የኢየሱስ ስቅለት እና ሞት በሕክምና ባለሙያዎች ዓይን እንዴት ይተነተናል?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የሰውን ልጅ በስቅላት መቅጣት ለመጀመሪያ ጊዜ ተግባራዊ የሆነው ከክርስቶስ ልደት በፊት በ479 ዓመተ ዓለም በፋርሶች ነበር።
ከዚያ በኋላ ግን ሮማውያን ከክርስቶስ ልደት በፊት በ100 ዓመተ ዓለም አሁን የሚታወቅበትን መልክ ሰጥተው ተግባራዊ ማድረግ ጀመሩ።
ይህንን የቅጣት ዓይነት ባለሙያዎች በሰው ልጆች ከሚፈጸሙት የሞት ቅጣቶች ሁሉ የከፋው ሲሉ ይገልጹታል።
ይህ የሞት ቅጣት የሚፈረድባቸው ሰዎች በከፍተኛ ወንጀል የተጠረጠሩ እና የተፈረደባቸው ወንዶች ናቸው።
በመስቀል ላይ ተቸንክሮ እንዲሞት የሚቀጣ የትኛውም ወንጀለኛ የሚሞተው በሚያጋጥመው ከባድ ስቃይ ቀስ በቀስ ነው።
ስቅላት የሚፈጸመው አላፊ አግዳሚ እንዲያይ በአደባባዮች ላይ ሲሆን፣ ወንጀለኛውም ሕይወቱ የሚያልፈው ከሰዓታት በኋላ ነው።
በሰዓታት ውስጥም የተሰቀሉ ሰዎች መታፈን፣ የደም መፍሰስ፣ ከፍተኛ የውኃ ጥም እንዲሁም የተለያዩ የሰውነታቸው ክፍሎቻቸው ሥራቸውን ማቆም ያጋጥማቸዋል።
በዚህም ምክንያት ሞት ይከሰታል።
ሮማውያን የሰቀሉትን ወንጀለኛ ሞት የሚያፋጥኑት እግሩን ከጉልበት በታች በመዶሻ ወይም በብረት ዱላ በመምታት እና በመስበር ነው።
ኢየሱስ ከመሰቀሉ በፊት በጅራፍ በተደጋጋሚ ተገርፏል።
ጅራፉ ስል የብረት ቁርጥራች እና የሾሉ አጥንቶች ያሉት ሲሆን፣ በዚህም ብዙ ደም ፈስሶታል።
የታሪክ ድርሳናት እንደሚያሳዩት በመገረፍ ብቻ የሞቱ ሰዎች አሉ፤ ኢየሱስ ግን እስከ ጎለጎታ ድረስ ስቃዩን እየተቀበለ ወጥቷል።
በእርግጥ ኢየሱስ ከደረሰበት ግርፋት የተነሳ ወደ ጎልጎታ መስቀሉን ተሸክሞ መሄድ እስኪያቅተው ድረስ ተዳክሟል።
ኢየሱስ ክርስቶስ በደረሰበት ከፍተኛ ድብደባ ምክንያት በመዳከሙ የተነሳ፣ የሮማ ወታደሮች ስምዖን መስቀሉን ተሸክሞ ክርስቶስ ከሁለት ወንበዴዎች ጋር ወደሚሰቀልበት ከከተማ ወጣ ያለ ስፍራ እንዲያደርስ አስገደዱት።
ክርስቶስ ላይ የተፈጸመው ስቅላት እጅግ ጭካኔ እና ስቃይ የተሞላበት፣እንዲሁም ቀስ በቀስ የሚገድል ነበር።
በተሰቀለበት ወቅት የእጆቹ አንጓዎች፣ እንዲሁም እግሮቹ በሚስማር ተቸንክረዋል።
በአይሁዶች እና ሮማውያን ችሎት ፊት ቆሞ የተፈረደበት ኢየሱስ በጥፊ ተመትቷል፣ተገርፏል፣ ተራቁቷል፣ የእሾህ አክሊል ተደፍቶበታል።
ክርስቶስ በመስቀል ላይ ተቸንክሮ እንዲሰቀል ሲደረግ የአካል ክፍሎቹ መቋቋም ይችላሉ ተብሎ የማይታሰቡ ስቃዮችን አልፈዋል።
ሐሙስ ለአርብ አጥቢያ እጁ ከተያዘበት ሰዓት ጀምሮ እስከ አርብ ቀን 9፡00 ሰዓት ድረስ ከፍተኛ ስቃይ ደርሶበታል።
በዚህ ሁሉ ሰቆቃ፣ ድብደባ፣ መውደቅ እና መነሳት ውስጥ ብዙ ደም ፈስሶታል። ተጠምቷል። ከዚያም ለህልፈት ተዳርጓል።
የሕክምና ባለሙያዎች ኢየሱስ የደረሰበትን እንግልት፣ ድብደባ እና ስቅላት ከሙያቸው አንጻር እንዲህ ተመልክተውታል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
'የደም ላብ እያላበው'
ኢየሱስ ከመሞቱ በፊት በብርቱ ተጨንቆ እንደነበር መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል።
የኢየሱስ ሕይወት እና ሞትን በዝርዝር የጻፉት አራቱ ሐዋርያት ማቴዎስ፣ ማርቆስ፣ ሉቃስ እና ዮሐንስ በወቅቱ የነበረውን በዝርዝር አስፍረዋል።
ሮማውያን የሚገድሏቸውን ሰዎች በምን ያህል ጭካኔ እንደሚያሰቃይዋቸው ኢየሱስ ጠንቅቆ ያውቃል።
"አባትህ ሆይ ብትፈቅድ ይህችን ጽዋ ከእኔ ውሰድ" እያለ ይጸልይ እንደነበር በሉቃስ ወንጌል ላይ ተጽፎ ይገኛል።
በዚሁ ወንጌል ላይ "በፍርሃትም ሲጣጣር አጽንቶ ይጸልይ ነበር። ወዙም በምድር ላይ እንደሚወርድ እንደ ደም ነጠብጣም ነበረ" ይላል።
በኢየሱስ ስቅላት ላይ ጥናት ያደረጉ የሕክምና ባለሙያዎች፣ ምንም እንኳን ይህ በጣም አልፎ አልፎ የሚከሰት ቢሆንም፣የደም ላብ (hematidrosis ወይም hemohidrosis) በከፍተኛ ጭንቀት ውስጥ የሚሆኑ ሰዎች ወይም የደም መፍሰስ ችግር ባለባቸው ሰዎች ላይ ሊከሰት ይችላል ይላሉ።
የሕክምና ባለሙያዎች በዘ ጆርናል ኦቭ ዚ አሜሪካን ሜዲካል አሶሲዬሽን ላይ፣ አንድ ሰው ከፍተኛ የስሜት ውጥረት ሲያጋጥመው ቀጫጭን የሆኑት የደም ሥሮች ሊፈነዱ እና ደም ከላቡ ጋር ሊቀላቀል ይችላል፤ ይህ ደግሞ ግለሰቡ ደም እያላበው ያለ እንዲመስል ያደርጋል ሲሉ ሉቃስ በወንጌሉ የጻፈውን ያጠናክራሉ።
እኩለ ሌሊት እንዳለፈ ኢየሱስ በጌቴሰማኔ በካህናት፣በአለቆች፣ በሽማግሌዎች እና የቤተመቅደስ አዛዦች ቁጥጥር ስር ዋለ።
በካህናት አለቆች ፊት ቀርቦ ሠራ የተባለው ወንጀል ተጠቅሶ ተመሰከረበት። ከዚያ በኋላም የካህናት አለቆች ለጲላጦስ አሳልፈው ሰጡት።
ኢየሱስ በጌቴሰማኔ በመልካም ጤንነት ላይ የነበረ ቢሆንም፣ ሐሙስ ከምሽቱ 3 ሰዓት ጀምሮ እስከ አርብ ቀን 9 ሰዓት ድረስ በበርካታ ስቃይ ውስጥ ማሳለፉን በኢየሱስ ስቅለት ዙርያ የተለያዩ ጥናቶችን ያደረጉ ምሁራን ያስረዳሉ።
የቅርቤ በሚላቸው ሰዎች መከዳት፣አካላዊ ድብደባ እንዲሁም አስጨናቂ እና እንቅልፍ አልባ ሌሊቶች ማሳለፍ ከተመዘገቡት መካከል ናቸው።
ኢየሱስ ከአይሁድ ወደ ጲላጦስ ችሎት ሲመላለስ ቢያንስ 4 ኪሎ ሜትር ያህል እንደተጓዘ 'ኦን ዘ ፊዚካል ዴዝ ኦፍ ጂሰስ ክራይስት' በሚል ርዕስ የቀረበው ጥናት ላይ ሰፍሯል።
በመጨረሻም ኢየሱስ በጲላጦስ ፊትም ቀርቦ በስቅላት እንዲሞት ተፈረደበት።
ኢየሱስ ከመሰቀሉ በፊት በሮማ ወታደሮች የብረት ቁርጥራጮች እና የሾሉ አጥንቶች ባሉት ጅራፍ በተደጋጋሚ ተገርፏል።
የሕክምና ባለሙያዎች ኢየሱስ በሮማ ወታደሮች ጀርባውን ሲገረፍ፣ በጅራፉ ላይ የታሰሩት ሹል ብረቶች እና አጥንቶች ሥጋውን ቦጭቀው ያነሱ እንዲሁም የደም ስሩን ይቀረድዱት እንደበር ጽፈዋል።
ኢየሱስ በጾም የደከመው ሰውነቱ፣ በግርፋት እና ድብደባ የዛለው አካሉ፣ ከከፍተኛ ደም መፍሰስ ጋር ተዳምሮ ከመሰቀሉ በፊት በብርቱ ለመሰቃየቱ ተጠቃሽ መሆኑን በዚህ ዙሪያ ጥናት ያደረጉት እነዚህ ባለሙያዎች ይናገራሉ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የኢየሱስ ስቅላት
ስቅላት የተጀመረው በፋርሶች እንደሆነ ይገመታል።ታላቁ እስክንድር ይህንን የቅጣት ዓይነት ለግብፅ እና ጥንታዊ የሜዴትራኒያን ሕዝቦች አስተዋውቋል።
ሮማውያን ደግሞ ከጥንታዊ የሜዴትራኒያን አስተዳዳሪዎች ተማሩ።
ምንም እንኳን ሮማውያን ስቅላትን ባይፈጥሩትም የሞት ቅጣት በከፍተኛ ስቃይ ዘገምተኛ ሞትን እንዲያስከትል አድርገውታል።
የኢየሱስ እጆች እና እግሮች የተቸነከሩባቸው ሚስማሮች ርዝመታቸው ከ13 እስከ 18 ሴንቲ ሜትር እንዲሁም ውፍረታቸው 1 ሴንቲ ሜትር ሊደርስ ይችላል ይላሉ ዶ/ር ዊሊያም ዲ ኤድዋርድስ።
ኢየሱስ ሲሰቀል እግሮቹም ተጠፍረው ታስረው በመደራረብ ከእግሮቹ ከፍ ብሎ በሚገኘው አጥንት ላይ ሚስማሩ እንዲቸነከር ተደርጓል።
ጉልበቱም ትንሽ አጠፍ ብሎ ነበር። ይህ በዘመኑ በስቅላት የሚቀጡ ወንጀለኞች ሁሉ የሚሰቀሉበት መንገድ ነው።
ዶ/ር ቪንስ ሚለር የኢየሱስ እግሮች በመስቀል ላይ ሲቸነከሩ 45 ዲግሪ እንዲታጠፉ ሆኖ ነው ይላሉ።
በመስቀሉ ላይ የተሰቀለው ኢየሱስ አብዛኛው የሰውነቱን ክብደት ያረፈው በሚስማር በተቸነከሩት እግሮቹ ላይ ነበር።
እግሮቹ የታጠፉበት መንገድ፣ ጡንቻዎቹ ህመም ሳይሰማቸው ከጥቂት ደቂቃዎች በላይ ሊቆዩ የሚችሉበት የሰውነት አቀማመጥ አይደለም።
ከጉልበቱ በታች የሚገኙት የታፋው ጡንቻዎች ሲዝሉ ክብደቱ ወደ ትከሻዎቹ፣ እጆቹ እና መዳፎቹ መጋጠሚያዎች ላይ ይዞራል።
ኢየሱስ መስቀል ላይ በተሰቀለ በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ ትከሻዎቹ፣ ክርኑ እና የመዳፉ መገጣጠሚያ አንጓዎች ውልቃት እንዳጋጠማቸው ባለሙያዎች ይናገራሉ።
ለ15 ዓመታት ያህል የኢየሱስን የከፈን ጨርቅ (የቱሪን ከፈን) ያጠናው ስፔናዊ አርቲስት፣ ክርስቶስ በደረሰበት እንግልት እና ስቃይ በእጁ ላይ በደረሰበት ውልቃት የተነሳ ከመደበኛው በዘጠኝ ኢንች ረዝሞ እንደሚታይ ገልጿል።
ኢየሱስ ሆሊውድ በሠራው የስቅለት ፊልም ላይ እንደሚታየው በመስቀል ላይ ከእንቅስቃሴ ተገድቦ የቆየ አልነበረም።
በመስቀል ላይ ሳለ ለመተንፈስ በሚታገልበት ወቅት12 ኢንች ያህል ወደ ላይ እና ወደታች ይንቀሳቀስ እንደነበር ጥናቶች ያሳያሉ።
ለመተንፈስ የሚያደርገው ትግል ከፍተኛ ህመም እንደሚያስከትልበት እና ለመተንፈስም ይቸገር እንደነበር ባለሙያዎች ይናገራሉ።
ለዚህም ምክንያቱ እግሮቹ በ45 ዲግሪ እንዲታጠፉ ሆነው በመቸንከራቸው ነው።
በዚህም የተነሳ በከፍተኛ የጡንቻ መዛል እና ህመም ውስጥ በመሆኑ የአካል ብልቶቹ፣ የእግሩ ጡንቻዎቹ በቀላሉ ሊታዘዙት አይችሉም።
ኢየሱስ በመስቀል ላይ ሆኖ ለመተንፈስ፣ በሚስማር የተቸነከሩት እግሮቹን ወደ ታች በመግፋት ቀሪው የሰውነቱን ክፍሎችን ወደ ላይ ማንሳት ይኖርበታል።
በሕክምና ባለሙያዎች ዓይን ሳንባዎቹ በመስቀል ላይ እያለ አየር ወደ ውስጥ ለማስገባት እና ለማስወጣት ያዳግታቸዋል።
ኢየሱስ በመስቀል ላይ ሆኖ እግሮቹን በቀላሉ ወደ ታች መግፋት አይችልም።
ክርኑ፣ ትከሻዎቹ እና የመዳፉ አንጓዎች ላይ ውልቃት በማጋጠሙ እና ከደረቱ ዘንበል ሲል የሚፈጥረው ጫና ለመተንፈስ እጅግ በጣም አስቸጋሪ ያደርግበታል።
በዚህም የተነሳ በመስቀል ላይ በተሰቀለ በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ ለመተንፈስ (dyspnoeic) ይቸገራል።
ለመተንፈስ በሚታገልበት ወቅት በእግሮቹ፣ እንዲሁም ውልቃት በገጠማቸው የላይኛው የአካል ክፍሎቹ ላይ ከፍተኛ ህመም ይሰማዋል።
ምንም እንኳ በመስቀል ላይ በቆየባቸው ጊዜያት ያለው አንእቅስቃሴ እየቀነሰ ቢመጣም ለመተንፈስ በመቸገር እና አየር በማጣት በሚመጣው መታፈን የተነሳ በተደጋጋሚ ለመተንፈስ አካሉን ወደ ላይ ለማንሳት መታገል ይጠበቅበታል።
ኢየሱስ በሚስማር ሲቸነከር በሁለቱ መዳፎቹ የሚገኙት ነርቮች (ሚዲያን ነርቭ) ስለሚጎዱ በእያንዳንዱ እንቅስቃሴ ከባድ ህመምን ያጋጥመዋል።
ሜዲያን ነርቭ ከመዳፋችን እስከ ክርናችን ባለው ስፍራ የተዘረጋ የነርቭ ሥርዓት ነው።

የፎቶው ባለመብት, Dominio público
ጲላጦስ በሕዝቡ ጥያቄ መሠረት በርባንን ፈትቶ ኢየሱስን አሳልፎ ከሰጠ በኋላ፣ ክርስቶስ በደረሰበት መከራ እና ስቃይ የተነሳ በደም እና በላብ ተነክሮ ነበር።
ላቡ ሰውነቱ በደረሰበት እንግልት እና መከራ እንዲሁም ግርፋት በመዳከሙ ብቻ ሳይሆን አየር ለማስወጣት በሚያደርገው ትግል የተከሰተ ሊሆን እንደሚችል የሕክምና ባለሙያዎች ያብራራሉ።
ኢየሱስ በጎለጎታ ላይ ራቁቱን የነበረ ሲሆን፣ የአይሁድ መሪዎች፣ ሕዝቡ እንዲሁም በግራ እና በቀኝ የተሰቀሉት ወንበዴዎች ሲያላግጡበት፣ ሲዘልፉት እንዲሁም ሲስቁበት ነበር።
የኢየሱስ ሰውነት የደረሰበት ድብደባ፣ እንግልት እና ስቃይ የተነሳ ከባድ በሆኑ ህመሞች፣ ለሞት በሚዳርጉ ደም መፍሰሶች ውስጥ አልፏል።
ኢየሱስ በተገቢው ሁኔታ መተንፈስ ባለመቻሉ የተነሳ በዝግታ እና በማቃሰት ለመተንፈስ ተገድዶ ነበር፤ በአየር ማጣትም ተሰቃይቷል።
አንድ ሰው ለመተንፈስ ሲቸገር (hypoventilation) እና ከላይ ከላይ ሲተነፍስ ሰውነቱ የሚያስፈልገውን አየር በተገቢው ሁኔታ የማያገኝ ሲሆን፣ በሰውነቱ ውስጥ የሚከማቸው የተቃጠለ አየር መጠን (hypercapina) ይጨምራል።
በዚህም የተነሳ በደሙ ውስጥ ጥቂት ኦክስጅን ብቻ እንዲኖር (Hypoxia) እና አሲድ እንዲከማች ምክንያት ይሆናል።
በዚህ ጊዜም ራስን መሳት ይከሰታል።
በሰውነት ውስጥ የተቃጠለ አየር መጠን ሲጨምር የኦክስጅን መጠኑን ለመጨመር እና የተቃጠለውን አየር ለማስወጣት የልብ ምት ይጨምራል።
በዚህ ወቅት በኢየሱስ ጭንቅላት ውስጥ የሚገኘው የአተነፋፈስ ሥርዓት ማዕከል ወደ ሳንባው ቶሎ ቶሎ እንዲተነፍስ መልዕክት ስለሚልክ ማለክለክ ይጀምራል።
በዚህ ወቅት የኢየሱስ አካል በጥልቀት ወደ ውስጥ አየር መሳብ እና ማስወጣትን ስለሚጠይቀው ምንም እንኳ በከባድ ህመም ውስጥ ቢሆንም በመስቀል ላይ ወደ ላይ እና ወደታች በፍጥነት መንቀሳቀስ ይጀምራል።
ይህም የኢየሱስ ስቃይ የተሞላበት እንቅስቃሴ በስፍራው ተሰብስበው ለሚዘባበቱበት፣ ለሚሳለቁበት እና ለሚሰድቡት የሮማን ወታደሮች፣ የአይሁድ የእምነት አባቶች ደስታን ይፈጥራል።
ነገር ግን ኢየሱስ በመስቀል ላይ ተቸንክሮ በስቃይ ውስጥ ስላለ ሰውነቱ በእጅጉ የሚያስፈልገውን አየር ለማግኘት አዳጋች ያደርግበታል።
ኢየሱስ በዚያች ሰዓት በመስቀል ላይ ተቸንክሮ ሳለ በሰውነቱ ውስጥ ያለው የኦክስጅን መጠን ጥቂት በመሆኑ እንዲሁም የተቃጠለ አየር በመከማቸቱ የልብ ምቱ እንዲፈጥን ያደርጋል።
ይህም ልቡ ከተለመደው የሰው ልጅ የልብ ምት በተለየ እንዲመታ ስለሚገደድ ታቺካርዲያ (Tachycardia) እንዲያዳብር ያደርገዋል።
ዶ/ር ቪንስ ሚለር ኢየሱስ ያለፈበትን ስቃይ ከግምት ውስጥ በማስገባት የልብ ምቱ ምናልባት በደቂቃ 220 ሳይሆን አይቀርም ይላሉ።
ይህም የአንድ ሰው ልብ ሊመታ ከሚችለው በላይ እጅግ ከፍተኛው ነው።

የፎቶው ባለመብት, Dominio público
ኢየሱስ ተጠማ
ኢየሱስ ከሐሙስ ምሽት 6፡00 ጀምሮ ሲሰላ ለ15 ሰዓታት ያህል ምንም ዓይነት ፈሳሽ አልወሰደም።
ኢየሱስ በውሃ ጥም ተቃጥሎ፣ ጉሮሮው ደርቆ ነበር።
በደረሰበት ግርፋት የተነሳ ደም ይፈስሰው ነበር። የእሾህ አክሊል ሲደፋበት፣ እግሮቹ እና እጆቹ በሚስማር ሲቸነከሩ፣ መስቀል ተሸክሞ ሲወድቅ ሲነሳ በሚኖር መጋጋጥ የተነሳ በርካታ ደም ይፈስሰዋል።
በከፍተኛ ውሃ ጥም ውስጥ የሆነው ኢየሱስ፣ የደም ግፊቱም በከፍተኛ መጠን መውረዱ አይቀርም።
እንደ ሕክምና ባለሙያዎች ግምት ከሆነ የደም ግፊቱ 80 በ50 ይሆናል።
ስለዚህ በወቅቱ ኢየሱስ የነበረበትን ሁኔታ ሲገለጽ በመጀመሪያ ደረጃ ሾክ (First Degree Shock) ውስጥ ነበር።
ከፍተኛ የሆነ የደም መጠን መቀነስ፣ የልብ ምት መጨመር፣ ከላይ ከላይ ወዲያው ወዲያው መተንፈስ እንዲሁም በከፍተኛ ሁኔታ ማላብ ሊያሳያቸው የሚችላቸው ምልክቶች መሆናቸውን ባለሙያዎች ያስቀምጣሉ።
በቀኑ አጋማሽ ላይ የኢየሱስ የልብ ምት እየደከመ ሊመጣ ይችላል።
ሳንባው ደግሞ በከፍተኛ ፈሳሽ ስለሚሞላ መተንፈስ ይቸገራል።
ይህም በደረሰበት ስቃይ ምክንያት አጋጥሞት ያለውን የመተንፈስ ችግር ያባብሰዋል።
ኢየሱስ በልብ ምት እና በአተነፋፈስ ችግር፣ በከፍተኛ የውሃ ጥም (ዩሐንስ 19፡28) ላይ ነበር።
እንደ ሕክምና ባለሙያዎች ገለጻ ኢየሱስ ሕይወቱን ለማቆየት ደም እና ፕላዝማ ያስፍለገው ነበር።
ኢየሱስ በአግባቡ መተንፈስ ባለመቻሉ በአየር እጥረት ቀስ በቀስ ወደ ሞት እያዘገመ ነበር።
በዚህ ወቅት ኢየሱስ ምናልባት በተለያዩ የሰውነት ክፍሎቹ ውስጥ እንዲሁም በልቡ አካባቢ ደም እና ፕላዝማ ተከማችቶ ሊሆን ይችላል።
ይህ በልቡ አካባቢ ያለ ፈሳሽ ልቡ በተገቢው ሁኔታ እንዳይመታ በመከልከል የልብ ችግር እንዲያዳብር ያደርገዋል።
የኢየሱስ ልብ ደም ለመርጨት እና ለመቀበል የሚያደርገው ትግል እየጨመረ ሲመጣ እንዲሁም ደም እና ፕላዝማ በልቡ አካባቢ ሲከማች ልቡ ሊፈነዳ ይችላል።
ይህም ምናልባት የሞቱ ምክንያት ሊሆን ይችላል ይላሉ ባለሙያዎቹ።
የሮማ ወታደሮች በስቅላት የሚቀጡ ሰዎችን ሞት ለማፋጠን ጉልበታቸውን በመምታት እግራቸውን ይሰብራሉ።
በዚህም የተሰቀሉት ሰዎች የእግራቸውን ጡንቻ ተጠቅመው መተንፈስ ስለማይችሉ ሞታቸው ይፋጠናል።
አርብ ዘጠኝ ሰዓት ላይ ኢየሱስ "ተፈጸመ" (ዩሐ 19፡30) ብሎ ሞተ።
ወታደሮቹ እግሩን ለመስበር ሲመጡ ኢየሱስ ሞቷል። መጽሐፍ ቅዱስ ላይ በተቀመጠው ትንቢት መሠረትም (መዝ ዳዊት 34 ፡20፤ ዩሐ 19፡33፤ ዩሐ 19፤ 36) አንድም አጥንቱ አልተሰበረም።
ኢየሱስ የሰው ልጅ በመስቀል ላይ ከፈጠረው ሰቅጣጭ እና አስፈሪ ማሰቃየት በኋላ ሞተ።
የሮማ ወታደርም መሞቱን ለማረጋገጥ "ጎኑን በጦር ወጋው፤ ወዲያውም ደም እና ውኃ ወጣ" ዮሐ 19፡24-25።
የታሪክ ማስረጃዎች እንዲሁም የዘመናዊ ሕክምና ትንታኔዎች ኢየሱስ ከመስቀል ሲወርድ ሞቶ እንደነበር ያስረዳሉ።












