ለጉንፋን ያለሐኪም ትዕዛዝ መድኃኒቶችን መውሰድ ለከፋ አደጋ እንደሚያጋልጥ አስበው ያውቃሉ?

የፎቶው ባለመብት, DR. Tinsae
በቀላሉ የሚድኑ ሕመሞች ያጋጠመን በመሰለን ጊዜ መጀመሪያ የምናደርገው ከዚህ ቀደም ያሻሉንን መድኃኒቶች በድጋሚ ገዝቶ መውሰድ ሊሆን ይችላል።
ይህ ደግሞ ለራሳችን ብቻ ሳይሆን በዙሪያችን ላሉ ሰዎችም ያለ ሐኪም ትዕዛዝ 'ፍቱን ናቸው' ብለን ያሰብናቸውን መስጠትን ያካትታል።
ለራሳችን ወይንም ለሌሎች ባንሰጥ እንኳ ለወዳጅ ጓደኛ 'ይህ መድኃኒት ፍቱን ነው' በማለት መክረን እናውቅ ይሆናል።
የሕጻናት ሕክምና ስፔሻሊስት እና የሕጻናት ተላላፊ በሽታዎች ሕክምና ሰብስፔሻሊስት የሆኑት ዶ/ር ትንሳዔ አለማየሁ መድኃኒት የተላመደ በሽታ አምጪ ተህዋሲ (ባክቴሪያ) የዘመናችን አደጋ እየሆነ ነው ይላሉ።
በዚህም የተነሳ በፊት በቀላል መድኃኒቶች ማከም የሚቻሉ ኢንፌክሽኖች አሁን በጣም ጠንከር ያሉ መድኃኒቶችን ካልተጠቀምን ወይንም ደግሞ ራሳቸው የበፊቶቹን መድኃኒቶቹን ረዘም ላለ ጊዜ ካልተጠቀምን አይድኑም።
ፀረ ተህዋሲያንን የሚቋቋሙ ባክቴሪያዎች፣ ቫይረሶች፣ ፈንገሶች እና ጥገኛ ተህዋሲያን በሽታውን ለማከም አስቸጋሪ ያደርጋሉ።
ይህ ደግሞ ታካሚውን ለተራዘመ ሕመም፣ የሕክምና ተቋምን ለተጨማሪ ወጪ እና ለሥራ መደራረብ ያጋልጣል።
ከዚህ ሁሉ የከፋው ደግሞ ታካሚው ለረዥም ጊዜ የሆስፒታል ቆይታ፣ ባስ ሲልም ለሞት ሊያደርስ ይችላል።
የጊዜያችን አሳሳቢ የሆነ ሕመም
የጤና ወግ የተሰኘው የሕክምና ባለሙያዎች ቡድን ከዚህ ጋር ተያይዞ ባሠራጨው ጽሑፍ ላይ ፀረ ተህዋሲያንን በሰዎች፣ በእንስሳት እና በእጽዋት ላይ ያለ አግባብ እና ከልክ በላይ መጠቀም መድኃኒት የሚቋቋሙ በሽታ አምጪ ተህዋሲያን እንዲፈጠሩ እንደሚያደረግ ይገልጻል።
መድኃኒት የተላመደ ባክቴሪያ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በዓለም ላይ ወደ ቁጥር አንድ ገዳይነት እየሄደ መሆኑን ዶ/ር ትንሳዔ አለማየሁ ይናገራሉ።
እንደ አውሮፓውያኑ በ2019 ለ1.27 ሚሊዮን የዓለም ሞት መድኃኒቱን የተላመደ ባክቴሪያ ቀጥተኛ ምክንያት እንደነበረ እና ለ4.95 ሚሊዮን ሞት አስተዋጽኦ ማድረጉን የጤና ወግ ጽሑፍ ያስረዳል።
ዶ/ር ትንሳዔ ደግሞ በአሁኑ ሰዓት በዓለም ላይ መድኃኒቱን የተላመደ ባክቴሪያ ወይንም በሽታ አምጪ ተህዋሲ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሰዎችን ይገድላል ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ይህ ቁጥር በአውሮፓውያኑ 2050 ወደ 10 ሚሊዮን ከፍ ይላል።
ይህም ማለት አሁን ባለው አካሄድ ከቀጠለ ከ25 ዓመት በኋላ ከማንናውም ሕመም በላይ ዓለም ላይ የብዙ ሰዎችን ሕይወት የሚቀጥፍ ችግር ይሆናል ማለት ነው። ይህም ቁጥር አንድ ገዳይ ሕመም ያደርገዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
መድኃኒት የሚቋቋም ባክቴሪያ ለምን በፍጥነት እየተስፋፋ መጣ?
በአንድ ወቅት በፀረ ተህዋሲያን በቀላሉ ሊታከሙ የሚችሉ በርካታ በሽታዎች በአሁኑ ጊዜ በተለይ በማደግ ላይ ባሉ አገራት ውስጥ ይበልጥ መድኃኒቶችን የሚገዳደሩ እየሆኑ መጥተዋል።
ለዚህ ደግሞ ጥሩው ማሳያ የሳንባ ነቀርሳ (ቲቢ) መሆኑን ዶ/ር ትንሳዔ ያስረዳሉ።
ከፍተኛ መድኃኒት የመቋቋም አቅም በማዳበር ብዙ መድኃኒቶችን የሚቋቋም የሳንባ ነቀርሳ (MDR-TB) ተስፋፍቷል።
ይህ ብቻም ሳይሆን ወባ፣ የሳምባ ምች፣ የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን እና በግብረ ሥጋ ግንኙነት የሚተላለፉ በሽታዎች እንዲሁ በብዛት ጥቅም ላይ የሚውሉ ፀረ ተህዋሲያንን የመቋቋም ባህሪ እያሳዩ ነው።
አንድ ሰው ከጉንፋን ጀምሮ ሆስፒታል ተኝቶ መታከም እስከሚያስፈልጋቸው ኢንፌክሽኖች ድረስ ሊያዝ ይችላል።
በዚህ ወቅት የሕክምና ባለሙያ የሚያዘውን ፀረ ተህዋስ መድኃኒት ወይንም አንቲባዮቲኮች በትክክል እና በአግባቡ አለመውሰድ መድኃኒቱን የተላመደ ተህዋሲያን እንዲፈጠር ምክንያት ይሆናል።
ፀረ ተህዋሲያንን አላግባብ መጠቀም ሌላው መድኃኒቱን ለተላመደ ባክቴሪያ የመጋለጫ ምክንያት ነው።
ሰዎች ብዙ ጊዜ ተገቢውን የሕክምና ምክር ሳያገኙ ወይም ተገቢ የሆነ ምርመራ ሳይደረግላቸው ፀረ ተህዋሲ መድኃኒቶችን (አንቲባዮቲኮችን) መውሰድ ይጀምራሉ።
ከዚያም ያለ በቂ ምርመራ እና የሐኪም ማዘዣ ራሳቸውን በራሳቸው ሲያክሙ የተሳሳተ መድኃኒት ወይም አላስፈላጊ አንቲባዮቲክስ ይወስዳሉ።
አንድ የሕክምና ባለሙያ ታካሚው ለታመመበት ኢንፌክሽን እንዲያሽለው በሚል ለሰባት ቀን የሚወሰድ ፀረ ተህዋስያ ሲያዝ ሳይጨርሰው ከተወሰነ ቀን በኋላ መውሰድ ሲያቆም፣ ከተወሰነ ሳምንት በኋላ ቀላል የነበረው ባክቴሪያ ተጠናክሮ ይመጣ እና የከፋ ኢንፌክሽን ይፈጠራል።
ይህ የሆነበት ምክንያት ደግሞ መጀመሪያ ላይ መድኃኒቱን ሲያቋርጥ ባክቴሪያው ሞቶ የነበረው በግማሽ ብቻ በመሆኑ ነው።
ዳግመኛ ኢንፌክሽኑ ተጠናክሮ ሲመጣ ወደ ሙሉ ሰውነት ሊሠራጭ፣ በደም ዝውውር በኩል ወደ ሌላ ቦታ ሊሄድ ይችላል።
ዶ/ር ትንሳዔ በዚህም የተነሳ ታካሚው ወደ ሆስፒታል በድጋሚ በሚሄድበት ወቅት የሕክምና ባለሙያው ባክቴሪያው መድኃኒቱን በመላመዱ ለማከም ይቸገራል ይላሉ።
ስለዚህ አንደኛው ችግር ሰዎች የታዘዘላቸውን መድኃኒት በአግባቡ እስከ መጨረሻው አለመውሰዳቸው ነው።
ሁለተኛው ምክንያት የምንወስዳቸው መድኃኒቶች በሙሉ ጥሩ ጥራት ያላቸው አለመሆናቸው ነው።
በተለይ አፍሪካ እና እስያ ውስጥ የሚዘዋወሩት መድኃኒቶች ጥራታቸው የወረደ መሆኑን ዶ/ር ትንሳዔ ይናገራሉ።
ይህ ግን ለፀረ ተህዋሲያን የሚሰጡ መድኃኒቶች ላይ ብቻ ሳይሆን ሌሎችም መድኃኒቶች ላይም የሚታይ የጥራት ችግር አለ።
አብዛኞቹ አገራት መድኃኒቶቹ የት እንደተመረቱ፣ በምን ዓይነት ሁኔታ ወደ አገር ውስጥ እንደገቡ፣ በምን ዓይነት ሁኔታ ተከማችተው ወደ ተጠቃሚ እንደሚደርሱ የሚያደርጉት ቁጥጥር ደካማ ነው።
በዚያ ምክንያት በማሸጊያቸው ላይ ከተቀመጠው ግራም በታች ይዘት ያላቸው መድኃኒቶች ተጠቃሚው ጋር የመድረስ ዕድላቸው ሰፊ መሆኑን ዶ/ር ትንሳዔ ያስረዳሉ።
ሦስተኛው ችግር ያለ ሐኪም ትዕዛዝ የፀረ ተህዋሲያን መድኃኒቶችን ገዝቶ መውሰድ በኋላ ላይ መድኃኒቱን በተላመደ ተህዋሲ እንድንያዝ ያደርጋሉ።
ለጉንፋን የፀረ ተህዋሲያን የሚወስዱ ሰዎች መኖራቸውን የሚናገሩት ዶ/ር ትንሳዔ ኢንፌክሽኑ አንቲባዮቲክ አይፈልግም ይላሉ።
እረፍት ማድረግ፣ ብዙ ፈሳሽ መውሰድ እና ትኩሳት ካለ የትኩሳት ማስታገሻ መድኃኒት መውሰድ ብቻ በቂ ነው። ከዚያም ከተወሰነ ቀን በኋላ ይድናል።
ማንኛውም ሰው ያለ ሐኪም ትዕዛዝ የሚወስዳቸው መድኃኒቶች በማኅበረሰቡ ውስጥ በሽታውን የተላመደ ባክቴሪያ እንዲጨምር የራሱን አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ባለሙያው ያስጠነቅቃሉ።
በተጨማሪም መድኃኒት የተላመደ ባክቴሪያ በተያዝን ቁጥር ከበሽታው የመዳን ዕድላችን እየቀነሰ ይመጣል በማለት ያለውን አደገኛነት ያስረዳሉ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አገር ላይ የሚያደርሰው ጫና
ዶ/ር ትንሳዔ መድኃኒትን የተላመደ ተህዋሲ የሚያደርሰው አደጋ የሚታየው ቀስ በቀስ በመሆኑ እንደ "ዝምተኛ ገዳይ" ልንቆጥረው እንችላለን ይላሉ።
ፖሊሲ አውጪዎች፣ ሐኪሞች፣ ማኅበረሰቡ የሚዘናጉት ገዳይነቱ በፍጥነት ስለማይታይ ሊሆን እንደሚችልም ያክላሉ።
በግለሰብ ደረጃ ለእንደዚህ ዓይነት ተህዋሲ የሚጋለጥ ሕሙምን አክሞ ለማዳን ከባድ ይሆናል።
ስለዚህ የበሽታው ሁኔታ እየተባባሰ የሚሄድ ከሆነ አካላዊ ጉዳት ይጨምራል፤ እስከ ሞትም ያደርሳል ሲሉ አደጋውን ለማሳየት ይሞክራሉ።
በፀረ ተህዋሲ መድኃኒት በቀላሉ የማይድኑ በሽታዎች የሕክምናውን ውስብስብነት ይጨምራሉ፤ የበለጠ ሞት ያስከትላሉ።
ደካማ የጤና አጠባበቅ ሥርዓት ባላቸው ታዳጊ አገራት ውስጥ ደግሞ በአንድ ጊዜ ሊታከሙ ለሚችሉ ኢንፌክሽኖች ውጤታማ የሆኑ መድኃኒቶች ባለመኖራቸው እንደገና ገዳይ ሊሆኑ የሚችሉበት ቀውስ ውስጥ ይከትታሉ።
ዶ/ር ትንሳዔ በሁለተኛነት የሚያነሱት ሆስፒታሎች ላይ ጫና እንደሚያሳድር ነው።
"አንድ መቶ አልጋ ያለው ሆስፒታል ውስጥ መድኃኒትን በተላመዱ ተህዋሲያን የታመሙ ሕሙማን መጥተው ለረዥም ጊዜ አልጋ ይዘው የሚቆዩ ከሆነ ሌሎች ሕሙማንን አስተኝቶ ለማከም ስለማይቻል ጫና ይፈጥራል። ይህም የአገልግሎት አሰጣጥን ያዳክማል።"
እንደ ባለሙያው ገለጻ ሦስተኛው ነጥብ ኢንፌክሽኖቹ አቅማቸው በጠነከረ ቁጥር የምንጠቀማቸው መድኃኒቶችም ጠንካራ መሆን አለባቸው።
"እነዚያ ፀረ ተህዋሲያን መድኃኒቶች ደግሞ ውድ ናቸው። ሆስፒታሉ ሕይወት ለማትረፍ በሚል መድኃኒቶቹን በውድ ዋጋ ገዝቶ አገልግሎት ሲሰጥ በጀቱ ላይ የራሱ አሉታዊ ተጽእኖ ይኖረዋል። ይህ ደግሞ ተጠራቅሞ መንግሥት ላይ ጫና ይፈጥራል።"
ስለዚህ ሕሙማን ከሆስፒታል ማዘዣ መድኃኒት ተጽፎ ካልተሰጠ በስተቀር ከወዳጅ ዘመድ በሚመጣ ምክር ወይም ከዚህ በፊት ያሻለኝ ይህ ነው በሚል ምክንያት ያለማዘዣ ገዝቶ መጠቀምን ማቆም እንደሚኖርባቸው ይመክራሉ።
ዶ/ር ትንሳዔ ሐኪሞች ለሁሉም ኢንፌክሽን መድኃኒት መፍትሄ አለመሆኑን መገንዘብ አለባቸው ይላሉ።
"አብዛኛው ኢንፌክሽን በመድኃኒት የሚታከም አይደለም። ቀላል መፍትሄዎችን ታካሚው እረፍት እንዲወስድ ማድረግ፣ ፈሳሽ በደንብ እንዲጠጣ መምከር፣ ራሱን በምግብ እንዲንከባከብ በማድረግ የሚታከሙ በጣም ብዙ ኢንፌክሽኖች አሉ።"
ስለዚህ ለመጣው ታካሚ ሁሉ ፀረ ተህዋሲ መድኃኒትን ባለማዘዝ መድኃኒት የተላመደ ባክቴሪያን መከላከል ይቻላል ይላሉ።
"ከፊት ለፊታችን ያለው ኢንፌክሽን እውን መድኃኒት የሚፈልግ ነወይ የሚለውን በአግባቡ በማጣራት፣ ተገቢ የሆነ የላብራቶሪ ምርመራ ማድረግ ይኖርብናል። ካልተገደድን በስተቀር መድኃኒት አለማዘዝ ይመከራል።"
ዶ/ር ትንሳዔ ሆስፒታሎች ተገቢውን የኢንፌክሽን መከላከያ መንገዶችን አሠራራቸው ውስጥ ማስገባት ይኖርባቸዋል ብለዋል።
ለዚህ ደግሞ መሠረታዊ ከሆኑት መካከል አንዱ ውሃ ነው። 24 ሰዓት የማያቋረጥ ውሃ፣ አልኮል፣ ጓንት፣ በረኪና ያላቸው ሕክምና ተቋማት ኢንፌክሽንን በአግባቡ መከላከል ይችላሉ።
እንደ ዶ/ር ትንሳዔ መድኃኒትን የተላመደ ተህዋሲ አደጋ ሩቅ አይደለም። በቅርቡ እያለ አሁን እርምጃ መውሰድ የሚጠይቅ ነው።
ለጤና ወግ የሕክምና ባለሙያዎች ደግሞ በማደግ ላይ ባሉ አገራት ውስጥ መድኃኒት ከተላመዱ ተህዋሲያን ጋር የሚደረገው ፍልሚያ ለጤና ብቻ ሳይሆን ለኅልውና፣ ለደኅንነት፣ ለብልጽግና እና ለትውልድ ጤናማ የወደፊት ተስፋ የሚሰጥ ትግል ነው።
ዶ/ር ትንሳዔ "መንግሥት ይህንን መድኃኒት የተላመደ ተህዋሲ መቆጣጠር ካልቻለ፤ በ2025 ከማንኛውም ሕመም በላይ ቁጥር አንድ ገዳይ እንደሚሆን አውቆ ፖሊሲዎችን ማዘጋጀት እና መተግበር ያስፈልጋል" ሲሉ ይመክራሉ።















