የሞት ፍርድ በኢትዮጵያ እንዴት ይፈጸማል? ምን ያህልስ ተቀባይነት አለው?

የፎቶው ባለመብት, THINKSTOCK
በዓለም አቀፍ ደረጃ የሞት ቅጣት እየጨመረ መሆኑን ከሰሞኑ ይፋ ያደረገው አምነስቲ ኢንተርናሽናል፤ እአአ በ2023 ብቻ 1153 የሞት ቅጣት መመዝገቡን አስታውቋል።
ይህ አሃዝ በ2022 ከነበረው 883 የሞት ፍርድ አንጻር የ31 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱ ነው የተገለጸው። አምነስቲ በ2015 ብቻ 1634 ከመዘገበ በኋላ 2023 ከፍተኛው የሞት ቅጣት የተላለፈበት ዓመት ሆኗል።
የአምነስቲ ኢንተርናሽናል ሪፖርት በኢትዮጵያ ያለውን የሞት ቅጣት ቁጥር በይፋ አላስቀመጠም። ሆኖም አለፍ ገደም እያለ በአገሪቱ በተለያዩ ወቅቶች የሞት ቅጣት መተላለፉ ተዘግቧል።
በኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ዙሪያ በምትገኘው ሸገር ከተማ ቡራዩ ክፍለ ከተማ ውስጥ ከወራት በፊት ሁለት ህጻናትን በአሰቃቂ ሁኔታ የገደለችው የእንጀራ እናት ሞት ተፈረዶባታል። ጥፋተኛ ሆና በተገኘችው ግለሰብ ላይ ውሳኔውን ያስተላለፈው የሸገር ከተማ ከፍተኛ ፍርድ ቤትነው- ቢቢሲ።
ከሰሞኑ ከአባቱ ጋር በተፈጠረ የጥቅም ግጭት በኮንሶ ዞን ሰገን ዙሪያ ወረዳ አባቱን፣ እናቱን፣ አጎቱ እና የ9 ዓመት ታናሽ ወንድሙን የገደለው ግለሰብ በሞት እንዲቀጣ ተፈርዶበታል። ውሳኔውን ያሳለፈው የኮንሶ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ነው - ፋና።
በአዳማ ከተማ ቦሌ ክፍለ ከተማ በተለምዶ ደከ ኦዲ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ እናቱን በቢላዋ በአሰቃቂ ሁኔታ ወግቶ የገደለው ግለሰብ በሞት እንዲቀጣ ተወስኖበታል። ውሳኔውን ያሳፈው የአዳማ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ነው- ፋና።
በአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ ሕግ ክፍል መምህር የሆኑት ተባባሪ ፕሮፌሰር መሐሪ ረዳኢ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ የሞት ቅጣት የሚጣልባቸው ጉዳዮች “በጣም ውስን” መሆናቸውን ይገልጻሉ።
ጭካኔ እና ነውረኝነት በተሞላበት መንገድ ሆን ተብሎ የሚደረግ ግድያ እና ከአገር ክህደት ጋር በተያያዙ የተወሰኑ ጉዳዮች ላይ ብቻ የሞት ቅጣቱ እንደሚወሰን ሕጉን ጠቅሰው ለቢቢሲ አስረድተዋል።
“በተቻለ መጠን አጥብቦ ነው [የሞት ፍርድ ቅጣት] ሕጉ የሚተቀረጸው” የሚሉት የሕግ መምህሩ፣ በዚህ ምክንያትም ተፈጸማኒቱ አነስተኛ ነው።
ሕጉ አጥብቦ ከመቀረጹም በላይ ዳኞችም የሞት ቅጣት ሲያስተላልፉ ተከሳሽ የፍርድ ማቅለያ ምክንያቶችን ማቅረብ በማይችልበት ሁኔታ ነው። የወንጀለኛው ዕድሜም ከ18 ዓመት በላይ መሆን ይጠበቅበታል። “ከዚያ በታች ወንጀል በሚፈጸሙ ላይ [ቅጣቱ] አይጣልም።”
ብዙ ጊዜ የሞት ፍርድ ተላለፈ ተብሎ በመገናኛ ብዙኃን ይነገራል። ጉዳዩ እዚህ ጋር ያበቃ፤ የሞት ፍርዱ የሚፈጸም ቢመስልም ተጨማሪ ሂደቶች ይኖራሉ። ተከሳሽ ይግባኝ በማለት የተለየ ፍርድ ሊያገኝ ይችላል።
ይግባኙ ተቀባይነት አጥቶ ፍርድ ቤቱ የሞት ቅጣቱን ካጸና በኋላም በቀጥታ ወደ ማስፈጸም አይገባም። የሞት ቅጣቱ እንዲፈጸም በአገሪቱ ርዕሰ ብሔር መጽደቅ ይኖርበታል።
በቁጥር ብዙ ባይሆኑም በዚህ ሂደት ውስጥ አልፈው የሞት ቅጣት ተፈጻሚ የሆኑባቸው አጋጣሚዎች መኖራቸውን ተባባሪ ፕሮፌሰሩ ያስታውሳሉ።

የፎቶው ባለመብት, NurPhoto
የሞት ቅጣት ተፈጻሚነት በኢትዮጵያ
ሆኖም ባለፉት 25 እና 30 ዓመታት ውስጥ የሚታወቁ የሞት ቅጣት የተፈጸመባቸው ጥቂት መሆናቸውን አንስተዋል። በቀድሞው የግብፅ ፕሬዝዳንት ሆስኒ ሙባረክ ላይ አዲስ አበባ ውስጥ የመግደል ሙከራ አድርገው በተያዙት ከሱዳን የመጡ ናቸው በተባሉ አሸባሪዎች ላይ የሞት ቅጣት እንደተፈረደባቸው አስታውሰዋል።
“ጄኔራል ሃየሎም አርአያን የገደለው ሰው የሞት ፍርድ ተፈርዶበት እንደተፈጸመበት አስታውሳለሁ። በተመሳሳይም ክንፈ ገብረመድኅንን [የቀድሞው የደኅንነት ኃላፊ ነበሩትን] የገደለው ሰው የሞት ፈርድ ተወስኖበነት እንደተፈጸመበት፣ የአልሻባብ ታጣቂዎችም ይመስለኛል ድሬዳዋ ወይም ጅግጅጋ በፈጸሙት ጥቃት ተይዘው እንደተፈጸመባቸው አስታውሳለሁ” ሲሉ ተናግረዋል።
በሞት ቅጣቱ ላይ ርዕሰ ብሔሮች ውሳኔ እንዲሰጡበት መደረጉ “የፖለቲካ ጉዳይ ነው” ይላሉ ተባባሪ ፕሮፌሰር መሐሪ።
የሰው ሕይወት ጉዳይ ስለሆነ “ድንጋጌዎችን ብቻ አይቶ ከተወሰነ እና ከተፈጸመ ከባድ ሊሆን ይችላል። . . . ለፍርድ ቤት ብቻ ሊተው አይገባም። ርዕሰ ብሔር የአገር ተወካይ ስለሆኑ እዚያ ድረስ ጸድቆ ነው መወሰን ያለበት ከሚል የመነጨ ይመስለኛል” ብለዋል።
በዚህ ውሳኔ ላይ ርዕሰ ብሔሩ ተሳታፊ እንዲሆኑ መደረጋቸው የራሱ የሆነ ተጽዕኖ ሊኖረው ይችላል። በሞት ቅጣት አላምንም የሚል ርዕሰ ብሔር ከመጣ የሞት ቅጣት የተላለፈበት ግለሰብ ውሳኔው ተግባራዊ ሳይደረግበት ሊቀመጥ የሚችልበት ዕድል ይፈጠራል።
“ርዕሰ ብሔሮች በማጽደቁ ላይ እግር የመጎተት ነገር ስላለ አፈጻጸሙ አነስተኛ ነው” የሚሉት የሕግ ምሑሩ፣ “ለምሳሌ ፕሬዝዳንት ግርማ በነበሩበት ጊዜ የራሳቸው ፍልስፍና ስለነበራቸው ብዙም ሲያጸድቁ አልታየም። ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅም ያጸደቁበትን [ጊዜ] አላስታወስም። ስለዚህ የፍርድ ቤት ውሳኔ ብቻ ሳይሆን የርዕሰ ብሔር ውሳኔም ስላለበት . . . ቅጣቱ እየተፈጸመ አይመስለኝም።”
ፍርድ ቤት አንድ ተከሳሽ ሞት ይገባዋል ብሎ ወስኖ ይህን ውሳኔ ሲያሳልፍ ፍርዱን እንዲያጸድቅ ኃላፊነት የተሰጠው አካል [ርዕሰ ብሔር] በተለያየ ምክንያት አላጸድቅም ካለ ፍርደኛው የተጣለበት ቅጣት ተግባራዊ ሳይሆን እንዲቆይ ምክንያት ይሆናል።
“ሥርዓቱ እርስ በርስ የሚጠባበቅበት መንገድ አበጅቷል ተብሎ ነው የሚወሰደው። የሞት ቅጣት ያስፈልጋል የሚል ርዕሰ ብሔር ካለ ከፍርድ ቤት የሚመጣለትን እያጸደቀ እርምጃ ሊያስወስድ ይችላል። ተገቢ አይደለም የሚል ሲመጣ ደግሞ በተቀራኒው መሆኑ አይቀርም” ብለዋል።
ርዕሰ ብሔሩ የሞት ፍርዱ እንዲተገበር በፊርማቸው ካላረጋገጡ ወንጀለኛው ፍርደኛ ሆኖ ይቀመጣል። አንድ ሰው የተፈረደበትን የእስር ጊዜ 2/3ኛውን በማረሚያ ቤት ካሳለፈ በኋላ በሚያሳየው የባህሪ መሻሻል አመክሮ እንዲያገኝ የሚያስችለው የሕግ አግባብ አለ። ባህሪው ለውጥ ከሌለው ግን ሙሉውን የእስራት ጊዜ በማረሚያ ቤት እንዲያሳልፍ ይገደዳል።
ይህ ግን የሞት ቅጣት ለተላለፈበት ሰው አይተገበርም። ፍርደኛው በሞት እንዲቀጣ ርዕሰ ብሔሩ ባይፈርሙ እንኳ ቀሪውን ሕይወቱን በእስር አሳልፎ “አስከሬኑ ከማረሚያ ቤት ይወጣል ማለት ነው።”

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የሞት ቅጣት እንዴት ይፈጸማል?
ከሞት ቅጣት አፈጻጸም ጋር በተያያዘ የተለያዩ አገራት የተለያዩ ዘዴዎችን ይጠቀማሉ።
እንደአምነስቲ ዘገባ ከሆነ እአአ በ2023 አራት የታወቁ የሞት ቅጣት መፈጸሚያ ዘዴዎች ያሉ ሲሆን፣ አንገትን በመቅላት የሞት ቅጣት የምትፈጽው ብቸኛዋ አገር ሳዑዲ አረቢያ ናት።
ባለፈው የፈረንጆቹ ዓመት ሰባት አገራት በስቅላት፣ ስድስቱ ደግሞ በጥይት የሞት ቅጣት ሲፈጽሙ፣ ሦስት አገራት ደግሞ ገዳይ መርፌዎችን ተጠቅመዋል።
በኢትዮጵያ ደግሞ “ወታደር ከሆነ በጥይት ተደብድቦ ይገደላል ነው የሚለው። ሲቪል ከሆነ ግን በንጉሡ ጊዜ የነበረው ሕግ በአደባባይ ይሰቀላል ይላል። ከዚያ በኋላ የመጡት ሕጎች ግን በማረሚያ ቤት ግቢ በስቅላት ይገደላል ነው የሚሉት” ብለዋል ተባባሪ ፕሮፌሰሩ።
የሞት ፍርደኞችን በስቅላት መቅጣት ኢሰብዓዊ ድርጊት ነው በሚል ሌሎች አማራጮችን ለመተግበር ውይይት እየተደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል።
ከሞት ቅጣት ጋር በተያያዘ ብዙ የሚነሱ ጉዳዮች አሉ። አንደኛው ሕብረተሰቡ ተፈጸሙ ስለሚባሉ ወንጀሎች እና በራሱ ብያኔዎችን የሚሰጥበት መንገድ ነው።
በተለይም ከማኅበራዊ ሚዲያ መስፋፋት ጋር ተያይዞ ወንጀል ተሠራ በተባለ ቁጥር ግለሰቦች የየራሳቸውን ፍርድ ያስተላልፋሉ። በፍርድ ቤት በተሰጡ ውሳኔዎች ላይም አስተያየታቸውን ይሰጣሉ።
በዚህ መልኩ አንዳንድ ወንጀሎች ሕብረተሰቡን “ስሜታዊ” ያደርጋሉ። ‘የሞት ፍርድ ሊሰጥ ይገባል’ የሚሉ አስተያየቶችም ከየአቅጣጫው ይወረወራሉ። ጉዳዩ በፍርድ ቤት የሚታይበት መንገድ ደግሞ ከዚህ የተለየ ነው።
“የዳኝነት ነጻነት ሲባል ከእንደዚህ ዓይነት ግፊቶችም ነጻ መሆን ማለት ነው። እንደ ግለሰብ ዳኞችም በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በሚያይዋቸው ድርጊቶች ስሜታዊ ሊሆኑ ይችላሉ። የነጻነቱ አንዱ መገለጫ ከመንግሥት እና ከተቃዋሚ ፓርቲ ነጻ መሆን ብቻ ሳይሆን ከራስ ስሜትም ነጻ መሆንም ነው” ይላሉ የሕግ ባለሙያው።
ስሜታዊ የሚያደርጉ ወንጀሎች ሊፈጸሙ ቢችሉም አንዳንዴ ሰው ሳይሞት፤ ገዳይ የተባለው ተመስክሮበት ከተገደለ በኋላ ሞተ የተባለው ሰው በሕይወት ሊገኝ ይችላል። “የማይመለስ ጸጸት ያጋጥማል። ይህ ሁኔታ እንዳይፈጠር ደግሞ የሞት ቅጣት ሲወሰን እና ሲፈጸም ብርቱ ጥንቃቄ ያስፈልጋል” ብለዋል።
ተባባሪ ፕሮፌሰር መሐሪ በተማሪነታቸው ወቅት የሰሙትን የሕግ ጉዳይ እንደምሳሌ ያነሳሉ።
አንድ ግሰለብ ሞተ ይባልና ጉዳዩ ፍርድ ቤት ይደርሳል። ምስክሮችም ተደራጅተው ቀርበው እሱ ነው የገደለው ይላሉ። በመስቀለኛ ጥያቄም ምስክሮችን ማስተባበል አልተቻለም። እውነት ነው ሰው ሞቷል ይባልና ገዳይ የተባለው ሰው የሞት ቅጣት ተፈርዶበት ተፈጻሚ ይሆንበታል። ከተወሰነ ዓመታት በኋላ ግን ሞተ የተባለው ሰው ይመጣል።
“ስለዚህ በቁጭት እንኳን የማትመልሰው ነገር ይሆናል ማለት ነው። የፍትህ ሂደቱ ክፍተት እንዳለበትም ያሳያል” ብለዋል ተባባሪ ፕሮፌሰሩ። ለዚህም ነው ዳኞች ከስሜታዊነት በመውጣት ግራ ቀኙን ተመልክተው መወሰን አለባቸው የሚባለው።
የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችም ይህንን ሃሳብ ይጋራሉ። ሰዎች ከተገደሉ በኋላ ንጹህ ሆነው የሚገኙበት ዕድል በመኖሩ የሞት ቅጣትን ይቃወማሉ።

የሞት ቅጣት አስፈላጊ ነው?
ሌላው ከሞት ቅጣት ጋር የሚነሳው ጉዳይ አስተማሪነቱ ነው።
በአብዛኞቹ የሞት ቅጣት በሚተላለፍባቸው አገራት ፍርዱ የሚቀመጠወው “ወንጀልን ይከላከላል ከሚል ጽንሰ ሃሳብ የተነሳ ነው” ሲል የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ጽህፈት ቤት ገልጿል።
የማኅበራዊ ሳይንስ ሊቃውንት ግን የሞት ቅጣት መኖር ወንጀልን የመከላከል ውጤቱ ያልተረጋገጠ ነው ሲሉ፣ አንዳንዶች ወንጀልን በጣም የሚከላክለው ወንጀለኞችን በቁጥጥር ስር የማዋል እና የመቀጣት ዕድል ነው ይላሉ።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እአአ በ1988 በሞት ቅጣት እና በግድያ ምጣኔ መካከል ያለውን ግንኙነት የሚመለከት የዳሰሳ ጥናት አካሂዶ ነበር።
ይህ ጥናት በ1996 ማሻሻያ ተደርጎበታል። “የሞት ቅጣት ከዕድሜ ልክ እስራት የበለጠ ወንጀልን የመከላከል አቅም እንዳለው ሳይንሳዊ ማስረጃዎችን ማቅረብ አልተቻለም” ሲልም ደምድሟል።
ጉዳዩ አከራካሪ መሆኑን የሕግ ፕሮፌሰሩም ይጋሩታል።
የሞት ቅጣት ሊኖር አይገባም የሚሉ አገራት መኖራቸውን የሚጠቅሱት ተባባሪ ፕሮፌሰር መሐሪ፣ የሞት ቅጣት ሲፈረድ ማኅበረሰቡ ከወንጀለኛው የተሻለ አይደለም፤ የተሻለ መሆኑን ማሳየት አለበት የሚሉም አሉ ብለዋል።
“የገደለ ይሙት ካልን ዐይን ያጠፋ ዐይኑ ይጥፋ ዓይነት ባህላዊ ውሳኔ ነው የሚሆነው። እንዲያውም የሠለጠነ ማኅበረሰብ የሞት ቅጣትን ከሕጉ ማውጣት አለበት የሚሉ አገራትም አሉ። በሌላ በኩል ደግሞ ሕጉን አናወጣውም አንዳንዴ በሚያስፈልጋቸው ላይ መፈጸም አለብን የሚሉም አሉ” ሲሉ ያስረዳሉ።
በአሁኑ ወቅት በዓለም ላይ ያሉ በርካታ አገራት የሞት ቅጣትን ከሕጋቸው አውጥተዋል። በአውሮፓውያኑ 1991 የሞት ቅጣትን ያስወገዱ አገራት ቁጥር 48 የነበሩ ሲሆን፣ ይህ ቁጥር በ2023 ወደ 112 አገራት ከፍ ብሏል።
ዘጠኝ አገራት በጣም ከባድ ለሆኑ ወንጀሎች ብቻ የሞት ቅጣትን የሚተገበሩ ሲሆን፣ 23 የሞት ቅጣት ያለባቸው አገራት ደግሞ ቢያንስ ለአስር ዓመታት ፍርዱን ተግባራዊ አላደረጉትም።
ቅጣት የሚተላለፈው ተቀጪውን እና ሕብረሰተሰቡን ለማስተማር ነው። የሞት ቅጣት ግን ማኅበረሰቡ በወንጀሉ ላይ ያለውን መራራ ምላሽ እና እንደተንገሸገሸ የሚገለጸበት መንገድ ተደርጎ ይወሰዳል ያሉት የሕግ ባለሙያው “የሞት ቅጣት የተወሰነበት ግለሰብ አይማርም፣ ሌሎችን የማስተማሩ ጉዳይ ነው የሚያዘነብለው” ብለዋል።












