"ደቡብ አፍሪካውያን ቅድሚያ ሊሰጣቸው ይገባል" - የውጭ ዜጎች የጤና አገልግሎት እንዳያገኙ የሚያደርገው ፀረ ስደተኛ ቡድን

በደቡብ አፍሪካዋ ጆሃንስበርክ ከተማ ሰሜናዊ ክፍል የሚገኝ አንድ የማኅበረሰብ ክሊኒክ የፍጥጫ ማዕከል ሆኗል።
ደቡብ አፍሪካዊ ያልሆኑ የውጭ ዜጎች የሕዝብ የጤና ተቋማትን ሊጠቀሙ ይገባል ወይስ አይገባም የሚለው ክርክር እዚህ ክሊኒክም ደርሷል።
በ2013 ዓ. ም. በአንድ አካባቢ የተጀመረው ይህ ዓይነቱ እንቅስቃሴ ተስፋፍቷል። 'ኦፕሬሽን ዱዱላ' በመባል የሚጠራው ፀረ ስደተኞች ቡድን አባላት እንቅስቃሴውን ተግባራዊ ለማድረግ በጋውተንግ እና ኩዋዙሉ ናታል አውራጃዎች በሚገኙ ሆስፒታሎች ተሰማርተዋል።
በጤና ተቋማቱ ደጅ ላይ የሚቆሙት የቡድኑ አባላት፤ ወደ ክሊኒኮች የሚመጡ ሰዎችን የመታወቂያ ካርድ በማየት ደቡብ አፍሪካዊ ያልሆኑ ሰዎች እንዳይገቡ ይከላከላሉ።
የቡድናቸው መጠሪያ ያደረጉት 'ዱዱላ' የሚለው ቃል ከዙሉ ቋንቋ የተገኘ ነው። አንድን ነገር በኃይል ማስወገድ የሚል ትርጉምም አለው።
የአገሪቱ ባለሥልጣናት የተወሰኑ ሰዎችን በቁጥጥር ሥር ቢያውሉም በጤና ተቋማት ላይ የሚደረገውን የማንነት ማጣራት እንቅስቃሴ ማስቆም አልቻሉም።
ከሰሞኑ ይህ ዘመቻ እየተካሄደ ያለው ዲፕስሉት በተባለችው 200 ሺህ ገደማ ነዋሪዎች ባሉባት ድሃ ከተማ ነው።
ዛምቢያዊቷ ሲሴሎክሌ ሞዮ ከ1998 ዓ. ም. ጀምሮ የኖረችው ደቡብ አፍሪካ ውስጥ ነው።
የከባድ በሽታ ታማሚ የሆነችው ዛምቢያዊት ብዙውን ጊዜ በከተማዋ ወደሚገኘው ክሊኒክ በማምራት የሚያስፈልጋትን መድኃኒት ትቀበላለች።
አሁን ወደ ጤና ተቋሙ ደጃፍ ስትደርስ ያጋጠማት ከወትሮው የተለየ ነገር ነው።

"ኦፕሬሽን ዱዱላ - ማስ ዲፖርቴሽን" የሚል መፈክር የተጻፈበት ቲሸትር የለበሱ ሁለት ወንዶች ክሊኒኩ ደጅ ላይ ቆመው ነበር። ወደ ጤና ተቋሙ መግባት እንዲፈቀድላቸው የሚፈልጉ ሰዎች ሰነዶቻቸውን እንዲያቀርቡ እያስገደዱ ነበር።
"ፓስፖርት አለኝ አልኳቸው። ፓስፖርት እንደማይቀበሉ ነገሩኝ። የሚፈልጉት መታወቂያ ብቻ ነው" ስትል የተፈጠረባትን ስጋት ትህትና በተላበሰ ፈገግታ ለመሸፈን እየሞከረች ትናገራለች።
በአካባቢው የሚታየው እንቅስቃሴ ወደ ግጭት ሊያመራ የሚችል ቢሆንም ባልተለመደ ሁኔታ አብዛኛዎቹ ሰዎች የተረጋጉ እና ነገሩን ከማባባስ የተቆጠቡ ነበሩ።
ተገልጋዮቹ የኦፕሬሽን ዱዱላ አባላት ከዚህ ቀደም አመጽ አስነስተው እንደነበር ያውቃሉ።የደቡብ አፍሪካ መታወቂያ ማቅረብ ያልቻሉ ሰዎች በሙሉ ወደመጡበት እንዲመለሱ ተደርገዋል።
ሞዮ በዝግታ እየተራመደች ከክሊኒኩ ደጃፍ ዘወር ካለች በኋላ መንገድ ዳር ተሰብስበው የቆሙ ሰዎችን ተቀላቀለች። ሕጻናት ልጆቻቸውን አዝለው የተሰበሰቡት ሴቶች በቀጣይ ምን እንደሚሆን በመጠባበቅ ቆመዋል።
ዕድሜዋ በ40ዎቹ ውስጥ የሆነችው ቴንዳይ ሙስቫቫም ያጋጠማት ተመሳሳይ ሁኔታ ነው።
"ሰልፍ ቆሜ እያለሁ የሚፈልጉት መታወቂያ ያላቸውን ሰዎች [ብቻ] እንደሆነ ነገሩኝ። እኔ መታወቂያ የለኝም፤ ያለኝ ፓስፖርት ነው። የመጣሁት ከሞዛምቢክ ነው፤ ስለዚህ መታወቂያ ስለሌለኝ መድኃኒቴን መውሰድ አልችልም" ትላለች።
"አገራቸው ስለሆነ የፈለጉትን እንደሚያደርጉ ይሰማኛል። እኔ መናገር አልችልም። የሚሉኝን ሁሉ ማድረግ አለብኝ። ምርጫ የለኝም" ስትል የተሰማትን አጋዥ አልባነት ስሜት ትገልጻለች።

ደቡብ አፍሪካ ውስጥ 2.4 ሚሊዮን ስደተኞች ይኖራሉ። ይህ ቁጥር ከአጠቃላዩ የሕዝብ ብዛት ከአራት በመቶ በታች እንደሆነ ይፋዊ መረጃዎች ያሳያሉ።
ብዙዎቹ ስደተኞ እንደ ሌሴቶ፣ ዝምባብዌ እና ሞዛምቢክ ካሉ ለደቡብ አፍሪካ ባለጸጋ ነዋሪዎች ሠራተኛ በማቅረብ ከሚታወቁ ጎረቤት አገራት የመጡ ናቸው።
አንዳንድ ጊዜ የሰዎችን ሕይወት ወደሚቀጥፍ አመጽ የሚቀየረው መጤ ጠልነት ደቡብ አፍሪካ ውስጥ ረዥም ጊዜ ያስቆጠረ ችግር ነው። የፀረ ስደተኝነት ስሜትም በአገሪቱ ፖለቲካ ውስጥ ቁልፍ ጉዳይ እየሆነ ነው።
ኃይልን ይጠቀማል በሚል የሚከሰሰው ኦፕሬሽን ዱዱላ ሆኖ የተጀመረው በዘመቻ እንቅስቃሴነት ነው። አሁን የፖለቲካ ፓርቲ ሆኖ የተቋቋመ ሲሆን በአገሪቱ በሚካሄደው ቀጣይ የአካባቢ አስተዳደር ምርጫ የመሳተፍ ፍላጎት አለው።
የፓርቲው መሪ የሆነቸው ዛንዲሌ ዳቡላ ድርጅቱ በጆሃንስበርግ እና በሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች በሚገኙ የሕዝብ ክሊኒኮች ደጃፍ ላይ የሚያደርገው ተግባር ምክንያታዊ መሆኑን ትናገራለች።
"ለደቡብ አፍሪካውያን ቅድሚያ እንዲሰጥ እንፈልጋለን።ድንገተኛ ሕክምና ማግኘት እንዳለብህ እንረዳለን፤ ሕገ ወጥ ከሆንክ ግን ለሕግ አካላት ተላልፈህ መሰጠት አለብህ" ስትል ለቢቢሲ ተናግራለች።
ብዙ ስደተኞች ወደ አገሪቱ የገቡት በሕጋዊ መንገድ ስለመሆኑ ሲነሳም፤ በአገሪቱ ያለው ሀብት አነስተኛ በመሆኑ ለደቡብ አፍሪካውያን ቅድሚያ ሊሰጥ እንደሚገባ ትከራከራለች።
"ሕይወት ቅደሚያ የሚሰጠው ነገር ነው፤ እርሱን አንክድም። ነገር ግን ለሁሉም ሰው ነጻ ሊሆን አይችልም። ለዓለም ሁሉ ልናቀርብ አንችልም። ያለን በቂ አይደለም" ትላለች።

የደቡብ አፍሪካ ሕገ መንግሥት በአገሪቱ ውስጥ ያለ ማንኛውም ሰው ዜግነትም ሆነ የስደተኝነት ሁኔታው ሳይገድበው የጤና አገልግሎት የማግኘት መብት እንዳለው ይደነግጋል።
የፓርቲው መሪ ዳቡላ ግን ከአገሪቱ ሕዝብ 85 በመቶ ያህሉ የሚገለገልበት የሕዝብ የጤና ሥርዓት ከአቅሙ በላይ መሸከሙን ትናገራለች።
አንዳንድ ሰዎች በአቅራቢያቸው ወደሚገኙ ክሊኒኮች በጊዜ ካልደረሱ መድኃኒት እንደሚያልቅ ስለሚያውቁ ከሌሊት 10 ሰዓት ጀምሮ እንደሚሰለፉ ትከራከራለች።
ሀብት በጥቂቶች እጅ በተያዘባት ደቡብ አፍሪካ የማኅበረሰብ እኩልነት የለም። በአገሪቱ ሥራ አጥነት እና ድህነት ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሰዋል። ሰዎች በሕይወታቸው ለሚያጋጥሟቸው ችግሮች ከድሀ ማኅበረሰብ የመጡትን ስደተኞች ተጠያቂ ያደርጋሉ።
የኦፕሬሽን ዱዱላ እንቅስቃሴ ከአንዳንድ ዲፕስሉት ነዋሪዎች ድጋፍ አግኝቷል። የቡድኑን ዘዴ ከሚደግፉት አንዱ የሆነው ደቡብ አፍሪካዊው ሲፎ ሞሃሌ የኦፕሬሽን ዱዱላን ዘመቻ "አዎንታዊ ለውጥ" በማለት ይገልጸዋል።
"ከዚህ ቀደም ጤና ተቋም ስሄድ ሰልፉ ረዥም ነበር። አሁን ግን የምፈልገውን ተቀብዬ ለመውጣት የፈጀብኝ ሁለት ደቂቃ ብቻ ነው" ይላል።
ሌላኛዋ ነዋሪ ጄነፈር ሺንጋንጅም አክቲቪስቶቹ ወደ ዲፕስሉት መምጣታቸውን ትደግፈዋለች።
"ደቡብ አፍሪካውያን ወደ ክሊኒክ ስንመጣ የምንፈልገውን መድኃኒት ማግኘት አንችልም። የውጭ ዜጎች ክሊኒኩን መጠቀም ካቆሙ በኋላ ግን ልዩነት አለ" ብላለች።
በአስገራሚ ሁኔታ አንዳንድ ደቡብ አፍሪካውያንም የፀረ ስደተኞች ዘመቻው ሰለባ ከመሆን አለመጡም።

መታወቂያ ማሳየት ያልቻሉ ደቡብ አፍሪካውያም ከሕዝብ የጤና ተቋማት ደጅ እንዲመለሱ ተደርገዋል። 10 በመቶ የሚሆኑ ደቡብ አፍሪካውያን ማንታቸውን የሚያሳይ መደበኛ ሰነድ እንደሌላቸው ይገመታል።
በኦፕሬሽን ዱዱላ እንቅስቃሴ ውስጥ የሚታየው የሕገ መንግሥት ጥሰት በሌላኛው ወገን የቆሙ አክቲቪስቶችን አስቆጥቷል።
'ኸልዝ ጀስቲስ ኢኒሼዬቲቭ' በተባለው ድርጅት የምትሠራው የሰብአዊ መብቶች ጠበቃዋ ፋቲማ ሐሰን፤ "ማን እንደሚገባ እና ማን እንደሚወጣ እንዲቆጣጠር በመንግሥት ያልተሾመ አካል መኖሩ በጣም ችግር ነው" ስትል ተቃውሞዋን ታሰማለች።
"መንግሥት ይህንን ሁኔታ በአጭር ጊዜ ውስጥ ካልተቆጣጠረ የራሱን ሕግ እና ሥርዓት የማስከበር አቅም ያጣል" በማለት ታስጠነቅቃለች።
የደቡብ አፍሪካ የጤና ሚኒስትር ዴኤታ የሆኑት ጆ ፋህላ፤ መንግሥታቸው የውጭ ዜጎች ወይም በተለያዩ አካባቢ የሚገኙ ክሊኒኮች እና ሆስፒታሎች ለመጠቀም የሚሞክሩ ሌሎች ሰዎች ዒላማ መደረጋቸውን እንደሚቃወም ለቢቢሲ ተናግረዋል።
"ጤና ሰብአዊ መብት በመሆኑ በዚህ አካሄድ አንስማማም። የአገልግሎት አሰጣጡ በአግባቡ የተደራጀ መሆን እንዳለበት እንረዳለን። [ነገር ግን አገልግሎት አሰጣጡ] ጉልበተኛ በሆነ አካሄድ አይስተካከልም" ብለዋል።

'ኢኮኖሚክ ፍሬደም ፋይተርስ' እና 'ዴሞክራቲክ አሊያንስ'ን ጨምሮ በርካታ የአገሪቱ ዋነኛ የፖለቲካ ፓርቲዎች ኦፕሬሽን ዱዱላን አውግዘዋል።
በደቡብ አፍሪካ የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ለመውሰድ ያደረገው ሙከራ ግን በቴክኒካዊ ጉዳዮች ምክንያት ሳይሳካ ቀርቷል። ይህም ቡድኑ ዘመቻውን እንዲቀጥል በር ከፍቶለታል።
በሕዝብ ጤና ተቋማት ደጃፎች ላይ ቆመው ክልከላ ያደረጉ በርካታ የኦፕሬሽን ዱዱላ አባላት ባለፉት ሳምንታት በቁጥጥር ሥር ውለዋል። በኋላ ላይም ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸው ተለቅቀዋል። ይህ የፖሊስ እርምጃ ግን ቡድኑ እንቅስቃሴውን እንዳይቀጥል ያደረገው አይመስልም።
የሰብአዊ መብቶች ጠበቃዋ ፋቲማ፤ "ፖሊስ እና ወታደሮች [እርምጃውን] ለመከላከል ከመጀመሪያው ቀን አንስቶ እዚያው መሆን ነበረባቸው፤ ምክንያቱም ሕገ ወጥ ነው" ስትል ጠንካራ እርምጃ ያስፈልጋል የሚለውን አቋሟን ታስረዳለች።
ሚኒስትር ዲኤታው ዶ/ር ፋህላ፤ ጉዳዩ ላይ ምርመራ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል። ይሁን እንጂ ፖሊስ "እንደዚህ ዓይነት ክስተት ሲያጋጥም ለመከታተል እና በወቅቱ እርምጃ ለመውሰድ የሚያስችል አቅም እንደሌለው" መግለጹን ጠቅሰዋል።
የደቡብ አፍሪካ መንግሥት ኦፕሬሽን ዱዱላን በተመለከተ መውሰድ ያለበትን እርምጃ በመተለከተ እያመነታ ባለበት በዚህ ወቅት፤ ቡድኑ የበለጠ ድፍረት እያገኘ ይመስላል።
አሁን ደግሞ ቡድኑ ፊቱን ወደ ሕዝብ ትምህርት ቤቶች እያዞረ ነው። ይህ እርምጃውም ሕገ ወጥ ስደትን የመዋጋት ዘመቻ አንዱ አካል እንደሆነ ይናገራል።















