በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ የአሜሪካንን ባሕር ኃይል እየፈተኑ ያሉት የኢራን ትናንሽ ጀልባዎች

የፎቶው ባለመብት, NurPhoto via Getty Images
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በቅርቡ ባደረጉት ንግግር የኢራንን የባሕር ኃይል "ሙሉ በሙሉ አውድመናል" ብለዋል።
ከኢራን ባሕር ኃይል የቀረው "መትረየስ የተጠመደባቸው አነስተኛ ጀልባዎች" መሆናቸውን ተናግረዋል።
እነዚህ አነስተኛ የተባሉት ጀልባዎች በምዕራባውያን ተንታኞች ሞስኪቶ ፍሊት (mosquito fleet) የሚል ስያሜ ተሰጥቷቸዋል። በወባ ትንኝ የተመሰለው ስያሜያቸው መጠናቸውን እና ፍጥነታቸውን የሚያሳይ ነው።
ለወራት የኢራን መንግሥት በሆርሙዝ ወሽመጥ የመርከቦችን እንቅስቃሴ መግታት የቻለው በእነዚህ አነስተኛ ጀልባዎች ነው።
ኢራን በሆርሙዝ ወሽመጥ የሚደረግ እንቅስቃሴን በመግታት የዓለም ምጣኔ ሃብትን አናግታ አሜሪካ የምታደርስባትን ጥቃት እንድታቆም ጫና ማሳደር ትፈልጋለች።
ለመሆኑ እነዚህ አነስተኛ ጀልባዎች ምን ያህል ኢራንን እየጠቀሙ ነው።

"የሚወሩት፣ የሚያደናግሩት እና የሚያሰናክሉት ጀልባዎች"
አነስተኛ እና በፍጥነት ጥቃት የሚያደርሱ ጀልባዎች በኢራን መንግሥት ለመጀመሪያ ጊዜ የተሠሩት በአውሮፓውያኑ በ1980ዎቹ በኢራን-ኢራቅ ጦርነት ወቅት ነው።
ኢራን እየተዋጋች የነበረው ከኢራቅ ጋር ቢሆንም ጦርነቱ ወደ ፋርስ ባሕረ ሰላሴ መስፋፋቱ አልቀረም። አሜሪካም ነዳጅ ጫኝ መርከቦችን ለመጠበቅ ስትል ወደ ጦርነቱ ገብታለች።
ከአሜሪካ የባሕር ኃይል ጋር የተፋለመው የኢራን የባሕር ኃይል ከፍተኛ ጉዳት ደርሶበታል።
ከፍተኛ አቅም ያላቸው አገራትን ለመገዳደር በሚል አነስተኛ ጀልባዎች የጦርነቱ አካል እንዲሆኑም ተደረገ።
ኢራን ከሚሳዔል፣ ከሰው አልባ አውሮፕላን፣ ከባሕር ዳርቻ ከሚወነጨፉ መሣሪያዎች እና ፈንጂዎች በተጨማሪ እነዚህን አነስተኛ ጀልባዎች የውጊያ ስትራቴጂዋ አካል አድርጋለች።
በኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ የሚመራው የትንንሽ ጀልባዎቹ ውጊያ ከተለመደው የባሕር ፍልሚያ የተለየ መንገድ ይከተላል።
የኢራን መንግሥትን የሚቃወመው ዩናይትድ አጌንስት ኒውክሌር ኢራን ከፍተኛ አማካሪ እና በቴነሲ ዩኒቨርስቲ መምህር የሆኑት ተባባሪ ፕሮፌሰር ሳይድ ጎላካር "የሚወሩት፣ የሚያደናግሩት፣ የሚያጠቁት እና የሚያሰናክሉት ጀልባዎች" በማለት ይገልጿቸዋል።
የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ የአሜሪካን ባሕር ኃይል በተመለደው የውጊያ ስልት ማሸነፍ እንደማይችል እንደሚያውቅ ባለሙያው ይናገራሉ።
በፋርስ ባሕረ ሰላጤ የሚንቀሳቀሱ ኩባንያዎች ለአደጋ እንዲጋለጡ እና ወጪያቸው እንዲንር ማድረግ ዋነኛ አላማቸው ነው።
አነስተኛዎቹ ጀልባዎች በንግድ መርከቦች አቅራቢያ መተኮስን አንድ ስትራቴጂ አድርገው ይጠቀማሉ። ባሕር ላይ ፈንጂ ማጥመድ እና ከተለያዩ አቅጣጫዎች በርካታ ጀልባዎችን ማሰማራትም ሌላው ስልት እንደሆነ ተንታኞች ይገልጻሉ።
ፈጣን የሆኑት ጀልባዎች የጦር መሣሪያ፣ ሮኬት እና ፀረ መርከብ ሚሳዔል ይታጠቃሉ። አብዛኞቹ ጀልባዎች የሚመረቱት በኢራን ውስጥ ነው።
የተወሰኑት መርከቦች ለዓሣ አስጋሪዎች ጥቅም እንዲሰጡም ይሠራሉ።
በዋሽንግተን የሚገኘው ሀድሰን ኢንስቲትዩት የባለሙያዎች ቡድን አባል ካን ካስፓጉሉ እንደሚሉት፤ ጀልባዎቹ በተመጣጣኝ ዋጋ የሚሸጡ እና በቀላሉ የሚተኩ ናቸው።
ኢራን እነዚህን ጀልባዎች በመጠቀም የንግድ እና ወታደራዊ መርከቦችን "በአነስተኛ ዋጋ" እንደምታስፈራራ ያስረዳሉ።

የፎቶው ባለመብት, NurPhoto via Getty Images
"የባሕር ላይ ሽምቅ ውጊያ"
ኢራን የምትዝትባቸው መርከቦች ከፍተኛ ዋጋ የሚያወጡ ናቸው። ትንንሾቹ ጀልባዎች የባሕር ላይ ምጣኔ ሃብታዊ እንቅስቃሴን አደጋ ላይ ይጥላሉ።
የኢራን ግብ አሜሪካ ላይ ጫና በማሳደር ለወደፊት ጥቃቶች እንዳይሰነዘሩባት ማድረግ ነው።
እነዚህ ጀልባዎች ከውሃ በታች ዝቅ ብለው ይቆያሉ። በቅርብ እስከሚታዩ ድረስ መኖራቸውን ማወቅ ያዳግታል።
ጀልባዎቹን በቅርበት ለመከታተል ሰው አልባ አውሮፕላኖች እና ሄሊኮፕተሮች መጠቀም ያስፈልጋል።
እነዚህ ጀልባዎች ትክክለኛ ቁጥራቸው አይታወቅም። ምክንያቱም አብዛኞቹ በኢራን ደቡባዊ የባሕር ዳርቻ በሚገኙ በዋሻ ውስጥ አልያም ከምድር በታች በተገነቡ ክፍሎች ተደብቀው እንዲቆዩ ይደረጋል።
ተንታኞች እንደሚሉት ከሆነ ኢራን ከ500 እስከ አንድ ሺህ የሚደርሱ ትንንሽ ጀልባዎች ሊኖሯት ይችላል።
የባሕር ላይ የጦር ልምምድ ሲደረግ ጀልባዎቹ ጥቅም ላይ ይውላሉ።
ተንታኞች የኢራንን የጦርነት ስልት "የባሕር ላይ የሽምቅ ውጊያ" በማለት ይገልጹታል።
የአሜሪካ ባሕር ኃይል የኢራን ጀልባዎች በዕይታ ውስጥ ከሆኑ መምታት የሚችልበት አቅም አለው። ስለዚህም እስላማዊ አብዮታዊ ዘቡ ጀልባዎችን ለመደበቅ ይሞክራል።
የሀድሰን ኢንስቲትዩት ባለሙያው ካን ካስፓጉሉ እንደሚሉት፤ እነዚህ ጀልባዎች ቀጥተኛ ውጊያ ውስጥ እንዲገቡ አይደረግም።
"የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ ቀጥተኛ ውጊያ ላለማድረግ ይሞክራል። ጥቃት አድርሶ በፍጥነት መሸሽን እንደ ስልት ይጠቀማል። በተጨማሪም መውረር፣ ፈንጂ መጣል፣ በሰው አልባ አውሮፕላን መምታት፣ ሚሳዔል መጠቀም እና አነስተኛ ጀልባ ማሰማራት ይገኙበታል። አነስተኛ ጀልባዎች የአሜሪካ የንግድ እንቅስቃሴ ላይ ኪሳራ ያስከትላሉ" ይላሉ።

የፎቶው ባለመብት, NurPhoto via Getty Images
ኢራን ጀልባዎቹን በፍጥነት እና በአነስተኛ ወጪ ትተካለች። ከዚህ በተቃራኒው አሜሪካ እና አጋሮቿ የባሕር ላይ የንግድ እንቅስቃሴን ለማስቀጠል ውድ መርከቦችን ወይም አውሮፕላኖችን በማሰማራት ጥበቃ ማድረግ ግድ ይላቸዋል።
ኢራን መርከቦች ላይ ጥቃት ባትፈጽምም እንኳን መርከቦች ጥቃት ሊደርስባቸው ይችላል የሚለው ስጋት የኢንሹራንስ ዋጋ እንዲጨምር ያስገድዳል። ኩባንያዎች መርከባቸውን በዚያ መስመር እንዳያሳልፉም ጫና ያሳድራል።
በባሕር ላይ እንቅስቃሴ ወቅት ጥቃት ሊፈጸም ይችላል የሚለው ስጋት የመርከቦችን ዝውውር እና ፍጥነት ይቀንሳል።
የሆርሙዝ ወሽመጥን የሚከታተለው ድረ ገጽ እንደሚለው አሁን ላይ በአንድ ቀን ውስጥ ወደ 10 የሚጠጉ መርከቦች ብቻ በባሕሩ ላይ ይታያሉ። ከዚህ ቀደም በአንድ ቀን ውስጥ እስከ 60 መርከቦች የሚተላለፉበት የባሕር መስመር ነበር።
የዩናይትድ ኪንግደም ባሕር ኃይል እንደሚለው አጠቃላይ የሆርሙዝ ወሽመጥ እንቅስቃሴ መጠን ከዚህ ቀደም ከነበረው 90 በመቶ ቀንሷል።
አሜሪካ፣ እስራኤል እና ኢራን የተኩስ አቁም ስምምነት ሲያደርጉ የመርከቦች እንቅስቃሴ መሻሻል ቢያሳይም ከስምምነቱ ከቀናት በኋላ አሜሪካ ከኢራን የሚወጡ ሸቀጦች ላይ ማዕቀብ መጣሏ ነገሮችን አባብሷል።
በሆርሙዝ ወሽመጥ የሦስት አገራት መርከቦች ላይ ጥቃት መድረሱም ሌላው እንቅስቃሴ የተገደበበት ምክንያት ነው።
የዩኬ የባሕር ላይ ንግድ ማዕከል ባለፈው ሳምንት እንዳለው በሰሜን ምሥራቅ ኳታር ሸቀጦችን የጫነ መርከብ "ባልታወቀ የመሣሪያ ፍንጣሪ" ተመትቷል። በጥቃቱ ምክንያት መጠነኛ እሳት ቢነሳም ሰዎች አልተጎዱም።
የኢራኑ ፋርስ የዜና ወኪል እንደዘገበው መርከቡ የአሜሪካ ሰንደቅ አላማ ያለው ሲሆን፣ ንብረትነቱም የአሜሪካ ነው።
በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ በተጣለው እገዳ ምክንያት ወደ 1,500 የሚጠጉ መርከቦች እና 20 ሺህ የመርከብ ሠራተኞች መንቀሳቀስ እንዳልቻሉ የተባበሩት መንግሥታት የባሕር ላይ ትራንስፖርት ተቋም አስታውቋል።
የተፈጠረው የነዳጅ እጥረት በቅርብ ጊዜ ውስጥ ታይቶ የማይታወቅ ቀውስ የፈጠረ ሲሆን፣ የነዳጅ ዋጋ ከዚህ ቀደም ባልታየ መጠን እንዲንርም ምክንያት ሆኗል።














