ቀይ መስቀል በሰሜን ኢትዮጵያ የመድኃኒት እና የሕክምና መገልገያ እጥረት አሳስቦኛል አለ

ቀይ መስቀል

የፎቶው ባለመብት, Reuters

በሰሜን ኢትዮጵያን ጦርነት ተከትሎ በአካባቢው የመድኃኒት እና የሕክምና መገልገያ መሳሪያዎች አቅርቦት አለመኖር በእጅጉ እንዳሳሰበው ዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴ አስታወቀ።

አንድ ዓመት ካለፈው ጦርነት ጋር ተያይዞ በትግራይ፣ በአማራ እና በአፋር ክልሎች የሚገኙ የሕክምና ተቋማት ውድመት የገጠማቸው ሲሆን፣ ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ በአሁኑ ወቅት የአስፈላጊ አቅርቦቶችን ችግር እንደገጠማቸው ተነግሯል።

"የሕክምና አገልግሎት አቅራቢዎች መሠረታዊ ግብዓቶችን እያገኙ አይደለም፤ እንዲሁም በአንዳንድ መሠረተ ልማቶች ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸዋል" ብሏል ዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴ (አይሲአርሲ) ጥር 09/2014 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ።

ቀይ መስቀል የመድኃኒት እና ሕክምና መስጫ መሳሪዎች እጥረት ከጤና መሠረተ ልማት ውድመቶች ጋር ተደማምሮ የጤና አገልግሎት አቅርቦትን እጅግ አስቸጋሪ አድርጎታል ይላል።

ቀይ መስቀል በሰሜን ኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ፤ "ሰዎች ለመኖር የሚያስፈልጋቸውን መሠረታዊ ነገር ከመከልከል" ጋር የሚስተካከል ነው ብሏል።

አይሲአርሲ ካለው ተጨባጭ ሁኔታ አንጻር የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦቱን የበለጠ ተጎጂ በሆኑት ላይ ትኩረት እያደረኩ ነው በሏል።

"የሕክምና አቅርቦቶች በመቀነሳቸው ምላሽ የመስጠት አቅማችንን ተገድቧል" ያለው ቀይ መስቀል፤ ጦርነት፣ የደኅንነት እጦት እና ገደቦች የሰብዓዊ እርዳታውን ፈተና ውስጥ ከከተቱት ምክንያቶች መካከል ቀዳሚ መሆናቸውን በትናንቱ መግለጫው አስታውቋል።

"በአማራ ክልል አንዳንድ ሆስፒታሎች በመድኃኒት እጥረት ምክንያት ተዘግተዋል" ሲሉ በአማራ እና አፋር ክልሎች የቀይ መስቀል ተወካይ ሚቻ ዌዲኪንደ ተናግረዋል።

"ሥር የሰደዱ በሽታዎች ያለባቸው ሰዎች በየዕለቱ እየሞቱ ነው። የጤና ተቋማት አገልግሎት እየሰጡ ባለመሆናቸው፤ ውሃ ወይም መብራት ስለማይኖራቸው እናቶች በቤት ውስጥ እየወለዱ ነው" ብለዋል የዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴ የአማራ እና አፋር ክልል ተወካይ።

ከአማራ እና አፋር በተጨማሪ በትግራይ ክልልም ከፍተኛ የሆነ መድኃኒት እና የሕክምና ቁሳቁሶች እጥረት መኖሩ ቀይ መስቀል በመግለጫ ተመልክቷል።

"በትግራይ ለአንድ ጊዜ ብቻ ጥቅም ላይ የሚውሉ እንደ ጓንት፣ የቀዶ ሕክምና ቁሳቁሶች እና ሰውነት ውስጥ የሚገቡ የሕክምና ቱቦዎች ሳይቀሩ እየታጠቡ ዳግም ጥቅም ላይ እንዲውሉ እየተደረገ ነው" ሲሉ በኢትዮጵያ የቀይ መስቀል የጤና አስተባባሪ አፖሎ ባራሳ።

ከላይ የተጠቀሱት አይነት ለአንድ ጊዜ ብቻ ጥቅም ላይ መዋል ያለባቸውን የጤና መሳሪያዎችን ዳግም መጠቀም፤ ለኢንፌክሽን የመጋለጥ እድልን ያሰፋል ይላሉ ተወካይዋ።

በአንዳንድ አካባቢዎች ታካሚዎች የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ያለፈባቸው መድኃኒቶችን ከመውሰዳቸውም በተጨማሪ ሐኪሞች የሰዎችን ቁስል ለማጽዳት ጨው ለመጠቀም መገደዳቸውን ጭምር አፖሎ ባራሳ ይገልጻሉ።

ዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴ በጦርነቱ ተሳታፊ የሆኑ ሁሉም አካላት በፍጥነት የሰብዓዊ እርዳታ እንዲደርስ የበኩላቸውን እንዲወጡ በመግለጫው ጠይቋል።

ኮሚቴው ከኢትዮጵያ የቀይ መስቀል ማኅበር ጋር በመሆን እአአ 2021 ላይ በአማራ፣ በአፋር፣ በትግራይ፣ በኦሮሚያ እና በሶማሌ ክልሎች ለሚገኙ 130 የጤና ተቋማት ድጋፍ ማድረጉን ገልጿል።

በዚህም ወደ 120 ሺህ የሚጠጉ ሰዎች ድጋፉን ማግኘታቸውን በመግለጫው አመልክቷል።

የቀይ መስቀል ኮሚቴ እያደረገ ካለው የሕክምና ድጋፍ በተጨማሪ በሰሜን ኢትዮጵያ ባሉ አካባቢዎች ያለው የምግብ እና የኑሮ ሁኔታ ያሳስበኛልም ብሏል።

ኮሚቴው በስድስት ወራት ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ በአማራ ክልል ላልይበላ ከተማ እንዲሁም በመቀለ ከተማ ከ3 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ሰዎች ድጋፍ ማድረጉን ገልጿል።

በመጨረሻም ዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴ ጨምሮም በቅርቡ ንጹሃን ዜጎችን ለጉዳት የዳረገ ግጭት መኖሩ አሳስቦኛል ብሏል። ኮሚቴው የግጭቱ ተሳታፊዎች ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ እርዳታ ሕግጋቶችን እንዲያከብሩ ጠይቋል።

ከጦርነቱ ጋር ተያይዞ በሰሜን ኢትዮጵያ ባሉ ክልሎች ውስጥ በሚገኙ የሕዝብ መገልገያ መሠረተ ልማቶች ላይ በተለይም የሕክምና ተቋማት ላይ ዘረፋና ውድመት መፈጸሙ የተለያዩ መንግሥታዊና የተራድኦ ድርጅቶች ያወጧቸው ሪፖርቶች አመልክተዋል።

የጤና ተቋማት በገጠማቸው ችግርና በመድኃኒትና በሕክምና መገልገያዎች አለመኖር ምክንያት በአካባቢዎቹ ያሉ ነዋሪዎች ከባድ የጤና ችግር ያለባቸው ሰዎች ለአደጋ መጋለጣቸው እተነገረ ነው።