በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ሁለት ቱርካውያን ጎብኚዎችን ጨምሮ ሦስት ሰዎች በታጣቂዎች ተገደሉ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ሱሪ ወረዳ ጉብኝት ላይ የነበሩ ሁለት የቱርክ ዜጎች እና አንድ ኢትዮጵያዊ በታጣቂዎች መገደላቸውን የወረዳው አስተዳደር ገለጸ። የክልሉ መንግሥት ጎብኚዎቹ ላይ ለደረሰው ጥቃት "ያልታወቁ አርብቶ አደር ሽፍቶች" ያላቸውን አካላት ተጠያቂ አድርጓል።
የቱርክ ዜግነት ላላቸው ሁለት ጎብኚዎች እና አብሯቸው ለነበረው አሽከርካሪ ህልፈት ምክንያት ሆነው ጥቃት የተፈጸመው ሰኞ ጥር 4/2018 ዓ.ም. ጠዋት ላይ እንደሆነ የሱሪ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ባርዱላ ኦሌጱሴኒ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
አንድ የአካበቢው አስጎብኚ ለቢቢሲ እንደገለጸው ሁለቱ የቱርክ ዜጎች ምዕራብ ኦሞ ዞን ውስጥ በሚገኘው ሱሪ ወረዳ ሁለት ቀን መቆየታቸውን ለቢቢሲ ገልጿል። ጥቃቱ የተፈጸመባቸውም በአካባቢውን የነበራቸውን ጉብኝት ጨርሰው እየወጡ በነበሩበት ሰዓት እንደሆነ አስረድቷል።
ጥቃቱ የተፈጸመው "ቱሚ" ወደተባለችው የማጂ ወረዳ ቀበሌ እየተጓዙ ሳለ ባንክ የተባለ ቀበሌ ላይ እንደሆነም አክሏል። የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ አቶ ባርዱላም፤ ጥቃቱ የተፈጸመው ከማጂ ወረዳ ጋር በሚያጎራብት ስፍራ ላይ እንደሆነ ተናግረዋል።
"እኛ ጋር ቱሪስቶች የሚያርፉባቸው ቦታዎች አሉ። እዚህ ጊዜያቸውን ጨምርሰው ወደ ማጂ ለመሄድ መንገድ ላይ እያሉ ነው፤ በእኛ እና በማጂ መካከል [ባለ ስፍራ] እንደዚህ ዓይነት ነገር የተፈጠረው" ብለዋል።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ሰኞ ምሽት ባወጣው መግለጫ፤ "ሁለት ቱርኪዬ ዜግነት ያላቸዉ የውጭ ሀገር ጎቢኚዎች እና አንድ ኢትዮጵያዊ ዜግነት ያለዉ አሽከርካሪ" መገደላቸውን አስታውቋል። የክልሉ መንግሥት ጥቃቱን ያደረሱት "ያልታወቁ የአርብቶአደር ሽፍቶች" እንደሆኑ በመግለጫው ላይ ጠቅሷል።
"የክልሉ መንግሥት ይህንን አረመኔያዊ ድርጊት የፈጸሙትን ሽፍቶች ተከታትሎ ለሕግ ለማቅረብ የተቀናጀ የፀጥታ ኃይል በማሰማራት ሰፊ የሕግ ማስከበር ሥራ እያካሄደ ይገኛል" ሲልም ጥቃት ፈጻሚዎቹን ለመያዝ እንቅስቃሴ ላይ መሆኑን ገልጿል።
በጥቃቱ ሕይወታቸው ያለፈው የቱርክ ዜጎች አስከሬን ወደ አዲስ አበባ መላኩን የሱሪ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ባርዱላ ለቢቢሲ ተናግረዋል።















