ሳዑዲ አረቢያ ለሃብታም የውጭ አገር ዜጎች የአልኮል መጠጥ እገዳን አነሳች

የአልኮል መጠጥ ዬኣዙ ብርጭቆዎችን የሚያጋጩ እጆች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

ሳዑዲ አረቢያ ከ73 ዓመታት እገዳ በኋላ በአገሪቷ የሚኖሩ ቱጃር የውጭ አገር ዜጎች የአልኮል መጠጥ እንዲገዙ መፍቀድ ጀመረች።

ይህም ትልቅ እርምጃ እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን አስተያየት ሰጪዎች አገሪቷ አሁን ላይ ያላላችውን ሕግ ወደ ጎብኝዎች ታሰፋዋለች ብለው እንደሚጠብቁ የቢቢሲው ሰሚር ሃሽሚ ከሪያድ ዘግቧል።

ዲፕሎማሲያዊ መቀመጫ የሆነችው ሪያድ ለአስርተ ዓመታት ያህል የአልኮል መጠጥ ሽያጭን አግዳ ቆይታለች።

በኤምባሲዎች፣ በቅንጦት ዘመናዊ መኖሪያ ቤቶች ፣ ጥላ ባላቸው የእግረኛ መንገዶች፣ አረንጓዴ ቦታዎች እና በካፍቴሪያ ባህሏ የአገሪቷን ወጣቶች እና የውጭ ዜጎችን ቀልብ የምትስበው ከተማዋ፤ አሁን ላይ ይህንን ሕጓን አላልታለች።

በዚህም ሃብታም እና ሙስሊም ያልሆኑ የውጭ አገር ነዋሪዎች የአልኮል መጠጦችን እንዲገዙ መፍቀድ ጀምራለች።

ሁለት የእስልምና ቅዱስ ከተሞች ያሏት ሳዑዲ አረቢያ፣ የአልኮል መጠጥ ሽያጭን ያገደችው እአአ በ1952 ነበር።

ነገር ግን ገጽታዋን ለመገንባት በምታደርገው ጥረት ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ለውጦችን በማድረግ ለኢንቨስትመንት ምቹ መሆኗን እያሳየች ነው።

በልዑል አልጋ ወራሽ መሐመድ ቢን ሰልማን አስተዳደር ሲኒማ ቤቶች እንደገና የተከፈቱ ሲሆን ትላልቅ የሙዚቃ ዝግጅቶችም ተካሂዶባታል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ከዚህም በተጨማሪ አስተዳደሩ ሴቶች መኪና እንዳያሽከረክሩ ተጥሎ የነበረውን እገዳ አንስቷል፤ እንዲሁም ይፈሩ የነበሩት ሃይማኖታዊ ፖሊሶችን ሥልጣንም ገድቧል።

ሕጋዊ የአልኮል መጠጥ ሽያጭ ጉዳይ ግን አከራካሪ ሆኖ ነበር የቆየው።

የአልኮል መጠጦች መደብር መጀመሪያ ላይ የተከፈተው እአአ ጥር 2024 የነበረ ሲሆን፤ መጀመሪያ ላይ ሙስሊም ያልሆኑ ዲፕሎማቶች እንዳይገቡ ገደብ ተጥሎ ነበር።

ከዚያ ግን በ2025 ያለምንም ይፋዊ ማስታወቂያ በተዋወቀ አዲስ ደንብ ሃብታም እና ሙስሊም ያልሆኑ የውጭ አገር ነዋሪዎች ወደ መደብሩ በማምራት ቢራ፣ ዋይን እና ስፕሪት መግዛት እንዲችሉ ተፈቅዷል።

ለዚህም በሪያድ ብዙም ሰዎች በማይደርሱበት ሰፈር ውስጥ የሚገኝ እና ሚስጢራዊ እና ምልክት በሌለው ሕንጻ ውስጥ የሚገኝ አነስተኛ መደብርም ይህ የፖሊሲ ለውጥ የሚፈተሽበት ቦታ ሆኗል።

ወደ መደብሩ ገብተው መጠጦችን መግዛት የሚፈቀድላቸው በዓመት 27 ሺህ ዶላር የሚያስከፍል 'ፕሪሚየር' የመኖሪያ ፈቃድ ያላቸው ወይም በወር 50 ሺህ የሳዑዲ ገንዘብ ሪያል የሚከፈላቸው መሆኑን ማሳየት የሚችሉ ብቻ ናቸው።

ፕሪሚየር የመኖሪያ ፈቃድ ፕሮግራም የተለያዩ መስፈርቶች ያሉት ሲሆን በተለይ ለከፍተኛ የውጭ አገር ኃላፊዎች ፣ ኢንቨስተሮች እና የተለየ ክህሎት ላላቸው ሙያተኞች የሚሰጥ ነው።

በዚህ መሠረት የመኖሪያ ፈቃዱ ያላቸውም ሆነ የሌላቸው አልኮል መጠጥ ለመግዛት መታወቂያቸውን ማሳየት ይጠበቅባቸዋል።መታወቂያው ላይ ሃይማኖታቸው እና የመኖሪያ ሁኔታቸው በዝርዝር የሰፈረበት ነው።

የመኖሪያ ፈቃድ የሌላቸው ደግሞ በመሥሪያ ቤታቸው የተረጋገጠ የደመወዛቸውን መጠን የሚያሳይ ደብዳቤ ማሳየት ይጠበቅባቸዋል። የውጭ ጎብኝዎች ግን ወደ መደብሩ መግባት አይፈቀድላቸውም።

ሪያድ ከተማ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ሳዑዲ አረቢያ ከ73 ዓመታት በኋላ ሃብታም እና ሙስሊም ያልሆኑ የውጭ አገር ነዋሪዎች በሪያድ ከተማ የአልኮል መጠጥ እንዲገዙ የሚፈቅድ አዲስ ሕግ አስተዋውቃለች።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው ስማቸው የማይጠቀስ ደንበኞች ወደ መደብሩ ከመግባታቸው በፊት ስልካቸውን ማስቀመጥ እንደሚጠበቅባቸው እና ከአንድ ሰዓት በላይ ተሰልፈው እንደተጠባበቁ ተናግረዋል። ወደ ውስጥ ከገቡ በኋላ ግን አገልግሎቱ ቀጥተኛ እንደሆነ እኝሁ ተጠቃሚዎች ገልጸዋል።

አንድ አውሮፓዊ ነዋሪ መደብሩ ሙሉ እንደነበር፤ ዋጋው ግን ከምዕራባውያን አገር ገበያ በሁለት በሦስት እጥፍ እንደሚልቅ ሆኖም ከሳዑዲ አረቢያ ጥቁር ገበያ የተሻለ ዋጋ እንዳላቸው ተናግሯል።

መደብሩ ወርሃዊ የኮታ ሥርዓት አለው። ተጠቃሚዎች እንዳሉት አንድ ሰው በወር ውስጥ አንድ ደርዘን ስፕሪትስ መግዛት ይፈቀድለታል። ዲፕሎማቶች ደግሞ የዋጋ ቅናሽ ይደረግላቸዋል።

በዚህ ላይ ከመንግሥት የተሰጠ ይፋዊ ማስታወቂያም ሆነ ማብራሪያ የለም።

በርካታ ሸማቾች መጀመሪያ ላይ የፖሊሲ ለውጡን የሰሙት በወሬ እንደሆነ ተናግረዋል። የመደብሩ ስምም በበይነ መረብ ካርታዎች ላይ አይታይም።

" አንድ ጓደኛዬ ነው በጉግል ማፕ አድራሻውን ያጋራኝ " ብሏል አንድ እስያዊ ነዋሪ።

ተንታኞች እንደሚሉት በአዲሱ የአልኮል ፖሊሲ ለውጥ ላይ ባለሥልጣናት የፈጠሩት ውዥንበር፣ እርምጃው ምን ያህል እንደሚያስኬድ ለማየት ሆነ ተብሎ የተደረገ እንደሆነ ይናገራሉ።

በጀርመን የቲንክ ታንክ ተቋም ካርፖ የመካከለኛው ምሥራቅ ከፍተኛ ተመራማሪ የሆኑት ሰባስቲያን ሰን ፣ "ባለሥልጣናት በጥንቃቄ ነው እየተጓዙ ያሉት፤ አንገብጋቢ በሆኑ ጉዳዮች ላይ አስፈላጊ ከሆነ ሁለት እርምጃ ወደፊት አንድ እርምጃ ወደኋላ ለመጓዝ ፈቃደኛ ናቸው። አልኮል መጠጥን በተመለከተም ተመሳሳይ ሊሆን ነው የሚችለው" ብለዋል።

በእስልምና ሕግ አልኮል መጠጥ ክልክል ነው በአብዛኛው የሳዑዲ አረቢያ ነዋሪዎች ዘንድም ይወገዛል።

በዚህ ምክንያት ለአስርት ዓመታት እገዳ ተጥሎ ቢቆይም በቤት ውስጥ ከሚዘጋጁት ጀምሮ ከውጭ እስከሚገቡት ድረስ አልኮል መጠጥ በድብቅ ይዘዋወራል። በመኖሪያ ቦታዎች በሚዘጋጁ ግላዊ በሆኑ ድግሶች ላይም ይቀርባሉ።

መለያ ያላቸው የአልኮል መጠጦችም ለዲፕሎማሲ በተፈቀደ መብት በኤምባሲዎች በኩል ያለ ገደብ የሚገቡ ሲሆን መደበኛ ባልሆኑ ገበያዎች እንደሁም ወደ ጥቁር ገበያ ይገባሉ።

ቁጥጥር የማይደረግባቸው በቤት ውስጥ የሚዘጋጁ መጠጦች እና በሕገ ወጥ የሚገቡ ውድ መጠጦችም መዘዋወራቸውን ቀጥለዋል። በመሆኑም አሁን ላይ ያላላችውን ሕግ ወደ ቱሪስቶች ልታስፋፋው እንደምትችል ይገመታል።

ለባሕረ ሰላጤዋ አገር ቱሪዝም የ2030 ያስቀመጠችው ራዕይ ወሳኝ አካል ነው።

አገሪቷ ወደ 30 ሚሊዮን የሚጠጉ ዓለም አቀፍ ቱሪስቶችን መሳብ የቻለች ሲሆን ከጎብኝዎቿ ግማሽ ያህሉ ሃይማኖታዊ ባልሆኑ ጉዞዎች የገቡ እንደሆኑ የቱሪዝም ሚኒስትር አሕመድ አል ካትብ ተናግረዋል።

በ2030 ደግሞ ይህንን ቁጥር ወደ 70 ሚሊዮን ለማሳደግ እቅድ ይዛለች።

አገሪቷ በ2034 የሚካሄደውን የዓለም የእግር ኳስ ዋንጫን ጨምሮ ሌሎች ትላልቅ ዓለም አቀፍ ሁነቶችን ለማሰናዳትም እየተዘጋጀች ነው።