ወልዲያ ከተማ፡ በፈታኞቹ ወራት የወልዲያ ነዋሪዎችን ያገለገሉት አቡነ ኤርሚያስ እና ሲስተር ተስፋነሽ

ወልዲያ ከተማ/የሰሜን ወሎ አገረ ስብከት ሊቀጳጳስ ብፁዕ አቡነ ኤርሚያስ

የፎቶው ባለመብት, Woldia Communication/ Facebook

በአማራ ክልል የሰሜን ወሎ ዞን መቀመጫ የሆነችው ወልዲያ በህወሓት አማጺያን ቁጥጥር ሥር የገባችው ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር መጀመሪያ ላይ ነበር።

በአማጺያኑ እጅ በቆየችባቸው አራት ወራት ከተማዋን ጨምሮ ወደ አካባቢው ምንም ዓይነት ዓለም አቀፍም ሆነ መንግሥታዊ ሰብዓዊ እርዳታ እንዳልገባ ነዋሪዎች ይናገራሉ።

የመብራት፣ የውሃ፣ የስልክና የኢንተርኔት አገልግሎቶችም ተቋርጠው ነው የቆዩት።

የሕክምና እና የንግድ ተቋማት ሥራ በማቆማቸው ነዋሪዎች በምን ሁኔታ ውስጥ እንደነበሩ በውል የሚያውቅም አልነበረም።

እናት ከልጅ፣ ባል ከሚስት ተለያይተዋል። ማን በምን ሁኔታ ውስጥ እንዳለ የሚያውቅበት አጋጣሚ አልነበረም።

አብዛኛው ነዋሪ ከእጅ ወደ አፍ የሆነ ኑሮ በሚገፋባት ከተማ ሰው ምን ልሶ፣ ምን ቀምሶ ያድር ይሆን? የበርካቶች ጭንቀት ነበር።

በከተማዋ ሕይወት ምን ይመስል ነበር?

ከተማዋ በአማጺያኑ እጅ ከገባች በኋላ ሁሉም በቤቱ ተከተተ። ከታጣቂዎቹ በስተቀር በከተማዋ የሚንቀሳቀስ አልነበረም። ወልዲያ ፀጥ ረጪ አለች ይላሉ ነዋሪዎች።

በጨለማ ውስጥ ውሎ ማደርን መለማማድ ያዘች።

የስልክ፣ የኢንተርኔትና የትራንስፖርት አገልግሎት በመቋረጡም ከዘመድ አዝማድ ጋር መገናኘት፣ ስለደኅንነት መጠያየቅም ቀረ።

ወልዲያ ከሌሎች ከተሞችም ከዓለምም ተነጠለች።

ጉዳይ ገጥሞት አሊያም እግሬን ላፍታታ ብሎ ከቤቱ የተንቀሳቀሰ ካለም ይዞ የወጣውን ይዞ መግባት ዘበት ሆነ።

"ታጣቂዎቹ አምስት ብርም አይምሩም። ሰው ስልክም ሆነ ብር ሳይዝ ለመንቀሳቀስ ይሞክራል፤ ነገር ግን ብሔር ተኮር ስድብ ስለሚሳደቡ ላለመጋጨት ሰዉ ቤት ውስጥ ነበር የሚያሳልፈው" ይላል የከተማዋ ነዋሪ ኑሩሁሴን አሕመድ።

ለወትሮው ሰው የሚተራመስበት ፒያሳ አደባባይ ላይ የሚታየውም አንድ ሁለት ሰው ነበር።

የግለሰብም ሆነ የተቋማት ንብረት መዘረፍና መውደም የዕለት ከዕለት ክስተት እንደነበርም ነዋሪዎች ያስታውሳሉ።

የባንክ አገልግሎት ባለመኖሩም ነዋሪው እጁ ላይ ያለችውን ሳንቲም ማስላት ጀመረ።

"እስከ መቼ ያዛልቀኝ ይሆን?" የባለሃብቱም የድሃውም ጥያቄ ሆነ።

እንዲህ እንዲህ እየተባለ ሳምንታት ነጎዱ። ችግሩ ግን እንዲሁ በስሌት ብቻ የሚታለፍ አልሆነም።

ለመረዳዳት እና ለመተሳሰብ እንግዳ ያልሆኑት ነዋሪዎቿ ነፍሳቸው የሚያተርፍላቸው 'አንተ ትብስ፣ አንቺ ትብሽ' መባባል እንደሆነ ተረዱ።

ማኅበረሰቡ ያለውን እያዋጣ አብሮ መብላት፣ መጠጣት ጀመረ።

"በወቅቱ በህወሓት እጅ ካልገቡ ከተሞች መድኃኒትም ሆነ ማንኛውም ነገር መግባት ስለማይችል፤ መተሳሳቡ መድኃኒት እስከመካፈልም የደረሰ ነበር " ይላል በእንጨት ሥራ የሚተዳደረው ኑሩሁሴን።

መድኃኒት መካፈል

ኑሩሁሴን ወንድሞቹንና ወላጆቹን የሚረዳው በእንጨት ሥራው ከሚያገኘው ገቢ ነው። እርሱም አካል ጉዳተኛ ነው። እናቱ ደግሞ የስኳር ህመምተኛ።

አንደኛው ወንድሙ ደግሞ ከባጃጅ ወድቆ አደጋ ገጥሞታል። ባለው አቅም ሁለቱን ማስታመም ለእርሱ ቀላል አልነበረም።

በተለይ እናቱ የሚወስዱትን መድኃኒት ለመፈለግ ያልለመኑበት፣ ያልሄዱበት የለም፤ ግን ማግኘት አልቻሉም ነበር።

"እናቴ በአላህ ምህረት ነው በሕይወት የቆየችው" የሚለው ኑሩሁሴን በኋላ ላይ የአራት ወርና ከዚያ በላይ ለሚሆን ጊዜ መድኃኒት ቀድመው የገዙ ለሌላቸው ማካፈል ጀመሩ ይላል።

"እስካሁን ያቆየን መረዳዳት መተዛዘኑ ነው፤ ሁለት መድኃኒት ያለው ለነገው ሕይወቱ ሳይሳሳ ለሌለው ያካፍላል። ይህ ነፍስን ቆርጦ እንደመስጠት ነው" ይላል ኑሩሁሴን የነዋሪውን የመረዳዳት ልክ ሲያስረዳ።

ሌላኛው የከተማዋ ነዋሪ እሸቱ አሰፋ ደግሞ ብቻውን ይኖር የነበረ የስኳር ህመምተኛ ጓደኛው ሕይወቱ አልፎ ከሁለት ቀን በኋላ እንዳገኙት ይናገራል።

"ስልክ ስለማይሰራ ደውሎም ሊጠራን አልቻለም ነበር። የእርሱን ስለማውቅ ነው እንጂ ሌሎች በየቤታቸው በመድኃኒት እጦት ብቻ ሕይወታቸው ያለፈ ይኖራል" ብሏል።

መስከረም ላይ ቢቢሲ ያነጋገራቸው የሰሜን ወሎ ዞን ጤና መምሪያ ኃላፊ ወ/ሮ ሰላማዊት አያሌው ወልዲያን ጨምሮ በዞኑ ከ18ሺህ በላይ የስኳር ታካሚዎች፣ ከ20 ሺህ በላይ የፀረ ኤችአይቪ መድኃኒት ተጠቃሚዎችና 1145 የቲቢ ታካሚዎች እንደነበሩ ገልጸዋል።

ከምግብና መድኃኒት እጥረቱ ባሻገር የሥነ ልቦና ጫናው ቀላል እንዳልነበረም ኑሩሁሴን ይናገራል።

"ሰው ይገደላል፤ ሌሊት በሰቀቀን አድረን ጠዋት ሲነጋ ደግሞ 'ማን ተገድሎ ይሆን?' የሚለው ጭንቀት ከባድ ነበር " ይላል።

በሹፌርነት ሙያ የሚተዳደረው እሸቱም እንጀራ ቆርሰው እየተካፈሉ ቀኑን እንደገፉት ይናገራል።

"እኔን ጨምሮ አብዛኛው ነዋሪ ከሁለት ወር በላይ አስቤዛ አይዝም" የሚለው እሸቱ የህወሓት ኃይሎች ከቆቦም ሆነ ከደሴ የሚገቡ ሸቀጦች እንዳይገቡ ይከለክሉ ስለነበር ጊዜው ፈታኝ ነበር ይላል።

የምግብና ሸቀጦች ዋጋ

ነዋሪዎቹ የምግብና ሸቀጦች ዋጋ እጅግ ንሮ እንደነበር ይናገራሉ። እርሱም ከተገኘ ነው።

ለወትሮው በየሱቁ በርካሽ የሚገኘውና 15 እና 20 ብር ሲሸጥ የነበረው የምግብ ጨው 150 ብር ተሸጧል። ኩንታሉ ጨው ታይቶም ተሰምቶም በማይታወቅ ሁኔታ 6500 ብር ገብቶ ነበር ይላሉ ነዋሪዎቹ።

"ጨው ከመጥፋቱ የተነሳ አሞሌ ጨው እየከሰከስን ነበር ምግብ ላይ ስንጠቀም የነበረው" ይላል እሸቱ።

ዘይት አንድ ሊትር 350 ብር የገባ ሲሆን ለአመል ያህል ጠብ ማድረጉም ቀርቶ ቅንጦት ሆኖ ነበር።

ሽሮ አንድ ኪሎ 150 ብር ተሸጧል። "በርበሬ ግን አሁንም ድረስ የውሃ ሽታ እንደሆነ ነው" ብለዋል ነዋሪዎቹ።

ጤፍ በኩንታል ከ7 ሺህ ብር በላይ ነበር የሚሸጠው።

በእርግጥ ፈታኙ ነገር የምግብ ፍጆታ ዋጋ መጨመር ብቻ አልነበረም። እንዴት ይፈጫል? በምን ይበሰላል? የሚለውም ነው።

መብራት ስለሌለ እንደምንም ተብሎ የተገዛውን አስፈጭቶ ለምግብነት ማዘጋጀት ቀላል አልነበረም።

አብዛኛው ሰው በድንጋይ ወፍጮ [በእጅ ወፍጮ] ነበር እህል የሚፈጨው። በኋላ ላይ ግን ብፁዕ አቡነ ኤርሚያስ የህወሓት ኃይሎችን ለምነው የባንክ ቤቶች የነበሩ ጀኔሬተሮች ለወፍጮ ቤት ተሰጡ።

ቢሆንም ግን አንድ ጀሪካን ናፍጣ 7 ሺህ ብር ገብቶ ስለነበር የእህል ማስፈጫ ዋጋው የሚቀመስ አልነበረም።

አንድ ኪሎ ለማስፈጨት የሚጠየቀው 100 ብር ነው።

ያኔ ባንኮችም ዝግ ስለነበሩ እንኳንስ 100 ብር 10 ብርም ማግኘት ብርቅ ነበር። በዚህም ምክንያት አብዛኛው ሰው የዕለት ምግቡን የሚያገኘው በእጁ እየፈጨ ነበር።

ተፈጭቶስ በምን ይቦካል? የከተማዋ የውሃ አገልግሎት ተቋርጧል።

እሸቱ እንደሚለው የመጀመሪያው ወር የክረምት ወቅት በመሆኑ በየቦታው ምንጭ ነበር። የዝናብ ውሃም እያጠራቀሙ ነበር የሚጠቀሙት።

ክረምቱ አልፎ መስከረም ሲጠባ ግን በየቦታው የፈለቁት ምንጮች መድረቅ ጀመሩ።

ያኔ ውሃ ፍለጋ ኪሎ ሜትሮችን ማቆራረጥ ግድ ሆነ። "ከከተማው 5 ኪሎሜትር ያህል ገደማ ተጉዘን ጥቁር ውሃ ከሚባለው ወንዝ ነበር ውሃ የምንቀዳው" ይላል እሸቱ።

አካባቢው የጦርነት ቀጠና በመሆኑም ለማገዶ የሚሆን እንጨትና ከሰልም እንዲህ በቀላሉ የሚገኝ አልነበረም።

"ኩርታ እና የሀራ ተራሮች"

የወልዲያ ነዋሪዎች አራቱን ወራት ያለፉት ሰው ከሰው ጋር ብቻ ሳይሆን ከወንዝ፣ ከምንጩ፣ ከተራራውና ከጋራው ጋርም በመተባበር ነበር።

ኩርታ እና የሀራ ተራሮች የወልዲያ ነዋሪዎች መርዶም ሆነ ብስራትን የሚሰሙባቸው ማማዎች ናቸው።

ከከተማዋ ውጭ በጭንቀት እየተናጡ ላሉ የቤተሰብ አባላቶቻቸው ዳገቱን ወጥተው በስልክ 'በሕይወት አለን' ይሉባቸዋል።

እፎይታው ቀላል አይደለም። ግን ይህ እድል የሚገኘው ስንት ውጣ ውረድ ታልፎ ነው። አንድ ጊዜ "ሃሎ!" ለማስባል ቢያንስ 500 ብር ያስፈልጋል።

ገንዘቡ ቢገኝ እንኳ ወደ ተራራዎቹ በሰላም ደርሶ መመለስም ቀላል አይደለም። ስልካቸውና ገንዘባቸው ከአማጺያኑ ንጥቂያ የሚተርፍላቸው በለስ የቀናቸው ብቻ ናቸው።

"ለማን መረጃ እየሰጣችሁ ነው? ለመከላከያ ምን እያላችሁ ነው?" በሚልም መንገላታት ይደርስባቸው እንደነበር ነዋሪዎቹ ይናገራሉ።

"ብዙ ጊዜ እናቶችንና በእድሜ የገፉ ሰዎችን አይነኩም ስለሚባል እነርሱ እንደምንም ይሄዳሉ" ይላል እሸቱ።

ይሁን እንጂ ተራራ ለመውጣትም ሆነ ዞር ዞር ብሎ ከሌላ አካባቢ ሾልኮ የገባን ኔትወርክ መፈለግ ጉልበት ስለሚጠይቅ ገንዘብ ያላቸው ባጃጅ ልከው ማስደወልን ይመርጣሉ።

ሾለክ ብለው በባጃጅ በመሄድ ስልክ የሚደውሉ ወጣቶች አሉ።

እዚያ ለመሄድ ቤንዚንም ውድ ስለሆነ ለአንድ ባጃጅ 1500 ብር መክፈል ግድ ይላል።

ይህን መክፈል የሚችሉት ግን ገንዘብ ያላቸው ጥቂት ግለሰቦች ናቸው።

መሄድ የቻሉት "ላልሰሙት አሰሙ" ሲሉ ለቀሪው ቤተሰብ ፣ ወዳጅ ዘመድ እየደወሉ እንዲነግሩ መልዕክት ይሰዳሉ።

ከከተማዋ ውጭ ያለው ቤተሰብ እርስ በርሱ መረጃ ይለዋወጣል "ከተማው ሰላም ነው፣ ቤተሰብ በሕይወት አሉ ብለዋል" ይባባላሉ።

አልፎ አልፎም ከአንዳንድ አካባቢዎች ሾልከው ከሚመጡ ሰዎች በተቀረው የአገሪቷ ክፍል ስላለው ሁኔታም ሆነ ስለቤተሰብ ወሬ ይሰማል።

ሌላኛው የመረጃ ምንጫቸው ደግሞ ራዲዮ ነበር።

የብፁዕ አቡነ ኤርሚያስ ውለታ

ኑሩሁሴን በእምነቱ ሙስሊም ነው። የሰሜን ወሎ አገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ኤርሚያስ የዋሉትን ውለታ ግን መቼም የሚዘነጋው አይደለም።

"የእርሳቸው መኖር ለወልዲያ ወጣትና ለነዋሪው ህይወት ሆኗል" ይላል።

አቡነ ኤርሚያስ በዚያ የመከራና እና ጭንቅ ሰዓት ነዋሪዎች እርስ በርስ ተባብረውና ተጋግዘው እንዲኖሩ በየመስጊዱና ቤተክርሰቲያኑ እህል እየተዋጣ ነዋሪዎች ተካፍለው እንዲመገቡ ሲያደርጉ ነው የቆዩት።

"በእርሳቸው አቅምና በእርሳቸው ኃይል ነው እዚህ የደረስነው። የእርሳቸውን እድሜ ያርዝምልን፣ ያቆይልን ነው የምንለው" ይላል ኑሩሁሴን።

ከተማዋ በአማጺያኑ እጅ ከገባች በኋላ አቡነ ኤርሚያስ የእስልምና መሪዎችና የአገር ሽማግሌዎች ያሉበት የሰላም ኮሚቴ እንዳቋቋሙ ነዋሪዎቹ ይናገራሉ።

አቡነ ኤርሚያስ ያቋቋሙት ኮሚቴ በመስጊዶችና በሁሉም አድባራት ሰዎችን በመሰየም፣ ውስጥ ለውስጥ ባለሃብቶችን በመቀስቀስ ገንዘብ ያለው ገንዘብ፣ እህል ያለው እህል እንዲለግስ ተደርጎ ለሌላቸውና በከፋ ችግር ላሉ ሰዎች እርዳታ ያከፋፍል ነበር።

አቡነ ኤርሚያስ መጀመሪያ ላይ ነዋሪው በቤቱ ካለው እህል እየቀነሰ ወደ ቤተክርስቲያን እንዲወስድ በማድረግ ለከፋ ችግር ለተዳረጉት ማካፈል ጀመሩ።

ቀኑ እየጨመረ ሲሄድ ግን ይህም በቂ አልሆነም።

በከተማዋ ያሉ ባለሃብቶችን እየቀሰቀሱ እጃቸው ላይ ያለውን ገንዘብ በብድርም ሆነ በልግስና እንዲሰጡ በማድረግ በሚሊየን የሚቆጠር ብር በመሰብሰብ ለባሰባቸው አከፋፈሉ።

"ውስጥ ለውስጥ ባለሃብቶችን ቀስቅሰው ካሰባሰቡት ገንዘብም ለተቸገረ ሁለት ሺህ ብር ለመስጠት ታስቦ የነበረ ቢሆንም፤ በርካታ ሰው በመምጣቱ እኔን ጨምሮ አንድ አንድ ሺህ ብር እንዲደርሰን አድርገዋል" ይላል እሸቱ።

በዚህም ሁሉንም ሕዝብ ማዳረስ አልተቻለምና አቡነ ኤርሚያስ ሌላ መላ ዘየዱ።

በወቅቱ አካባቢው ያለው የአርሶ አደር እህል በመድረሱ በየአካባቢው ሰው እየላኩ አርሶ አደሩ ካለው እንዲያካፍል አደረጉ። አርሶ አደሩም ሳይሰስት ያለውን እየቋጠረ መስጠት ጀመረ። ቀኑም እንዲህ ተገፋ።

እሸቱ እንደሚለው የብሔርም ሆነ የእምነት ልዩነት ሳይኖር ሁሉም ችግርን የሚጋፈጠው በአንድ ላይ ነበር። ይህም ሕዝቡን ይበልጥ አቀራርቦታል።

ይህ ብቻም አይደለም ታጣቂዎቹ የግለሰቦችን ቤት ሲዘርፉ አቡነ ኤርሚያስ "'እባካችሁ!' እያሉ እየተማጸኑ ያስጥሉ ነበር" ይላል ነዋሪው።

ነዋሪዎቹ እንደሚሉት አማጺያኑ እርሳቸውን ከነኩ ሕዝቡም ወደ ሌላ ነገር ይገባል ብለው ስለሰጉ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን አቡነ ኤርሚያስን ይሰሟቸው ነበር።

በእርግጥ የአቡነ ኤርሚያስ መንቀሳቀሻ መኪና እና የቤተ ክህነቱ ሌላ መኪና በአማጺያኑ ተወስደዋል።

የቤተ ክህነት ተማሪዎችን ጨምሮም ሌሎች ሰላማዊ ሰዎችም ተገድለዋል።

በዚህ ሁሉ ውስጥ ግን አቡነ ኤርሚያስ ለነፍሳቸው ሳይሳሱ የተቸገረውን እየለዩ ጦማቸውን እንዳያድሩ ሲደክሙ ነው የቆዩት።

አቡነ ኤርሚያስ በአንድ ቃለ ምልልስ ላይ ለምን ከተማዋን ለቀው እንዳልወጡ ሲጠየቁ "እኔ እረኛ ነኝ። በጎቼን ትቼ የት እሄዳለሁ?!" ሲሉ ነበር የመለሱት።

እሸቱ እንደሚለው ከተማዋ ውስጥ የቀሩ ሐኪሞችን አስተባብረው 'ለነፍሳችሁ ስትሉ መስራት አለባችሁ' በማለት ባለው ነገር ሕክምና ሲያሰጡ የነበሩትም አቡነ ኤርሚያስ ናቸው።

"ሐኪሞቹ የተጎዱ ሲቪሎችን ሲያክሙ ነበር። ቀዶ ሕክምና ማድረግ ባይችሉም ቀላል የማዋላድ፣ ቁስልን የማከም አገልግሎት ይሰጡ ነበር" ብሏል እሸቱ።

ለዚህ ሲስተር ተስፋነሽ በሪሁንም ምስክር ናቸው።

ሲስተር ተስፋነሽ "የእርሳቸው እኮ መለኪያ የለውም! እርሳቸው ባይኖሩ ወልዲያ ወድማለች፤ ፈርሳለች። የእርሳቸው መኖር ከብዙ መቅሰፍት ጠብቆናል። እርሳቸው ባይኖሩ የተረፈውን ሕዝብ ይዘን መቆየት አንችልም ነበር" ይላሉ።

ሲስተር ተስፋነሽ ስለአቡነ ኤርሚያስ ይህን ይበሉ እንጅ እርሳቸውም በመከራ ቀን ከሕዝብ ጎን የቆሙ ሴት ናቸው።

ሲስተር ተስፋነሽ በሪሁን

የፎቶው ባለመብት, Tesfanesh Berihun FB

ለብዙዎች ተስፋ የሆኑት ሲስተር ተስፋነሽ

ሲስተር ተስፋነሽ የሦስት ልጆች እናት ናቸው። በርካታ የዘመድ አዝማድ ልጆችን፣ በቅርባቸው ድጋፍ የሚሹ በርካታ ሰዎችን አስተምረው ለወግ ማዕረግ አብቅተዋል።

ሲስተር ተስፋነሽ በሕክምና ሙያ የመጀመሪያ ድግሪ አላቸው። የሚሰሩት በራሳቸው የግል ክሊኒክ ነው።

ከተማዋ በአማጺያኑ እጅ የገባችው እርሳቸው የኩላሊት ሕክምና አድርገው [አንድ ኩላሊታቸውን በቀዶ ሕክምና አስወጥተው] ለክትትል ቀጠሮ አስይዘው ወልዲያ ከገቡ ብዙም ሳይቆይ ነበር።

ምንም እንኳን ከተማዋን ለቀው ለመውጣት የሚችሉበት አጋጣሚ ቢኖርም እርሳቸው ግን ከቤታቸውና ከሙያቸው ንቅንቅ ማለት አልፈለጉም።

ከ30 ዓመታት በላይ በሕክምና ሙያ ያገለገሉት ሲስተር ተስፋነሽ "የዛሬ 30 ዓመትም ህወሓቶች ወልዲያ ሲገቡ እዚያው ሙያዬ ላይ ነበርኩ። በርካታ ሴቶችና እናቶች ሲጎዱ አይቻለሁ። ውስጤ እንደተጎዳ ነበር ያሳለፍኩት። አሁን ይህ እንዲሆን አልፈለኩም። ዛሬም እዚሁ ቤቴ ላይ ሲያገኙኝ እናቶችን በእኔ እጅ ልረዳ እንደምችል አሰብኩ" በማለት እዚያው ሆነው የቻሉትን እያደረጉ ለመቆየት መወሰናቸውን ይናገራሉ።

ለ12ኛ ክፍል ተማሪ ልጃቸው ስጋት ቢያድርባቸውም የሚያደርጉት ነገር አልነበራቸውም።

"አንድ የማይታይ ቤት ውስጥ ዘግቼ አስቀምጫት ነው ሥራ ስሰራ የነበረው" ብለዋል። ልጆቻቸው የሚሰሩባቸው የንግድ ተቋማትም ወድመውባቸዋል፣ ተዘርፈውባቸዋል።

በዚህ ሁኔታ ግን በድብቅም ቢሆን የተጎዱ እናቶችን ሲያክሙ፣ ሲያዋልዱ፣ የሞቱትን ሲያዘጋጁ ቆይተዋል።

የጤና ተቋማትን ጨምሮ በርካታ የግልና የመንግሥት ተቋማት መዘረፋቸውን የሚናገሩት ሲስተር ተስፋነሽ፤ ቀድመው የተወሰኑ የሕክምና እቃዎችን በመደበቃቸው የተወሰኑ ሰዎችን ማከም እንደቻሉ ይናገራሉ።

አንድ የላብራቶሪ ባለሙያ እና ሦስት ነርሶች እንደነበሯቸውና ሲፈልጉ ከቤት እየጠሯቸው በጋራ ለእናቶችና ሕጻናት ሕክምና ሰጥተዋል።

"ሌሊት ጀኔሬተር ማስነሳት አንችልም። ቀን ላይ ብቻ ነበር የምንሰራው፤ የሕክምና ገዋንም አንለብስም ነበር" የሚሉት ሲስተር ተስፋነሽ እስካለፈው ሳምንት ድረስ 90 እናቶችን እንዳዋለዱ ይናግራሉ።

ይሁን እንጂ የቀዶ ሕክምና አገልግሎት መስጠት ስለማይችሉ "አራት ጨቅላ ህጻናት ታፍነው ለሞት ተዳርገዋል" ብለዋል።

ቃሊም ከሚባል የገጠር አካባቢም ከወለደች ከሳምንት በኋላ ለሕክምና ወደ እርሳቸው የመጣች እናትም ሕይወቷ ማለፉን በሐዘን ያስታውሳሉ።

"ይህችን እናት በወሬ ወሬ ሰምተው እኔ ጋር ያመጧት በወለደች በሳምንቱ ነው። ልጇ እዚያው እንደተወለደ ሕይወቱ አልፏል። ሳያውቁት እንግዴ ልጁ ሆዷ ውስጥ ቀርቶ ነበርና እኔ ጋ ካመጧት ከአንድ ሰዓት በኋላ ነው ያረፈችው" ብለዋል ሲስተር ተስፋነሽ።

ይሄ ሁሉ ሆኖም በፈታኝ ጊዜ ውስጥ የበርካታ እናቶችን ሕይወት መታደግ በመቻላቸው ደስተኛ ናቸው።

"እኔም ቆሜ ስሰራ ሰውነቴ ያብጣል፤ ግን እናቶች ልጆቻቸውን በሰላም ተገላግለው አቅፈው ሲሄዱ ደስ ይለኝ ነበር" ይላሉ።

ወልዲያ አሁን ላይ

ባለፈው ሳምንት ከአራት ወራት የመንግሥት ኃይሎች ወደ ከተማ ሲገቡ ሕዝቡ ወደ አውራ ጎዳናዎች በመውጣት አቀባበል ሲያደርግላቸው ታይቷል።

የከተማዋ ነዋሪ ኑሩሁሴን ነጻነት የሚባለውን ነገር ቦታ እንድሰጠው ያደረገኝ ይህ አጋጣሚ ነው ይላል።

"በቃ ወጥተን እንሳሳቃለን፤ በነጻነት እንወጣለን እንገባለን።" በማለት በወቅቱ የነበረውን ስሜት ያስታውሳል።

እሸቱም በበኩሉ ከተማዋ ወደ ወትሮው እንቅስቃሴዋ ለመግባት ዱብ ዱብ እያለች እንደሆነ ታዝቧል።

በእርግጥ ነዋሪዎቹን እስካነጋገርናቸው ታኅሣሥ 15/2014 ዓ.ም ድረስ የመብራትና የውሃ አገልግሎት አልተጀመረም።

አሁንም ወደ ከተማዋ የገባ ዓለም አቀፍ የእርዳታ ድርጅት አለመኖሩን ነዋሪዎቹ ተናግረዋል።

"ሰው አሁንም ችግር ላይ ነው። ባንክ ቤቶች ተዘርፈዋል፤ እነርሱን ለማደራጀትም ብዙ ሥራ የሚጠይቅ ነው። ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የምጣድ ክዳን ሳይቀር ነው የተዘረፈው። አብረን ብዙ ባሳለፍነው ወንድሞቻችን ይህን መደረጉ ያሳዝናል" ሲልም ኅብረተሰቡ ከዚህ ስሜት አለመውጣቱን እሸቱ ይናገራል።

በወልዲያ ከተማ የወልዲያ ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ በጤና ተቋማት፣ ባንኮች፣ ትምህርት ቤቶች፣ የንግድ ተቋማትና መሠረተ ልማቶች ላይ ከፍተኛ ዘረፋ እና ውድመት እንደተፈፀመ ተዘግቧል።

ከተማዋ ውስጥ ብዙ መርዶ እየተሰማ መሆኑን የሚናገረው እሸቱ፤ ተፈናቅለው ይሁን ሞተው የት እንዳሉ ያልታወቁ ብዙ ሰዎች መኖራቸውን ገልጿል።

"ይመጡ እንደሁ ተብለው እየተጠበቁ ነው። በየቤቱ የጎደለው ሰው ገና እየተጣራ ነው" ሲልም አክሏል።

ሲስተር ተስፋነሽ በበኩላቸው እስካሁን የመንግሥትም ሆነ የግል የጤና ተቋማት እምብዛም ሥራ አለመጀመራቸውን ገልጸው እርሳቸው ግን ሥራቸውን በነጻነት መቀጠላቸውን ገልጸዋል።

"በዚያ በጭንቅ ሰዓት ያዋለድኳቸው እናቶችም ልጆቻቸውን ይዘው እየመጡ እያሳዩኝ ነው። ብዙ ቤተሰብ አፍርቻለሁ" ብለዋል።

በእናታቸው ማህጸን ሆነው ይህችን ዓለም በሰላም ይቀላለቀሉ ይሆን ተብሎ በጭንቅ ሲጠበቁ የነበሩትአሁን የሦስትና የአራት ወር ህጻናት ሆነዋል።