ሳዑዲ አረቢያ ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ በርካታ የውጭ ዜጎችን ከአደንዛዥ ዕፅ ወንጀል ጋር በተያያዘ በሞት ቀጣች -አምነስቲ

የሳዑዲ አረቢያ ካርታ፣ የከተማዋ ፎቶ እና የገመድ ሸምቀቆን የሚያሳይ ምስል

አምነስቲ ኢንተርናሽናል ሰኞ ዕለት ባወጣው ሪፖርት በሳዑዲ አረቢያ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በተለይም ከአደንዛዥ ዕፅ ጋር በተያያዙ ወንጀሎች ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ በርካታ የውጭ አገር ዜጎች ላይ የሞት ቅጣት መፈጸሙን አስታውቋል።

ባለፈው ዓመት በሳዑዲ አረቢያ ከአደንዛዥ ዕጽ ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ በውጪ ዜጎች ላይ የሚፈጸም የሞት ቅጣት ከፍተኛ ደረጃ ላይ መድረሱን አምነስቲ በሪፖርቱ ላይ ገልጿል።

ሳዑዲ አረቢያ ባለፈው ዓመት 345 ሰዎችን በሞት የቀጣች ሲሆ፣ ይህም አምነስቲ ባለፉት ሦስት አስርት ዓመታት ከመዘገበው ከፍተኛው ቁጥር ነው ብሏል።

ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ ብቻ 180 ሰዎች በሞት ተቀጥተዋል ያለው የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ቡድኑ፣ ይህም ቁጥር ሊጨምር እንደሚችል አመልክቷል።

እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከጥር 2014 እስከ ሰኔ 2025 ባለው ጊዜ ውስጥ ሳዑዲ አረቢያ 1,816 ሰዎችን በሞት መቅጣቷን የአገሪቱ የፕሬስ ኤጀንሲ አስታውቋል።

ከእነዚህ የሞት ቅጣቶች መካከል ከሦስቱ አንዱ ከአደንዛዥ ዕፅ ጋር በተያያዙ ወንጀሎች የተፈፀመ ሲሆን፣ እነዚህም በዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ሕግ እና መስፈርቶች በሞት የማያስቀጡ ወንጀሎች መሆናቸውን አምነስቲ በሪፖርቱ ላይ ገልጿል።

ባለፉት አስር ዓመት ጊዜ ውስጥ ከአደንዛዥ ዕፅ ጋር በተያያዙ ወንጀሎች የሞት ቅጣት ከተቀበሉት 597 ሰዎች መካከል 75 በመቶ የሚሆኑት የውጭ አገር ዜጎች መሆናቸውንም ገልጿል።

እንደ አውሮፓውያኑ በ2024 ሳዑዲ አረቢያ 345 የሞት ቅጣት ፈፅማለች።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ባለፉት ስድስት ወራት፣ ከጥር እስከ ሰኔ 2025 ባለው ጊዜ ውስጥ ሳዑዲ አረቢያ በድምሩ 180 ሰዎችን በሞት ቀጥታለች።

በሰኔ 2025 ብቻ አገሪቱ 46 ሰዎችን በሞት የቀጣች ሲሆን 37ቱ ከአደንዛዥ ዕፅ ጋር በተያያዘ ነው።

ይህም ማለት ከአደንዛዥ ዕጽ ጋር በተያያዘ በቀን በአማካይ ከአንድ ሰው በላይ በሞት ይቀጣል ማለት እንደሆነ አምነስቲ በሪፖርቱ ላይ አመልክቷል።

ከእነዚህም መካከል 34ቱ ከግብፅ፣ ከኢትዮጵያ፣ ከዮርዳኖስ፣ ከናይጄሪያ፣ ከፓኪስታን፣ ከሶማሊያ እና ከሶሪያ የመጡ የውጭ አገር ዜጎች መሆናቸውን አምነስቲ ገልጿል።

የአምነስቲ ኢንተርናሽናል የመካከለኛው ምሥራቅ እና ሰሜን አፍሪካ ዳይሬክተር ክሪስቲን ቤከርል "ሳዑዲ አረቢያ ያለመታከት እና ያለ ርህራሄ የሞት ቅጣትን ከኢፍትሃዊ የፍርድ ሂደቶች በኋላ መጠቀሟ ለሰው ልጅ ሕይወት ያላትን ንቀት የሚያሳይ ብቻ ሳይሆን፣ ከአደንዛዥ ዕፅ ጋር ለተያያዙ ወንጀሎች መተግበሩም በከፍተኛ ሁኔታ የዓለም አቀፍ ሕግ እና ደረጃዎችን መጣስ ነው።"

አክለውም ". . . ይህ ሪፖርት ባለሥልጣናቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለመሳል ከሚሞክሩት ተራማጅ ምሥል በስተጀርባ ያለውን ጨለማ እና አደገኛ እውነታ አጋልጧል" ብለዋል።

እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2024 የተፈፀሙት 345 የሞት ቅጣቶች አምነስቲ ኢንተርናሽናል በሳዑዲ አረቢያ ከሦስት አስርት ዓመታት በላይ ከመዘገባቸው የሞት ቅጣቶች ሁሉ ከፍተኛውን ቁጥር ይዘዋል።

ከእነዚህ ውስጥ 35 በመቶው ወይም 122 ሰዎች የተገደሉት ከአደንዛዥ ዕፅ ጋር በተያያዙ ወንጀሎች ሲሆን፣ ይህም በ1990 አምነስቲ በሳዑዲ አረቢያ የሞት ቅጣት መመዝገብ ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ በዓመት ውስጥ የታየ ከፍተኛው ቁጥር ነው።

በሳዑዲ አረቢያ ከአደንዛዥ ዕፅ ጋር በተያያዘ ክስ የተመሠረተባቸውን ግለሰቦች በሞት መቅጣት በአውሮፓውያኑ 2020 አግዳ ነበር።

ከሁለት ዓመታት በፊትም ልዑል አልጋወራሽ ሞሐመድ ቢን ሳልማን የሞት ቅጣት ተፈጻሚነት የግድያ ወንጀል የፈጸመ ግለሰብ ላይ ብቻ እንዲወሰን አውጀው ነበር።

ሆኖም በዚያው ዓመት ከጥቂት ወራት በኋላ ሳዑዲ ምንም ዓይነት ምክንያት ሳትሰጥ ከአደንዛዥ ዕፅ ጋር በተያያዘ የተከሰሱ ግለሰቦች ላይ የሞት ቅጣትን ተፈጻሚ ማድረግ ጀምራለች።

ሳዑዲ አረቢያ ኢራንን፣ ኩዌትን እና የተባበሩት አረብ ኤሚሬትስን ጨምሮ ከአደንዛዥ ዕፅ ጋር በተያያዙ ክሶች የሞት ቅጣት ከሚፈጸምባቸው በርካታ የመካከለኛው ምሥራቅ አገራት አንዷ ነች።

የሳዑዲው አልጋ ወራሽ ልዑል መሃመድ ቢን ሳልማን

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, የሳዑዲው አልጋ ወራሽ ልዑል መሃመድ ቢን ሳልማን የሞት ቅጣት ተፈጻሚነት የግድያ ወንጀል የፈጸመ ግለሰብ ላይ ብቻ እንዲወሰን አውጀው ነበር

የውጭ አገር ዜጎች እና ከአደንዛዥ ዕፅ ጋር የተያያዙ የሞት ቅጣቶች

የአምነስቲ ኢንተርናሽናል ሪፖርት ከአደንዛዥ ዕፅ ጋር በተያያዙ ወንጀሎች በአስደንጋጭ ሁኔታ የውጭ ዜጎች እንዴት እንደሚገደሉ አጉልቶ ያሳያል።

በተለይ ባለፉት አስርት ዓመታት 155 ፓኪስታናዊ፣ 66 ሶሪያዊያን፣ 50 ዮርዳኖሳውያን፣ 39 የመናውያን፣ 33 ግብፃውያን፣ 32 ናይጄሪያውያን፣ 22 ሶማሌያውያን እና 13 ኢትዮጵያውያን በሞት መቀጣታቸውን አምነስቲ ገልጿል።

ከዚህም በተጨማሪ በርካታ ተጨማሪ የውጭ ዜጎች የሞት አደጋ ላይ ናቸው።

አምነስቲ ኢንተርናሽናል አብሯቸው ከሚሠራ የተለያዩ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ጋር በመሆን ከግብፅ፣ ከኢትዮጵያ፣ ከዮርዳኖስ፣ ከፓኪስታን እና ከሶማሊያ የተውጣጡ የውጭ አገር ዜጎች በአደንዛዥ ዕፅ ወንጀል ተከስሰው በአሁኑ ጊዜ የሞት ፍርድ የሚጠብቃቸው ወይም በሳውዲ አረቢያ በሞት የተቀጡ 25 የውጭ ዜጎች ጉዳይ መዝግቧል።

እነዚህ የሞት ፍርድ የተፈረደባቸው ግለሰቦች ምንም ዓይነት የሕግ ውክልና የላቸውም ወይም ውስን ውክልና ብቻ ያገኛሉ ብሏል።

ከእነዚህ 25 ሰዎች መካከል የ13ቱን ቤተሰቦች፣ የማኅበረሰብ አባላት እና የቆንስላ ጽ/ቤት ኃላፊ እንዲሁም የፍርድ ቤት ሰነዶችን የመረመረው አምነስቲ፣ እነዚህ የሞት ፍርደኛ የውጭ አገር ዜጎች የትምህርት ውስንነት እንዲሁም ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግር ስላለባቸው በስደት ወቅት ለብዝበዛ የተጋለጡ መሆናቸውን አስታውቋል።

በዚህም የተነሳ በሳዑዲ አረቢያ የሕግ ውክልና ማግኘት አስቸጋሪ እንዲሆንባቸው ማድረጉን ገልጿል።

አንድ የሞት ፍርድ የተፈረደበት ኢትዮጵያዊ ቤተሰብ አባል ለአምነስቲ ኢንተርናሽናል "የፍርድ ቤት ወረቀት እንደያዙ አናውቅም… በአገር ውስጥ ጉዳዩን የሚከታተልልን ማንም ሰው ስለሌለ፤ ሕጋዊ ተወካይ ስለሌለን፣ ምንም ዓይነት ሕጋዊ ሰነድ ማግኘት አንችልም። የቋንቋ ችግርም አለ። ወንድሜ ኢትዮጵያን ለቅቆ በሄደ በሳምንቱ ነው የየመን ድንበርን ሲያቋርጥ በቁጥጥር ስር የዋለው። በሳዑዲ ድንበር ምን እንደሚያጋጥመው የሚያውቀው ምንም ነገር የለም" ሲሉ ተናግረዋል።

የአምነስቲ ሪፖርት የሞት ፍርደኞቹ ፍትሃዊ ዳኝነት የማግኘት መብታቸውን ለማረጋገጥ ያሉባቸውን እንቅፋቶች ዘርዝሯል።

ከእነዚህም መካከል የሕግ ተወካይ አለማግኘት፣ በቂ ያልሆነ የቆንስላ ድጋፍ እና አስተርጓሚ አለመኖር ይገኙበታል።

ከተከሰሱት ሰዎች መካከል ቢያንስ አራቱ "የእምነት ክህደት ቃላቸውን" ለመቀበል ዳኛ ፊት ከመቅረባቸው በፊት ማሰቃየት ወይም እንግልት እንደተፈፀመባቸው ሪፖርት አድርገዋል።

የስምንት ልጆች አባት የሆነው የ57 ዓመቱ ጎልማሳ ሁሴን አቡ አል ኬር ችሎት ፊት በቀረበበት ወቅት የሰጠውን "የእምነት ክህደት ቃል" በተደጋጋሚ በምርመራ ወቅት ድብደባ እንደተፈጸመበት በመግለጽ አስተባብሏል።

ዳኛው ግን ችሎት ፊት ስለራሱ የተናገረውን እንደ ማስረጃ ተጠቅመው ጥፋተኛ ሲሉ በይነውበታል።

እንደዚህ ዓይነት ድርጊቶች ሳዑዲ አረቢያን በፀረ ስቃይ ኮንቬንሽን የገባቻቸውን ግዴታዎች እንዲሁም ሌሎች የሞት ቅጣት የሚደርስባቸውን ሰዎች መብት ጥበቃ የሚያረጋግጡ ዓለም አቀፍ ጥበቃዎችን ይጥሳሉ።

አምነስቲ ኢንተርናሽናል የሞት ፍርድ በተፈረደባቸው ሰዎች እና በቤተሰቦቻቸው ላይ የደረሰው የሥነ ልቦና ጉዳት እጅግ ከፍተኛ ነው ሲል ገልጿል።

ብዙዎች የይግባኝ ጥያቄያቸው ከምን እንደደረሰ ወይም መቼ የሞት ቅጣቱ እንደሚፈጸምባቸው አያውቁም።

አንዳንድ ጊዜ የእስር ቤት ኃላፊዎች ከአንድ ቀን በፊት ብቻ ይነገራቸዋል። ቤተሰቦች ስለ ግድያው ከሌሎች እስረኞች ወይም ከሚዲያ ዘገባዎች ነው የሚያውቁት።

አምነስቲ ኢንተርናሽናል የተመለከታቸው ሁሉም የሞት ቅጣቶች የሳዑዲ ባለሥልጣናት የተገደሉትን ሰዎች አስከሬን በመከልከል ቤተሰቦች በሃይማኖታቸው መሠረት ቀብር እንዳይፈጽሙ በማድረግ ሐዘናቸውን የመወጣት መብታቸውን ከልክሏል።

ይህ ድርጊት በተባበሩት መንግሥታት እንግልት እንደማድረስ ስለሚቆጠር የተወገዘ ነው።

በመጋቢት ወር 2023 በሳዑዲ አረቢያ በሞት የተቀጣው የዮርዳኖሳዊው ሁሴን እህት የሆነችው ዘይነብ አቦ አልከሂር "በጣም አዝነናል፤ በተለይ ሐዘናችንን ገልፀን የምንቀብረው አስከሬን ማግኘት ባለመቻላችን አዝነናል። የቀብር ሥርዓት አልተፈፀመም. . . በአማን የሚገኙት ቤተሰቦቼ ዜናውን ሲሰሙ ሳሎናቸው ውስጥ ተቀምጠው፤ እንደ እብድ መጮህ ጀመሩ። ይህ ልቤን የሚሰብረው ምሥል ነው" ብላለች።