አሜሪካዊቷ ድምጻዊት ቴይለር ስዊፍት በተለያዩ ሥራዎቿ ዘዬዋን የምትቀያይረው ለምንድን ነው?

የፎቶው ባለመብት, PA Media
"የድሮ ዘፈኖቿ ከአሁን ሙዚቃዋ የተለየ ነው"።
ይህን "ስዊፍቲ" በሚል የወል ስማቸው የሚታወቁት የቴይለር ስዊፍት አድናቂዎች የሚመሰክሩት ነው።
ቴይለር በቅርቡ በመላው ዓለም የሙዚቃ ድግሶቿን በ'ዘመናት' ከፋፍላ ስታቀርብ ሥራዎቿ ባለፉት ዓመታት ውስጥ የተሻሻሉ ይመስላል።
ይሁን እንጂ በቅርብ የተደረገ ምርምር የድምፃዊቷ ድምፅ መቀየሩን አረጋግጧል።
በአሜሪካ የሚኒሶታ ዩኒቨርስቲ ተመራማሪዎች የድምፃዊቷን የሙዚቃ ሕይወት በሦስት "ዘመናት" ከፍለው ቴይለር ያደረገቻቸውን የ100 ደቂቃ ቃለ ምልልሶች መርምረዋል።
ናሽቪል ከተማ እያለች እ.አ.አ በ2008 የለቀቀችው 'ፊርለስ'፣ በ2012 ወደ ፖፕ ሙዚቃ መሸጋገሪያ የሆናት 'ሬድ' እና በ2019 ኒውዮርክ ከተማ ኑሮዋን አድርጋ ለጆሮ ያደረሰችው 'ላቨር' አልበም በዘመናት ከፋፍለው ተመልክተዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በአሜሪካ አኩስቲካል የምርምር መፅሔት የታተመው ጥናቱ ቴይሌር ስዊፍት በሙዚቃ ጉዞዋ ድምጿ እና ዘዬዋ መለወጡን አረጋግጧል።
በብሪታኒያ የሚገኘው ቸስተር ዩኒቨርስቲ የእንግሊዘኛ ቋንቋ መምህርት የሆኑት ዶ/ር ሄለን ዌስት ራሳቸውን 'ስዊፍቲ' ብለው የሚጠሩ የድምፃዊቷ አድናቂ ናቸው። በዚህ ጥናት ባይሳተፉም የቴይለር ዘዬ እንዴት እንደተለወጠ የሚያሳይ ተመሳሳይ ጥናት አድርገዋል።
እንደዚህ ዓይነት ጥናት ተመራማሪዎች ውስብስብ የሆነውን የሰው ልጅ ለማጥናት ይረዳል ይላሉ።
ለምሳሌ የሰው ልጅ በከባቢው ከሚነገሩ ድምፅች ውስጥ የትኛውን መስማት ይችላል ወይም በአንዳንድ የማኅበራዊ ሁነቶች ላይ አንዳንድ ሰዎች ከሌሎች ሰዎች በተለየ ለምን ዘያቸውን ይቀይራሉ የሚለውን ለመመለስ ያግዛል።
የዘዬ ለውጥ
የጥናቱ ግኝት እንደሚያሳው ቴይለር ስዊፍት በአሜሪካ እየተዟዟረች ሙዚቃዋን ስታዳብር አንዳንድ አናባቢዎችን የምትጠራበት መንገድ ተቀይሯል።
የሙዚቃ ሕይወት ጅማሬዋ ላይ 'አይ'ን ስትጠራ አጭር ነበር። 'ራይድ' ለማለት 'ሮድ' ብሎ እንደመጥራት ቅልብጭ ያለ አጠራርን ትጠቀም ነበር። ተመራማሪዎች ይህም የደቡባዊ አሜሪካዊያን ዘዬ ነው ይላሉ።
ሌላም የተቀየረው 'ኦው' የሚለው ቃል አጠቀቃሟ ነው።
በደቡባዊ አሜሪካ ክፍል በአብዛኛው አናባቢዎች ከጉሮሮ ከመውጣት ይልቅ ከምላስ ወይም በከንፈር የሚወጡ ናቸው።
ተመራማሪዎች ቴይለር ናሽቪል እያለች 'ኦው' የሚል ድምጿ ከሌላው የሙዚቃ ዘመኗ ጋር ሲነፃፀር በሦስት እጥፍ ከከንፈር ጫፍ የወጣ ነው ብለዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የድምፅ ለውጥ
ተመራማሪዎች ባለፉት ዓመታት የቴይለር ስዊፍት ድምፅም መቀየሩን በምርምራቸው አግኝተዋል።
ጥናት በተደረገባቸው በሁለቱ የሙዚቃ ዘመኖቿ ድምጿ ተመሳሳይ የነበረ፤ ኒው ዮርክ ከተማ መኖር ስትጀምር ግን ድምጿ ወረድ ብሏል።
ይህ ለውጥ በእድሜዋ ምክንያት ሊሆን ይችላል።ጥናት የተደረገበት የመጀመሪያው የሙዚቃ ዘመኗ 19 ዓመት ሲሆን የመጨረሻው ደግሞ 30 ዓመቷ ላይ ነው።
ነገር ግን ተመራማሪዎች ይህ ለውጥ የፆታ አድልዎ እና የሙዚቀኞች መብት በመሰሉ ማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ ተከራካሪ ከመሆኗ ጋር ሊያያዝ ይችላል ብለዋል። በሙዚቃዎቿም እነዚህን ጉዳዮች ዳሳለች።
ተመራማሪዎች የድምፅ ለውጡ "በራስ በመተማመን ለመናገር እና ብቃቷን ለማሳየት" ሆን ብላ ያደረገችው ሊሆን እንደሚችል ጠቁመዋል። ዶ/ር ዌስትም ይህ የመሆኑ እድሉ ተጨባጭ ነው ይላሉ።
ዘዬዎች ለምን ይለወጣሉ?
ተመራማሪዎች እንደሚሉት ዘዬ ሊቀየርባቸው የሚችሉባቸው በርካታ ምክንያቶች አሉ። ከማኅበረሰብ ጋር ለመቀላቀል ሲባል የሚደረግ ለውጥ አንዱ ሲሆን፤ ይህንም ቴይለር ከፊላደልፊያ ወደ ኒው ዮርክ ስትዘዋወር አድርጋው ሊሆን ይችላል።
ጥናቱ ለውጡን በከፊል ቴይሌር ከምትፅፋቸው የሙዚቃዎች ዓይነት ጋር አገናኝቶታል።ተመራማሪዎች የደቡባዊ ዘዬዋ በወቅቱ የአገረ ሰብ ሙዚቃ አቀንቃኝ እያለች ትልቅ አስተዋፅኦ ተጫውቷል ብለዋል።
ተመራማሪዎች ከዚህ ቀደም የተደረገ አንድ ጥናት የጠቆመውን ቁልፍ ክፍል ያነሱ ሲሆን፤ ይህም "የዘውግ ትክክለኛነት" ነው። ሀሳቡ አቀንቃኞች ራሳቸውን ሳይሆኑ እንደ ገፀ ባህሪ ሚና ተጨዋች ከመሆን ይልቅ በግልፅ ማንነታቸውን ማንፀባረቅ የሚል ነው።
ጥናቱ ቴይለር ስዊፍት አሁንም ድረስ የደቡባዊ ዘዬዋን በንግግሮቿ ወቅት እንደምትጠቀመው ገልጿል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ዶ/ር ዌስት ቴይለር ስዊፍት የአገረ ሰብ ትዕይንቱ ውስጥ እንዳለች እንደምታስተውል እና ትክክለኛ ማንነቷን ለማንፀባረቅ የምታሳየውን አቋም ይገልፃሉ።
"ይህንም ለማድረግ እያቀነቀነች ካልሆነ፤ በንግግሮቿ ተመሳሳይ መልዕክት ታስተላልፋለች። 'የዚህ አካል ነኝ፤ እዚህ ዘውግ ላይ አለሁ' ለማለት"።
ዶ/ር ዌስት ቴይለር በአብዛኛው ሰዎች ሳይታወቃቸው የሚሰሟቸውን ድምፆች እየሰማች እንደሆነ ማስረጃ አለ ይላሉ። ይህም ማለት በአካባቢዋ በምትሰማቸው ድምፆች ምክንያት ሳይታወቃት ድምጿን እየቀየረች ሊሆን ይችላል።
ታይሌር ስዊፍትን ማጥናት ለምን?
ዶ/ር ሄለን ዌስት፣ ቴይለር ስዊፍት ባለፉት ዓመታት ድምጿ ተመዝግቦ ከመገኘቱ ባሻገር እንቅስቃሴዋ የምርምር ማዕከል ለመሆን አስደናቂ ናት ይላሉ።
ተመራማሪዎች እንደ ቴይለር ስዊፍት ዓይነት ሰዎችን ማጥናታቸው የሰው ልጅ እርስ በእርስ ያለውን መስተጋብር ለመረዳት ያግዛል ይላሉ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
"[ቴይለር] ልንረዳቸው በምንሞክራቸው በማኅበረሳዊ፣ እውቀት እና ስነ-ልቦናዊ ፅንሰ ሀሳቦች ጠቃሚ መነፅር ሆና ታገለግላለች" ሲሉ ይገልፃሉ።
"ሰዎች ለመተሳሰብ እንደሚሞክሩ እናውቃለን፤ የሚያወሩትን ሰው መሰረት አድርገው ድምፃቸውን እንደሚቀይሩ እናውቃለን። ነገር ግን ሰዎች በተለያየ መጠን ነው የሚያደርጉት"።
ዶ/ር ዌስት የሰው ልጅ ምን ያህል ውስብስብ ፍጡር እንደሆነ ለመረዳት በርካታ ጉዳዮችን ማጥናት ይቻላልም ይላሉ።















