋል።

    እንደ ዳንኤል ገለጻ፤ ፍሰት ማጋጠሙ ከታወቀበት ማክሰኞ ዕለት አንስቶ 80,000 በርሜል ነዳጅ ፈስሷል ተብሎ እንደሚገመት አስረድተዋል። ነዳጁ ወደ ደቡብ ምዕራብ አቅጠጣጫ እየተስፋፋ መሆኑን የሚናገሩት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፤ በሁለት ሳምንት ጊዜ ውስጥ ወደ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች፣ ኳታር ወይም ሳዑዲ አረቢያ የባሕር ዳርቻዎች ሊደርስ እንደሚችል መናገራቸውን ኤፒ ዘግቧል።

    ‘ኮንፍሊክት ኤንድ ኢንቫይሮመንት ኦብዘርቫቶሪ’ በተባለው ተቋም ተመራማሪ የሆኑት ሎዮን ሞርላንድ በበኩላቸው፤ ፍሰቱ 45 ስኩዌር ኪሎ ሜትር ይሸፍናል ተብሎ እንደሚገመት ለሮይተርስ ተናግረዋል።

    በደሴቱ የነዳጅ መፍሰስ የተከሰተው በነዳጅ ምርት ላይ ባጋጠመ ችግር፣ በአየር ጥቃት ወይም በሌላ ምክንያት ስለመሆኑ እስካሁን በውል አልታወቀም። ኢራን ጦርነት በተጀመረበት ወቅት የአሜሪካ ኃይሎች በደሴቱ የሚገኙ ወታደራዊ ዒላማዎችን ማውደማቸውን ገልጸው ነበር።

    ነዳጅ እየፈሰሰ እንደሆነ የታወቀው የአሜሪካ ባሕር ኃይል ወደ ኢራን ደሴቶች ለመግባት እና ለመውጣት የሚሞክሩ መርከቦች ጉዞ ላይ እገዳ በጣሉበት ወቅት ነው።

  6. ኢራን የአሜሪካን የባሕር እገዳ ለተጨማሪ አራት ወራት መቋቋም እንደምትችል የሲአይኤ ሪፖርት ማሳየቱ ተዘገበ

    መርከቦች

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    ኢራን፤ የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ኢኮኖሚያዊ ጫና ለማሳደር እና ስምምነት ላይ እንድትደርስ ለማስገደድ በሚል የጣለውን የባሕር ጉዞ እገዳን ለተጨማሪ ወራት መቋቋም ትችላለች የሚል ድምዳሜ ላይ መደረሱን የአሜሪካው የስለላ ተቋም ሲአይኤ ሪፖርት አሳየ።

    የአሜሪካው ጋዜጣ ዋሽንግተን ፖስት እና የዜና ወኪሉ ሮይተርስ ያወጡት ዘገባ እንደሚያሳየው፤ ኢራን ወደ ወደቦቿ የሚደረግ ጉዞ ላይ በተጣለው እገዳ ምክንያት ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ውስጥ ሳትገባ ቢያንስ ለሦስት ወይም ለአራት ወራት መቋቋም እንደምትችል ሲአይኤ ባደረገው ትንተና ደምድሟል።

    እንደ ዋሽንግተን ፖስት ዘገባ፤ የፕሬዝዳንት ትራምፕ ጦርነቱን የመቋጨት ተስፋ ላይ ጥያቄ ያስነሳው ይህ የግምገማ ሰነድ ለዋይት ሀውስ የቀረበው በዚህ ሳምንት ነው። የግምገማ ሰነዱ እዚህ ድምዳሜ ላይ መድረሱ በነዋሪዎች ዘንድ ከፍተኛ ድጋፍ የሌለውን ጦርነት ለመቋጨት እየሞከረች ያለችው አሜሪካ ኢራን ላይ ያላት ተጽዕኖ የመፍጠር አቅም ውስን መሆኑን እንደሚያመለክት ሮይተርስ ያነገጋራቸው አንድ ምንጭ ተናግረዋል።

    በተጨማሪም የሲአይኤ ሪፖርት፤ ኢራን በአሜሪካ እና እስራኤል ለሳምንታት የቆየ ድብደባ ቢፈጸምባትም አሁንም ከፍተኛ የባለስቲክ ሚሳዔል አቅም እንዳላት ማሳየቱን ዋሽንግተን ፖስት ዘግቧል።

    ኢራን ከጦርነቱ በፊት ከነበሯት ተንቀሳቃሽ ሚሳዔል ማስወንጨፊያዎች ውስጥ 75 በመቶውን እንዲሁም ከሚሳዔል ክምችቷ 70 በመቶውን አሁንም እንደያዘች ተገልጿል።

    ጋዜጣው ያነጋገራቸውን አንድ ባለሥልጣን፤ የኢራን መንግሥት ምድር ሥር ያሉ የመሣሪያ ማከማቻዎችን መልሶ መክፈት መቻሉን እና የተጎዱ ሚሳዔሎችን መጠገኑን ገልጸዋል። ጦርነቱ ከመጀመሩ በፊት ለመጠናቀቅ ተቃርበው የነበሩ አዲስ ሚሳዔሎችን ጭምር እየገጣጠመ መሆኑን የሚያሳዩ ማስረጃዎች መኖራቸውን ተናግረዋል።

    ለሮይተርስ ምላሽ የሰጡ አንድ ከፍተኛ የስለላ ባለሥልጣን ግን የሲአይኤ ሪፖርት አሳይቷል የተባለውን ድምዳሜ “ሐሰት” ሲሉ አጣጥለውታል። ወደ ኢራን ወደቦች የሚደረግ ጉዞ ላይ የተጣለው እገዳ “ንግድን በማቋረጥ፣ ገቢን በማውደም እና ሥርዓታዊ የኢኮኖሚ ውድቀትን በማፋጠን ኢራን ላይ እውነተኛ እና እየተደራረበ የሚሄድ ጉዳት እያደረሰ ነው" ብለዋል።

  7. ፕሬዝዳንት ትራምፕ አሜሪካ ላቀረበችው የድርድር ዕቅድ የኢራንን ምላሽ እየጠበቁ መሆኑን ተናገሩ

    ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ

    የፎቶው ባለመብት, EPA

    ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጦርነቱን ለመቋጨት በቀረበው የአሜሪካ የስምምነት ዕቅድ ላይ የኢራንን ምላሽ ለማግኘት እየጠበቁ መሆኑን ለጋዜጠኞች ተናገሩ።

    አሜሪካ ባለ 14 ነጥብ የስምምነት ዕቅድ አዘጋጅታ ወደ ኢራን መላኳ የተሰማው በዚህ ሳምንት ነበር። የመግባቢያ ስምምነት እንደሚሆን የተገለጸው ይህ ሰነድ ከያዛቸው ነጥቦች መካከል ኢራን ኒውክሌር የማበልጸግ ተግባሯን እንድታቆም ስለማድረግ የሚለው ይገኝበታል።

    ኢራን ላይ የተጣሉ ማዕቀቦችን ማንሳት እና በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል የሚደረግ ነጻ ጉዞን መመለስም ተካትተዋል። በመጨረሻ ይደረሳል ተብሎ የሚጠበቀው የሰላም ስምምነት የሚመሠረተው በዚህ ዕቅድ ውስጥ በተካተቱት ነጥቦች ላይ እንደሚሆንም ተዘግቦ ነበር።

    ኢራን ዕቅዱን እየገመገመች መሆኑን በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ በኩል አስታውቃ ነበር። ይሁን እንጂ ሁለቱ አገራት ሐሙስ ምሽት አንዳቸው በሌላኛቸው ላይ ጥቃት ፈጽመዋል።

    ትናንት አርብ ምሽት ኢራን ለዕቅዱ ምላሽ ሰጥታ እንደሆነ የተጠየቁት ትራምፕ፤ “ምናልባት ዛሬ ምሽት [ምላሻቸውን] እንሰማለን" ብለዋል።

    ኢራን ሆን ብላ ድርድሩን እያጓተተች ነው ብለው ያምኑ እንደሆን የተጠየቁት ትራምፕ፤ "አላውቅም" የሚል ምላሽ መስጠታቸውን ሲኤንኤን ዘግቧል። "በቅርቡ እናውቃለን" ሲሉም አክለዋል።

    ትራምፕ ይህንን ከማለታቸው ሰዓታትን አስቀድሞም የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ኢራን ዛሬ ምላሽ ትሰጣለች ተብሎ እንደሚጠበቅ ተናግረው ነበር።

    ሚኒስትሩ ጣሊያን ውስጥ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት "ምላሻቸውን ዛሬ የሆነ ሰዓት ላይ እንሰማለን ብለን እንጠብቃለን. . . ምላሻቸውም የምር እንደሚሆን ተስፋ አደርጋለሁ” ብለዋል።

    እስካሁኑ ሰዓት ድረስ ግን ኢራን ምላሽ ስለመስጠቷ አልተረጋገጠም።

  8. አሜሪካ ሁለት የኢራን ነዳጅ ጫኝ መርከቦችን መምታቷን አስታወቀች

    ከተመቱት መርከቦች አንዱ

    የፎቶው ባለመብት, @CENTCOMArabic

    የምስሉ መግለጫ, ጥቃት ከተፈጸመባቸው የኢራን መርከቦች አንዱ

    አሜሪካ እና ኢራን ጦርነት ለማቆም በተዘዋዋሪ ንግግር እያደረጉ ባሉበት በአሁኑ ጊዜ የሁለቱ አገራት ኃይሎች አልፎ አልፎ እየተጋጩ መሆናቸውን ዘገባዎች አመለከቱ።

    ዛሬ አርብ አሜሪካ በሆርሙዝ ወሽመጥ በኢራን መርከቦች ላይ የጣለችውን እገዳ ጥሰው ለማለፍ የሞከሩ ሁለት ነዳጅ ጫኝ መርከቦችን መምታቷን አስታውቃለች።

    የኢራን ዜና ወኪል የሆነው ፋርስ ደግሞ በሆርሙዝ መተላለፊያ ላይ በኢራን ኃይሎች እና በአሜሪካ ባሕር ኃይል መካከል “ግጭቶች” መካሄዳቸውን ዘግቧል።

    የአሜሪካ ጦር ሠራዊት ባወጣው መግለጫ ሳምንታት ያስቆጠረውን በኢራን ወደቦች ላይ የተጣለውን ዕገዳ ለመጣስ የሞከሩ የኢራን ሰንደቅ ዓለማን የሰቀሉ ሁለት መርከቦችን ዒላማ አድርጎ እንዳይንቀሳቀሱ ማድረጉን አስታውቋል።

    የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ (ሴንትኮም) እንዳለው የባሕር ኃይል ተዋጊ አውሮፕላንን በመጠቀም በመርከቦቹ ላይ በተወሰደው እርምጃ መርከቦቹ ወደ ኢራን እንዳይመለሱ ተደርገዋል።

    ጨምሮም ሁለቱ ነዳጅ ጫኝ መርከቦች በአሜሪካ የተጣለውን እገዳ ለማስፈጸም ከጥቃቱ በፊት የተሰጣቸውን ማስጠንቀቂያ “ባለመቀበላቸው” እርምጃ እንደተወሰደቸባው ገልጿል።

    የአሜሪካ ሠራዊት ማዕከላዊ ዕዝ በኢራን የነዳጅ መርከቦች ላይ ስለተወሰደው እርምጃ ካወጣው መግለጫ ጋር ጥቃቱ ሲፈጸም የሚያሳይ ቪዲዮን አያይዞ አጋርቷል።

  9. የአሜሪካ ዕገዳ 13 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣ ነዳጅ የጫኑ መርከቦችን ማስቆሙ ተገለጸ

    የኢራን ነዳጅ ጫኝ መርከብ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የአሜሪካ ኃይሎች በኢራን ላይ የባሕር ዕቀባ ማድረግ ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ ከኢራን ወደቦች የሚነሱ እና ወደ ኢራን ወደቦች ያቀኑ የነበሩ ከ70 በላይ ነዳጅ ጫኝ መርከቦችን ማገዳቸውን የአሜሪካ ሠራዊት ማዕከላዊ ዕዝ (ሴንትኮም) አስታወቀ።

    እነዚህ የመንቀሳቀስ ዕቀባ የተጣለባቸው ግዙፍ ነዳጅ ጫኝ የንግድ መርከቦች “ከ13 ቢሊዮን ዶላር በላይ ዋጋ የሚያወጣ ከ166 ሚሊዮን በርሜል በላይ ነዳጅ” የጫኑ እንደነበሩ ማዕከላዊ ዕዙ ባወጣው መግለጫ ላይ አመለክቷል።

    ኢራን ወሳኙን የሆርሙዝ ወሽመጥን መዝጋቷን ተከትሎ በምላሹ አሜሪካ ከሚያዝያ 5/2018 ዓ.ም. ጀምሮ በኢራን መርከቦች ላይ እንዳይንቀሳቀሱ ዕገዳ ጥላለች።

    በዚህም በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል ከኢራን ወደቦች የሚነሱ እና ወደ ኢራን ወደቦች የሚጓዙ ሁሉም መርከቦች እንዳይንቀሳቀሱ በአሜሪካ ኃይሎች ዕገዳ ተጥሎባቸዋል።

  10. አሜሪካ ከኢራን ምላሽ እየጠበቀች መሆኗን ስትገልጽ፣ ኢራን አሜሪካን በወታደራዊ ጀብደኝነት ከሰሰች

    ማርኮ ሩቢዮ እና አባስ አራግቺ
    የምስሉ መግለጫ, የአሜሪካ እና የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ማርኮ ሩቢዮ እና አባስ አራግቺ

    አሜሪካ ጦርነቱን ለማብቃት ለኢራን ላቀረበችው የሰላም ሐሳብ ምላሽ እየጠበቀች ሲሆን፣ ኢራን ደግሞ አሜሪካ ዲፕሎማሲን በወታደራዊ ጀብደኝነት እየተካች ነው ስትል ወቀሰች።

    የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ኢራን ለቀረበላት የሰላም ሐሳብ ዛሬ አርብ ምላሽ ትሰጣለች ብላ አሜሪካ እየጠበቀች መሆኑን ተናግረዋል።

    ሚኒስትሩ ጣሊያን ውስጥ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት "ምላሻቸውን ዛሬ የሆነ ሰዓት ላይ እንሰማለን ብለን እንጠብቃለን. . . ምላሻቸውም የምር እንደሚሆን ተስፋ አደርጋለሁ” ብለዋል።

    የኢራኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ ትናንት ሐሙስ እንደተናገሩት አገራቸው በአሜሪካ በኩል የቀረበውን የሰላም ሐሳብ እየመረመረች መሆኗን ተናግረው ነበር።

    ይህ በእንዲህ እንዳለ የአሜሪካ እና የኢራን ኃይሎች አንዳቸው በሌላኛቸው ላይ ጥቃት ከፈጸሙ በኋላ ፕሬዝዳንት ትራምፕ የተኩስ አቁሙ እንደፀና መሆኑን አስታውቀዋል።

    አሜሪካ በኢራን ሚሳዔሎች፣ ድሮኖች እና ፈጣን ጀልባዎች ጥቃት እንደተፈጸመባት ስትከስስ፣ ኢራን ደግሞ እርምጃ የወሰደችው አሜሪካ በሆርሙዝ ወሽመጥ በኢራን ነዳጅ ጫኝ እና በሌላ መርከብ ላይ ለፈጸመችው ጥቃት አጸፋ መሆኑን ገልጻለች።

    ይህንን ተከትሎም አራግቺ በኤክስ ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሑፍ አሜሪካ “የዲፕሎማሲ መፍትሔ ጠረጴዛ ላይ ሲቀርብ ፊቷን ወደ ሞኝ ወታደራዊ ጀብደኝነት ታዞራለች” ሲሉ ከስሰዋል።

    አሜሪካ ለፈጸመችው ጥቃት ምክንያቱ “ጫና ለመፍጠር የተደረገ ጭፍን ዘዴ” ወይም “የአሜሪካ ፕሬዝዳንትን ከማይወጡበት አዘቅትት ለመክተት” የታለመ “አሳሳች የአሻጥረኞች” ተግባር እንደሆነ ተናግረዋል።

    ውጤቱም እንደከዚህ ቀደሙ ተመሳሳይ እንደሚሆን ያመለከቱት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ “ኢራናውያን ፈጽሞ የሚንበረከኩ ባለመሆናቸው ሁልጊዜም ዲፕሎማሲ እንዳይሳካ ምክንያት ይሆናል” ብለዋል።

  11. በአሜሪካ እና በኢራን መካከል ውጥረቱ ሲባባስ የዶላር ዋጋ ተዳከመ

    ዶላር

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    በአሜሪካ እና በኢራን መካከል ዳግም ግጭት ማገርሸቱን ተከትሎ ዶላር ያለው አቅም ላይ መዳከም መታየቱን ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘገበ።

    ኢራን በአሜሪካ መርከቦች ላይ አሜሪካ ደግሞ በኢራን ከተሞች ላይ ጥቃት መፈጸማቸውን ተከትሎ ነው ዶላር ላይ መዳከም የታየው። ቢሆንም ግን ፕሬዝዳንት ትራምፕ በሁለቱ አገራት መካከል የተደረሰው የተኩስ አቁም አለማብቃቱን ገልጸዋል።

    በጦርነቱ ምክንያት አቅሙ የወረደው ዶላር ትናንት በተካሄደው ግጭት ሰበብ ደግሞ ተጨማሪ ቅናሽ አሳይቷል፤ እንዲሁም በነዳጅ ዋጋ ላይ መጠነኛ ጭማሪ ተከስቷል።

    በዚህም ምክንያት ዋነኛው የነዳጅ ግዢ መገበያያ የሆነው ዶላር በገበያ ላይ ያለው ዋጋ ከሌሎች ዋና ዋና ገንዘቦች አንጻር የ0.14 በመቶ ቅናሽ ታይቶበታል።

    በተቃራኒው የጃፓኑ የን፣ የአውሮፓ ዩሮ እና የብሪታኒያው ፓወንድ ጭማሪ አሳይተዋል። በዚህም ዩሮ በ0.16 በመቶ እና በ0.26 በመቶ ጭማሪ በማሳየት በገበያው ላይ ጥንካሬ አግኝተዋል።

  12. በባሕረ ሰላጤው ጦርነት የተነሳ የዓለም የምግብ ዋጋ ጭማሪ መሳየቱን ቀጠለ

    ፋኦ

    የፎቶው ባለመብት, FAO

    የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የምግብ እና እርሻ ድርጅት (ፋኦ) በባሕረ ሰላጤው ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ ለሦስተኛ ተከታታይ ወር ሚያዝያ ላይም የዓለም የምግብ ዋጋ ጭማሪ ማሳየቱን አስታወቀ።

    ይህ ጭማሪ በዋናነት የተከሰተው አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን ላይ ጥቃት መፈጸም መጀመራቸውን ተከትሎ በአትክልት ዘይቶች ላይ በተከሰተ የዋጋ መጨመር ምክንያት ነው።

    ፋኦ በዓለም ላይ ለግብይት የሚቀርቡ የምግብ ሸቀጦች ዋጋን የሚከታተልበት የዓለም የምግብ ዋጋ ጠቋሚ ሰንጠረዥ እንደሚያመለክተው የምግብ ሸቀጦች ዋጋ በሚያዝያ ወር በ1.6 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል።

    በኢራን ላይ የተከፈተው ጦርነት ከጀመረ በኋላ በባሕረ ሰላጤው በሚገኘው ወሳኙ የጭነት መርከቦች መተላለፊያ ሆርሙዝ ወሽመጥ የሚደረገው እንቅስቃሴ የተገደበ ሲሆን፣ አሁንም ይኸው ችግር ባለበት እንደቀጠለ ነው።

    ሃያ በመቶ የሚሆነው የዓለም የነዳጅ ፍጆታ በሆርሙዝ በኩል የሚያልፍ ከመሆኑ በተጨማሪ፣ ለግብርና ሥራ ከሚውለው የኬሚካል ማዳበሪያ አንድ ሦስተኛው የሚጓጓዘውም በዚሁ ወሽመጥ ነው።

    የመተላለፊያው መዘጋት የነዳጅ፣ የማዳበሪያ እና ለምግብ ምርት እና አቅርቦት የሚውሉ ሌሎች ግብዓቶች ላይ እጥረት አስከትሏል። በዚህም ሳቢያ የማዳበሪያ ዋጋ በ80 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል።

  13. የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ነዳጅ ጫኝ መርከቦችን በድብቅ በሆርሙዝ ወሽመጥ ማሳለፏን ሮይተርስ ዘገበ

    የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች መርከብ

    የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images

    የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች እና የነዳጅ ምርቷን የሚፈልጉ ገዢዎች ድፍድፍ ነዳጅ የጫኑ መርከቦችን የአቅጣጫ ጠቋሚ በማጥፋት በኢራን ጥቃት ሳይፈጸምባቸው በሆርሙዝ ወሽመጥ ማለፋቸውን ሮይተርስ ዘገበ።

    ዜና ወኪሉ የኢንዱስትሪ ምንጮችን እና የመርከብ ጉዞ መረጃዎችን ዋቢ በማድረግ ያወጣው ዘገባ እንደሚያሳየው፤ አቡ ዳቢ ናሽናል ኦይል የተሰኘው ኩባንያ በአራት መርከቦች የተጫነ ስድስት ሚሊዮን በርሜል ድፍድፍ ነዳጅ አጓጉዟል።

    ጭነቱ ከወሽመጡ ከወጣ በኋላ በሦስት መንገዶች ተጓጉዞ ሊሆን እንደሚችል ዘገባው ያስረዳል። የመጀመሪያው አማራጭ ነዳጁ ከአንድ መርከብ ወደ ሌላ መርከብ በማዛወር በኋላ ላይ ወደ ደቡብ ምስራቅ እስያ የነዳጅ ማጣሪያ እንዲሄዱ ማድረግ ነው።

    ሁለተኛው በኦማን ውስጥ እንዲከማቹ ማድረግ ሲሆን ሦስተኛው ደግሞ በቀጥታ ወደ ደቡብ ኮሪያ የነዳጅ ማጣሪያዎች እንዲጓዙ ማድረግ ነው።

    መርከቦቹ በኢራን ኃይሎች የመታየት ዕድላቸውን ለመቀነስ ጉዞ የሚያደርጉት የመርከብ መለያ መረጃን የሚያስተላልፉ መሣሪያዎቻቸውን አጥፍተው እንደሆነ ዘገባው ጠቅሷል። ኢራን በአሜሪካ ማዕቀብ የተጣለበትን ነዳጇን ለማጓጓዝ የምትጠቀመው ይህንኑ ዘዴ ነው።

    የኢራን ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ የኤምሬቶቹ ነዳጅ አምራች ኩባንያ በአንድ ቀን ወደ ውጭ የሚልከውን ምርት ብዛት ከአንድ ሚሊዮን በርሜል በላይ ቀንሷል።

    በአሜሪካ እና እስራኤል የተከፈተባትን ጥቃት ተከትሎ ሆርሙዝን የዘጋችው ኢራን፤ በወሽመጡ ለማለፍ የሚሞክሩ መርከቦች ላይ ጥቃት እንደምትፈጽም ዝታለች።

  14. ኢራን በሆርሙዝ በኩል የሚያልፉ መርከቦችን የምትቆጣጠርበት የመንግሥት መሥሪያ ቤት ማቋቋሟ ተዘገበ

    በሆርሙዝ ወሽመጥ የሚጓዝ መርከብ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    ኢራን በወሳኙ የባሕር መተላለፊያ ሆርሙዝ በኩል የሚያልፉ መርከቦችን የምትቆጣጠርበት እና ታክስ የምታስከፍልበት የመንግሥት መሥሪያ ቤት ማቋቋሟን አንድ የመርከብ ጉዞ መረጃ ኩባንያ አስታወቀ።

    በአሜሪካ እና እስራኤል ጥቃት ከተፈጸመባት በኋላ ሆርሙዝ የዘጋችው ኢራን፤ በወሽመጡ ላይ ያላትን ቁጥጥር ሕጋዊ ቅርጽ ለማስያዝ የምታደርገውን ጥረት ቀጥላለች። ከዚህ በፊት በመተለላፊያው የሚጓዙ መርከቦችን ታክስ የምታስከፍልበት ረቂቅ ሕግ ማዘጋጀቷ ተገልጾ ነበር።

    አሁን ደግሞ በወሽመጡ የሚደረጉ ጉዞዎችን የሚፈቅድ እና ክፍያዎችን የሚሰበስብ የመንግሥት ኤጀንሲ መቋቋሙን ‘ሎይድስ ሊስት ኢንተለነጀስ’ የተሰኘው የመርከብ ጉዞ ዳታ ተቋም ማስታወቁን የዜና ወኪሉ አሶሺዬትድ ፕሬስ ዘግቧል።

    “የፋርስ ባሕረ ሰላጤ ወሽመጥ ባለሥልጣን” የሚል ስያሜ የተሰጠው ይህ ተቆጣጣሪ መሥሪያ ቤት፤ “ራሱን በወሽመጡ ለሚደረጉ ጉዞዎች ፈቃድ የመስጠት ብቸኛ ሥልጣን ያለው አካል አድርጎ ማቅረቡን” ኩባንያው ሐሙስ ዕለት ባወጣው መረጃ ገልጿል።

    እንደ ኩባንያው ገለጻ፤ የኢራን ባለሥልጣናት በወሽመጡ ማለፍ በሚፈልጉ መርከቦች የሚሞላ ማመልከቻን የያዘ የኢሜይል መልዕክት አሠራጭቷል።

    ኢራን የሆርሙዝ ወሽመጥን በመዝጋቷ በባሕር መስመሩ ያልፉ የነበሩ የነዳጅ፣ የጋዝ፣ የማዳበሪያ እና ሌሎች የፔትሮሊየም ምርቶች ጉዞ ተስተጓጉሏል። አሜሪካም በምላሹ ወደ ኢራን ወደቦች የደሚረጉ ጉዞዎችን አግዳለች።

    በወሽመጡ የተጣለው እገዳ የነዳጅ ዋጋ ጣሪያ እንዲነካ እና የዓለም ኢኮኖሚ እንዲቃወስ አድርጓል።

    የአሶሺየትድ ፕሬስ (ኤፒ) ዘገባ እንደሚያሳየው፤ አዲሱ የኢራን መሥሪያ ቤት የአገሪቱ መንግሥት በጦርነቱ ወቅት መርከቦችን ያሳልፍ እና ክፍያ ይሰበስብ ለነበረበት አሠራር ሕጋዊ ቅርጽ የሚሰጥ ነው።

    ኢራን በወሽመጡ የትኛዎቹ መርከቦች እንደሚያልፉ መቆጣጠር እንዲሁም ለጭነታቸው ታክስ የማስከፈል ሀሳብ አላት።

  15. ሆርሙዝ በመዘጋቱ 1,500 መርከቦች መተላለፊያ አጥተው ለወራት መቆማቸው ተነገረ

    መርከቦች

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    ኢራን በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ በጣለችው ዕገዳ ምክንያት 1,500 የጭነት መርከቦች እና 20 ሺህ ባሕርተኞች መተላለፊያ አጥተው በፋርስ ባሕረ ሰላጤ አካባቢ እንደሚገኙ የተባበሩት መንግሥታት የባሕር ትራንስፖርት ድርጅት አስታወቀ።

    የድርጅቱ ዋና ፀሐፊ አርሴኒዮ ዶሚንጌዝ፤ "በአሁኑ ወቅት ወደ 1,500 የሚጠጉ መርከቦች እና ባሕረተኞች በአካባቢው መንቀሳቀሻ አጥተው እየተጉላሉ ነው” በማለት የመርከብ ሠራተኞቹ ከቁጥጥራቸው ውጪ በመሆነ እና በማይመለከታቸው ሁኔታ ችግር ላይ መውደቃቸውን ገልጸዋል።

    በመካከለኛው ምሥራቅ የሚካሄደው ጦርነት መጀመሩን ተከትሎ ከፍተኛ የነዳጅ ምርት በሚተላለፍበት የሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ በተፈጠረ የደኅንነት ስጋት ምክንያት ግዙፍ የጭነት መርከቦች መንቀሳቀስ ሳይችሉ ባሉበት ቆመው ወራት ተቆጥረዋል።

    ጦርነቱን ለመቋጨት በአሜሪካ እና በኢራን መካከል እየተደረጉ ያሉት ድርድሮችም ዋነኛ ትኩረታቸውን የሆርሙዝ የባሕር ወሽመጥን ማስከፈት ላይ ነው።

    እንዲሁም በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ አሜሪካ መተላለፊያ ያጡ መርከቦችን በማጀብ በሆርሙዝ በኩል እንዲያልፉ የሚያስችል ዘመቻ ብትጀምርም ከአንድ ቀን በኋላ ሰርዛዋለች።

    በፓኪስታን አደራዳሪነት እየተደረገ ባለው ንግግር ኢራን ከአሜሪካ የቀረበላትን ጦርነት የማቆም እና የሆርሙዝ ወሽመጥን የመክፈት ሃሳብን እያጤነችው መሆኑ ተዘግቧል።

    የካቲት 21/2018 ዓ.ም. እስራኤል እና አሜሪካ በኢራን ላይ ጥቃት በመክፈታቸው በተጀመረው ጦርነት ምክንያት ኢራን በወሰደችው የአጸፋ ምላሽ ወሳኙ የዓለም ነዳጅ ጫኝ መርከቦች መተላለፊያ የሆርሙዝ ወሽመጥ ተዘግቶ ቆይቷል።

  16. ከአሜሪካ እና ኢራን ተኩስ ልውውጥ በኋላ የነዳጅ ዋጋ ጨመረ

    ነዳጅ የሚቀዳ እጅ

    የፎቶው ባለመብት, Anadolu via Getty Images

    አሜሪካ እና ኢራን በወሳኙ የባሕር መተላለፊያ ሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ ተኩስ መለዋወጣቸው ከተሰማ በኋላ አርብ ሌሊት የእስያ ገበያ ሲከፈት የነዳጅ ዋጋ ጨምሮ ታየ።

    የአሜሪካ ጦር “ትንኮሳ ሳይኖር” የተሰነዘሩ ያላቸውን የኢራን የሚሳዔል፣ ድሮን እና የአነስተኛ ጀልባ ጥቃቶችን ማክሸፉን፤ በምላሹም የራስ መከላከል ጥቃት መፈጸሙን አስታውቋል።

    ከዚህ ጥቃት በኋላ፤ የዓለም የነዳጅ ዋጋ መለኪያ የሆነው ብሬንት ዋጋው በ1.5 በመቶ ጨምሮ በበርሜል 101.60 ዶላር ተሽጧል። በአሜሪካ ገበያ የሚሸጠው ነዳጅ ደግሞ ዋጋው በ1.1 በመቶ አድጎ 95.87 ዶላር ሆኗል።

    በአውስትራሊያ ጀምስ ኩክ ዩኒቨርሲቲ ተባባሪ ፕሮፌሰር የሆኑት ጂያጂያ ያንግ እንደሚናገሩት፤ የነዳጅ ዋጋ በድጋሚ የጨመረው በሆርሙዝ ወሽመጥ የሚወሰደው ወታደራዊ እርምጃ በስትራቴጂካዊው የንግድ መስመር የሚጓጓዘው የኤነርጂ አቅርቦትን አደጋ ላይ ሊጥል ይችላል የሚል ስጋት በመጨመሩ ነው።

    በሲንጋፖር ናሽናል ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚ ተመራማሪ የሆኑት ሁይፌንግ ቻንግ በበኩላቸው፤ አሜሪካ እና ኢራን ውጥረቱን ለማርገብ እየሞከሩ ቢሆንም እንኳ ነጋዴዎች ተኩስ አቁሙን “በቀላሉ የሚጣስ” አድርገው ስለሚመለከቱት አካሄዳቸውን በዚያው ልክ ማድረጋቸውን አስረድተዋል።

    ከእስራኤል ጋር በመሆን በየካቲት ወር ጦርነት የከፈተችው አሜሪካ፤ ግጭቱን ለመቋጨት ከኢራን ጋር ለምታደርገው ድርድር የሚሆን የስምምነት ማዕቀፍ እያዘጋጀች መሆኑን አስታውቃለች። ፕሬዝዳንት ትራምፕ ጦርነቱ "በፍጥነት ያበቃል" ሲሉ በዚህ ሳምንት ተናግረዋል።

    ጥቃት የተከፈተባት ኢራን በአጸፋው ቁልፍ የነዳጅ እና ጋዝ መተላለፊያ የሆነውን ሆርሙዝ ወሽመጥ እንደምትዘጋ ከዛተችበት ከጦርነቱ ጅማሬ አንስቶ የኤነርጂ ዋጋ በከፍተኛ መጠን ጨምሯል። ከዓለም የነዳጅ እና የጋዝ አቅርቦት ውስጥ አንድ አምስተኛው የሚያልፈው በዚህ የባሕር መስመር ነው።

  17. የጀርመኑ ሚኒስትር በአገራቸው ለተፈጠረው የኢኮኖሚ መቀዛቀዝ የትራምፕን “ኃላፊነት የጎደለው ጦርነት” ተጠያቂ አደረጉ

    የጀርመን የፋይናንስ ሚኒስትር ላርስ ክሊንግቤል

    የፎቶው ባለመብት, EPA

    የጀርመን የፋይናንስ ሚኒስትር የአሜሪካው ፕሬዝዳንትን እያካሄዱት ያሉት “ኃላፊነት የጎደለው ጦርነት” በአገሪቱ ሊሰበሰብ ታስቦ የነበረው የታክስ ገቢ በከፍተኛ መጠን እንዲቀንስ ማድረጉን ተናገሩ።

    ሚኒስትሩ ላርስ ክሊንግቤል የአሜሪካው ፕሬዝዳንት እርምጃዎች በቀጣናው “ዓለም አቀፍ የኤነርጂ ቀውስ” እንዲፈጠር ማድረጉን በማንሳትም ወቅሰዋል።

    የጀርመን ባለሥልጣናት ከ2026 እስከ 2030 ለመሰብሰብ አስቀምጠውት የነበረውን የታክስ ገቢ ዕቅድ በ82 ቢሊዮን ዶላር ቀንሰዋል። ይሄ የእቅድ ቅነሳ “በኢራን የሚደረገው ጦርነት ምን ያህል ኢኮኖሚያችንን እየጎዳ እንደሆነ ያሳያል” ሲሉ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

    ከሳምንታት በፊት የጀርመኑ መራሔ መንግሥት ፍሬድሪክ መርዝ ዋይት ሃውስ በኢራን ተደራዳሪዎች “እየተዋረደ ነው” የሚል ንግግር ማድረጋቸው ትራምፕን አበሳጭቶ ነበር። በዚህ ንግግር የተነሳም ትራምፕ በጀርመን በሚገኙ የአሜሪካ የጦር ሠፈሮች ከሰፈሩ ወታደሮች ውስጥ አምስት ሺህ ያህሉን እንደምታስወጣ ዝተዋል።

    የጀርመኑ መራሔ መንግሥት ባለፈው ዓመት ወደ ሥልጣን ከመጡ ወዲህ የትራምፕ ፖሊሲዎች ከዚህ ቀደም በአሜሪካ እና ጀርመን መካከል የነበረውን ጥብቅ ግንኙነት መቀየሩን ሲጠቁሙ ቆይተዋል።

    ባለፈው የካቲት ላይ “በአውሮፓ እና አሜሪካ መካከል ጥልቅ ክፍተት ተፈጥሯል” በማለት መናገራቸው አንዱ ማሳያ ነው። ይሁን እንጂ የጀርመኑ መሪ በአሜሪካ እና አውሮፓ መካከል ያለውን ግንኙነት ለማለሳለስ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ሁለቴ ወደ ዋይት ሃውስ ተጉዘዋል።

    እንደ ሌሎች የአውሮፓ አገራት ሁሉ ጀርመንም አሜሪካ እና እስራኤል በየካቲት ወር ኢራን ላይ የከፈቱትን ጦርነት ተችታለች። ጦርነቱ የዓለም ኢኮኖሚ ላይ የሚያደርሰው ተጽዕኖ ትልቅ እንደሚሆን ተፈርቷል።

    የጀርመን ጥምር መንግሥት በከፍተኛ የኤነርጂ ዋጋ እና በኤክስፖርት ፍላጎት መቀነስ ምክንያት ለዓመታት ባለበት ቆሞ ያለውን የአገሪቱን ኢኮኖሚ ለማነቃቃት እየጣረ ነው።

    ባለፈው ወር መራሔ መንግሥቱ መርዝ ለተማሪዎች ባደረጉት ንግግር፤ “አሜሪካውያኑ ምንም ስትራቴጂ እንደሌላቸው ግልጽ” መሆኑን እንዲሁም ሊመርጡ የሚችሉት “ስትራቴጂያዊ መውጫ” እንደማይታያቸው ሲናገሩ ተደምጠዋል።

  18. ቴህራን የአሜሪካ ጦር መርከብን ዒላማ ስታደርግ ዋሽንግተን በኢራን ከተሞች ጥቃት ፈጸመች

    ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    አሜሪካ እና ኢራን ሐሙስ ምሽት አንዳቸው በሌላኛቸው ላይ ጥቃት ከፈጸሙ በኋላ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በሁለቱ አገራት መካከል የተደረሰው ተኩስ አቁም አሁንም ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን ተናገሩ። በትናንቱ የተኩስ ልውውጥ ማን ቀድሞ ጥቃት እንደፈጸመ ግልጽ አይደለም።

    የኢራን ከፍተኛ ወታደራዊ አዛዥ አሜሪካ ወደ ሆርሙዝ ወሽመጥ እየተጠጉ የነበሩ የኢራን ነዳጅ ጫኝ እና ሌላ መርከብን ዒላማ እንዳደረገች እንዲሁም፤ በተለያዩ የባሕር ዳርቻ አካባቢዎች ላይ የአየር ጥቃት መፈጸሟን ተናግረዋል።

    አሜሪካ በበኩሏ ወሽመጡ ላይ በሰፈረው ሚሳዔል ተሸካሚ አውዳሚ መርከቧ ላይ ለፈጸመችባት ጥቃት “የራስን መከላከል ጥቃቶችን” በማድረስ ምላሽ መስጠቷን አስታውቃለች።

    ሁለቱ አገራት ወታደራዊ እርምጃ መውሰዳቸው የተሰማው የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አሜሪካ ያቀረበችው የድርድር ዕቅድ እየተገመገመ መሆኑን በተናገሩ ማግሥት ነው።

    የኢራን መንግሥት መገናኛ ብዙኃን በቅድሚያ ባወጣው ዘገባ በሆርሙዝ ወሽመጥ “ፍንዳታ” መሰማቱን አስታውቆ ነበር። ሁኔታውንም “ከጠላት” ጋር የተደረገ “የተኩስ ልውውጥ” ሲል ገልጾታል። ሌላ የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ደግሞ ቴህራን ውስጥ ፍንዳታ መሰማቱን ዘግቧል።

    ከቆይታ በኋላ መግለጫ ያወጡት የኢራን ከፍተኛ ወታደራዊ አዛዥ በበኩላቸው አሜሪካ በፈጸመቻቸው “የአየር ጥቃቶች” ባንዳር ኻሚር፣ ሲሪክ እና ቃሽም ደሴት መመታታቸውን አስታውቀዋል።

    ኢራን ወዲያውኑ የአሜሪካ የጦር መርከብን በመምታት ምላሽ እንደሰጠች እና በዚህም “ከፍተኛ ጉዳት” ማድረሷን ገልጸዋል። አሜሪካ “የተኩስ አቁም ጥሰት” ፈጽማለች ሲሉም ከስሰዋል።

    የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ (ሴንትኮም) የኢራንን ጥቃቶች “ትንኮሳ ሳይኖር” የተፈጸሙ በማለት ገልጿቸዋል። የኢራን ኃይሎች በወሽመጡ እያለፈ በነበረው የአሜሪካ አውዳሚ የጦር መርከብ ላይ “በርካታ ሚሳዔሎች፣ ድሮኖች እና አነስተኛ ጀልባዎችን” ማሰማራታቸውን አስታውቋል።

    “የተቃጡ ስጋቶችን ማስወገዱን” የገለጸው ማዕከላዊ ዕዙ፤ “አሜሪካ ላይ ለተፈጸመው ጥቃት ተጠያቂ የሆኑ እንደ የሚሳኤል እና የድሮን ማስወንጨፊያ ቦታዎችን፣ የዕዝ እና የቁጥጥር ማዕከላትን፣ እንዲሁም የመረጃ፣ የክትትል እና የስለላ ይዞታዎች ያሉ የኢራን ወታደራዊ ተቋማትን መምታቱን” ገልጿል።

    "ማዕከላዊ ዕዙ ውጥረቱ እንዲባባስ አይፈልግም፤ ነገር ግን የአሜሪካ ኃይሎችን ለመጠበቅ በተጠንቀቅ እና በዝግጁነት ላይ ይገኛል" ሲል በመግለጫው ጠቅሷል።

    ትሩዝ ሶሻል በተሰኘው የማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ የጻፉት ፕሬዝዳንት ትራምፕ አሜሪካ በርካታ የኢራን አነስተኛ ጀልባዎችን ማውደሟን ገልጸዋል።

    “ቢራቢሮ ወደ መቃብሯ እንደምትወርድ ሁሉ፤ በጣም በሚያምር ሁኔታ ወደ ውቅያኖሱ ሰምጠዋል" ብለዋል። “በኢራን አጥቂዎች ላይ ትልቅ ጉዳት እንደደረሰም” ተናግረዋል።

    ፕሬዝዳንቱ በጽሑፋቸው የሰላም ስምምነቱን በተመለከተ በድጋሚ ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል። “ዛሬ በድጋሚ እንደዘረርናቸው ሁሉ፤ ስምምነታቸውን በፍጥነት ካልፈረሙ ወደፊት በበለጠ ጥንካሬ እና ከፍ ባለ ኃይል እንዘርራቸዋለን” ብለዋል።

    በትናንቱ ጥቃት ላይ “የእስራኤል ተሳትፎ እንዳልነበረ” አንድ የእስራኤል ምንጭ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

  19. የኢራኑ ፕሬዝዳንት በሕዝብ ታይተው ከማያውቁት ጠቅላይ መሪ ጋር መወያየታቸውን ተናገሩ

    ፕሬዝዳንት ፔዜሽኪያን እና ጠቅላይ መሪው ሞጅታባ

    የፎቶው ባለመብት, IRNA

    የምስሉ መግለጫ, ፕሬዝዳንት ፔዜሽኪያን እና ጠቅላይ መሪው ሞጅታባ

    የኢራኑ ፕሬዝዳንት ማሱድ ፔዜሽኪያን የኢራን ጠቅላይ መሪ ከሆኑ በኋላ የጽሁፍ መልዕክት ከማስተላለፍ ውጪ አስካሁን በይፋ ያልታዩትን ሞጅታባ ኻሜኒን አግኝተው መወያየታቸውን ተናገሩ።

    ፕሬዝዳንቱ ጠቅላይ መሪውን ሞጅታባ ኻሜኒን “ለሁለት ሰዓት ተኩል” ያህል አግኝተው መወያየታቸውን ከመግለጽ ውጪ ጊዜውን እና ቦታውን ከማሳወቅ ተቆጥበዋል።

    ፔዜሽኪያን ከሞጅታባ ኻሜኒ ጋር በነበራቸው ውይይት “እርጋታ እና ብልህነትን” በኢራን አስላማዊ አብዮታዊ ጠቅላይ መሪ ላይ መመልከታቸውን ገልጸዋል።

    እስራኤል እና አሜሪካ በኢራን ላይ ጥቃት በከፈቱበት ዕለት የተገደሉትን አባታቸውን በመተካት ከሳምንት በኋላ መንበሩን የተረከቡት ሞጅታባ ኻሜኒ የኢራን እስላማዊ ሪፐብሊክ ከተመሠረተች በኋላ ሦስተኛው ጠቅላይ መሪ ናቸው።

    በአሜሪካ እና በእስራኤል ጥቃት አባታቸው እና ሌሎችም የቤተሰቦቻቸው አባላት የተገደሉባቸው አዲሱ የኢራን ጠቅላይ መሪ ሞጅታባ ኻሜኒ በጥቃቱ ከባድ ጉዳት እንደደረሰባቸው ሲዘገብ ቆይቷል።

    አስካሁን ድረስም ጠቅላይ መሪው በይፋ ወጥተው ወይንም በቴሌቪዥን ቀርበው ለሕዝብ ያልታዩ ከመሆኑ በተጨማሪ ድምቸጻውም ተሰምቶ አያውቅም። በተለያዩ ጊዜያት የኢራን መገናኛ ብዙኃን የጠቅላይ መሪው ናቸው የተባሉ መልዕክቶችን በንባብ ሲያቀርቡ ቆይተዋል።

    የኢራኑ ፕሬዝዳንት ፔዜሽኪያን ከጠቅላይ መሪው ጋር ለሰዓታት የዘለቀ ውይይት ማድረጋቸውን ዛሬ ሲያስታውቁ ሞጅታባ ኻሜኒ የእስላማዊው ሪፐብሊክ ጠቅላይ መሪነትን ከተረከቡ በኋላ የተደረገ የመጀመሪያው ግንኙነት ስለመሆኑ የታወቀ ነገር የለም።

  20. ሳዑዲ አረቢያ የትራምፕ ሆርሙዝን የማስከፈት ዘመቻ እንዲቋረጥ ማድረጓን ኤንቢሲ ዘገበ

    የሳዑዲው ልዑል እና ዶናልድ ትራምፕ

    የፎቶው ባለመብት, REUTERS

    የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በሆርሙዝ ወሽመጥ መንቀሳቀስ ያልቻሉ መርከቦችን አጅቦ ለማስወጣት የነበራቸውን ዕቅድ ያቋረጡት በሳዑዲ አረቢያ ምክንያት መሆኑን ኤንቢሲ ዘገበ።

    ኤንቢሲ ሁለት የአሜሪካ ባለሥልጣናትን ጠቅሶ እንደዘገበው ሳዑዲ አረቢያ እሁድ ዕለት ትራምፕ ዕቅዳቸውን ይፋ ሲያደርጉ መደነቃቸውን ተናግረዋል።

    የሳዑዲ አረቢያ ባለሥልጣናት የአሜሪካ ወታደራዊ አውሮፕላኖችም ሆኑ የጦር ጄቶች ከሳዑዲ የልዑል ሱልጣን የአየር ኃይል መነሳት ወይም በሆርሙዝ ወሽመጥ መውጫ ያጡትን መርከቦች ለማጀብ በሚደረገው ዘመቻ የሳዑዲ አየር ክልል መጠቀም አንደማይችሉ መናገራቸውን ምንጮቹ ለኤንቢኤስ ተናግረዋል።

    ትራምፕ በጉዳዮ ላይ ከሳዑዲው ልዑል ሞሐመድ ቢን ሳልማን ጋር ቢነጋገሩም ሊያሳምኗቸው እንዳልቻሉ ጨምረው ተናግረዋል።

    ከዚህ በኋላ ትራምፕ ወሳኝ የሆነውን የአየር ክልል ‘ፕሮጀክት ፍሪደም’ ሲሉ ለሰየሙት ወታደራዊ ዘመቻ መጠቀም ስለሚያስፈልግ ዕቅዳቸውን ለጊዜው ለማዘግየት ወስነዋል ሲሉ ምንጮቹ ለኤንቢኤስ ተናግረዋል።

    አሜሪካ ከእስራኤል ጋር በመሆን በኢራን ላይ ጦርነት በከፈተችበት ወቅት ሳዑዲ አረቢያ የጦር ሠፈሯን እና የኤር ክልሏን የዩናይትድ ስቴትስ ጦር እንዲጠቀምበት ፈቅዳ ነበር።

    አንድ የአሜሪካ ባለሥጣን ለኤንቢሲ አንደተናገሩት የሳዑደ አረቢያ ትብብር በቀጠናው ለሚደረግ ማንኛውም ዘመቻ ወሳኝ ነው።

    ዶናልድ ትራምፕ የሆርሙዝ ወሽመጥን ለማስከፈት ይዘውት በነበረው ዕቅድ የጦር አውሮፕላኖች የመከላከያ ሽፋን ለመስጠት ወሳኝ በመሆኑ በቀጣናው የሚገኝ የአየር ክልልን መጠቀም አስፈላጊ አድርጎታል።

    ማክሰኞ ምሽት አሜሪካ በሆርሙዝ ወሽመጥ ቆመው የሚገኙትን መርከቦች እያጀበች ለማስወጣት ይዛ የነበረውን ዕቅድ "ለአጭር ጊዜ" እንደምታቆም ፕሬዚዳንት ትራምፕ አስታውቀዋል።

    ሰኞ ዕለት የተጀመረው "ፕሮጀክት ፍሪደም" እንዲቆም የተደረገው ከኢራን ጋር እየተደረገ ያለው ውይይት "ትልቅ መሻሻል" እያሳየ በመምጣቱ ምክንያት "በጋራ ስምምነት" ከውሳኔ ላይ መድረሳቸውን ጨምረው ገልጸዋል።