የኢትዮጵያ ኤምባሲ ኢትዮጵያውያን ላይ ስለተፈጸመው ግድያ ለደቡብ አፍሪካ መንግሥት ጥያቄ ማቅረቡን አስታወቀ

ትናንት ጆሃንስበርግን ጨምሮ በተለያዩ የደቡብ አፍሪካ ከተማዎች ጸረ ስደተኛ ተቃውሞዎች ተካሂደዋል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ትናንት ጆሃንስበርግን ጨምሮ በተለያዩ የደቡብ አፍሪካ ከተማዎች ጸረ ስደተኛ ተቃውሞዎች ተካሂደዋል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ከተማ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ባለፉት ቀናት በኢትዮጵያውያን ላይ የተፈጸመውን ግድያ በተመለከተ "በአስቸኳይ እርምጃ እንዲወሰድ" እና "ችግር በሚታይባቸው አካባቢዎች ልዩ ጥበቃ" እንዲደረግ ለአገሪቱ መንግሥት ጥያቄ ማቅረቡን አስታወቀ።

ኤምባሲው ትናንት ረቡዕ ሚያዝያ 21/2018 ዓ.ም. ደቡብ አፍሪካ ውስጥ ለሚገኙ ኢትዮጵያውያን ባወጣው "ማሳሰቢያ" ኢትዮጵያውያን ላይ "በግፈኞች እየደረሰ ባለው ግድያ እና በደል" የተሰማውን "ጥልቅ ሀዘን" ገልጿል።

ኤምባሲው ይህንን መልዕክት ያስተላለፈው በቀናት ልዩነት አራት ኢትዮጵያውያን መገደላቸው ከተሰማ በኋላ ነው። የደቡብ አፍሪካ መገናኛ ብዙኃን ያወጧቸው ዘገባዎች እንደሚያመለክቱት ኢትዮጵያውያኑ የተገደሉት ጆሃንስበርግ ከተማ ውስጥ በሚገኘው 'ሲቢዲ' የተሰኘው የንግድ ሥፍራ ነው።

ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በተሰራጨ እና በደኅንነት ካሜራ የተቀረጸ ቪዲዮ ላይ አንድ ግለሰብ በርካታ ሰዎች በሚተላለፉበት የገበያ ስፍራ ውስጥ ሲያልፍ እና መደብር አጠገብ ከቆመ ግለሰብ ጀርባ ሲቆም ያሳያል።

ወዲያውኑም ሽጉጥ አውጥቶ ከቅርብ ርቀት ግለሰቡ ጭንቅላት ላይ ሲተኩስ እና ግለሰቡ ሲወድቅ ቪዲዮው ላይ ይታያል። የወደቀው ሰው ላይ በድጋሚ ከተኮሰበት በኋላ ከአካባቢው ሲሄድ ተቀርጿል።

አዲስ ስታንዳርድ ማክሰኞ ዕለት ባወጣው ዘገባ የጠቀሳቸው በፕሪቶሪያ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ጉዳይ አስፈጻሚ ደሴ አራት ሰዎች መገደላቸውን ለመገናኛ ብዙኃኑ አረጋግጠዋል።

ኤምባሲው ትናንት ባወጣው ማሳሰቢያ ምን ያህል ኢትዮጵያውያን እንደተገደሉ አልጠቀሰም። ይሁን እንጂ "የሚመለከተው የደቡብ አፍሪካ የጸጥታ መዋቅር"፤ "ግድያውን እየፈጸሙ ያሉ አካላት" ላይ "በአስቸኳይ ሕጋዊ ምርመራ" እንዲያካሂድ በደብዳቤ መጠየቁን ገልጿል። የምርመራው ውጤት ኤምባሲው "በአስቸኳይ እንዲገለጽለም" ማሳሰቡንም ጠቅሷል።

ኤምባሲው ባወጣው መግለጫ ግድያዎቹ በደቡብ አፍሪካ ከሚታየው መጤ ጠልነት ጋር የተያያዘ ሊሆን እንደሚችል ጠቁሟል።

"ከቅርብ ጊዜ ወዲህ" ደቡብ አፍሪካ ውስጥ "የውጭ ዜጎች በተለይም የጥቁር አፍሪካዊ ስደተኛ ጠል እንቅስቃሴ መበራከቱን መገንዘብ ተችሏል" ብሏል። ይህ አይነቱ እንቅስቃሴ "በቅርቡ በሰፊው" መነሳቱንም አክሏል።

ከዚህ በፊትም "ኢትዮጵያውያን በተለያዩ ጊዜያት አካላዊ፣ ቁሳዊ እና ስነ ልቦናዊ ጉዳት" እየደረሰባቸው እንደነበር ኤምባሲው አስታውሷል። በወቅቱ "ይህ አስቸጋሪ ጉዳይ ትኩረት ሊሰጠው እና ተገቢው ጥበቃ እንዲደረግ" ለአገሪቱ መንግሥት ጥያቄ አቅርቦ፤ "ለፀጥታ አስከባሪ አካላት መመሪያ" ስለመውረዱ ተገልጾለት እንደነበር አክሏል።

ሰሞነኛውን ግድያዎች ተከትሎም፤ "በቀጣይም ተጨማሪ ሕይወት እንዳይጠፋ ችግሮች በሚታዩባቸው አካባቢዎች ልዩ ጥበቃት እንዲደረግ" ጥያቄ ማቅረቡን አስታውቋል።

"በመካከልም ችግሩን በተመለከተ ከሚመለከታቸው ተቋማት እና ግለሰቦች ጋር በግንባር ቀርቦ መነጋገር እንዲቻል የውይይት መድረኮች እንዲመቻቹለትም" መጠየቁን ገልጿል።

ፕሪቶሪያ ከተማ ውስጥ በተካሄደ ሰልፍ ላይ "ለአገሬ መታገል መጤ ጠል ከሆነ፤ እንግዲያውስ ኩሬ መጤ ጠል ነኝ" የሚል መፈክር ታይቷል

የፎቶው ባለመብት, BBC / Thuthuka Zondi

የምስሉ መግለጫ, ፕሪቶሪያ ከተማ ውስጥ በተካሄደ ሰልፍ ላይ "ለአገሬ መታገል መጤ ጠልነት ከሆነ፤ እንግዲያውስ ኩሩ መጤ ጠል ነኝ" የሚል መፈክር ታይቷል

ኤምባሲው፤ "አሁን ያለው ችግር መፍትሔ እስከሚያገኝ ድረስ" ደቡብ አፍሪካ ውስጥ የሚገኙ ኢትዮጵያውን "ከወትሮው በተለየ መልኩ" እንዲተባበሩ አሳስቧል።

"ከሌሎች አፍሪካ አገራት ስደተኞች ጋር በመቀናጀት፣ ራሳቸውን እና ንብረቶቻቸውን እንዲጠብቁ" እንዲሁም ከጸጥታ አካላት ጋር "ተቀራርበው እንዲሰሩ" መክሯል።

የደቡብ አፍሪካ መገናኛ ብዙኃን ዘገባዎች እንደሚያመለክቱት ኢትዮጵያውያኑ ላይ ግድያ የተፈጸመበት ምክንያት እስካሁን ግልጽ አይደለም።

ይሁን እንጂ በጆሃንስበርግ ሲቢዲ ኢትዮጵያውያን በጥይት ተመትተው የተገደሉት ከተደራጁ ወንጀሎች፣ ከሕገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች እና ከዝርፊያ ጋር የተያያዘ ሊሆን እንደሚችል ያላቸውን ግምት ጠቅሰው ዘግበዋል።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው በደቡብ አፍሪካ የሚገኙ አንድ ኢትዮጵያዊ "በተለያየ ምክንያት ሰው ቀጥረው እያስገደሉ ነው ያሉት" ያሉ ሲሆን በኢትዮጵያውያን መካከል "እርስ በእርስ" የተፈጸመ ድርጊት ሊሆን እንደሚችል ጠቁመዋል። ቢቢሲ ይህንን ጉዳይ በገለልተኝነት አላረጋገጠም።

ይህም ቢሆን ግን ከሰሞኑ ደቡብ አፍሪካ ውስጥ ፀረ ስደተኞች እንቅስቃሴዎች ታይተዋል። በደቡብ አፍሪካ መጤ ጠል የሆኑ ግለሰቦች በሚያደርሱት ጥቃት የተለያዩ የአፍሪካ አገራት ዜጎች መገደላቸውም ተዘግቧል።

ይህንን ተከትሎም በደቡብ አፍሪካ ዋና ከተማ ፕሪቶሪያ የሚኖሩ አፍሪካውያን ስደተኞች ፀረ ስደተኛ ሠልፍ በሚካሄድበት ወቅት ጥቃት እዳይደርስባቸው "ከፍተኛ ጥንቃቄ" እንዲያደርጉ በአገራቶቻቸው ተቋማት ተነግሯቸዋል።

ትናንት ረቡዕ በጆሃንስበርግ ተመሳሳይ ሰልፍ ሲካሄድ በርካታ መደብሮች ተዘግተው እንደነበር ቢቢሲ ያነጋገራቸው አንድ ነዋሪ ገልጸዋል።