በመካከለኛው ምሥራቅ እየተካሄደ ባለው ጦርነት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ምን ያህል ገቢ አጣ?

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦይንግ አውሮፕላን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

በመካከለኛው ምሥራቅ አሜሪካ እና እስራኤል ቅዳሜ ዕለት በኢራን ላይ የከፈቱትን ጦርነት ተከትሎ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ አስር መዳረሻዎች የሚያደርጋቸውን በረራዎች መሰረዙን ለቢቢሲ ገለፀ።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በመካከለኛው ምሥራቅ እየተካሄደ ባለው ጦርነት ምክንያት በሳምንት እስከ 137 ሚሊዮን ዶላር የሚገመት ገቢ እንደሚያጣ ለቢቢሲ ተናግሯል።

የአየር መንገዱ የንግድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ለማ ያዴቻ ስድስተኛ ቀኑን በያዘው አሜሪካ እና እስራኤል ከኢራን ጋር የሚያደርጉት ጦርነት በአየር መንገዱ ላይ ትልቅ ጉዳት እንደሚያስከትል ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ መካከለኛው ምሥራቅ አገራት መንገደኞችን እንዲሁም ጭነቶችን ያመላልሳል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነት ከመቀስቀሱ አስቀድሞ ወደ ዱባይ በቀን ሦስቴ በረራ የነበረው ሲሆን ወደ ሻርጃ ደግሞ አንዴ ይበር ነበር።

ወደ እስራኤል በቀን ሦስቴ፣ አቡዳቢ ደግሞ አንዴ በረራ የሚያደርገው አየር መንገዱ ወደ አማን በቀን ሁለቴ መንገደኞችን ያመላልሳል።

በዚህም የተነሳ "በአማካኝ በየዕለቱ 15 በረራዎችን እንሰርዛለን ማለት ነው" ሲሉ የድርጅቱ ኃላፊ ለቢበሲ ተናግረዋል።

ይህም ማለት ይላሉ ኃላፊው "በሳምንት የመንገደኞችን ብቻ ወደ 101 በላይ በረራዎችን እየሰረዝን ያለው።"

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የጭነት ማመላለሻዎችን በተመለከተ ሲናገሩ ደግሞ በየቀኑ ወደ እያንዳንዱ መዳረሻ አንድ አንድ በረራዎች እንደሚኖር አስታውሰው የመንገደኞች እና የእቃ ጭነት በአንድ ላይ ተደምሮ "ወደ 160 በረራዎችን ለመሰረዝ እንገደዳለን ማለት ነው" ብለዋል።

አየር መንገዱ በቀጠናው ከፍተኛ ቁጥር ያለው መንገደኞችን እንደሚያመላልስ የጠቀሱት ኃላፊው "በሳምንት ከ45 እስከ 50 ሺህ መንገደኛ እናጓጉዛለን። እንግዲህ የእነዚህ መንገደኞች መቅረት በገቢ ደረጃ ትልቅ ጉዳት ያደርስብናል" ሲሉ ተናግረዋል።

አቶ ለማ ያዴቻ በመካከለኛው ምሥራቅ የተከሰተው ጦርነት በዚሁ የሚቀጥል ከሆነ አየር መንገዱ ከመንገደኞች ጉዞ "135 ሚሊዮን ዶላር ገደማ" በሳምንት እንደሚያጣ የተናገሩት ኃላፊው ከጭነት አገልግሎት ደግሞ "ወደ 2 ሚሊዮን ዶላር ልናጣ እንችላለን" ብለው አንደሚያስቡ ተናግረዋል።

በአማካኝ ከዚህ መስመር "ከ130 እስከ 137 ሚሊዮን ዶላር ልናጣ እንችላለን" ብለዋል።

አቶ ለማ አክለውም ይህ ግን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ላይ ያን ያህል ኪሳራ ያደርሳል ማለት አለመሆኑን ጨምረው ተናግረዋል።

ይህንንም ሲያብራሩ በዚህ መስመር ላይ እየሰሩ የነበሩ አውሮፕላኖችን በጊዜያዊነት በሌሎች መስመሮች ላይ መድበው እያሰሩ መሆኑን ጠቅሰው ከዚህ መስመር የምናጣቸውን አብዛኞቹን ነገሮች ከሌላ መስመር ማግኘት እንችላለን ሲሉ ተናግረዋል።

በመካከለኛው ምሥራቅ በተቀሰቀሰው ጦርነት የትራንስፖርት ኢንዱስትሪው በጣም ይጎዳል የሚሉት ኃላፊው "መንገደኞችን እና እቃ እያጓጓዝን ነበር ገቢ የምናገኘው ያ በሚቀርበት ጊዜ የገቢ ጉዳት ያጋጥማል" ሲሉ ተጽዕኖውን ያብራራሉ።

በወጪም ደረጃ የመካከለኛው ምሥራቅ አገራት ከፍተኛ የነዳጅ አምራች በመሆናቸው እና ቀጠናው ሰላም አለመሆኑ በነዳጅ ዋጋ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ እንደሚያሳርፍ አስታውሰዋል።

ይህም የኢትዮጵያን ጨምሮ ማንኛውም አየር መንገድ የነዳጅ ዋጋ ከጨመረ ለከፍተኛ ወጪ ስለሚዳርገው ኢንዱስትሪውን ይጎዳዋል ሲሉ ግጭቱ ያለውን ተጽዕኖ አስረድተዋል።

ችግሩ በቶሎ ተፈትቶ ወደ ሥራ በቶሎ እንመለሳለን የሚል ተስፋ አለን ያሉት ኃላፊው፣ ያ እስኪሆን ድረስ ግን መስመሩ በመዘጋቱ የሚመጣውን ወጪው ለማካካስ አውሮፕላኖቹን ወደ ሌሎች መስመሮች በማሰማራት እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።

አሜሪካ እና የእስራኤል ከኢራን ጋር የሚያደርጉት ጦርነት በመካከለኛው ምሥራቅ ያለውን የአየር ጉዞ አስተጓጉሎ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን እንዳይንቀሳቀሱ አድርጓል።

በቀጣዮቸ ቀናት በእነዚህ የመካከለኛው ምሥራቅ አገራት ስለሚኖር የበረራ ሁኔታ እርግጠኛ ሆኖ መናገርም አይቻልም።

ኤኤፍፒ ያናገራቸው ባለሙያዎች በሚቀጥሉት ቀናትና ሳምንታት የሚደረጉ በረራዎች መስተጓጎላቸውን ሊቀጥሉ እንደሚችሉ አፅንዖት ያስረዳሉ።

በተለይም የባህረ ሰላጤው አገሮች የአጸፋ እርምጃ የሚወስዱ ከሆነ ጦርነቱ እየሰፋ እንደሚሄድ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚደረጉ በረራዎች ላይ ተጽዕኖዎችን ያስከትላል።

የመካከለኛው ምሥራቅ አገራት የአየር ክልላቸውን ዘግተው የሚቆዩ ከሆነ እና ጦርነቱ ካልቆመ ከባህረ ሰላጤው አገራት ወደ አውሮፓ፣ አፍሪካ እና እስያ የሚሄዱ ተጓዦች ተጨማሪ ተግዳሮቶች ይገጥማቸዋል።