የምያንማር የቀድሞ መሪ አን ሳን ሱ ኪ ወደ ቤት ውስጥ እስር መዛወራቸውን የአገሪቱ ጦር አስታወቀ

የፎቶው ባለመብት, Myanmar state TV
በመፈንቅለ መንግሥት ከሥልጣን የተወገዱት የምያንማር መሪ አን ሳን ሱ ኪ ከማረሚያ ቤት ወጥተው ቤት ውስጥ የቁም እስረኛ መሆናቸውን የአገሪቱ ብሔራዊ መገናኛ ብዙኃን ዘገቡ።
የ80 ዓመቷ የኖቤል ሎሬት ተሸላሚ እአአ በ2021 በመፈንቅለ መንግሥት ከመሪነት ሥልጣናቸው ከወረዱ ጊዜ ጀምሮ በእስር ላይ ይገኛሉ።
አን ሳን ሱ ኪ እስካሁን ድረስ የቆዩት በዋና ከተማዋ በሚገኝ ናይ ፒ ታው ወታደራዊ እስር ቤት እንደሆነ ይታመናል።
መፈንቅለ መንግሥቱን በመሩት የጦሩ አዛዥ ሚን ኡንግ ህሌይንግ የተሰጠው መግለጫ "ቀሪውን የእስር ጊዜያቸውን በተዘጋጀላቸው የመኖሪያ ቤት እንዲጨርሱ" መወሰኑን ይገልጻል።
አን ሳን ሱ ኪ ወደ ሥልጣን የመጡት እአአ በ2015 የወቅቱ የምያንማር መሪ የነበሩት መሪ ዲሞክራሲያዊ ለውጦችን ካስተዋወቁ በኋላ ነበር።።
ከዚያ በፊት ግን ለአስርት ዓመታት በዘለቀው ወታደራዊ አመራር ውስጥ የዲሞክራሲ አቀንቃኝ የነበሩ ሲሆን ከ15 ዓመታት በላይ በቤት ውስጥ እስር ላይ ቆይተዋል።
የአገሪቱ ብሔራዊ መገናኛ ብዙኃን ከሁለት ወታደሮች ጋር ተቀምጠው የሚያሳይ ምስልን አጋርተዋል።
ልጃቸው ኪም አሪስ በሕይወት መኖራቸውን የሚያሳይ ምንም ዓይነት ማስረጃ እንደሌለው በመግለጽ የጦሩን መግለጫ በጥርጣሬ እንደሚመለከተው ተናግሯል።
በአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን የታየው ምስል በ2022 የተወሰደ ይሆናል በማለት "ዋጋ ቢስ ነው" ብሏል።
"እውነት ይሆናል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። ወደ መኖሪያ ቤቷ መወሰዷን የሚያሳይ ተጨባጭ ማስረጃ እስካሁን ድረስ አላየሁም" ሲል ለቢቢሲ ተናግሯል።
"ስለዚህ እንዳነጋግራት እስኪፈቀድ ወይም ሌላ አካል በገለልተኝነት ስላለችበት ሁኔታ እና ስለጤንነቷ እስኪያረጋግጥልኝ ድረስ ምንም ነገር ማመን አልችልም" ብሏል።
ኪም አሪስ በታሕሳስ ወር እንዳለው ከዚህ የጦሩ መግለጫ በፊት ስለ አን ሳን ሱ ኪ ጤንነት ወይም ስለሚኖሩበት ሁኔታ ምንም የሚታወቅ ነገር አልነበረም።
ለዓመታት ስለ እናቱ ምንም ነገር አለመስማቱን የሚናገረው ኪም አሪስ ብቻ ሳይሆን የሕግ ቡድናቸውም ቢሆን ስለ ቤት ውስጥ እስሩ ምንም ዓይነት በቀጥታ የተነገራቸው ነገር እንደሌለ ሮይተርስ ዘግቧል።
ከአምስት ዓመታት በፊት የታጠቁ ኃይሎች በምርጫ ያሸነፈውን መንግሥት አስወግደው አን ሳን ሱ ኪን በቁጥጥር ስር ካዋሉበት ቀን ጀምሮ ስላሉበት ሁኔታ የታየው ጥቂት ሲሆን ምንም የተሰማ ነገር የለም።
ጠበቆቻቸው ከሦስት ዓመት በላይ አላይዋቸውም፤ ቤተሰቦቻቸውም ቢሆን ከሁለት በላይ ከእርሳቸው ጋር ምንም ግንኙነት አልነበራቸውም።
ስለእርሳቸው የታየው ብቸኛ ምስል እአአ በግንቦት 2021 ጦሩ የመሰረተባቸውን እና የፈጠራ ብለው ያስተባበሏቸው ተከታታይ ክሶች በፍርድ ቤት መታየት በጀመሩበት ወቅት የተነሳ ነው።
በወቅቱ ተፈርዶባቸው የነበረው የ33 ዓመት ፍርድ በተደጋጋሚ እንዲቀንስ ተደርጓል።
አን ሳን ሱ ኪ በድንገት በመገናኛ ብዙኃን ላይ ምስላቸው መታየቱ ወታደራዊ ባለሥልጣናቱ በእርሳቸው ዙሪያ ተጨማሪ ለውጦችን ለማድረግ እየተዘጋጁ ይሆናል የሚል ጥርጣሬን አጭሯል። ምናልባት አን ሳን ሱ ኪ ከዚህ በኋለ በከፊል ወይም ሙሉ በሙሉ ነጻ ሊወጡ ይችላሉ የሚል ግምት አሳድሯል።
የመፈንቅለ መንግሥቱ መሪ ሚንኡንግ ህሌይንግ አገዛዛቸው የደረሰበት ዓለም አቀፍ መገለል እንዲያበቃ ፍላጎት አላቸው።
ጦራቸው ከታጣቁ የተቃዋሚ ቡድኖች ጋር ያደረገውን ውጊያን ካሸነፈ በኋላ የበለጠ በራስ መተማማን ተሰምቷቸዋል።
ወታደራዊው አገዛዝ በዚህ ዓመት መጀመርያ ላይ የአገሪቱን ዲሞክራሲያዊ መንግሥት ለማስቀጠል በሚል ምርጫ አካሄዷል። ነገር ግን አሁንም በሥልጣን ላይ ያለው የአገሪቱ ጦር ነው።
አን ሳን ሱ ኪ ከዚህ ቀደም በቤት ውስጥ እስር ውስጥ በነበሩበት ወቅት፣ በሰላማዊ ተቃውሞዋቸው የተነሳ በምያንማር እና በዓለም አፍ ደረጃ ድጋፍ አግኝተዋል። ከቤታቸው በመሆን አልፎ አልፎ ለደጋፊዎቻቸው ንግግር ያደርጉ የነበሩትት አን ሳን ሱ ኪ የኖቤል የሰላም ሽልማትን እአአ በ1991 ተሸልመዋል።
ነገር ግን በዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት አገራቸው ምያንማርን እአአ በ2017 በሮሂንጂያ ሙስሊሞች ላይ የፈጸመችውን የዘር ማጥፋት ወንጀል መከላከላቸው ዓለም አቀፍ ዝናቸው ላይ ጥላ አጥልቶበታል።














