በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል በሦስት የማዕድን ስፍራዎች ላይ በተፈጸሙ ጥቃቶች ሰባት ሰዎች ተገደሉ

በወርቅ ቁፋሮ ላይ ያለ ስካቫተረ ተሽከርካሪ እና የማጠቢያ ማሽን

የፎቶው ባለመብት, Bero Woreda Communication

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ውስጥ በሚገኘው ቤሮ ወረዳ በትናንትናው ዕለት ታጣቂዎች በሦስት የወርቅ እና የእምነበረድ ማውጫ ስፍራዎች ላይ በፈጸሙ ጥቃቶች ሰባት ሰዎች መገደላቸውን የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ እና የፖሊስ አዛዥ ለቢቢሲ ተናገሩ። በዛሬው ዕለትም "በሌላ የማዕድን ስፍራ ላይ" የተኩስ ልውውጥ መደረጉን ተገልጿል።

በምዕራብ ኦሞ ዞን ስር በሚገኘው ቤሮ ወረዳ ሐሙስ ታኅሣሥ 17/2018 ዓ.ም. በሦስት ስፍራዎች ላይ ጥቃት የደረሰው "ከረፋድ አምስት ሰዓት እስከ ሰባት ሰዓት ተኩል" ባለው ጊዜ ውስጥ መሆኑን የወረዳው ፖሊስ አዛዥ ዋና ሳጅን ደመላሽ አኩ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ አቶ ገመዳ ካይዳድ በበኩላቸው እንደተናገሩት የመጀሪያው ጥቃት የተፈጸመው "ቤሮ ማይኒንግ" በተባለ በወርቅ ማዕድን ፍለጋ ላይ በተሰማራ የማዕድን አውጪ ኩባንያ ላይ ነው። ኩባንያው በአካባቢው ወርቅ ለመፈለግ "ከፌደራል መንግሥት የሦስት ዓመት ፈቃድ ወስዶ የተሰማራው ከአንድ ዓመት በፊት" እንደሆነ ጠቅሰዋል።

"ቤሮ ማይኒንግ ጥበቃ ላይ ያሉ መከላከያዎች ወደ ከተማ ሲሄዱ እነሱ ላይ ተኮሱ። [...] እነሱ ጋር እንደተተኳኮሱ ወዲያውኑ አንድ ሳይት ላይ ገብተው [ጥቃት ከፈቱ]" ሲሉ በጋቢሳ ቀበሌ የተፈጠረውን የመጀመሪያውን ክስተት ገልጸዋል።

በወርቅ ማውጫ ስፍራ ላይ በተፈጸመው የመጀመሪያው ጥቃት የአንድ ሰው ሕይወት እንዳለፈ ሁለቱ ባለሥልጣናት ገልጸዋል። በጥቃቱ የተገደለው ግለሰብ በማዕድን ማውጫው ስፍራ ላይ የሚሠራ "የአይሱዚ መኪና ረዳት" እንደሆነ ዋና አስተዳዳሪው አንስተዋል።

የፖሊስ አዛዡ ዋና ሳጅን ደመላሽ በበኩላቸው ከሞት በተጨማሪ አንድ ሌላ ሰው ላይ ጉዳት መድረሱን አክለዋል።

ዋና አስተዳዳሪ አቶ ገመዳ እንደሚናገሩት በዚህ ስፍራ የነበሩ ሌሎች ሰዎችም ጥቃት ተከፍቶባቸው ነበር። "የሳይቱን ሰው ከበቡ፤ ከዚያ ሚሊሻ አስተባብረን ከዚያ ሳይት አስለቀቅን። ትንሽ ስንቆይ እዚያው ማዕድን ማውጫው ስፍራ ላይ ከመከላከያ ጋር ለረጅም ሰዓት ተዋጉ" ሲሉ ቀጥሎ የተፈጠረውን ክስተት አብራርተዋል።

በጥበቃ ላይ ከነበሩት የመከላከያ ሠራዊት አባላት ጋር በተደረገው "የተኩስ ልውውጥ ምንም ጉዳት" እንዳልደረሰ ገልጸዋል። ይሁን እንጂ ጥቃቱ የእምነበረድ ማዕድን ማውጫ ስፍራው ላይ ቀጥሏል።

ሁለተኛው ጥቃት የተከፈተው የእምነበረድ ማዕድን ማውጫ ስፍራውን ሲጠብቁ በነበሩ ሰዎች ላይ እንደሆነ ዋና አስተዳዳሪው ተናግረዋል። በስፍራው ላይ ተሰማርተው የነበሩት ስድስት የጥበቃ ሠራተኞች እንደሆኑ የሚገልጹት አቶ ገመዳ፤ ጥቃቱ በደረሰበት ሰዓት ግን ሦስቱ በሥራ ላይ እንዳልነበሩ ጠቅሰዋል።

"[ታጣቂዎቹ] ሦስቱ ጥበቃ ላይ ያሉትን መቱ። ሁለቱን ገድለው መሳሪያቸውን ይዘው ሄደዋል። አንዱ እና ምግብ የሚሠሩ ሴቶች ተርፈዋል" ብለዋል። የወረዳው ፖሊስ አዛዥም በተመሳሳይ በዚህ ጥቃት ሁለት ሰዎች መገደላቸውን ተናግረዋል።

ሦስተኛው ጥቃት የተፈጸመው ከእምነበረው ማውጫው ስፍራ "በሦስት ኪሎ ሜትር" ርቀት ላይ በሚገኝ "ሻምበል ሰጠኝ" በተባለ የወርቅ ማውጫ ላይ ነው። በክልል ደረጃ የሚሰጥ "ልዩ አነስተኛ" የወርቅ ማዕድን ቁፋሮ ፈቃድ ወስዶ እየሠራ ያለ ማኅበር የሚንቀሳቀስ በዚህ ስፍራ ላይ ሁለት ሴቶች እና አንድ ወንድ መገደላቸውን ሁለቱ ባለሥልጣናት ገልጸዋል።

ከጥቃቱ በተጨማሪ የቁፋሮ ስፍራው ንብረቶችን በእሳት የማቃጠል እና የመዝረፍ ድርጊት መፈጸሙን አስረድተዋል።

ዋና አስተዳዳሪው አቶ ገመዳ፤ "አንድ ኤክስካቫተር፣ አንድ ሎደር በእሳት ተቃጥሏል። ካምፑን ሙሉ በሙሉ አፍርሰዋል። [...] አንድ አዲስ ኤክስካቫተርን ሊያቃጥሉት ሲሞክሩት ስላልቻሉ መስታወቱን ሰባብረው ሄደዋል" ብለዋል። የፖሊስ አዛዡ ዋና ሳጅን ደመላሽም በተመሳሳይ ይህንኑ ገልጸዋል።

በወርቅ ፍለጋ ላይ ያሉ ወጣቶች

የፎቶው ባለመብት, ETV/YOUTUBE SCREENSHOT

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ከእነዚህ ጥቃቶች በተጨማሪ "ሚዛን እና ነዳጅ ጭኖ ወደ ሳይት እየተጓዝ" የነበረ አንድ የጭነት መኪና አሽከርካሪም መገደሉን ዋና አስተዳዳሪው አክለዋል።

ዋና አስተዳዳሪው እና የፖሊስ አዛዡ እንደሚናገሩት በአንድ ቀን ውስጥ በሰዓታት ልዩነት በማዕድን ማውጫ ስፍራዎች ላይ በተፈጸሙት ጥቃቶች በአጠቃላይ ሰባት ሰዎች ተገድለው፤ ሁለት ሰዎች ቆስለዋል።

በዛሬው [አርብ] ዕለትም በሌላ የማዕድን ቁፋሮ ቦታ ላይ የተኩስ ልውውጥ እየተደረገ መሆኑን ባለሥልጣናቱ ተናግረዋል። አቶ ገመዳ፤ "ዛሬ አሁን በዚህ ሰዓት አንድ ሳይት ላይ በከፍተኛ ውጊያ አለ። የክልሉ አድማ በታኝ፣ ሌላ ኃይልም ወደዚያ እየላክን ነው ያለነው" ሲሉ ያለውን ሁኔታ አንስተዋል።

ሁለቱም ባለሥልጣናት ለተፈጸሙት ጥቃቶች ተጠያቂ የሚያደርጉት ከአጎራባቹ ሱሪ ወረዳ ይነሳሉ ያሏቸውን "የሱሪ ታጣቂዎችን" ነው። ጥቃቱ ከመድረሱ በፊት ታጣቂዎቹ "ከብቶቻቸውን ወደ ማዕድን ስፍራዎቹ አስጠግተው" እንደነበር ጠቅሰዋል።

"የሱሪ አርብቶ አደር ነው። ከብት አለ፤ ከከብት ጀርባ የታጠቀ የሱሪ አርብቶ አደር አለ። ሌላ ኃይል የለም" የሚሉት ዋና አስተዳዳሪው፤ ታጣቂዎቹ የሚንቀሳቀሱት "በተደራጀ" መልኩ እንደሆነ በመጥቀስ ይከስሳሉ። "ከ100 እስከ 150 ኃይል ነው የሚዋጋው" ሲሉም የአሁኑ ጥቃት "ከዚህ ቀደም ባልታየ ደረጃ" የተፈጸመ መሆኑን አንስተዋል።

ቢቢሲ በጉዳዩ ላይ ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል፣ ከምዕራብ ኦሞ ዞን እና ከሱሪ ወረዳ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ያደረጋቸው ጥረቶች አልተሳኩም። የምዕራብ ኦሞ ዞን የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ደሳለኝ ጌልታ፤ "በዚህ ዙሪያ የተጣራ መረጃ የለኝም" ብለዋል።

ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ የሺዋስ አለሙ በበኩላቸው ለቢቢሲ የስልክ ጥሪ እና የጽሁፍ መልዕክት ምላሽ አልሰጡም።