የዩኬ እና ኖርዌይ ፖለቲከኞችን ያናወጠው የወሲብ ወንጀለኛው ኤፕስቲን ሰነድ

የኖርዌይ ልዕዕል አልጋ ወራሽ ሜቴ-ማሪት ስማቸው ከመቶ ጊዜ በላይ በኤፕስቲን ሰነዶች መጠቀሱን ተከትሎ "የተሳተ አካሄድ ነበር" ብለዋል።

የፎቶው ባለመብት, Visionhaus/Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የኖርዌይ ልዕልት አልጋ ወራሽ ሜቴ-ማሪት ስማቸው ከመቶ ጊዜ በላይ በኤፕስቲን ሰነዶች ውስጥ መጠቀሱን ተከትሎ ድርጊታቸው "የተሳሳተ አካሄድ" እንደነበር ተናግረዋል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የወሲብ ወንጀለኛው ጄፍሪ ኤፕስቲን ተጨማሪ ሰነዶች ይፋ መሆናቸውን ተከትሎ የዩናይትድ ኪንግደም የሕዝብ እንደራሴ ሎርድ ፒተር ማንደልሰን ከሌበር ፓርቲ ለቅቀዋል።

ከኤፕስቲን ጋር ግንኙነት እንደነበራቸው ሰነዶቹ መጠቆማቸውን ተከትሎ "ተጨማሪ ሀፍረት ላለመፍጠር" በሚል ከፓርቲው ራሳቸውን እዳገለሉ ገልጸዋል።

በሌላ በኩል የኖርዌይ ልዕልት አልጋ ወራሽ ሜቴ-ማሪት ስማቸው ከመቶ ጊዜ በላይ በኤፕስቲን ሰነዶች ውስጥ መጠቀሱን ተከትሎ ድርጊታቸው "የተሳተ አካሄድ ነበር" ብለዋል።

የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ጆንስ ጋር ስቶሬም ከልዕልት አልጋ ወራሿ ጋር እንደሚስማሙ ገልጸዋል።

ልዕልት አልጋ ወራሽ ሜቴ-ማሪት እአአ ከ2011-2014 ባሉት ዓመታት ውስጥ ከኤፕስቲን ጋር በተያያዘ ከመቶ ጊዜ በላይ ስማቸው መነሳቱን የአሜሪካ የፍትሕ መሥሪያ ቤት ይፋ ያደረጋቸው ሰነዶች ይጠቁማሉ።

የልዕልት አልጋ ወራሿ የ38 ዓመት ልጅ ማሪየስ ቦርግ ሆይቢ፤ በመድፈር እና ጥቃት በማድረስ ወንጀሎች በተከሰሰበት ወቅት የኤፕስቲን ሰነዶች ይፋ መሆን ንጉሣዊ ቤተሰቡን የበለጠ ማጋለጡ ተገልጿል።

የዩናይትድ ኪንግደም የሕዝብ እንደራሴ ሎርድ ፒተር ማንደልሰን ከሌበር ፓርቲ ለቅቀዋል።

የፎቶው ባለመብት, PA Media

የምስሉ መግለጫ, የዩናይትድ ኪንግደም የሕዝብ እንደራሴ ሎርድ ፒተር ማንደልሰን ከሌበር ፓርቲ ለቅቀዋል

ይፋ በተደረጉት ሰነዶች ውስጥ ስማቸው የተጠቀሰው የዩኬ የሕዝብ እንደራሴ ሎርድ ፒተር ማንደልሰን አምና ከአሜሪካ አምባሳደርነታቸው የተነሱትም ከኤፕስቲን ጋር በነበራቸው ትስስር ነው።

ኤፕስቲን እአአ ከ2003 እስከ 2004 በሦስት የተለያዩ አጋጣሚዎች ለሎርድ ማንደልሰን 75,000 ዶላር መስጠቱ ተገልጿል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ሎርድ ማንደልሰን ለሌበር ፓርቲ ዋና ጸሐፊ በላኩት ደብዳቤ "ከኤፕስቲን ጋር የሚያገናኙኝ ተጨማሪ ሰነዶች ይፋ ወጥተዋል። አዝናለሁ፤ ይጸጽተኛልም። ከ20 ዓመት በፊት ገንዘብ እንደሰጠኝ ተገልጿል። ይሄንን አላስታውስም፤ እውነተኛ ነው ብዬም አላምንም" ብለዋል።

"ሆኖም ተጨማሪ ሀፍረት ላለመፍጠር ከሌበር ፓርቲ አባልነቴ ለቅቄያለሁ። በዚህ አጋጣሚ ድምጻቸው ከዓመታት በፊት መሰማት ለነበረበት ሴቶች ያለኝን ሐዘኔታ እገልጻለሁ" ሲሉም አክለዋል።

የኤፕስቲን ሰነዶች ትክክለኛ መሆናቸውን እርግጠኛ እንዳልሆኑ ከዚህ ቀደም የተናገሩት ሎርድ ማንደልሰን ከኤፕስቲን ጋር እንደሚተዋወቁም አላመኑም ነበር።

የሌበር ፓርቲ አባል ጎርደን ሜኬት ለቢቢሲ እንደተናገሩት፤ ሎርድ ማንደልሰን ከፓርቲው መልቀቃቸው "ትክክለኛ ውሳኔ" ነው።

በሌላ በኩል የኖርዌይ ልዕልት አልጋ ወራሽ ሜቴ-ማሪት ከኤፕስቲን ጋር የተለዋወጧቸው ኢሜሎች ይፋ መውጣታቸውን ተከትሎ በኖርዌይ ፖለቲከኞች ዘንድ ዋነኛ መነጋገሪያ ሆኗል።

"ድርጊቴ የተሳሳተ ነበር። ከኤፕስቲን ጋር ማንኛውንም ግንኙነት በማድረጌ ተጸጽቻለሁ፤ አሳፋሪ ነው" ብለዋል።

ኤፕስቲን ብዝበዛ ላደረሰባቸው ተጎጂዎች "ጥልቅ ሐዘኔን እገልጻለሁ፤ ከጎናቸውም እቆማለሁ" ሲሉም ተናግረዋል።

የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ልዕልት አልጋ ወራሿ መሳሳታቸውን ገልጸዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ የንጉሣዊ ቤተሰቡ ላይ ትችት መሰንዘራቸው የተለመደ አይደለም።

የቀድሞው የኖርዌይ ጠቅላይ ሚኒስር ቶርቦጃን ጃግላንድ በኤፕስቲን የግል ደሴት የቤተሰብ ጉብኝት ለማድረግ አቅደው እንደነበር አዲስ የወጡት ሰነዶች ጠቁመዋል።

ከጠቅላይ ሚኒስትር ጆንስ ጋር በተያያዘም አስተያየት የሰጡት የአሁኑ መሪ ስቶሬ፤ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር "ተሳስተው ነበር" ብለዋል።