ታዋቂዋ ዘፋኝ ዱዋ ሊፓ ያለ ፈቃዷ ምስሏን በተጠቀመው ሳምሰንግን ላይ የ15 ሚሊዮን ዶላር ክስ መሰረተች

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ታዋቂዋ ፖፕ ሙዚቃ አቀንቃኝ ዱዋ ሊፓ፤ ሳምሰንግ ኩባንያ ፈቃድ ሳያገኝ ምስሏን በቴሌቪዥን ማሸጊያ ካርቶኖች ላይ መጠቀሙን በመግለጽ የ15 ሚሊዮን ዶላር ክስ መሠረተች።
አርብ ዕለት በካሊፎርኒያ በሚገኘው የአሜሪካ ዲስትሪክት ፍርድ ቤት የቀረበው የክስ ሰነድ እንደሚያሳየው፤ ሳምሰንግ በመላው አሜሪካ በሚሸጡ የተለያዩ የቴሌቪዥን ሞዴሎች ላይ የሊፓን ፊት ያለፈቃዷ በጉልህ በሚታይ ደረጃ ተጠቅሟል የሚል ውንጀላ ቀርቦበታል።
የክስ ሰነዱ፤ የሳምሰንግ ማሸጊያ "ሊፓ በከፍተኛ ጥረት ያገኘችውን ስኬት የሳምሰንግ ምርቶችን ለማስተዋወቅ እና ለመሸጥ ሲባል ያለ አግባብ የተዘጋጀነ ነው" ይላል።
ቢቢሲ ስለ ክሱ የሳምሰንግን አስተያየት ጠይቋል።

የፎቶው ባለመብት, US District Court for the Central District of California
በተጨማሪም ክሱ የቅጂ መብት እና የንግድ ምልክት ጥሰቶች እንዲሁም የዱዋ ሊፓ ገጽታ እና ምስልን አላግባብ መጠቀም የሚሉ ውንጀላዎችን አካትቷል።
የክስ መዝገቡ እንደሚያስረዳው በሳምሰንግ ማሸጊያዎች ላይ የሚታየው ምስል የተነሳው ዱዋ ሊፓ በ2024 ኦስቲን ከተማ ውስጥ በተዘጋጀ ፌስቲቫል ላይ ስራዋን ባቀረበችበት ወቅት ነው። የምስሉ የቅጂ መብት የአርቲስቷ እንደሆነም ተጠቅሷል።
ሊፓ ፎቶዋ በሳምሰንግ ማሸጊያዎች ላይ እንደሚታይ ያወቀችው ባለፈው ዓመት ሰኔ ላይ ነው ተብሏል። አድናቂዎቿ "የዱዋ ሊፓ የቲቪ ካርቶን" ከሚል ጽሑፍ ጋር ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ መለጠፍ ጀምረው ነበር።
የክስ ሰነዱ ኢንስታግራም ላይ የተሰጡ ሁለት አስተያየቶችን (ኮሜንት) በማሳያነት ጠቅሷል። አንደኛው አስተያየት "ዱዋ ስላለችበት ብቻ ቲቪውን ግዙ" ይላል። ሁለተኛው ደግሞ "ምንም ነገር እንዲሸጥላችሁ ከፈለጋችሁ የዱዋ ሊፓን ምስል ብቻ አስቀምጡበት" የሚል ነው።
የ30 ዓመቷን ድምጻዊ የወከለው የጠበቆች ቡድን እንደሚገልጸው፤ ሳምሰንግ "መብቷን ከመጣስ እንዲቆጠብ በተደጋጋሚ የቀረበለትን ጥያቄ" ችላ ብሏል።
አቀንቃኟ እንደ ፑማ ፣ ቨርሳቺ እና ኢቭ ሳን ሎረን ካሉ ኩባንያዎች ጋር የንግድ አጋርነት ስምምነት እንዳላት ክሱ ላይ ተጠቅሷል።
በተጨማሪም ከአፕል ፣ ፖርሽ እና ሽኔል ጋር በትብብር እየሰራች ያለችው ዱዋ ሊፓ፤ በቅርቡም የነስፕሬሶ ዓለም አቀፍ አምባሳደር ሆናለች።
ሊፓ 'ራዲካል ኦፕቲሚዝም' የተሰኘው የመጨረሻ አልበሟ የተለቀቀው 2024 ላይ ነበር።













