በእስራኤል ጥቃት ቀኑን የጀመሩት የቤይሩት ነዋሪዎች ከተማውን ለቅቀው መውጣት ጀምረዋል

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የሊባኖስ ዋና ከተማ ቤይሩት ነዋሪዎች ሌሊት ዘጠኝ ሰዓት (በኢትዮጵያ ሰዓት አቆጣጠር ከሌሊቱ 10 ሰዓት) አካባቢ ላይ በመላው ከተማ በተሰማው የእስራኤል ተከታታይ ጥቃቶች በፈጠሩት የፍንዳታ ድምጽ ከተኙበት ነቅተዋል።
እነዚህ ድምጾች የተሰሙት በኢራን የሚደገፈው ሄዝቦላህ የሮኬት ጥቃት የተፈጸመባት እስራኤል፤ የቡድኑ ይዞታዎችን ዒላማ ያደረገ ጥቃት መፈጸም በመጀመሯ ነው።
ሄዝቦላህ ባወጣው መግለጫ ጥቃቱን የፈጸመው፤ በኢራኑ ጠቅላይ መሪ አያቶላህ አሊ ኻሜኒ ላይ የተፈጸመው ግድያ የአጸፋ ምላሽ ለመስጠት እንደሆነ አስታውቋል። እርምጃውንም “ሕጋዊ ራስን የመከላከል እርምጃ” ሲል ገልጾታል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሄዝቦላህ፤ “ትክክለኛ ዒላማቸውን የሚመቱ ሮኬቶችን እና በብዛት ተጉዘው ጥቃት የሚያደርሱ ድሮኖችን” በሰሜናዊ እስራኤል በሚገኝ የሚሳዔል መከላከያ ስፍራ ላይ ማስወንጨፉን ገልጿል። ለሄዝቦላህ ጥቃት ምላሽ መስጠት መጀመሩን ያረጋገጠው የእስራኤል ጦርም፤ ጥቃቱ “ሄዝቦላህ በዘመቻው ለመሳተፍ ያሳለፈው ውሳኔ ላይ” የሚፈጸም እንደሆነ አስታውቋል።
ሄዝቦላህ፤ “ለእስራኤል መንግሥት ስጋት እንዲጋርጥ እና በሰሜን እስራኤል በሚገኙ ንጹኃን ላይ ጉዳት እንዲያደርስ” እንደማይፈቅድ ጠቅሷል። የእስራኤል ጦር ሊባኖስ ውስጥ ባሉ ከ50 በላይ መንደሮች ውስጥ የሚገኙ ነዋሪዎች አካባቢያቸውን ለቀው እንዲወጡ ትዕዛዝ ሰጥቷል።
ይህንንም ተከትሎ አገሪቱ ዜጎች መኖሪያቸውን ለቅቀው እየወጡ ነው። ቤይሩት እና ሲዶን ከተሞች ውስጥ የሚገኙ ነዋሪዎች ለቅቀው በሚወጡበት ወቅት ከፍተኛ የትራፊክ መጨናነቅ መከሰቱን የሚያሳዩ ምሥሎች ወጥተዋል።
ከአንድ ዓመት በላይ ቆየው እና እስራኤል በሄዝቦላህ ላይ ከፍተኛ ጥቃት የፈጸመችበት ውጊያን ለማስቆም በአውሮፓውያኑ 2024 በአሜሪካ አሸማጋይነት በተደረሰ ስምምነት እስራኤል እና ሊባኖስ፤የተኩስ አቁም ለማድረግ ተስማምተው ነበር። ኋላ ላይ ግን ተኩስ አቁሙ ለመጣሱ አንዳቸው ሌላኛቸውን ተጠያቂ አድርገዋል።
እስራኤል ስምምነቱ ከተፈጸመም በኋላ፤ ከሄዝቦላህ ጋር ግንኙነት አላቸው ባለቻቸው የሊባኖስ ግዛቶች ላይ በየቀኑ በሚባል ደረጃ ጥቃት ስትፈጸም ቆይታለች።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የፎቶው ባለመብት, Reuters



