በእስራኤል እና ሊባኖስ የተኩስ አቁም መክሸፍ መሀል የቀጠለው የሄዝቦላህ ድጋፍ

ባለፈው ቅዳሜ ምሳ ሰዓት ላይ ያለምንም ማስጠንቀቂያ የተፈፀመ የእስራኤል የአየር ጥቃት በደቡብ ሊባኖስ ከጦርነት የተፈናቀሉ ቤተሰቦች የተጠለሉበትን ሕንፃ አውድሟል።
ባለፈው ወር የተደረሰው የተኩስ አቁም ስምምነት በእስራኤል እና በሊባኖሱ የሺአ ሙስሊም ታጣቂ ቡድን በሆነው ሄዝቦላህ መካከል ያለውን ግጭት ማቆም አልቻለም።
በዚህ የአገሪቱ ክፍል የእስራኤል ጥቃቶች ቀንና ሌሊት እየተፈጸሙ ናቸው።
የቢቢሲ ዘጋቢ አካባቢው ሲደርስ የሕይወት አድን ሠራተኞች ፍለጋቸውን አጠናቀው ነበር። በፍርስራሹ አናት ላይ አንድ ሰው በዝምታ ቆሞ የፈራረሰውን ሕንፃ ይመለከት ነበር። ጎረቤቶች የተጎዳ የሕፃን ብስክሌት እና በትቢያ የተሞላ ወይን ጠጅ ቀለም ያለው አሻንጉሊት አግኝተዋል።
በዚያ ቦታ ዘጠኝ ሰዎች ተገድለዋል። የእስራኤል ጦር የሄዝቦላህ አባላት ለወታደራዊ አገልግሎት የሚጠቀሙበት ሕንፃ ላይ ጥቃቱ ማነጣጠሩን እና አባላቱ "አስቸኳይ ስጋት" ደቅነው እንደነበር ገልጿል።
ከዚህ ውጭ ግን ጦሩ ተጨማሪ ዝርዝር አልሰጠም።
የሟች ዘመዶች እንደሚናገሩት ተጎጂዎቹ በ70ዎቹ ዕድሜ ውስጥ የነበሩ ሴት፣ ልጃቸው እና የልጃቸው ባለቤት፣ ሌላ ልጃቸው፣ አራት የልጅ ልጆቻው እና የሁለት ዓመት ዕድሜ ያላት የልጅ ልጅ ልጃቸው ነበሩ።
የእስራኤል ጦር በጦርነቱ ተሳትፎ በሌላቸው ሲቪል ሰዎች ላይ የደረሰ ጉዳት ስለመኖሩ ሪፖርቶችን እየመረመረ እንደሆነ ገልጿል።
ፀሐይ ስትጠልቅ የቢቢሲ ዘጋቢ አካባቢውን ለቅቆ እንዲወጣ በነዋሪዎች ተነግሮታል። "ጥቃቶች በሰማይ የሚጨምሩት ያን ጊዜ ነው" ሲል አንድ ነዋሪ አስጠንቅቆታል።
ደቡብ ሊባኖስ የአገሪቱ የሺአ ሙስሊም ማኅበረሰብ ዋነኛ ማዕከል ሲሆን ሄዝቦላህም ዋና ድጋፉን ከዚህ ያገኛል።
አካባቢው የእስራኤል የአየር ጥቃት የሚዘንብበትም ነው። በሌላ በኩል በኢራን የሚደገፈው ታጠቂ ቡድን እና የፖለቲካ ፓርቲ የሆነው ሄዝቦላህ በሰሜን እስራኤል እና ሊባኖስ በሚገኙ የእስራኤል ወታደሮች ላይ የሮኬትና የድሮን ጥቃቶችን ይፈፅማል።
ባለፉት ሁለት ሳምንታት በደቡብ ሊባኖስ የሚገኙ ከተሞች እና መንደሮችን የጎበኘው ዘጋቢው ቁጥር ስፍር የሌላቸው ሕንፃዎች ፈራርሰው መንገዶች ወና ሆነው ተመልክቷል።
ያገኛቸው አንዳንድ ሊባኖሳዊያን አላባራ ባለው ጦርነት እንደታከቱ ተናግረዋል። የእስራኤል ጥቃቶች እና ወረራ በመቀጠሉ አብዛኞቹ እነርሱን ለመከላከል የሚችል ኃይል ሄዝቦላህ ብቻ መሆኑን ያመናሉ።

6,000 ሰዎች ይኖሩበት በነበረው የ'አረብ ሳሊም' መንደር ሕይወት የቆመች ትመስላለች። በዋና አውራ ጎዳናው የረመዳን ጌጣጌጦች አሁንም እንደተሰቀሉ ናቸው። ሁሉም በሚያስብል ሁኔታ ቤቶች ያለባለቤቶቹ ባዶ ሆነዋል። መንደሩ ፀጥ ረጭ ብሏል፤ ነገር ግን ሰላም የለም።
በመስጊዱ አቅራቢያ በ80ዎቹ ዕድሜ ክልል ያሉ የአንደ እቤተሰብ አባላት "በርካታ ጦርነቶችን አይተናል። ነገር ግን መቼም ወጥተን አናውቅም። ምንም ይፈጠር ምን ለቅቀን ከመውጣት ይልቅ በቤታችን መሞት ይሻላል ብለን እናስባለን" ብለዋል።
በመላው ሊባኖስ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሰዎች ተፈናቅለዋል። ወይም ከአጠቃላይ የአገሪቱ ሕዝብ ከአምስቱ አንዱ በአብዛኛው ሄዝቦላህ ከሚቆጣጠራቸው የደቡባዊ ሊባኖስ አካባቢዎች ለቅቀው ወጥተዋል። አብዛኖቹ አሁንም ድረስ መንገድች እና አደባባዮች ላይ በጣሏቸው ድንኳኖች ይኖራሉ።
ከልጃቸው እና የልጅ ልጃቸው ጋር በአካባቢው የሚኖሩት የ65 ዓመቱ ሁሴን ሀይደር "የቦንብ ፍንዳታ ስንሰማ [ሕፃኑ] አጠገብ ሆነን እንስቃለን። ስንስቅ ሲያየን ጨዋታ ይመስለዋል" ይላሉ።
ከፊል ውድመት የደረሰበት መደብራቸው ላይ የሄዝቦላህ ሰንደቅ ዓላማ ተሰቅሏል። "ማኅበረሰቡ ሄዝቦላህን ይደግፋል። ምክንያቱም እየተከላከሉን ነው" ይላሉ። "መሬታችን ላይ እንድንሆን እየጠበቁን ያሉት እነርሱ ብቻ ናቸው።"

በአረበኛ "የፈጣሪ ፓርቲ" የሚል ትርጉም ያለው ሄዝቦላህ እ.አ.አ በ1980ዎቹ እስራኤል ሊባኖስን በወረረችበት ወቅት ነው የተመሠረተው። ቡድኑ ከምስረታው ጀምሮ ገንዘብ፣ ሥልጠና እና መሣሪያ ድጋፍ የሚያገኘው ከኢራን ነው። የእስራኤል ውድመት የቡድኑ ይፋዊ ግብ መሆኑ አሁንም እንደቀጠለ ነው።
የአሁኑ ግጭት የተቀሰቀሰው እስራኤል እና አሜሪካ በአጋርነት በከፈቱት ጥቃት የኢራኑ ታላቅ መሪ አያቶላህ አሊ ኻሜኒ መገደላቸውን ተከትሎ፤ ሄዝቦላህ የካቲት 23 እስራኤል ላይ ሮኬት በመተኮሱ ነው።
እስራኤል በመላው ሊባኖስ መጠነ ሰፊ ጥቃት በመፈፀም እና የአገሪቱን ደቡባዊ ክፍል በመውረር የአጸፋ እርምጃ ወስዳለች።
ባለፈው ሚያዚያ 8 የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በእስራኤል እና ሊባኖስ መካከል የተኩስ አቁም ስምምነት መደረሱን አስታውቀዋል።
አሜሪካ እና ዩናይትድ ኪንግደምን ጨምሮ በተለያዩ አገራት የሽብር ቡድን ተብሎ የተፈረጀው ሄዝቦላህ በዚህ ስምምነት በይፋ ባይሳተፍም በተኩስ አቁሙ እንደሚገዛ ተጠቁሟል።
ይህ እፎይታ ግን በአጭር የተቀጨ ነው። በቀናት ውስጥ እስራኤል ሄዝቦላህ ስምምነቱን አፍርሷል በሚል በተለይም በደቡባዊ ሊባኖስ ጥቃቷን ቀጥላለች። ከዚያም ሄዝቦላህ እስራኤል እና በሊባኖስ በሚገኙ የእስራኤል ወታደሮችን ወደማጥቃቱ ተመልሷል።
ጦርነቱ ከተጀመረ ወዲህ እንደ ሊባኖስ ጤና ሚኒስቴር መረጃ ቢያንስ 2,800 ሰዎች ተገድለዋል። ከእነዚህም ውስጥ 400 የሚሆኑት የተኩስ አቁም ስምምነቱ ከተደረሰ በኋላ ተገደሉ ናቸው። (የሊባኖስ ጤና ሚኒስቴር ተዋጊዎችን ከንጹኃ ለያይቶ መረጃ አያወጣም።)
እስራኤል በበኩሏ በጦርነቱ 18 ወታደሮች እና ሁለት ሰላማዊ ዜጎች እንደተገደሉባት አስታውቃለች።
እስራኤል በሊባኖስ የወረረችው መሬት ከአገሪቱ ግዛት አምስት በመቶ ሲሆን፤ በአንዳንድ አካባቢዎች ከአገራቱ ድንበር 10 ኪሎ ሜትር ገደማ ድረስ ዘልቃ ገብታለች።
አገሪቱ በጋዛ እንዳደረገችው ሁሉ በአየር ድብደባዎች በሊባኖስም ሙሉ መንደሮችን አውድማለች። የእስራኤል ጦር ሕንፃዎቹ ሄዝቦላህ የሚጠቀምባቸው እንደሆኑ ይናገራል።
የሰብአዊ መብት ቡድኖች ደግሞ በሲቪሊ መሠረተ ልማቶች ላይ ሆን ተብሎ የሚፈፀም ውድመት የጦር ወንጀል ነው ይላሉ።
የእስራኤል ባለሥልጣናት ዓላማቸው በድንበር አቅራቢያ ከሄዝቦላህ ነፃ የሆነ፣ የአገሪቱን ማኅበረሰቦች ከቡድኑ ሮኬቶች እና ድሮኖች እንዲሁም የምድር ወረራ መጠበቅ የሚያስችል የደኅንነት ቀጣና መፍጠር እንደሆነ ይገልፃሉ።

የደከመው ሄዝቦላህ በአገር ውስጥ ብቻውን ሲሆን፤ የሊባኖስ ፕሬዝዳንት ጆሴፍ አውን ቡድኑን ትጥቅ ለማስፈታት ቃል ገብተዋል።
የሄዝቦላህ የትጥቅ ጉዳይ አገሪቱን የከፋፈለ ነው። ሆኖም የቡድኑ መሪ ናይም ቃሲም ትጥቃቸውን መፍታትን ውድቅ ያደርጋሉ።
የቀድሞ ወታደራዊ አዛዥ የሆኑት ፕሬዝዳንት አውን ሄዝቦላህን መሣሪያ ማስፈታት በኃይል የሚሆን እንዳልሆነ እና የሺአ ሙስሊም ማኅበረሰቡን የሚያነሳሳ እና በኃይማኖት ቅርንጫፎች መካከል ውጥረት የሚፈጥር እንደሆነ ይናገራሉ።
ተቃዋሚዎች ሄዝቦላህ ሊባኖስን ወደአልተፈለገ ጦርነት በመውሰድ እና የኢራንን ጥቅም በመከላከል ይከሱታል።
ደጋፊዎቹ ደግሞ የሊባኖስን መሬት የመውረር ፍላጎት ካላት እና ጠላታቸው ብለው ከሚመለከቷት ከእስራኤል የሚከላከላቸው ብቸኛው ኃይል ነው ይላሉ። ከእነዚህ ደጋፊዎች ውስጥ ከኻሜኒ ግድያ በኋላ ሄዝቦላህ እስራኤል ላይ ጥቃት መፈፀሙን የሚቃወሙ አሉ።
በሊባኖስ ሄዝቦላህ ከሚሊሻ በላይ ነው። በፓርላማ እና መንግሥት ወኪሎች ያሉት የፖለቲካ ፓርቲም ነው። በትምህርት ቤቶች እና ሆስፒታሎች አገልግሎት የሚሰጥ የማኅበረሰብ ንቅናቄም ነው።
ለበርካታ ዘመናት ለተገለሉ ማኅበረሰቦች ቡድኑ በመሠረታዊነት የሕይወታቸው እና የማንነታቸው አካል ነው።
የሕዝብ ድምፅ መረጃዎች አብዛኖቹ ሊባኖሳዊያን ሄዝቦላህ ትጥቁን እንዲፈታ ፍላጎት እንዳላቸው ቢያመላክቱም የቢቢሲ ዘጋቢ ያነጋገራቸው ሰዎች ግን አሁን ላይ ትጥቁን እንዳይፈታ እንደሚፈልጉ ጠቁመዋል። ሪዳ ጂጃዚ የተባለ ሊባኖሳዊ "ሊባኖስ በወረራ እና በስጋት ሥር እስከሆነች ድረስ ማንንም አናምንም" ሲል ተናግሯል።














