በሳዑዲ አረቢያ ቢያንስ 65 ኢትዮጵያውያን ስደተኞች የሞት ፍርድ እንደሚጠብቃቸው ሂውማን ራይትስ ዎች አስታወቀ

የሳዑዲ አረቢያን ከተማ እና ካርታ የሚያሳይ ምስል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

በሳዑዲ አረቢያ ቢያንስ 65 ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ከአደንዛዥ ዕጽ ጋር በተያያዘ ክስ የሞት ፍርድ እንደሚጠብቃቸው ሂውማን ራይትስ ዎች አስታወቀ።

የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ የሳዑዲ አረቢያ ባለሥልጣናት ባለፈው ሳምንት ማክሰኞ ሚያዚያ 13/2018 ዓ.ም. ሦስት ኢትዮጵያውያንን በሞት መቀጣታቸውን ገልጾ የሌሎቹ ፍርድ ተፈጻሚነት ግን እንዲዘገይ መደረጉን በሪፖርቱ አመልክቷል።

ዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብቶች ተቋም ሚያዚያ 21/2018 ዓ.ም. ባወጣው ሪፖርት በሳዑዲ አረቢያ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በተለይም ከአደንዛዥ ዕፅ ጋር በተያያዙ ወንጀሎች ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ በርካታ የውጭ አገር ዜጎች ላይ የሞት ቅጣት መፈጸሙን አስታውቋል።

የሂውማን ራይትስ ዎች ረቡዕ የስደተኞች እና ሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ተመራማሪ የሆኑት ናዲያ ሃርድማን "ሳዑዲ አረቢያ መሠረታዊ የፍትህ ሂደትን የተነፈጉ የውጭ አገር ዜጎች አመጽ ባልተቀላቀለባቸው ወንጀሎች የተነሳ በሞት ለመቅጣት ፍቃደኛ መሆኗ ለመብታቸው እና ለሕይወታቸው ከፍተኛ ግድ የለሽነት እንዳላት ያሳያል" ብለዋል።

አክለውም "ከመርፈዱ በፊት የሳዑዲ አረቢያ አጋሮች በፍጥነት ጣልቃ መግባት አለባቸው" ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።

ሂውማን ራይትስ ዎች በአሲር ክልል ካህሚስ ሙሻይት ማረሚያ ቤት የታሰሩ ሦስት ጉዳዩን የሚያውቁ ሰዎችን ማነጋገሩን በመግለጫው ጠቅሷል።

የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ያነጋገራቸው ግለሰቦች የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነትን ሸሽተው ሕይወታቸውን ለመለወጥ በማሰብ በየመን በኩል ወደ ሳዑዲ አረቢያ መግባታቸውን ገልጸዋል።

ስደተኞቹ በጉዟቸው ላይ ገንዘብ ለማግኘት እና ሕይወታቸውን ለማቆየት በማሰብ ጫት ይዘው መገኘታቸውን ለሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ አስረድተዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ድርጅቱ ካነጋገራቸው መካከል አንዱ ግለሰብ ሕገወጥ የሰው አዘዋዋሪዎች ከየመን ወደ ሳዑዲ አረቢያ እንዲገባ እንደሚረዱት እና እርሱ በምትኩ ጫት ይዞላቸው እንዲሄድ እንዳስገደዱት መናገሩን በሪፖርቱ ሰፍሯል።

ሂውማን ራይትስ ዎች ያነጋገራቸው ሰዎች አንዳቸውም በሳዑዲ ግዛት ጫት ይዞ መገኘት ወንጀል መሆኑን እንደማያውቁ ገልጸዋል።

የሳዑዲ ባለሥልጣናት ሦስቱን ግለሰቦች እአአ በ2023 እና 2024 አባሃ በተባለ ክልል በሥራ ላይ ሳሉ በቁጥጥር ስር እንዳዋሏቸው ተናግረዋል።

ቃለ መጠይቅ የተደረገላቸው እነዚህ ግሰለቦች ክሳቸው በጣም አጭር በሆነ ሂደት መታየቱን፣ አንዳንዶቹ በቪዲዮ መከታተላቸውን እና የሕግ ወኪል ወይም አስተርጓሚ እንዳልነበራቸው ገልጸዋል።

ስለቀረበባቸው ክስ እንዳልተነገራቸው ለሂውማን ራይትስ የገለጹት እነዚህ ግለሰቦች፣ በጸጥታ አካላት ድብደባ እንደደረሰባቸው፣ የማያውቁት ሰነድ ላይ በግዴታ ፊርማቸውን እንዲያኖሩ መደረጉን አስረድተዋል።

የችሎቱ ዳኛ "ለሌሎች ምሳሌ ትሆናላችሁ" ብሎ መናገሩን ሂውማን ራይትስ ዎች ያነጋገራቸው ኢትዮጵያውያን አስረድተዋል።

የሳዑዲ መንግሥት ማረሚያ ቤት ውስጥ ያሉት እና ሞት የተፈረደባቸው ኢትዮጵያውያን ከሁለት ዓመት በላይ ለሚሆን ጊዜ በእስር ላይ መቆየታቸውን እና ይግባኝ የማለት ዕድል እንደሌላቸው ተናግረዋል።

ከአደንዛዥ ዕፅ ጋር በተያያዘ የሞት ፍርድ ከተፈረደባቸው 65 ኢትዮጵያውያን መካከል በግድያ እና በሌሎች ወንጀሎች የተከሰሱ የሳዑዲ ዜጎች ጋር አብረዋቸው እንደታሰሩ አብራርተዋል።

የሳዑዲ መገናኛ ብዙኃን በካሃሚስ ሙሻይት ማረሚያ ቤት የሚገኙ ከ200 በላይ ኢትዮጵያውያን የሞት ፍርድ እየጠበቁ መሆኑን ዘግበዋል።

ሂውማን ራይትስ ዎች ግን ይህንን ቁጥር ማረጋገጥ እንዳልቻለ ጠቅሷል።

በሳዑዲ አረቢያ ከአደንዛዥ ዕፅ ጋር በተያያዘ ክስ የተመሠረተባቸውን ግለሰቦች በሞት መቅጣት በአውሮፓውያኑ 2020 አግዳ ነበር።

ከሁለት ዓመታት በፊትም ልዑል አልጋ ወራሽ ሞሐመድ ቢን ሳልማን የሞት ቅጣት ተፈጻሚነት የግድያ ወንጀል የፈጸመ ግለሰብ ላይ ብቻ እንዲወሰን አውጀው ነበር።

ሆኖም በዚያው ዓመት ከጥቂት ወራት በኋላ ሳዑዲ ምንም ዓይነት ምክንያት ሳትሰጥ ከአደንዛዥ ዕፅ ጋር በተያያዘ የተከሰሱ ግለሰቦች ላይ የሞት ቅጣትን ተፈጻሚ ማድረግ ጀምራለች።

የሳዑዲ አረቢያ ንጉሥ ሰልማን እአአ በ2015 ዘውዱን ከተረከቡ እና ልዑል መሐመድ ቢን ሰልማንን እአአ በ2017 ከሾሙ ጀምሮ ከ2,000 በላይ ሰዎችን በሞት ተቀጥተዋል።

የሳዑዲ አረቢያ አገር ውስጥ ሚኒስቴር ሚያዚያ 13/2018 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ ሦስት ኢትዮጵያውያን "ሃሺሽ ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት በመተባበራቸው" በሞት መቀጣታቸውን አስታውቋል።

እአአ በ2024 የሳዑዲ ባለሥልጣናት 345 ሰዎችን፤ በ2025 ደግሞ 356 ፍርደኞችን በሞት ቀጥተዋል።

እአአ በ2025 በውጭ ዜጎች ላይ ከተፈጸሙት የሞት ቅጣቶች ከፍተኛ ቁጥር ያለው ከአደንዛዥ ዕጽ ጋር የተያያዘ ወንጀል ነው።

በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውን በሳዐዲ አረቢያ ኑሯቸውን አድርገዋል።

በርካቶቹ ወደ ሳዑዲ የመጡት ሥራ ፍለጋ፣ አገራቸው ውስጥ ያለውን የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ሽሽት እንዲሁም በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል ያለውን ጦርነት በመሸሽ መሆኑን ይናገራሉ።

ከዚህ በፊት ሂውማን ራይትስ ዎች ወደ መካከለኛው ምሥራቅ በየመን በኩል አድርገው የሚመጡ ስደተኞች በርካታ የመብት ጥሰቶች እንደሚፈጸምባቸው ገልጾ ነበር።

ሳዑዲ አረቢያ፣ ኢራን፣ ኩዌት እና የተባበሩት አረብ ኤሚሬትስ ከአደንዛዥ ዕፅ ጋር በተያያዙ ክሶች የሞት ቅጣት ከሚፈጸምባቸው በርካታ የመካከለኛው ምሥራቅ አገራት መካከል ናቸው።