የታዋቂ ሰዎችን ስም መነጋገሪያ ያደረገው የወሲብ ወንጀለኛው ጄፍሪ ኤፕስቲን ማን ነው?

ኤፕስቲን ከማክስዌል ጋር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ኤፕስቲን ከማክስዌል ጋር
የንባብ ጊዜ: 6 ደቂቃ

"እኔ ወሲባዊ ጥቃት አድራሽ ወንጀለኛ ሳልሆን ጥፋተኛ ነኝ" ሲል ጄፍሪ ኤፕስቲን ከኒው ዮርክ ፖስት ጋር በአውሮፓውያኑ 2011 ባደረገው ቃለ ምልልስ ተናግሮ ነበር።

ኤፕስቲን በሰጠው ቃል ምልልስ ላይ 'sexual predator' እና 'offender' የሚሉት ቃላትን ልዩነት በመግለጽ 'የወሲብ ወንጀለኛ' እንዳልሆነ ገልጿል።

"ሰው የገለደ እና ዳቦ የሰረቀ ሰው ልዩነት አለው" ሲልም ለኒው ዮርክ ፖስት ተናግሮ ነበር።

ኤፕስቲን በ2019 ነሐሴ ላይ ኒው ዮርክ በሚገኝ እስር ቤት ሞቷል። በወሲብ ንግድ ዝውውር ተከስሶ፣ የዋስትና ጥያቄው ውድቅ ተደርጎ፣ ብይን እየተጠባበቀ ሳለ ነበር የሞተው።

ታዳጊዎችን ለወሲብ ንግድ በማቅረብ ወንጀል 'sex offender' በሚል ከተፈረጀ በኋላ ታዳጊዎችን ለወሲብ ንግድ የሚያቀርበው "መጠነ ሰፊ በሆነ የወንጀል መረብ ነው" በሚል ተከስሷል።

ኤፕስቲን ጥፋተኛ አይደለሁም ሲል ተከራክሯል።

ኅዳር 2025 ላይ የአሜሪካ ኮንግረስ ሁለቱም ምክር ቤቶች የኤፕስቲን ሰነዶች ለሕዝብ ይፋ እንዲደረጉ ውሳኔ አሳልፈዋል።

ውሳኔው 'Epstein Files Transparency Act' ይሰኛል። የአገሪቱ የፍትሕ መሥሪያ ቤት ሰነዶቹን ይፋ እንዲያደርግ ትዕዛዝ ተሰጥቶታል።

ሰነዶቹ ይፋ ሲደረጉ ሰዎች ፈልገው ሊያገኙት እና በኮምፒውተር/ስልክ ሊጭኑ በሚችሉበት መንገድ እንዲሆንም ታዟል።

የኤፕስቲን ፋይሎች ይፋ መደረግ ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ የዓለም መገናኛ ብዙኃንን ተቆጣጥረዋል። ፖለቲከኞች፣ ባለሃብቶች፣ ታዋቂ ሰዎች እና ተጽዕኖ ፈጣሪዎችን እያጋለጡ ነው።

አሁንም ድረስ ይፋ ያልተደረጉ ሰነዶች አሉ። በሺዎች የሚቆጠሩ ገጾች ያሏቸው ሰነዶች ሕዝብ ሊያገኛቸው በሚችለው ድረ ገጽ ላይ መውጣታቸውን ቀጥለዋል።

የፋይናንስ ዘርፍ ባለሙያ ከነበረው ኤፕስቲን ጋር ግንኙነት የነበራቸው ሰዎች ዝርዝር ይፋ እየተደረገ ነው።

ታኅሣሥ ወር መጀመሪያ ላይ የተለቀቁ ሰነዶች ከዚያ በፊት ያልታዩ ምሥሎችን ይዘዋል። የኤፕስቲን የግል ደሴት ላይ የሚገኘው ቤቱ ውስጥ የተነሱ ምሥሎችን አካተዋል።

በርካታ መፀዳጃ ቤቶች እና ግድግዳ ላይ የተሰቀሉ የፊት መሸፈኛ ጭምብሎች በምሥሎቹ ይታያሉ።

በወሲብ ንግድ ዝውውር ተከስሶ፣ የዋስትና ጥያቄው ውድቅ ተደርጎ፣ ብይን እየተጠባበቀ ሳለ ነው የሞተው።

የፎቶው ባለመብት, Florida Department of Law Enforcement

የምስሉ መግለጫ, ኤፕስቲን በወሲብ ንግድ ዝውውር ተከስሶ፣ የዋስትና ጥያቄው ውድቅ ተደርጎ፣ ብይን እየተጠባበቀ ሳለ ነው የሞተው።

ከሒሳብ አስተማሪነት ወደ ዋል ስትሪት

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ኒው ዮርክ ተወልዶ ያደገው ኤፕስቲን ከ1970ዎቹ አጋማሽ አንስቶ፤ ዳልተን በተባለ ትምህርት ቤት ውስጥ የሒሳብ እና ፊዚክስ መምህር ነበር።

ከተማሪዎቹ የአንደኛው አባት በኤፕስቲን ብቃት ተደንቆ የአሜሪካ እና የዓለም የመዋዕለ ነዋይ ማዕከል ከሆነው የኒው ዮርኩ ዋል ስትሪት ውስጥ ከሚገኙ ባንኮች ዋና ኃላፊዎች ከአንዱ ጋር የመተዋወቅ ዕድክ አገኘ።

በባንኩ ውስጥ አጋር ሆኖ ለአራት ዓመታት ከሠራ በኋላ 'ጄ ኤፕስቲን ኤንድ ኮ' የተባለ የራሱን ድርጅት መሠረተ።

ድርጅቱ ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ ያላቸው ቱጃሮችን ሃብት በማስተዳደር ስኬታማ ሆነ።

ፍሎሪዳ ባለው ቅንጡ መኖሪያው፣ ኒው ሜክሲኮ ባስገነባው ቤት እንዲሁም ኒው ዮርክ በሚገኘው መኖሪያው ከታዋቂ ሰዎች፣ ከአርቲስቶች እና ከፖለቲከኞች ጋር መገናኘት ጀመረ።

የኒው ዮርኩ ቤት በከተማዋ ከሚገኙ የግል መኖሪያዎች ትልቁ እንደሆነ ይነገርለታል።

ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በ2002 ከኒው ዮርክ መጽሔት ጋር ባደረጉት ቆይታ "ጄፍን ለ15 ዓመታት አውቀዋለሁ። ድንቅ ሰው ነው" ብለዋል።

"ከእሱ ጋር መሆን አዝናኝ ነው። የእኔን ያህል ቆንጆ ሴቶች እንደሚወድም ይነገርለታል። አብዛኞቹ ሴቶች ደግሞ ታዳጊ ናቸው። ጄፍሪ ሕይወትን እንደሚያጣጥም ጥያቄ የለውም" ማለታቸውም ተዘግቧል።

ፕሬዝዳንቱ ኋላ ላይ በሰጡት ቃለ ምልልስ ከኤፕስቲን ጋር ያላቸው ግንኙነት በ2000 መባቻ ላይ መቋረጡን ገልጸዋል።

ይህም ኤፕስቲን ለመጀመሪያ ጊዜ ከመታሰሩ በፊት ነው።

ትራምፕ ከኤፕስቲን ጋር በተያያዘ አንዳችም የወንጀል ድርጊት ውስጥ አለመሳተፋቸውን ደጋግመው ተናግረዋል።

ኤፕስቲን "ሴቶች ላይ እየፈጸመ በነበረው ጸያፍ ድርጊት ምክንያት" ከዓመታት በፊት ትራምፕ ከክለባቸው እንዳባረሩት ዋይት ሐውስ አስታውቋል።

በኤፕስቲን ሰነዶች ስማቸው የተጠቀሰ ዝነኞች ብዙ ናቸው። በእርግጥ ስማቸው መጠቀሱ አንዳች ስህተት መፈጸማቸውን በቀጥታ የሚያመላክት አይደለም።

በ2002 የቀድሞው ፕሬዝዳንት ቢል ክሊንተን፣ ተዋናይ ኬቨን ስፔሲ እና ክሪስ ታከር በኤፕስቲን የግል ጄት ወደ አፍሪካ ተጉዘዋል።

በ2003 የወሲባዊ ጥቃት ክሶች ከቀረቡበት የፊልም ፕሮዲውሰር ሀርቪ ዌይንስታይን ጋር በመሆን ኒው ዮርክ መጽሔትን ለመግዛት ሞክረዋል። በዚያው ዓመት ለሀርቫርድ ዩኒቨርስቲ 30 ሚሊዮን ዶላር ለግሷል።

ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በ2002 ከኒው ዮርክ መጽሔት ጋር ባደረጉት ቆይታ "ጄፍን ለ15 ዓመታት አውቀዋለሁ። ድንቅ ሰው ነው" ብለዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በ2002 ከኒው ዮርክ መጽሔት ጋር ባደረጉት ቆይታ "ጄፍን ለ15 ዓመታት አውቀዋለሁ። ድንቅ ሰው ነው" ብለዋል።

የኤፕስቲን ተጨማሪ ሰነዶች ይፋ መሆናቸውን ተከትሎ የዩናይትድ ኪንግደም የሕዝብ እንደራሴ ሎርድ ፒተር ማንደልሰን ከሌበር ፓርቲ ለቅቀዋል።

ከኤፕስቲን ጋር ግንኙነት እንደነበራቸው ሰነዶቹ መጠቆማቸውን ተከትሎ "ተጨማሪ ሀፍረት ላለመፍጠር" በሚል ከፓርቲው ራሳቸውን እዳገለሉ ገልጸዋል።

ሎርድ ፒተር ማንደልሰን አምና ከአሜሪካ አምባሳደርነታቸው የተነሱትም ከኤፕስቲን ጋር በነበራቸው ትስስር ነው።

ኤፕስቲን እአአ ከ2003 እስከ 2004 በሦስት የተለያዩ አጋጣሚዎች ለሎርድ ማንደልሰን 75,000 ዶላር መስጠቱ ተገልጿል።

የኖርዌይ ልዕልት አልጋ ወራሽ ሜቴ-ማሪት ስማቸው ከመቶ ጊዜ በላይ በኤፕስቲን ሰነዶች ውስጥ መጠቀሱን ተከትሎ ድርጊታቸው "የተሳተ አካሄድ ነበር" በማለት አምነዋል።

የኖርዌይ ልዕልት ከኤፕስቲን ጋር የተለዋወጧቸው ኢሜይሎች ይፋ መውጣታቸውን ተከትሎ በኖርዌይ ፖለቲከኞች ዘንድ ዋነኛ መነጋገሪያ ሆኗል።

"ድርጊቴ የተሳሳተ ነበር። ከኤፕስቲን ጋር ማንኛውንም ግንኙነት በማድረጌ ተጸጽቻለሁ፤ አሳፋሪ ነው" ብለዋል።

ኤፕስቲን "ዘ ዱክ" ከተባለ ግለሰብ ጋር ያደረገው የኢሜይል ልውውጥም ይፋ የተደረገ ሲሆን፤ ግለሰቡ የቀድሞው የእንግሊዙ ልዑል አንድሪው እንደሆነ ይታመናል።

ሁለቱ ግለሰቦች በባኪንግሀም ቤተ መንግሥት "ምሥጢራዊ በሆነ ሁኔታ" እራት እንደበሉ የኢሜይል ልውውጣቸው ያሳያል።

ሌላ መልዕክት ኤፕስቲን "ዘ ዱክ" የተባለውን ግለሰብ ከ26 ዓመት ሩሲያዊት ጋር ለማስተዋወቅ ሲሞክር ያሳያል።

ግለሰቦቹ መልዕክት የተላላኩት በ2010 ሲሆን፤ ይህም ኤፕስቲን 18 ዓመት ያልሞላትን ታዳጊ ለወሲብ ማታለሉን ካመነ ከሁለት ዓመት በኋላ ማለት ነው። ኤፕስቲን በወቅቱ በቁም እስር ላይ ነበር።

የኤፕስቲን ሰነዶች ከዓለም ቁጥር አንድ ባለሃብት ኢላን መስክ ጋር የተደረጉ የኢሜይል ልውውጦችንም ይዟል።

ከኤፕስቲን ጋር በተያያዘ ምንም ዓይነት ክስ ያልቀረበበት መስክ፤ ከዚህ ቀደም ኤፕስቲን ወደ ደሴቱ መጥቶ እንዲጎበኘው ቢጠይቀውም ይህን እንዳልተቀበለ ይናገራል።

አሁን የተለቀቁት ኢሜይሎች እንደሚያሳዩት፤ መስክ ከአንድ ጊዜ በላይ የኤፕስቲን ደሴትን ለመጎብኘት ጥያቄ አቅርቧል።

በ2012 መስክ ለኤፕስቲን በላከው መልዕክት " ቀጣዩ ድግስ የሚካሄደው የትኛው ቀን/ምሽት ነው?" ሲል ይጠይቃል።

ኤፕስቲን ከሚስ ስዊድን ኤቫ አንደርሰን ዱቢን ጋር የፍቅር ግንኙነት ነበረው። የአሳታሚው ሮበርት ማክስዌል ልጅ ከጄስሌን ማክስዌል ጋርም የፍቅር ግንኙነት ቢኖረውም ትዳር አልመሠረተም።

የቀድሞዋ የቲፋኒ ኤንድ ኮ ኃላፊ ሮዛ ሞክተን፤ በ2003 ከ'ቫኒቲ ፌር' መጽሔት ጋር ባደረገችው ቃለ ምልልስ "ኤፕስቲን መግነጢሳዊ ኃይል ያለው፣ ጨዋታ ለመጀመር የማይከብደው ነው" ብላለች።

"ኤፕስቲንን አውቄዋለሁ ብላችሁ ስታስቡ ሁሌም አዳዲስ ማንነቶች ታገኛላችሁ። ኤፕስቲን ከሚያሳያችሁ ማንነት የዘለለ ማንነቶች አሉት" ስትልም ተናግራለች።

ኤፕስቲን "ዘ ዱክ" ከተባለ ግለሰብ ጋር ያደረገው የኢሜይል ልውውጥም ይፋ የተደረገ ሲሆን፤ ግለሰቡ የቀድሞው የእንግሊዙ ልዑል አንድሪው እንደሆነ ይታመናል።

የፎቶው ባለመብት, News Syndication

የምስሉ መግለጫ, ኤፕስቲን "ዘ ዱክ" ከተባለ ግለሰብ ጋር ያደረገው የኢሜይል ልውውጥም ይፋ የተደረገ ሲሆን፤ ግለሰቡ የቀድሞው የእንግሊዙ ልዑል አንድሪው እንደሆነ ይታመናል።

ኤፕስቲን ላይ የቀረቡ ክሶች

ኤፕስቲን በ2005 በፓልም ቢች በሚገኘው ቤቱ የ14 ዓመት ሴት ልጅ ላይ ጥቃት ማድረሱን በመግለጽ ተከስሰሷል።

ፖሊስ ቤቱን ሲፈትሽ የታዳጊ ሴቶች ምሥሎች ተገኝተዋል።

'ማያሚ ሄራልድ' ጋዜጣ ባወጣው ዘገባ መሠረት፤ ኤፕስቲን በታዳጊ ሴቶች ላይ የፈጸመው ብዝበዛ ከዓመታት በፊት የጀመረ ነው።

የፓልም ቢች ፖሊስ ኃላፊ ማይክል ሬይተር "እነዚህ የስሚ ስሚ ክሶች አይደሉም። ሴቶቹ እየተናገሩ ያሉት ተመሳሳይ ነገር ነው" ብለዋል።

በ2007 በኒው ዮርክ መጽሔት ላይ በወጣ ጽሑፍ አምደኛው ማይክል ውልፍ "የሴቶች ጉዳይ በምሥጢር የያዘው ነገር አይደለም" ብለው ጽፈዋል።

"በአንድ ወቅት ባደረግነው ቃለ ምልልስ 'ምን ልበልህ፤ ታዳጊ ሴቶችን እወዳለሁ' ብሎኛል" ሲሉም አክለዋል።

ኤፕስቲን በፌደራል ደረጃ ሊቀርብበት ከሚችለው ክስ በማምለጡ የዕድሜ ልክ እስራት ሊያስፈርድበት በሚችል ክስ ለ18 ወራት ብቻ እንዲታሰር ተወስኗል።

በእስራቱ ወቅት በቀን ለ12 ሰዓት ያህል ወደ ቢሮው እየሄደ እንዲሠራ ይፈቀድለት ነበር። ከ13 ወራት በኋላ ከእስር ተለቋል።

የኤፕስቲን የግል ደሴት ላይ የሚገኘው ቤቱ ውስጥ የተነሱ ምሥሎች በርካታ መፀዳጃ ቤቶች እና ግድግዳ ላይ የተሰቀሉ የፊት መሸፈኛ ጭምብሎች ያሳያሉ።

የፎቶው ባለመብት, US Congress

የምስሉ መግለጫ, የኤፕስቲን የግል ደሴት ላይ የሚገኘው ቤቱ ውስጥ የተነሱ ምሥሎች በርካታ መፀዳጃ ቤቶች እና ግድግዳ ላይ የተሰቀሉ የፊት መሸፈኛ ጭምብሎች ያሳያሉ።

የማያሚ ሄራልድ ዘገባ እንደሚያሳየው፤ የፌደራል ዐቃቤ ሕግ አሌክሳንደር አስኮታ ኤፕስቲን ጥፋተኛነቱን እንዲያምን በተደረገ ስምምነት አማካኝነት የሠራቸው ወንጀሎች በአጠቃላይ ይፋ እንዳይወጡ አድርገዋል። በዚህ ምክንያትም ኤፍቢአይ እያደረገ የነበረው ምርመራ ተቋርጧል።

በኤፕስቲን ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች እና ከኤፕስቲን ጋር ትስስር ያላቸው ኃያል ሰዎች ቁጥር ይፋ ከተደረገውም በላይ ሊሆን እንደሚችል ዘገባው ይጠቁማል።

የፌደራል ዐቃቤ ይፋ በተደረጉ ቅሌቶች ምክንያት በ2019 ሥራቸውን ለቅቀዋል።

ከ2008 ጀምሮ ኤፕስቲን በኒው ዮርክ የወሲብ ጥቃት አድራሾች መዝገብ ሦስተኛው እርከን ላይ ስሙ ተካቷል። ይህም በድጋሚ ወሲባዊ ጥቃት ሊያደርስ እንደሚችል የሚጠቁም እርከን ነው።

ኤፕስቲን በወንጀል ከተፈረደበት በኋላም ሃብት ንብረቱን አላጣም።

ኤፕስቲንን ከከሰሱ ሴቶች አንዷ የሆነችው ቨርጂንያ ሮበርትስ እንዳለችው ከልዑል አንድሪው ጋር ወሲብ እንድትፈጽም የተገደችው በ17 ዓመቷ ነው።

ልዑል አንድሪው ክሱን አስተባብለዋል። ከእሷ ጋር ፎቶ መነሳታቸውን እንደማያስታውሱም ገልጸዋል።

ሆኖም ግን ልዑል አንድሪው የቀረበባቸውን የወሲባዊ ብዝበዛ ክስ 2022 ላይ ሚሊዮኖች ለመክፈል በመስማማት አልፈዋል።

ኤፕስቲን የታሰረው ሐምሌ 2019 ላይ በግል ጄቱ ከፓሪስ ሲመለስ ነበር። የተከሰሰባቸውን ወንጀሎች በአጠቃላይ እንዳልፈጸመ ተናግሯል።

የዋስትና ጥያቄው በፍርድ ቤት ውድቅ ከተደረገ በኋላ በኒው ዮርክ ታስሮ ቆይቷል።

ከታሰረ በኋላ አንገቱን እንደታመመ ቢገለጽም የማረሚያ ቤት አስተዳደር እና ጠበቆቹም በጉዳዩ ላይ አስተያየት አልሰጡም።

ለመጨረሻ ጊዜ ፍርድ ቤት ከቀረበ በኋላ ለአንድ ዓመት እንደሚታሰር እየተጠበቀ ነበር። ዐቃቤ ሕግም ፍርዱ እንዲዘገይ እንደማይፈልግ ገልጿል።

ከሞተ በኋላ የቀድሞ ፍቅረኛው ማክስዌል መነጋገሪያ ሆናለች።

ነሐሴ 2020 ላይ በቁጥጥር ሥር የዋለችውም ከኤፕስቲን ጋር በማበር ተከስሳ ነው። በ2021 ከስድስት ክሶች በአምስቱ ጥፋተኛ ተብላ የ20 ዓመት እስራት ተፈርዶባታል።

ኦክስፎርድ የተማረችው ማክስዌል፤ ኤፕስቲን ቢል ክሊንተን እና ልዑል አንድሪውን ጨምሮ ከሌሎችም ተጽዕኖ ፈጣሪዎች ጋር እንዲተዋወቅ ማድረጓ ተገልጿል።

ማክስዌል ታዳጊ ሴቶችን በመመልመል በኤስቲን የወሲብ ብዝበዛ መረብ ውስጥ እንዲወድቁ አድርጋለች ተብላም ተከስሳለች።