‘የአፍሪካ አቪየሽን አባት’ የሚባሉት አቶ ግርማ ዋቄ ማን ናቸው? ለምንስ ከሰሞኑ አነጋጋሪ ሆኑ?

አቶ ግርማ ዋቄ

የፎቶው ባለመብት, ETHIOPIAN/FB

የምስሉ መግለጫ, አቶ ግርማ ዋቄ

በንጉሡ ዘመን አቶ ግርማ ዋቄ 4 ኪሎ የሒሳብ ተማሪ ነበሩ። ኳስ መጫወት ነፍሳቸው ነበር።

ከዕለታት አንድ ቀን የኳስ ጓደኞቻቸው “ና ቦሌ ደርሰን እንምጣ” አሏቸው።

ግርማ ዋቄ “ለምን?” ሳይሉ ተከተሏቸው።

ለካንስ ጓደኞቻቸው ለአብራሪነት ሊፈተኑ ነበር።

አቶ ግርማ ግን በጭራሽ ሐሳቡ አልነበራቸውም።

እዚያ ሲደርሱ ወረቀት ይታደላል። “ኧረ እኔ ገና የ2ኛ ዓመት ተማሪ ነኝ” አሉ።

“ችግር የለውም ተፈተን” ተባሉ፤ ወረቀት ተሰጣቸው። ተፈተኑ፤ አውሮፕላን አብራሪ ለመሆን። ክፋቱ ደግሞ አለፉ።

የሚገርም አጋጣሚ ነበር።

መሠልጠንም ጀመሩ። ትንሽ ቆይቶ ግን የሕይወታቸው የበረራ አቅጣጫ ተቀየረ።

አስተማሪዎቻቸው ጥሩ አብራሪ እንደማይሆኑ ነገሯቸው። ወደ ማርኬቲን ቀየሯቸው።

አቶ ግርማ እነሆ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የሚበሩበት ከፍታ እየጨመረ፣ ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ በኢትዮጵያ የአቪየሽን ሰማይ ላይ ነበሩ፤ እስካለፈው ሳምነት ድረስ።

‘ተወልደን ፀጉር እያለው ነው የማውቀው’

በፍጥነት ካልበረርን የአቶ ግርማ ዋቄን ረዥም የሥራ ዘመን አንዘልቀውም።

ሕይወታቸውን በወፍ በረር ብቻ እንቃኝ።

ከዘመናት በኋላ አቶ ግርማ ከተራ ኦፊሰርነት ጀምረው የካርጎ ክፍል ኃላፊ ሆነው ተመደቡ። በአየር መንገዱ የመጀመሪያው የካርጎ ዳይሬክተርም ሆኑ።

ድሮ አውሮፕላን ሰውን ያሳፍራል እንጂ እንደ መናኛ አይዙሱ ዕቃ ተሸክሞ፣ ኩሊነት ሠርቶ፣ ገንዘብ ያመጣል ተብሎ ብዙም አይዳነቅም ነበር።

በዚህ የተነሳ ለካርጎ የሚሰጠው ትኩረት አናሳ ነበር። ኧረ ዞር ብሎ የሚያየውም አልነበረም።

“ካርጎ ራሱን ችሎ ትልቅ ቢዝነስ እንዲሆን ያስቻሉት አቶ ግርማ ናቸው” ይላሉ በአቪየሽን ጉዳዮች ጋዜጠኛ እና ተንታኝ አቶ ቃለየሱስ በቀለ።

አቶ ግርማ ዋቄ ካርጎ ክፍል ዳይሬክተር ሳሉ አንድ ነፍሰ ቀጭን፣ ጎረምሳ ከወዲያ ወዲህ ‘ቱር ቱር’ ሲል ይመለከታሉ።

ይህ ወጣት ከማርኬቲንግ ተመርቆ ገና ካርጎ ክፍል መግባቱ ነበር። ትጋቱ ገረማቸው።

እያቀረቡት መጡ። ከአቶ ግርማ ቅርብ ሆኖ ረዥም ዘመን አገለገለ።

በኋላም አየር መንገዱን ለመምራት በቃ። ያ ወጣት አቶ ተወልደ ገብረማሪያም ነው።

በኋላ እርሳቸውን ተክቶ የአየር መንገዱ ሥራ አስፈጻሚ ሆነ።

አቶ ግርማ ዋቄ፤ አቶ ተወልደን መቼ እንደሚያውቋቸው ሲናገሩ፣ “ገና ሳይመለጥ - ሙሉ ፀጉር እያለው ነዋ የማውቀው” ብለው ይቀልዳሉ።

አቶ ግርማ ዋቄ በሽልማት ሥነ ሥርዓቱ ላይ

የፎቶው ባለመብት, kaleyesus bekele

የምስሉ መግለጫ, አቶ ግርማ ዋቄ በኢትዮጵያ አየር መንገድ የቦርድ ሊቀመበርነት የመንግሥትን ኃላፊነት በብቃት በመወጣት የበጎ ሰው ሽልማትን አግኝተዋል

የአቶ ግርማ ዋቄ ቀይ መስመር

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

አቶ ግርማ ዋቄ የአየር መንገዱ ከፍተኛ አመራር እያሉ የመጀመሪያው ቦርድ ሊቀመንበር ያን ጊዜ ከበረሃ የመጡት አቶ ስዬ አብረሃ ነበሩ።

ህወሓት መሩ ኢህአዴግ ሥልጣን ሲይዝ ጊዜ አየር መንገዱ ተፈተነ። ካፒቴን መሐመድን የመሰሉ ስመ ጥር ሥራ አስፈጻሚዎች ያጸኑት አየር መንገድ ተናወጠ።

ለ22 ዓመታት የአቪየሽን ጉዳዮችን በመዘገብ የሚታወቁት አቶ ቃለየሱስ አየር መንገዱ በኢህአዴግ ጊዜ ብቻ ሳይሆን በመንግሥት ለውጦች ጊዜ ሁሉ የአስተዳደር መንገጫገጭ (management Turbulence) ይገጥመው ነበር ይላሉ።

ለምሳሌ ንጉሡ ሲወርዱ ደርግ ከአየር ኃይል ጄኔራል አምጥቶ በኃላፊነት ሾመ። ካድሬዎችንም በውስጡ ሰግስጎ ነበር።

የደርግ ጥላቻ መነሻው የነበረው አየር መንገዱ ‘የንጉሡ አየር መንገድ ነው’ ከሚል እሳቤ ነበር።

በኋላ ግን ደርግ ትንፋሽ ሲወስድ ከስህተቱ ተምሮ አየር መንገዱን አንጻራዊ የአስተዳደር ነጻነትን አጎናጸፈው።

አቶ ግርማ ዋቄ በወቅቱ ደርግ ለአየር መንገዱ የነበረውን አሉታዊ ስሜት ሲገልጹ፣ “ጭራሽ አየር መንገድ አያስፈልገንም” የሚሉ ሰዎችም ነበሩበት ይላሉ።

ለምን ሲባሉ “አውሮፕላን ‘ለንጉሡ ጉራ እና ሽርሽር ሲባል እንጂ ለዚች ድሃ አገር ምን ይፈይድላታል?’ ብለው ይሉ ነበር-ደርጎች” ሲሉ ያስታውሳሉ።

ኢህአዴግ ሲመጣ ሌላ ጣጣ መጣ።

አየር መንገዱን ጥምድ አድርጎ ያዘው፤ የኢህአዴግ በጎ ያልሆነ አመለካከት መነሻው ደግሞ ሌላ ነው። አየር መንገዱ በደርግ ጦርነት ጊዜ “ስንቅ እና ትጥቅ እያቀበለ አስፈጅቶናል” የሚል።

በዚያ አስቸጋሪ ዘመን የቦርድ ሊቀመንበሩ አቶ ስዬ አብረሃ ነበሩ።

የመንግሥት ጣልቃ ገብነት በዛ። በርካታ ጎምቱ የአየር መንገዱ ሠራተኞች መልቀቅ ያዙ። አቶ ግርማ ዋቄም ቀድመው ለቀቁ። 37 ሌሎች ከፍተኛ አመራሮችም ተከተሏቸው።

አንጋፋው አየር መንገድ ክንፉ የተመታ ያህል መንገታገት ያዘ።

አቶ ግርማ ዋቄ ለአምስት ወር ሥራ ፈተው አዲስ አበባ ተቀመጡ።

ከዚያም የገልፍ አየር መንገድ በሚያጓጓ ደመወዝ ወሰዳቸው።

ከገልፍ በተሻለ ደመወዝ ዴኤችኤል (DHL) ወሰዳቸው።

ከዴኤችኤል እንደገና ገልፍ በተሻለ ኃላፊነት እና ደመወዝ መልሶ ወሰዳቸው። እንዲህ እንዲያ እያሉ 9 ዓመት ውጭ ቆዩ።

የገልፍን የካርጎ ክፍል በኃላፊነት እያስተዳደሩ ሳለ አንድ ቀን ከከባድ ባለሥልጣን፣ ከባድ የስልክ ጥሪ ደረሳቸው።

ለካንስ አገር ቤት ለአየር መንገዱ የቦርድ ሰብሳቢ ለውጥ ተደርጎ ነበር።

ቦታውን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የነበሩት አቶ ስዩም መስፍን ተረክበውታል። ወደ ግርማ ዋቄ የደወሉትም እርሳቸው ነበሩ።

ከ5ሺህ ዶላር ወደ 5ሺህ ብር ደመወዝ

አየር መንገዱ ፈተና ውስጥ ገብቶ ነበር፤ በዚያ ዘመን።

አቶ ስዩም መስፍን አመራሩን ሰብስበው “ታዲያ ምን ተሻለን?” ብለው አማከሩ።

“ግርማ ዋቄ የሚባል ጎበዝ ሰው አለ እሱን አምጣው” ተባሉ።

ለዚያ ነበር አቶ ስዩም ወደ ግርማ ዋቄ ስልክ የመቱት።

ደግሞ መጥተህ አናግረኝ አይደለም ያሏቸው። መጥቼ ላናግርህ ነበር ያሏቸው።

የአንድ አገር የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እንዴት እኔን መጥቶ ያናግረኛል፤ “ባይሆን እኔ መጥቼ ላናግርዎ” ብለው አቶ ግርማ ዋቄ ቅዳሜ ቀን ኢትዮጵያ ከተፍ አሉ።

አቶ ስዩም መስፍን ሊያግባቧቸው ሞከሩ። “እባክህ ያሳደገህን አየር መንገድ ታደገው” ተባሉ።

በዚያን ወቅት (በፈረንጆች 2003/04) የአቶ ግርማ ደመወዝ ጥቅማ ጥቅም ሳይጨምር 5ሺህ ዶላር ነበር። ደመወዝ ሲጠየቁ “ያው ብስራትን የምትከፍሉትን ክፈሉኝ፤ ይበቃኛል” አሉ።

“አገርህ ትፈልግሃለች ስለው 5ሺህ ዶላሩን ትቶ በ5ሺህ ብር ወደ ኢትዮጵያ አየር መንገድ መጣ” ብለው አቶ ስዩም መስፍን ሲመሰክሩላቸው በቦታው ነበርኩ ይላሉ ጋዜጠኛ ቃለየሱስ በቀለ።

አቶ ግርማ በአንድ ወቅት በአንድ የአገር ውስጥ ቴሌቪዥን ይህንኑ አስመልክተው ሲናገሩ፣ “የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሥራ አስፈጻሚ ደመወዝ እኮ አፍሪካ ውስጥ 3 አውሮፕላን ከሚያስተዳድር አንድ ግለሰብ ደመወዝ ያነሰ ነው፤ እርካታው ግን የትየሌሌ ነው” ብለው ነበር።

“በደመወዝማ ቢሆን ማንም ሰው ኢትዮጵያ አየር መንገድ አይሠራም ነበር” ሲሉም ጨምረው ተናግረዋል።

ብቻ “ያሳደገህን አየር መንገድ ና እና ተረከብ” ተብለው ሲጋበዙ ዐይናቸውን አላሹም። ግን ደግሞ አንድ ጥብቅ ቅድመ ሁኔታ አስቀመጡ።

“ጣልቃ ከገባችሁብኝ እለቃለሁ” ብለው አስፈራሩ። አቶ ስዩም ቃል ገቡላቸው።

“አንድም ቀን ቃላቸውን አላጠፉብኝም፤ ሰባት ዓመት ሙሉ ነጻነቴን ጠብቀውልኛል” ብለዋል አቶ ግርማ ዋቄ የቀድሞውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ስዩም መስፍንን ሲያመሰግኑ።

ከዚያስ ምን ሆነ?

ከዚያማ አሥራ አንድ ዓመታት የተለዩትን አየር መንገድ ማቃናት ጀመሩ።

ሥልጣኑን በተረከቡ ማግስት ‘ትክክለኛ ባለሙያዎችን ትክክለኛ ቦታ ላይ በመመደብ’ ጀመሩ።

መንገጫገጭ የገጠመውን አየር መንገድ መስመር አስያዙት።

አቶ ተወልደ ያኔ ኒውዮርክ ሄደው ነበር።

አቶ ግርማ ዋቄ ለአቶ ተወልደ ጥሪ አደረጉላቸው። “ና ባክህ አግዘኝ” አሏቸው። ድሮ በካርጎ ክፍል ይተዋወቁ የለ?

አቶ ተወልደ ሳይውሉ ሳያድሩ ወደ ኢትዮጵያ ተመለሱ።

ቺፍ ኦፕሬቲንግ ኦፊሰር አድርገው መደቧቸው።

ጊዜው ክንፍ አውጥቶ በረረ።

በፈረንጆች 2014 ነገሮችን ለማስተካከል ብቻ ቃል ገብተው ሥራ የጀመሩት ግርማ ዋቄ፣ ከአየር መንገዱ ጋር ሊለያዩ አልቻሉም።

እርሳቸው ልልቀቅ ሲሉ - አቶ ስዩም “በፍጹም!” ሲሏቸው እንደቀልድ ዓመታት ነጎዱ።

በመጨረሻም እአአ ጃንዋሪ 2011 “አሁንስ በቃ ልሂድ” ብለው ቆረጡ። እንግዲያውስ የምትተማመንበትን ተተኪ አምጣ ተባሉ።

“ተወልደ ይረከበኝ” አሉ። በክብር ሽኝት ተደርጎላቸው ለቀቁ። በክብር ብቻ ሳይሆን በለቅሶ ተሸኙ።

አቶ ግርማ ዋቄ ከቀናት በፊት በናይሮቢ የአቪየሽን ጉባኤ ላይ በተሳተፉበት ወቅት

የፎቶው ባለመብት, Aviadev Africa

የምስሉ መግለጫ, አቶ ግርማ ዋቄ ከቀናት በፊት በናይሮቢ የአቪየሽን ጉባኤ ላይ በተሳተፉበት ወቅት

የአቶ ግርማ ‘ድሪምላየነሮች’

አቶ ግርማ ለአየር መንገዱ ብዙ አልመዋል። ካለሟቸው ብዙዎቹን አሳክተዋል ይላሉ የአቪየሽን ጋዜጠኛ እና ተንታኝ አቶ ቃለየሱስ።

ከእነዚህ አንዱ ካርጎ ክፍሉን ሁነኛ የገቢ ምንጭ ማድረግ ነው።

ሌላው የድሪምላይነር 787 አሥር አውሮፕላኖችን በወቅቱ 1.5 ቢሊየነር ዶላር ወጪ አስደርገው ግዢ ማሳካታቸው ነው።

“ከፍተኛው ስኬታቸው ርዕይ-2010 (VISION 2010) ቀርጸው ማስተግበራቸው ነው” ይላሉ አቶ ቃለየሱስ።

ይህን ያሳኩት ደግሞ ከአቶ ተወልድ ጋር በመሆን ነበር። ለአየር መንገዱ ትልቅ ለውጥ ያመጣ የአምስት ዓመት ስትራቴጂ ነበር።

ይህ ስትራቴጂ በ2010 (እአአ) አየር መንገዱን የአንድ ቢሊዮን ዶላር ገቢ ያለው አየር መንገድ ማድረግ አስቻለ።

ድሮ የናይጄሪያ እና ደቡብ አፍሪካ አየር መንገዶች የኢትዮጵያ አየር መንገድን ቁልቁል ይመለከቱት ነበር። ድሮ አንዳንድ የአረብ አገራት አየር መንገዶች የኢትዮጵያ አየር መንገድ አጠገባችን ለምን ይቆማል ብለው ይንቁት ጀምረው ነበር።

አሁን የብዙ አገራት ሕልም ኢትዮጵያ አየር መንገድን መሆን ነው። “ይህ እንዲሆን ብዙ ሰዎች ተግተዋል፤ ግን ደግሞ የግርማ ዋቄ ሚና ትልቅ ነው ይላሉ” የአቪየሽኑ ተንታኝ።

አቶ ግርማን አፍሪካዊያን ለምን ያደንቋቸዋል?

አቶ ግርማ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ በጡረታ እንደተገለሉ ተሻምታ የወሰደቻቸው ርዋንዳ ናት።

አቶ ግርማ ግን ማረፍ ፈልገው ነበር። ከልጆቻቸው ጋር ዘለግ ላለ ጊዜ መቆየት፤ የባለቤታቸውን የከብት ርቢ ማገዝ ወዘተ ነበር ዕቅዳቸው።

ማረፍ የቻሉት ግን አንድ ዓመት ብቻ ነው።

ርዋንዳ ሁለት ኃላፊነት ሰጠቻቸው።

የርዋንዳ አየር መንገድን ‘በሁለት ክንፉ እንዲበር’ ማስቻል አንዱ ነው። ለዚህ የቦርድ ሊቀመንበር ተደርገው ተሾሙ።

ሁለተኛው ደግሞ የርዋንዳ የትራንስፖርት ሚኒስትር የአቪየሽን ጉዳዮች አማካሪ ሆኑ።

አቶ ግርማ ርዋንዳ በድምሩ አምስት ዓመት አገለገሉ።

“በቆይታቸው ለአየር መንገዱ ጥሩ መሠረት ጥለዋል፤ ለኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች የሥራ ዕድልን ከፍተዋል” ይላሉ ጋዜጠኛ ቃለየሱስ።

ከሩዋንዳ በኋላ የቶጎ ፕሬዝዳንት የአቪየሽን ጉዳዮች አማካሪም ሆነዋል።

በሌሎች የአፍሪካ አገራትም ኦፊሳላዊ ባልሆነ መንገድ ምክር ይለግሱ ነበር።

በትልልቅ የኢቪየሽን ጉባኤዎች ላይ እየተጋበዙ የአፍሪካ አየር መንገዶች እርስ በእርስ ተጋግዘው መሥራት እንዳለባቸው ይመክሩ፣ ይዘክሩ ነበር።

በዚህ የተነሳ የአፍሪካ አቪየሽን አባት (The father of African Aviation) የሚል ተቀጽላን አገኙ።

“ቅጽል ስም ብቻ አይደለም፤ ‘Girma Waqe life achievement award’ የሚባል የሕይወት ዘመን ሽልማት በስማቸው ይሰጣል” ይላሉ የአቪየሽን ጋዜጠኛ ቃለየሱስ።

ይህ ጽሑፍ ሲጠናቀር አቪያዴቭ (Aviadev) የሚባለው የአፍሪካ አቪየሽን ጉባኤ ተደርጓል። ናይሮቢ ውስጥ በስማቸው ሽልማት ተበርክቷል። ሸላሚውም አቶ ግርማ ዋቄ ራሳቸው ነበሩ።

በአፍሪካ የአቶ ግርማ ስም ከፍ ያለ ነው የሚሉት ጋዜጠኛ ቃለየሱስ፣ ለዚህ የሚጠቅሱት ማስረጃ ከአንድም ሁለት ሦስቴ ርዋንዳ በሥራ አጋጣሚ በተጓዙባቸው ወቅቶች የታዘቧቸውን ሁኔታዎች ነው።

“በቃ ሁሉም ዋቄ ዋቄ ሲሉ ነው የሚሰማው፤ ዝቅ ብለው በአክብሮት ጭምር ነው የሚጨብጧቸው፤ አቶ ግርማ እዚያ ትልቅ ስም ነው ያላቸው፤ ያስደንቃል።”

አቶ ግርማ ዋቄ፣ አቶ መስፍን ጣሰው (የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ) እና አቶ ቃለየሱስ በቀለ (የአቪየሽን ጉዳዮች ጋዜጠኛ እና ተንታኝ)

የፎቶው ባለመብት, kaleyesus bekele

የምስሉ መግለጫ, አቶ ግርማ ዋቄ፣ አቶ መስፍን ጣሰው (የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ) እና አቶ ቃለየሱስ በቀለ (የአቪየሽን ጉዳዮች ጋዜጠኛ እና ተንታኝ)

አቶ ግርማ ከቦርድ መልቀቃቸው ለምን አነጋገረ?

የኢትዮጵያ አየር መንገድን በሕይወት ዘመኑ በርካታ የፖለቲካ እና ወታደራዊ ሰዎች በቦርድ ሊቀመንበርነት መርተውታል።

አቶ ስዬ አብረሃ ከትግል በረሃ መጥተው ቦርድ ሊቀመንበር ሆነዋል። አቶ ስዩም መስፍን፣ አቶ አዲሱ ለገሠ፣ አቶ አባዱላ ገመዳ፣ ዳግማዊት ሞገስም አንዲሁ።

ቦርድ ሊቀመንበር መሆን ያለበት የአቪየሽን ሰው ብቻ ነው ወይ የሚለውን ቁልፍ ጥያቄ ጋዜጠኛ ቃለየሱስ “የግድ አይደለም” ይላሉ።

የጄኔራል ይልማ መርዳሳ መምጣትንም በበጎ መንፈስ ነው የሚመለከቱት።

በቦርድ አባልነት ለአቪየሽን ቅርብ የሆነ ሰውን ማካተት ጥቅሙ ብዙ እንደሆነም ያስረዳሉ።

ለዚህም በዋቢነት ብዙ ማስረጃዎችን ያነሳሉ።

ነገር ግን 22 ዓመታት በአቪየሽን ጉዳዮች የጻፉት ጋዜጠኛ ቃለየሱስ፣ አንድ ሁለት ነገሮች ሳያሳስቧቸው አልቀረም። ይህ መንግሥት እጁን ወደ አየር መንገዱ አርዝሞ እያስገባ ይሆን? የሚለው አንዱ ነው።

አቶ ግርማ ዋቄ በሚገባቸው ክብር አለመሸኘታቸውም ጥሩ አዝማሚያ እንዳልሆነ ይሰማቸዋል።

የመንግሥት ሰው ቦርድ ሊቀመንበር ቢሆን ምንድነው ችግሩ?

በእርግጥ የቦርድ ሚና ምንድነው?

በአጭሩ የማኔጅመንትን የሥራ ዕቅድ ተመልክቶ ገምግሞ ማጽደቅ ነው።

የአቪየሽን ዕውቀት ያለው ሰው በቦርዱ ሲካተት ዝም ብሎ የቀረበለትን ሁሉ አያጸድቅም።

“ነገር ግን ሊቀመንበሩ የግድ የአቪየሽን ዕውቀት ይኑረው አይባልም” ይላሉ ጋዜጠኛ ቃለየሱስ።

የቀድሞው ሥራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደም በዚህ ሐሳብ የሚስማሙ ይመስላል።

ለአንድ የአገር ቤት ቴሌቪዥን በሰጡት አንድ ቆየት ባለ ቃለ ምልልሳቸው ላይ፣ የአቶ ግርማ ዋቄን የቦርድ ሊቀመንበርነት ሚና ሲያወሱ አንዲህ ተናግረው ነበር፤ አቶ ተወልደ።

“የአየር መንገድ ኢንዱስትሪ ጸባዩ የተለየ ነው፤ በዚህ ሥራ ያለፈ ሰው ቦርድ ላይ ሲቀመጥ አስተዋጽኦው ቀላል አይደለም። ሥራ አስፈጻሚ ጡረታ ሲወጣ ቦርድ ይመራል፤ በዓለም አቀፍ ደረጃም የሚሠራበት ነው” በማለት የቀድሞው የሉፍታንዛ ሥራ አስፈጻሚ ቦርድ እየሠሩ እንደሆነ በዋቢነት ጠቅሰው ነበር።

አንድ የመንግሥት ባለሥልጣን ቦርድ ሊቀመንበር ቢሆን ታዲያ ችግሩ ምንድነው?

ጄኔራል ይልማ ለምሳሌ ላለፉት ሁለት ዓመታት ቦርድ አባል ነበሩ። የቀድሞው የአየር ኃይል አዛዥ ጄኔራል አደም መሐመድም ቦርድ አባል ነበሩ።

በደርግ ጊዜም ተመሳሳይ ሆኗል።

አሁን የአቶ ግርማ ዋቄ ተነስተው ጄኔራል ይልማ መምጣታቸው ለምን ይህን ያህል አነጋገረ? ለሚለው ማንም አጥጋቢ ምላሽ ያለው አይመስልም።

ጋዜጠኛ ቃለየሱስ “ከአቪየሽን ጋር የቅርብም የሩቅም ልምድ ያለውን ሰው በቦርድ አባልነት መያዝ ጥቅም እንጂ ጉዳት የለውም” ሲሉ በድጋሚ ያሰምሩበት እና አሳሳቢ የሚሉትን አዝማሚያ ግን ያስከትላሉ።

የአቶ ግርማን መነሳት አሳሳቢ ያደረገው ካላቸው የካበተ ልምድ አንጻር፣ ግልጽነት ባልሰፈነበት ሁኔታ ድንገት መነሳታቸው ይመስለኛል ካሉ በኋላ፤ “ይህ ደግሞ ጥሩ ልምድ አይደለም” ይላሉ።

“ለምሳሌ ልንገርህ፤ አሁን እዚህ አሜሪካ ነው ያለሁት፤ ይህ ዜና ከወጣ በኋላ እንኳ በሥራ አጋጣሚ የአቪየሽን ሰዎችን አግኝቻለሁ። ነገሩ ግር ብሏቸዋል።”

አቶ ግርማ ዋቄ እና አቶ መስፍን ጣሰው

የፎቶው ባለመብት, kaleyesus bekele

የምስሉ መግለጫ, አቶ ግርማ ዋቄ እና አቶ መስፍን ጣሰው

“ግርማ ዋቄ የሚለው ስም ለአበዳሪዎች ዋስትና ነው”

አቶ ግርማ ዋቄ የተሰናበቱበትን ሁኔታ ለየትኛውም ሚዲያ አልገለጹም።

ይህ ደግሞ የበለጠ ሁኔታውን ግራ አጋቢ አድርጎታል። የተነሱበት አግባብም ለትንበያ ክፍት አድርጎታል።

የአቪየሽን ጉዳዮች ጋዜጠኛ ቃለየሱስ፤ የእርሳቸው ቦርድ ሊቀመንበር ሆኖ መቀመጥ ልምዳቸው ብቻ አልነበረም ትርፉ ይላሉ። “ስማቸውም ብራንድ ነበር።”

ቃለየሱስ “ዋቄ የሚለው ስም ለአበዳሪዎች ጭምር መተማን ይፈጥራል” ብለው ይከራከራሉ።

አውሮፕላን የሚገዛው በዱቤ ነው። አበዳሪዎች ደግሞ እምነት ሊኖራቸው የግድ ነው።

ኤክዚም ባንክ፣ ዩሮፒያን ክሬዲት ኤጀንሲ የብድር ዋስትና ይሰጣሉ። ሲሰጡ ታዲያ ብድር አቅራቢዎች የአየር መንገዱን የብድር ታሪክ፣ የሒሳብ መዝገብ ብቻ አይደለም የሚያዩት። የተረጋጋ ማኔጅመንት እና ቦርድ አለ ወይ? ብለውም ይፈትሻሉ።

ይህ በብድር ሒደት ላይ የራሱ ነጥብ አለው የሚሉት ጋዜጠኛ ቃለየሱስ፣ አየር መንገድ ላይ የመንግሥት ጣልቃ ገብነቱ ከታየ አበዳሪዎች እምነታቸው ይሸረሸራል ሲሉ ያስረዳሉ።

“እርግጥ ነው አቶ ግርማ ስለለቀቁ አየር መንገዱ ነገ ችግር ላይ ይወድቃል የሚል እንደምታ መፈጠር የለበትም፤ ሆኖም ግን አዝማሚያው ያሳስበኛል።”

ቃለየሱስን ከሆነው ይልቅ የሚሆነው ያሰጋቸው ይመስላል።

“አቶ መስፍን ጣሰው ቀላል ልምድ ያላቸው ሰው አይደሉም። ከዩኒቨርስቲ ከወጡ ጀምሮ ለ39 ዓመታት አቪየሽን ላይ የቆዩ ናቸው፤ ነገ ደግሞ እርሳቸው ተነስተዋል ቢባልስ?”

እሱ ከአየር መንገድ ወጣ እንጂ አየር መንገዱ ከእርሱ አልወጣም ነበር

በሥራቸው ባህሪ የተነሳ አየር መንገዱ ቤት ነው የሚሉት ጋዜጠኛ ቃለየሱስ፣ አቶ ግርማ ዋቄ ቦርድ ሰብሳቢ ሆነውም ከቢሮ አካባቢ ንቅንቅ አይሉ እንደነበር ታዝበዋል።

“ይህ በቦርድ አሠራር የተለመደ አይደለም፤ ‘ቦርድ ሩም’ የሚባል አለ፤ የቦርድ ሰብሳቢን ግን ሁልጊዜ ማየት አልተመደም” የሚሉት ቃለየሱስ፣ አቶ ግርማ ግን ከአቶ መስፍን ጣሰው ቢሮ ፊት ለፊት ትንሽዬ ቢሮ ይዘው ሁልጊዜ ሲሠሩ ነበር የማያቸው። ሲሉ ትዝብታቸውን ለቢቢሲ አጋርተዋል።

የመንግሥት ጣልቃ ገብነት ላይ የማያወላዳ አቋም እንዳላቸው የሚታወቁት አቶ ግርማ፣ አሁን በምን አግባብ እንደለቀቁ ቢቢሲ ለማወቅ በእጅ ስልካቸው ተደጋጋሚ ሙከራ አድርጎ አልተሳካለትም።

ግርማ ዋቄ ቀደም ባሉ ቃለ ምልልሶቻቸው ደጋግመው ከሚያነሷቸው ጠንካራ ሐሳቦች መካከል “ጣልቃ ገብነትን አለመውዳቸው” ነው።

ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ “እከሌን ቅጠር፤ ወደዚህ ብረር፤ ያን አውሮፕላን ግዛ የሚለኝን አልወድም” ብለው ያውቃሉ።

ግርማ ዋቄ ድሮም ቢሆን ሥራ ለቀው አየር መንገዱን እርግፍ አድርገው መተው እንዳልቻሉ በቅርብ የሚያውቋቸው ይመሰክራሉ።

ለምሳሌ ከአየር መንገዱ ለ11 ዓመታት ተለይተው በገልፍ አየር መንገድ በሚሰሩበት ጊዜም ቢሆን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ነገር ያስጨንቃቸው ነበር።

በአንድ ወቅት የቀድሞው ሥራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ በሰጡት ቃለ ምልልስ “ጋሽ ግርማ ጡረታ ወጥቶ ሳለ እንኳ አንድ ነገር ኮሽ ባለ ቁጥር ይደውልልኝ ነበር” ሲሉ ለዚህ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።

ግርማ ዋቄ ከአየር መንገዱ ይወጣል እንጂ አየር መንገዱ ከግርማ ዋቄ አይወጣም።

ለመሆኑ አቶ ግርማ ዋቄ ለምን ለቀቁ?