
የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ኢራን አሜሪካ ጦርነቱን ለማቆም ላቀረበችው ዕቅድ የሰጠችውን ምላሽ “ፈጽሞ ተቀባይነት የሌለው”
ሲሉ ውድቅ አደረጉ።
በከፊል ከኢራን መንግሥት ጋር ግንኙነት ያለው ታስኒም የቴህራን ምላሽ በአሸማጋይዋ ፓኪስታን በኩል መላኩን ዘግቧል።
የዜና ወኪሉ የቴህራን ምላሽ ውስጥ በሁሉም ግንባሮች የሚካሄዱ ውግያዎች እንዲቆሙ፣ አሜሪካ የኢራን ወደቦች ላይ የጣለችው
እገዳ እንዲነሳ፣ እንዲሁም ወደፊት ኢራን ላይ ጥቃት እንደማይፈጸም ዋስትና እንዲሰጥ ይጠይቃል።
ከሁለት ወር በላይ በዘለቀው የኢራን ጦርነት አልፎ አልፎ የተኩስ ልውውጦች ቢኖሩም በአብዛኛው የተኩስ አቁሙ እንደቀጠለ
ነው።
ከዚህ ሳምንት ቀደም ብሎ ትራምፕ በኢራን ላይ የከፈቱት ጦርነት “በፍጥነት ይጠናቀቃል” ብለው ነበር።
ነገር ግን የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ጦርነቱ ተጠናቅቋል ከማለታችን በፊት ኢራን ያከማቸችው የበለጸገ
ዩራኒየም “መውጣት አለበት” ሲሉ ጠይቀዋል።
ኔታንያሁ ሲቢኤስ ላይ በሚቀረበው ‘60 ሚኒትስ’ ለተሰኘ ፕሮግራም በሰጡት ቃለ ምልልስ “አሁንም ያልወደሙ የማበልጸጊያ
ማዕከላት አሉ” ብለዋል።
እሁድ ዕለት የኢራኑ ፕሬዚዳንት ማሱድ ፔዜሽኪያን የሰላም ዕቅዱን በቀጥታ ሳይጠቅሱ “በጠላቶቻችን ፊት አንገታችንን አንደፋም።
የንግግር ወይም የድርድር ሃሳብ ሲመጣ እጅ መስጠት ወይም ማፈግፈግ ማለት አይደለም” ብለዋል።
ትራምፕ በትሩዝ ሶሻል ማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ “በተወካይ በኩል ቀረበ የተባለውን የኢራንን ምላሽ አነበብኩት፤ አልወደድኩትም።
ምንም ተቀባይነት የለውም” ሲሉ ጽፈዋል።
የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን የሆነው አክሲዮስ ውስጥ አዋቂ ምንጮችን ጠቅሶ እንደዘገበው አሜሪካ ያቀረበችው ባለ 14 ነጥብ
የሰላም ዕቅድ ኢራን ኒውክሌር ማበልጸጓን እንድታቋረጥ፣ የተጣለባት ማዕቀብ እንዲነሳ እና በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ የሚደረገው ነጻ
እንቅስቃሴ እንዲቀጥል የሚጠይቁ ሃሳቦችን የያዘ ነው።
መገናኛ ብዙኃኑ በዘገባው ስለ ዕቅዱ ማብራሪያ የተሰጣቸውን ሁለት በስም ያልተጠቀሱ የአሜሪካ ባለሥልጣናትን እና ሁለት ሌሎች ግለሰቦችን ጠቅሷል።
እንዚህ ምንጮች በመግባቢያ ሰነዱ ላይ የተጠቀሱት አብዛኛዎቹ ነጥቦች ለመጨረሻው ስምምነት መነሻ በመሆን ያገለግላሉ ብለዋል።
ኢራን የዓለም 20 በመቶ ነዳጅ እና ጋዝ የሚተላለፍበትን የባሕር ወሽመጡን እንደዘጋች ነው።
አሜሪካ በበኩሏ ወደ ኢራን ወደቦች የሚገቡ እና የሚወጡ መርከቦችን የከለከለች ሲሆን ይህም ቴህራን ወደ ድርድር ጠረጴዛ
እንድትመጣ ጫና ለመፍጠር ያለመ ነው።
ትራምፕ እአአ ግንቦት 6 በትሩዝ ሶሻል ሚዲያ ገጻቸው ላይ ኢራን በቀረበላት የሰላም
ሃሳብ የማትስማማ ከሆነ ዳግመኛ የቦምብ ድብደባው እንደሚጀመር ጽፈው “ከዚህ በፊት ከታየው ሁሉ የከፋ ይሆናል” ሲሉ አስጠንቅቀው
ነበር።