በምሥራቅ እስያ በርካቶች ሃይማኖታቸውን መተው ወይም መቀየርን ለምን መረጡ?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
“ጆን” ያደገው በደቡብ ኮሪያዊያን ክርስቲያን ቤተሰቦቹ መካከል ነው። እንደ አብዛኞቹ የአገሬው ሰዎች አሁን ሃይማኖቱን ቀይሯል።
አሁን በይፋ አግኖስቲክስ መሆኑን አውጇል። አግኖስቲክሶች ፈጣሪ ወይንም ሌላ ማንኛውም ኃይል መኖሩ አይታወቅም የሚሉ ናቸው።
“ምን እንዳለ አላውቅም። ፈጣሪ ሊኖር ይችላል፤ ወይም በትክክል እግዚአብሔር ላይሆንም ይችላል” ሲል ከሴዑል ሆኖ ምላሽ ሰጥቷል።
የጆን ወላጆች አሁንም ክርስቲያኖች ናቸው። እሱ አማኝ አለመሆኑን ካወቁ “ከባድ ሐዘን” እንደሚሰማቸው ተናግሯል። ሊያበሳጫቸው ደግሞ አይፈልግም። ለዚህም ነው ስሙን እንድንቀይር የጠየቀን።
የጆን ሕይወት ጉዞ ፒው ሪሰርች ከተባለው የአሜሪካ ተቋም አዲስ ጥናት ግኝቶች ጋር ተመሳሳይ ነው። በጥናቱ መሠረት በምሥራቅ እስያ በሚገኙ አገራት ያሉ ዜጎች በዓለም ላይ ሃይማኖታቸውን በመተው እና በመቀየር ከፍተኛ ቁጥር ያለባቸው መሆናቸውን ያሳያል።
ከ10 ሺህ በላይ ሰዎች ስለሃይማኖታቸው ተጠይቀው፣ ብዙዎቹ አሁን ያላቸው ሃይማኖት ካደጉበት የተለየ መሆኑን ተናግረዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሆንግ ኮንግ እና ደቡብ ኮሪያ በዝርዝሩ በቀዳሚነት ይመራሉ። 53 በመቶ የሚሆኑ የሁለቱ አገራት ምላሽ ሰጪዎች ሃይማኖታቸውን መቀየራቸውን አስታውቀዋል።
ከእነዚህ ውስጥ አንዳንዶቹ ሃይማኖታቸውን ሙሉ በሙሉ እርግፍ አድርገው ትተውታል። በታይዋን 42 በመቶ ሰዎች ሃይማኖታቸውን ቀይረዋል። በጃፓን ደግሞ ቁጥሩ 32 በመቶ ናቸው።
በአውሮፓ በ2017 ከተካሄደው የዳሰሳ ጥናት ጋር ይህንን ቁጥር ማነጻጸር ጠቃሚ ነው። በወቅቱ በአውሮፓ ሃይማኖት የመቀየር መጠኗ ከ40 በመቶ በላይ ያስመዘገበች አገር አልተመዘገበችም። ባለፈው ዓመት በአሜሪካ የተሰበሰበው መረጃ 28 በመቶ ያህሉ አዋቂዎች ያደጉበትን ሃይማኖት ቀይረዋል።
የጆን የአመለካከት ለውጥ ከቤት ሲወጣ እና ለአዳዲስ ሃሳቦች ከመጋለጡ ጋር ተገጣጥሟል። ቤተሰቦቹ ቤት ሲኖር በየቀኑ ጠዋት 12 ሰዓት ሁሉም ተነስተው መጽሐፍ ቅዱስ አንብበው ሃሳብ ይቀያየራሉ።
እያንዳንዱ ጠዋት “እንደ ትንሽ የአምልኮ ሥነ ሥርዓት ነበር” ይላል።
በ19 ዓመቱ ከቤት ወጣ። በሴዑል ከሚገኙት ትላልቅ አብያተ ክርስቲያናት ወደ አንዱ መሄድም ጀመረ። ቤተ ክርስቲያኑ በሺህዎች የሚቆጠሩ አባላት አሉት። የመጽሐፍ ቅዱስ አተረጓጎሙ ቀጥተኛ ነበር።
ለምሳሌ የዝግመተ ለውጥን ጽንሰ ሐሳብ ውድቅ ያደርጋል። ይህ ደግሞ ጆን ከተማረው የሳይንስ ንድፈ ሐሳብ ጋር አብሮ የሚሄድ አልነበረም። የዓለም ዕይታው በሌሎች መንገዶችም ተለውጧል።
“እኔ እንደማስበው ክርስትና ጥቁር እና ነጭ፤ ትክክል ወይም ስህተት የሚል ቀጥተኛ ሆነ አካሄድ አለው። ነገር ግን ሕብረተሰቡን ከታዘብኩ እና ከተለያዩ ሰዎች ጋር ከተገናኘሁ በኋላ ዓለም ብዙ አስተሳሰቦችን ያቀፈች እንደሆነች ማሰብ ጀመርኩ” ብሏል።
ጆን ካሉት ጓደኞቹ ግማሽ ያህሉ ያደጉበትን ሃይማኖት አይከተሉም። አብዛኞቹ ደግሞ ክርስትያኖች ነበሩ።
ከጓደኞቹ መካከል እምነታቸውን ቀየሩት ክርስትያኖቹ ብቻ አይደሉም። ቡዲሂስት ከነበሩት መካከል 20 በመቶዎቹ አሁን እምነታቸውን ትተዋል። በሆንግ ኮንግ እና ጃፓን ይህ ቁጥር 17 በመቶ ደርሷል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በአካባቢው አዲስ እምነት ለመከተል የሚመርጡ ሰዎችም አሉ። ለምሳሌ በደቡብ ኮሪያ የክርስትና እምነት ተከታዮች ቁጥር 12 በመቶ አድጓል። ቡድሂዝም ደግሞ 5 በመቶ ተከታዮችን አግኝቷል። በሆንግ ኮንግ ብቻ ክርስትና (9 በመቶ) እና ቡዲሂዝም (4 በመቶ) ተከታይ አግኝተዋል።
ሃይማኖታቸውን ከሚቀይሩት መካከል አብዛኞቹ አሁን ላይ ከየትኛውም ሃይማኖት ጋር ቁርኝት እንዳይኖራቸው የሚፍልጉ ናቸው። ይህ ቁጥር ከተቀረው ዓለም ይልቅ በምሥራቅ እስያ ከፍተኛ ነው።
በሆንግ ኮንግ 37 በመቶ እና በደቡብ ኮሪያ 35 በመቶ ሰዎች ተመሳሳይ አስተሳሰብ ሲኖራቸው፤ ይህ ቁጥር በኖርዌይ 30 በመቶ ይደርሳል፤ በአሜሪካ ደግሞ 20 በመቶ ነው።
ከሃይማኖት ተቋማት የመራቅ ነገር እየጨመረ የሚሄድ ቢመስልም በአገራቱ የሚገኙ በርካታ ሰዎች አሁንም በመንፈሳዊ ሥርዓቶች እንደሚሳተፉ ይናገራሉ።
ከየትኛውም ሃይማኖት ጋር ቁርኝት እንደሌላቸው የሚናገሩ እና በሁሉም አገራት በጥናቱ ከተሳተፉ ሰዎች ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ባለፉት 12 ወራት ውስጥ ቅድመ አያቶቻቸውን ለመዘከር በሚል በአምልኮ ሥርዓቶች ውስጥ መካፈላቸውን ተናግረዋል። አብዛኞቹም በአማልክት ወይም በማይታዩ ፍጥረታት እንደሚያምኑ ይናገራሉ።
የሃይማኖት ጥናት አዋቂ ለሆኑት ዶ/ር ሴ-ዎንግ ኩ ይህ አስደናቂ ግኝት አይደለም። በተለያዩ የሃይማኖቶች ሥነ ሥርዓቶች ላይ መሳተፍ ከሃይማኖቶቹ ታሪክ ጋር የሚስማማ ነው ብለዋል።
“ከታሪክ አንጻር፣ በምሥራቅ እስያ ልዩ የሆነ ሃይማኖታዊ መለያ በምትሉት ነገር ላይ ያተኮረ አልነበረም። ታኦኢስት ከሆንክ፣ በተመሳሳይ ጊዜ ደግሞ ቡዲስት ወይም የኮንፊሽያን መሆን አትችልም ማለት አይደለም። እነዚህ ድንበሮች ከምዕራቡ ዓለም ጋር ሲነጻጸሩ በግልጽ የተቀመጡ አልነበሩም” ብለዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ከምዕራባውያን ጋር ያለው ግንኙነት እና መስተጋብር መጨመሩን ተከትሎ በ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ነው አሁን የምናውቀው የሃይማኖት ጽንሰ ሃሳብ ወደ ምሥራቅ እስያ የገባው።
ብዙ ማንነቶችን እና ባህሎችን መያዝ መቻል በአካባቢው ፈጽሞ ያልጠፋ ነገር ነበር ይላሉ ዶ/ር ኩ።
ጉዳዩ በአገራቸውም ተመሳሳይ መሆኑን አይተዋል። ዶ/ር ኩ እንደሚሉት ከሆነ እናታቸው በተለያዩ አጋጣሚዎች ሃይማኖታቸውን ቀይረዋል።
“ባለፈው እሑድ በአካባቢያችን ባለው የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን አባል ሆና ተመዝግባለች። በቃ ወደዚያ ብቻ እንደምትሄድ እርግጠኛ ነበርኩ” ብለዋል።
ሆኖም በአካባቢያቸው ወደሚገኝ ኢቫንጀሊካል ቤተ ክርስቲያን “ለፈውስ በሚል የጸሎት ክፍለ ጊዜ እንደምትካፈል” ነገረችው።
ዶ/ር ኩም “እማዬ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ምን ሆነች?” ሲሉ ጠየቁ። በዚያን ወቅት የሚፈልጉት “ከምንም ነገር በበለጠ ፈውስ” መሆኑን ተናገሩ።
እናታቸው “ካቶሊክ ስለነበረች ወደ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን መሄድ ትፈልግ ነበር” በሆነ መንገድ ደግሞ እሳቸው ለሚፈልጉት ጣልቃ ገብነትን ለማግኘት ወደ ሌላ ሃይማኖት ሄደዋል ይላሉ።












