መድኃኒት የተላመዱ ተላላፊ በሽታዎች ሚሊዮኖችን እየገደሉ ነው- ጥናት

መድኃኒት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በአውሮፓውያኑ 2019 ብቻ ከ1.2 ሚሊየን በላይ የሚሆኑ ሰዎች መድሀኒቶችን የተላመዱ ከባክቴሪያ በሚከሰቱ ተላላፊ በሽታዎች መሞታቸውን አንድ ዓለም አቀፍ ጥናት ጠቁሟል።

ይህ ደግሞ በየዓመቱ በአጠቃላይ ወባ ወይም ኤችአይቪ ኤድስ ከሚገድሉት በላይ ነው።

ደሃ የሆኑት አገራት በነዚህ መድሀኒት በተላመዱ ተላላፊ በሽታዎች በብዛት የሚጠቁ ቢሆንም በባክቴሪያ የሚተላለፉ በሽታዎች ግን ለሁሉም ሰው አስጊ ናቸው ብሏል ሪፖርቱ።

አስቸኳይ የሆነ ኢንቨስትመንት መሰል በሽታዎችን መከላከያ መድሀኒቶች ላይ ፈሰስ እንዲደረግ የጠየቀው ሪፖርቱ አሁን ላይ አገልግሎት እየሰጡ የሚገኙትን መድሀኒቶችን በብልሀት መጠቀምም አስፈላጊ እንደሆን ጠቁሟል።

የባክቴሪያ መከላከያ መድሀኒቶችን ከመጠን በላይ አብዝቶ መጠቀም በሽታዎችን የመከላከልም ሆነ የማዳን አቅማቸው እየቀነስ እንዲመጣ እንደሚያደርገውም ተገልጿል።

በሪፖርቱ መሰረት ሰዎች ከዚህ በፊት በሚታወቁና ቀላል በሚባሉ ተላላፊ የባክቴሪያ በሽታዎች ሕይወታቸው እያለፈ ሲሆን ለዚህ ደግሞ ዋነኛ ምክንያቱ በሽታዎቹ መድሀኒቶችን እየተላመዱ መምጣታቸው ነው።

በሌላ በኩል ሰዎች መድሀኒቶችን በአግባቡ መጠቀም እስካልጀመሩ ድረስ ዓለማችን ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ ስታገግም መድሀኒቶችን የተላመዱ በባክቴሪያ የሚተላላፉ በሽታዎች ሌላ የጤና ስጋት ሊሆን ሊሆኑ እንደሚችሉ የዩኬ የጤና ኃላፊዎች አሳስበዋል።

በየዓመቱ በርካታ ሰዎችን የሚገድለው ይህ ጉዳይ ላይ ጥናት ያደረገው ላንሴት የተባለው ዓለም አቀፍ የላብራቶሪ እና ጥናት አገልግሎት የሚሰጠው ድርጅት በ204 አገራት መረጃውን ሰብስቧል።

በዚህ ጥናት መሰሰረትም በአጠቃላይ 2019 በመላው ዓለማችን እስከ 5 ሚሊየን የሚደርሱ ሰዎች በተለያዩ በሽታዎች ምክንያት ሕይወታቸው ያለፈ ሲሆን ከነዚህ ውስጥ ደግሞ 1.2 ሚሊየን የሚሆኑት የሞቱት በሽታን በተላመዱ የባክቴሪያ በሽታዎች ምክንያት ነው።

በዛው ዓመት ኤችአይቪ ኤድስ ለ860 ሺ ሰዎች ሕይወት ማለፍ ምክንያት ሲሆን ወባ ደግሞ 640 ሺ ሰዎችን ገድሏል።

ለነዚህ ሰዎች ሞት በዋነኛነት ከሚጠቀሱ ተላላፊ በሽታዎች መካከል የሳምባ ምች እና የደም ቧምቧ ኢንፌክሽን ይገኙበታል።

ታማሚዎችን የተመለከቱ የተለያዩ ሆስፒታሎችን መረጃዎች፣ ጥናቶችና ምንጮችንም ጭምር ከግምት ውስጥ አስገብቶ በተሰራው ጥናት በመሰል በሽታዎች ሕይወታቸው ከሚያልፈው ሰዎች መካከል ህጻናት ትልቁን ድርሻ እንደሚይዙ ተጠቁሟል።

ከእያንዳንዱ ከሚሞት አምስት ሰው አንዱ ከአምስት ዓመት በታች የሆነ ህጻን ነው።

እንደ ከሰሀራ በታች ባሉ እና ደቡባዊ እስያ ውስጥ በሚገኙ ደሃ አገራት በእያንዳንዱ 100 ሺ ሰው 24 ሰዎች በዚሁ ከላይ በተጠቀሰው ምክንያት የሚሞቱ ሲሆን ባደጉት አገራት ግን ቁጥር ወደ 13 ዝቅ ያለ ነው።