ትራምፕ በወሲብ ንግድ ወንጀለኛው ኤፕስቲን "ቤት" ከአንዲት ተጎጂ ጋር "ሰዓታት እንዳሳለፉ" የሚጠቅስ ሰነድ ይፋ ወጣ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ታዳጊዎችን በወሲብ ንግድ በማሰማራት ወንጀል በተፈረደበት ጄፍሪ ኤፕስቲን "ቤት" ከአንዲት የጥቃት ሰለባ ጋር "ሰዓታት ማሳለፋቸውን" የሚገልጽ የኢሜይል ልውውጥ ይፋ በወጣ አዲስ ሰነድ ላይ ተገኘ።
የአሜሪካ ኮንግረስ የቁጥጥር ኮሚቴ አባል የሆኑ ዴሞክራት ሕግ አውጪዎች፤ ከጄፍሪ ኤፕስቲን ጋር የተያያዙ ከ20 ሺህ ገጽ በላይ ብዛት ያላቸው ሰነዶችን ይፋ አድርገዋል።
ዴሞክራቶች በመጀመሪያ ይፋ ያደረጉት ሦስት የኢሜይል ልውውጦችን ነበር። ይፋ ከወጡት ልውውጦች ውስጥ፤ ከተፈረደበት በኋላ በአውሮፓውያኑ 2019 ራሱን ባጠፋው ጄፍሪ ኤፕስቲን እና የረዥም ጊዜ አጋሩ በነበረችው ጊዝላኔ ማክስዌል መካከል የተደረጉ የመልዕክት ልውውጦች ይገኙበታል። በአሁኑ ሰዓት ማክስዌል በወሲብ ዝውውር ወንጀል 20 ዓመት ተፈርዶባት በእስር ላይ ነች።
በቅድሚያ ይፋ የተደረገው የኢሜይል ልውውጥ በሁለቱ ግለሰቦች መካከል በአውሮፓውያኑ 2011 የተደረገ ነው። ኤፕስቲን ለማክስዌል በጻፈው መልዕክት ላይ፤ "እንድታስተውይ የምፈልገው አንድ ነገር፤ እስካሁን ያልጮኸው ውሻ ትራምፕ ነው ... [አንዲት የጥቃት ሰለባ] ከእርሱ ጋር ቤቴ ውስጥ ሰዓታትን አሳልፋለች" ብሏል።
አክሎም ትራምፕ "በፖሊስ አዛዥ" ጭምር "አንዴም ስሙ አልተነሳም" በማለት ጽፏል። ማክስዌል በበኩሏ "ስለዚህ ጉዳይ ሳስብ ነበር" በማለት እንደመለሰች አዲስ የወጣው ሰነድ አሳይቷል።
ዴሞክራቶች መጀመሪያ ላይ እነዚህን የኢሜይል ልውውጦች ይፋ ያደረጉት የጥቃት ሰለባዋን ስም ሰርዘው ነው። ኋላ ምንም ስረዛ ሳይደረግባቸው በኮሚቴው የተለቀቁ ሰነዶች ግን የተጎጂዋ ስም "ቨርጂኒያ" እንደሆነ አሳይተዋል።
ዋይት ሀውስ፤ የሰነዶቹን ይፋ መሆን ተከትሎ ባወጣው መግለጫ ተጎጂ የተባለችው በኤፕስቲን ላይ ውንጀላዎችን በማቅረብ የምትታወቀው እና ባለፈው ዓመር ራሷን ያጠፋቸው ቨርጂኒያ ጁፍሬ ነች ብሏል። ዋይት ሀውስ በመግለጫው፤ ቨርጂኒያ "ፕሬዝዳንት ትራምፕ ምንም መጥፎ ድርጊት ውስጥ እንዳልተሳተፉ በተደጋጋሚ ተናግራለች" ብሏል።
ግለሰቧ በአውሮፓውያኔ 2016 በሰጠችው ቃል ትራምፕ በማንኛውም የበደል ድርጊት ላይ ሲሳተፉ እንዳልተመለከተች ተናግራ ነበር። በ2024 በወጣው ግለ ታሪክ መጽሐፏ ላይም ትራምፕን በመጥፎ ድርጊቶች አልጠቀሰችም።
ይፋ የወጣ ሌላ ሰነድ ኤፕስቲን እና ትራምፕን በተመለከተ በርካታ መጻሕፍትን በጻፈው ማይክል ዎልፍ መካከል የተደረ የኢሜይል ልውውጥን ይዟል። ከልውውጦቹ አንዱ በ2015 ትራምፕ ለመጀመሪያ ጊዜ ፕሬዝዳንት ለመሆን የምርጫ ቅስቀሳ ላይ እያሉ ዎልፍ ለኤፕስቲን የጻፈው ነው።
ዎልፍ፤ የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን ሲኤንኤን ትራምፕ ከእርሱ ጋር ስላላቸው ግንኙነት "ቀጥታ ስርጭት ላይ ወይም ከዚያ በኋላ በሚኖር መግለጫ ላይ" ሊጠይቁ ማቀዳቸውን ገልጾለታል።
ኤፕስቲን በበኩሉ "ምላሽ ልናዘጋጅለት የምንችል ቢሆን ኖሮ፤ [ምላሹ] ምን መሆን አለበት ብለህ ታስባለህ?" ሲል ጠይቆታል።
ዎልፍ ለዚህ ጥያቄ ምላሽ ሲሰጥ፤ "ራሱ እንዲወጣው ማድረግ ያለብህ ይመስለኛል። [ከአንተ ጋር] አውሮፕላን ውስጥ ወይም ቤት ውስጥ እንዳልነበረ ከተናገረ፤ [ይህ ድርጊቱ] ዋጋ ያለው የገጽታ ግንባታ እና የፖለቲካ ጥቅም ይሰጥሃል" ብሎታል።
አክሎም ኤፕስቲን ትራምፕ "ራሱን አሳልፎ እንዲሰጥ በማድረግ አዎንታዊ ጥቅም ሊያስገኝ በሚያስችል" መልኩ ሊጠቀምበት እንደሚችል መክሮታል። ትራምፕ የሚያሸንፉ ከሆነም "ከእርሱ እገዛ በማድረግ እዳ ሊጭንበት እንደሚችል" ነግሮታል።
የዋይት ሀውስ ፕሬስ ሴክሬታሪ ካሮሊን ሌቪት በዲሞክራቶች "ተመርጠው ወጥተዋል" ያሏቸውን የኢሜይል ልውውጦች ተችተዋል። ይህ የተደረገውም "ፕሬዝዳንት ትራምፕን የሚያጠለሽ ሐሰተኛ ትርክት በሊብራል መገናኛ ብዙኃን እንዲፈጠር" ለማድረግ ነው ሲሉ ተችተዋል።














