ጦርነቱን ለማስቆም ተስፋ ሰጪ ጥረት እየተደረገ መሆኑን አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ገለጹ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በሰሜን ኢትዮጵያ የሚካሄደውን ጦርነት ለማብቃትና ሰላም ለማውረድ የሚያስችል የሚታይ ጥረት እየተደረገ መሆኑ እንዳስደሰታቸው የመንግሥታቱ ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ገለጹ።
ዋና ፀሐፊው ረቡዕ ዕለት የአፍሪካ ሕብረት የአፍሪካ ቀንድ ከፍተኛ ተወካይ ከሆኑት ከኦሉሴጎን ኦባሳንጆ ጋር በኢትዮጵያ ስላለው ጦርነት በስልክ ከተወያዩ በኋላ ባወጡት መግለጫ ነው ይህንን ያሉት።
ኦባሳንጆ ባለፈው ሳምንት ወደ አዲስ አበባ እና መቀለ በመጓዝ ከኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናትና ከህወሓት መሪዎች ጋር ውይይት ማድረጋቸው መዘገቡ ይታወሳል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ከኦባሳንጆ ጋር ባደረጉት የስልክ ውይይት፣ በሰሜን ኢትዮጵያ የሚካሄደውን ጦርነት ለማስቆም የኢትዮጵያ መንግሥትና ህወሓት እያደረጉት ስላላው ጥረት ከሕብረቱ ተወካይ መረዳታቸውን አመልክተዋል።
ጉተሬዝ ዛሬ ሐሙስ ጥር 12/2014 ዓ.ም ለቢቢሲ አፍሪካ እንደተናገሩት "በተመድ የፀጥታው ምክር ቤት ኢትዮጵያን የተመለከተ ግልጽ የሆነ የሃሳብ ልዩነት" ቢኖርም ለጦርነቱ መፍትሄው ቅርብ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ጦርነቱን በተመለከተ የምዕራባውያንን ተሳትፎ 'የውጪ ጣልቃ ገብነት ነው' በሚል ሲከላከል መቆየቱ ለችግሩ መፍትሄ ማፈላለግን አስቸጋሪ እንዳረገው ጠቅሰው፤ የሰብዓዊ እርዳታ እንዲደርስ "ሁሉም ተኩስ ማቆም አለባቸው" ብለዋል ጉቴሬዝ ለቢቢሲ።
"ችግሩን ለመፍታት ጉዳዩ ለእኛ ቀላል አልነበረም። ከጠቅላይ ሚንስትሩ ጋር ስገናኝ ነበር። ከህወሓት ጋር ስነጋገር ነበር። ከኦባሳንጆ፣ ከኡሁሩ ኬንያታ እና ከበርካታ የዓለም መሪዎች ጋር ስንጋገር ነበር። አሁን ወደ ተሻለ ዕድል እየተቃረብን ነው ብዬ አምናለሁ" ብለዋል ዋና ፀሐፊው።

ጉተሬዝ በረቡዕ ዕለቱ መግለጫቸው ላይ እንዳሉት ከኦሉሴጎን ኦባሳንጆ ጋር ባደረጉት ውይይት አሁን ለግጭቱ ተጨባጭ ፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ መፍትሔ ለማግኘት ዕድል እንዳለ ያላቸውን ተስፋ እንደገለጹላቸው ጠቅሰዋል።
በዚህም በኢትዮጵያና በአካባቢው የሚገኙ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ለችግር ያጋለጠውና ከአንድ ዓመት በላይ የተካሄደውን ወታደራዊ ግጭት በማብቃት ሰላም ለማውረድ የሚያስችል ተጨባጭ ጥረት እየተደረገ መሆኑ እንዳስደሰታቸው የመንግሥታቱ ድርጅት ዋና ፀሐፊ ገልጸዋል።
በአንዳንድ የኢትዮጵያ ክፍሎች እየተካሄደ ያለው ወታደራዊ ግጭት ሰላም ለመውረድ ለሚደረገው ጥረት ተግዳሮት መሆኑን የጠቀሱት ጉቴሬዝ፣ ይህም "በግጭቱ ተሳታፊ ወገኖች መካከል መተማመን ለመገንባት የሚወሰዱ እርምጃዎችን ያበላሻል" ብለዋል።
ዋና ፀሐፊው አሁንም የጦርነቱ ተሳታፊ ሁሉም ወገኖች ወደ ሰላም አቅጣጫ ወደ ሚመራውና ወሳኝ ወደሆነው ግጭቶችን ወደማቆም በፍጥነት እንዲያመሩ ጥሪ አቅርበው፤ ድርጅታቸው በኢትዮጵያ የሁሉን አቀፍ ውይይት፣ የሰላም፣ የደኅንነትና የዕርቅ ሂደትን ለመደገፍ ዝግጁ መሆኑን አመልክተዋል።
"በአፍሪካ ሕብረት የሚመራውን የሰላም ሂደት በታላቅ ተስፋ እየተከታተልን ባለበት ወቅት፣ በጦርነቱ በተጎዱ የተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች ያለው የሰብአዊ ቀውስ ሁኔታ ያሳስበናል" በማለት፣ ሁሉም ወገኖች እርዳታ ለማቅረብ የአገር ውስጥና ዓለም አቀፍ ጥረቶችን እንዲደግፉ ጥሪ አቅርበዋል።
የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት እና የአፍሪካ ሕብረት የአፍሪካ ቀንድ ከፍተኛ ተወካይ የሆኑት ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ ባለፈው ማክሰኞ ጥር 03/2014 ዓ.ም. ወደ ትግራይ ሄደው መቀለ ውስጥ ከህወሓት አመራሮች ጋር "መልካም ውይይት ማድረጋቸውን" አቶ ጌታቸው ረዳ ገልጸው ነበር።
ከመቀለ በኋላ ወደ አዲስ አበባ የተመለሱት ኦባሳንጆ ከጥቂት ወራት በፊት ለተመሳሳይ የሰላም ጥረት ወደ መቀለ ተጉዘው የነበረ ሲሆን ከጉቴሬዝ መግለጫ ውጪ፣ ስላለፈው ሳምንት ጉዟቸው ምንም የተባለ ነገር የለም።
ከአንድ ዓመት በላይ ሲካሄድ ቆይቶ በቅርቡ ጋብ ያለው የሰሜን ኢትዮጵያን ጦርነት ለማስቆም ከአፍሪካ ሕብረት ተወካዩ ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ በተጨማሪ የአሜሪካ መንግሥት ልዩ መልዕክተኛ የነበሩት ጄፍሪ ፌልትማን ጥረት ሲያደርጉ ቢቆይም ተጨባጭ ውጤት አልተገኘም።
አሁንም የቀድሞውን መልዕክተኛ የተኩት አዲሱ የአሜሪካ መልዕክተኛ ዴቪድ ሳተርፊልድ በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ኃላፊ ከሆኑት ሞሊ ፊ ጋር ዛሬ አዲስ አበባ እንደሚገቡ ይጠበቃል።
የአሜሪካ ልዑካኑ ወደ ኢትዮጵያ ሲሄዱ ፕሬዝዳንት ባይደን ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጋር ሰኞ ጥር 02/2014 ዓ.ም ያደረጉት "ገንቢ የስልክ ውይይት ተከታይ ጉዳዮችን" እንደሚያነሱ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ ባወጣው መግለጫ አመልክቷል።














