ትራምፕ እና ክሊንተንን ከወሲብ ወንጀለኛው ጄፍሪ ኤፕስቲን ጋር የሚያሳዩ ተጨማሪ ፎቶዎች ይፋ ተደረጉ

የፎቶው ባለመብት, House Oversight Committee
የአሜሪካ ኮንግረስ አባል የሆኑ ዴሞክራቶች፤ ከታዳጊዎች የወሲብ ንግድ ወንጀለኛው የጄፍሪ ኤፕስቲን መኖሪያ እንዲሁም ከሀብታም እና ኃያላን ሰዎች ጋር ያለውን ግንኙነት የሚያሳዩ ፎቶዎችን በሁለት ዙር ይፋ አደረጉ።
በፎቶዎቹ ላይ ከሚታዩት ታዋቂ ግለሰቦች መካከል የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ፣ የቀድሞው የዩናይትድ ኪንግደም ልዑል አንድሪው ማውንትባተን ዊንዘር እና የቀድሞው የትራምፕ አማካሪ ስቲቭ ባነን ይገኙበታል። ከፎቶዎቹ ውስጥ አብዛኛዎቹ ከዚህ ቀደምም የታዩ ሲሆኑ ምሥሎቹ በራሳቸው ጥፋት መፈጸምን አያመለክቱም።
አርብ ዕለት ይፋ የተደረጉት 100 ገደማ ፎቶዎች በፍርድ ቤት ትዕዛዝ ተላልፈው እንዲሰጡ ከተደረጉ ከ95,000 ምሥሎች መካከል እንደሆኑ የምክር ቤቱ የቁጥጥር ኮሚቴ አባላት የሆኑ ዴሞክራቶች ተናግረዋል።
በአንጻሩ፤ የአገሪቱ የፍትሕ መሥሪያ ቤት ከግለሰቡ ጋር የተያያዙ ሰነዶችን ይፋ እንዲያደርግ በሕግ የተቀመጠለት የጊዜ ገደብ አንድ ሳምንት ቀርቶታል።
ዴሞክራቶች በመጀመሪያው ዙር በተለቀቋቸው ፎቶዎች ላይ ከኤፕስቲን ጋር ከሚታዩት በርካታ ስመ ጥር ሰዎች መካከል አንዳቸውም እስካሁን በጉዳዩ ላይ አስተያየት አልሰጡም። በፎቶዎቹ ላይ የሚታዩት አብዛኛዎቹ ሰዎች ከዚህ ቀደም የፈጸሙት ስህተት አለመኖሩን ተናግረዋል።
አርብ ዕለት ከተለቀቁት ምሥሎች ውስጥ ሦስቱ ፕሬዝዳንት ትራምፕን የሚያሳዩ ናቸው። አንድ ፎቶ ላይ ትራምፕ ፊቷ እንዲሸፈን ከተደረገች አንዲት ሴት ጋር ይታያሉ።
በአውሮፓውያኑ 1997 በኒው ዮርክ ከተማ በተዘጋጀ የቪክቶሪያ ሴክሬት ድግስ ላይ የተነሳ ሌላ ፎቶ ደግሞ ትራምፕ ከኤፕስቲን አጠገብ ቆመው፤ ሞዴሏን ኢንግሪድ ሴይንሄቭ ሲያነጋግሩ የሚያሳይ ነው። ይህ ፎቶ ቀድሞውን ይፋ ወጥቷል።

የፎቶው ባለመብት, House Oversight Committee

የፎቶው ባለመብት, House Oversight Committee
ሶስተኛው ፎቶ፤ ትራምፕ ዙሪያቸውን ከከበዋቸው ከቆሙ ሴቶች ጋር የተነሱት ነው። ትራምፕ ፈገግ ብለው በሚታዩበት በዚህ ፎቶ ላይ ያሉት ሴቶች ፊት እንዲሸፈን ተደርጓል።
አንድ ተጨማሪ ፎቶ ደግሞ፤ የትራምፕን ምሥል የያዘ ቀይ አራት ማዕዘን አነስተኛ እሽግ የሚያሳይ ሲሆን፤ አጠገቡ "ትራምፕ ኮንዶም" የሚል ጽሑፍ የያዘ ምልክት ተቀምጧል።
በተለቀቁት ፎቶዎች ላይ አስተያየቱት የሰጠው ዋይት ሀውስ፤ "በተደጋጋሚ የተጋለጠ" "የዴሞክራት የፈጠራ ወሬ" እንደሆነ ገልጿል።
ከወሲብ ንግድ ወንጀለኛው ጋር በተያያዘ በተደጋጋሚ ስማቸው የሚነሳው ትራምፕ፤ ይህ ጉዳይ የሕዝብ ትኩረትን መንግሥታቸው ካገኛቸውን ስኬቶች ለማዞር በማሰብ ተቃዋሚዎቻቸው ያቀነባበሩት እንደሆነ በማንሳት ይከራከራሉ።

የፎቶው ባለመብት, House Oversight Committee
ከተለቀቁት ፎቶዎች መካከል የኤፕስቲን ግላዊ ምሥሎች ይገኙበታል። ከእነዚህ ውስጥ ኤፕስቲን የመታጠቢያ ገንዳ ውስጥ ሆኖ ይታያል። ሌላ ፎቶ ደግሞ የወሲብ መገልገያ እቃዎችን ያሳያል።
የቀድሞው አሜሪካ ፕሬዝዳንት ቢል ክሊንተን እና ቢሊዮነሩ ቢል ጌትስ ከፎቶዎቹ ላይ ከሚታዩ ሌሎች ታዋቂ ሰዎች ናቸው።
በአንዱ ፎቶ ላይ ክሊንተን ከኤፕስቲን እና ለኤፕስቲን ድርጊቶች ሁኔታዎችን በማመቻቸት በ2021 ከተፈረደባት ግዝሌን ማስክዌል ጎን ቆመው ይታያሉ። ክሊንተን ከኤፕስቲን ጋር በተያያዘ የፈጸሙት ጥፋት አለመኖሩን በመጥቀስ ከዚህ በፊት አስተባብለዋል።

የፎቶው ባለመብት, House Oversight Committee
ኤፕስቲን ስመ ጥር ከሆኑ በርካታ ሰዎች ጋር ያለው ግንኙነት እስካሁን ድረስ ሁሉንም የሚያስማማ ምላሽ ያልተገኘለት ጉዳይ ነው። ግለሰቡ በ2019 እስር ቤት ውስጥ ሆኖ ፍርዱን እየተጠባበቀ ሳለ ራሱን ማጥፋቱም ብዙዎች የራሳቸውን የሴራ ትንተና እንዲያስቀምጡ ምክንያት ሆኗል።
እነዚህ ጉዳዮች፤ በቢሊዮነሩ ግለሰብ ላይ የተደረገው ምርመራ እና ግኝቶቹ የበለጠ ግልጽ እንዲሆኑ የሚደረጉ ግፊቶች እንዲጨምር አድርገዋል። ይህንን ግፊት ተከትሎም የፍትሕ መሥሪያ ቤቱ ከግለሰቡ ጋር የተያያዙ ሰነዶችን ከሚቀጥለው ሳምንት አስቀድሞ እንዲለቅቅ የሚያስገድድ ሕግ በኮንግረስ ጸድቆ፤ በፕሬዝዳንቱ ተፈርሞበታል።















