በአማራ ክልል 11.4 ሚሊየን ሕዝብ የመልሶ ማቋቋም ድጋፍ እንደሚያስፈልገው ተገለጸ

የአማራ ክልል ተፈናቃዮች

በአማራ ክልል በደባርቅ ጊዜያዊ መጠለያ ከሚገኙት በስተቀር በጦርነቱ ሳቢያ ተፈናቅለው በጊዜያዊ መጠለያ የነበሩ ሁሉም ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው መመለሳቸው ተገለጸ።

የክልሉ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ፕሮግራሞች ማስተባበሪያ ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ የሆኑት አቶ እያሱ መስፍን ለቢቢሲ እንደገለጹት በጦርነቱ በክልሉ ውስጥ ተፈናቅለው በጊዜያዊ መጠለያ ውስጥ ተጠልለው የነበሩ ዜጎች ወደ ቀያቸው ተመልሰዋል።

ኃላፊው ጦርነቱ ወደ ደቡብ ወሎና ሰሜን ሸዋ ተስፋፍቶ በነበረበት ወቅት የተፈናቃዮች ቁጥር ከ2.3 ሚሊየን በላይ ደርሶ እንደነበርና ከእነዚህ መካከል ሁለት በመቶ ማለትም ከ45 ሺህ በላይ የሚሆኑ ዜጎች በጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያ ተጠልለው ይገኙ እንደነበር አስታውሰዋል።

ይሁን እንጂ አሁንም በደባርቅ ጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያ ውስጥ ከ5 ሺህ በላይ ተፈናቃዮች ተጠልለው እንደሚገኙ አቶ እያሱ ገልጸዋል።

በክልሉ ከቀያቸው ተፈናቅለው ከነበሩት ዜጎች መካከል በጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያ ተጠልለው የነበሩትን ጨምሮ ከ500 ሺህ በላይ ሰዎች መንግሥት ባዘጋጀው ትራንስፖርት ወደ ቀያቸው መመለሳቸውን ኃላፊው አረጋግጠዋል።

"98 በመቶ የሚሆነው ተፈናቃይ በዘመድ አዝማድ እና በማኅበረሰቡ ውስጥ ተጠልሎ ነው የቆየው። በመሆኑም እስካሁን በጠቅላላ ወደቀያቸው የተመለሱ ዜጎችን ቁጥር ለማወቅ እየተሰራ ነው" ብለዋል ኃላፊው።

በክልሉ በጦርነቱ ሳቢያ 9.1 ሚሊየን ሕዝብ ለከፋ የምግብና መድኃኒት ችግር ተዳርጎ እንደነበር ያስታወሱት አቶ እያሱ፤ በተለቀቁ አካባቢዎች ማኅበረሰቡ ምርት አምርቶ ራሱን እስከሚችል ድረስ በአጠቃላይ 11.4 ሚሊየን ሕዝብ የመልሶ ማቋቋም ድጋፍ እንደሚያስፈልገው ተናግረዋል።

ለዚህም ለአንድ ወር ብቻ 1.2 ሚሊየን ኩንታል እህል ያስፈልጋል ብለዋል።

አቶ እያሱ የመልሶ ማቋቋም ሥራ ለማከናወን በህወሓት ኃይሎች ተይዘው በነበሩ አካባቢዎች የደረሰው የጉዳት መጠን እየተጠና መሆኑንም አክለዋል።

በክልሉ በጦርነቱ በተጎዱ አካባቢዎች የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን፣ የዓለም ምግብ ፕሮግራም፣ የአማራ መልሶ መቋቋምና ልማት ድርጅት (አመልድ) እና ቀይ መስቀል በተለያዩ አካባቢዎች ተሰማርተው ድጋፍ እያደረጉ መሆናቸውን አመልክተዋል።

ነገር ግን በአካባቢዎቹ ባለ የትራንስፖርት ችግር እና በአማጺያኑ ውድመት የደረሰባቸው የወረዳና የዞን ተቋማት ገና እየተደራጁ በመሆናቸው ድጋፉ መቶ በመቶ ለተጠቃሚው ተደራሽ ሆኗል ለማለት እንደማያስደፍር አቶ እያሱ አስረድተዋል።

አቶ እያሱ እንዳሉት በአንዳንድ የክልሉ አካባቢዎች አሁንም የከባድ መሣሪያ ትንኮሳዎች መኖራቸውን በመጠቆምም እየተፈናቀሉ ያሉ ዜጎች መኖራቸውን አመልክተዋል።

እንደ አዲስ የተፈናቀሉ ዜጎች ከየት አካባቢ የተፈናቀሉ እንደሆኑ የተጠየቁት ኃላፊው፤ በደምሳሳው "ጦርነት እስካልቆመ ድረስ መፈናቀልና የዜጎች ስቃይ አይቆምም" በማለት አካባቢዎቹን ከመጥቀስ ተቆጥበዋል።

ከአንድ ዓመት በላይ በሆነው የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ምክንያት ከፍተኛ ሰብአዊ ቀውስ መከሰቱ የተነገረ ሲሆን በትግራይ፣ በአማራ እና በአፋር ክልሎች ውስጥ ከ9 ሚሊዮን በላይ ሰዎች እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ማስታወቁ ይታወሳል።