በጉጂ የመንግሥት ኃይሎች እና የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ግድያ እና ፆታዊ ጥቃቶች መፈጸማቸው ተነገረ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በኦሮሚያ ክልል በጉጂ ዞኖች ከሕግ ውጪ ግድያ እና ጾታዊ ጥቃቶችን የሚጨምሩ ከፍተኛ የመብት ጥሰቶች በመንግሥት እና በታጣቂዎች ኃይሎች እየተፈጸሙ መሆኑን አንድ ሪፖርት አመለከተ።
አገር በቀሉ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት የመብቶች እና ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከል (ካርድ) “የጉጂ ሰቆቃ፡ በኦሮሚያ ጉጂ ዞኖች ውስጥ የሚፈጸሙ ከባድ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች” በሚል ርዕስ ባወጣው ሪፖርት በዞኖቹ የሚፈጸሙ የመብት ጥሰቶችን ዘርዝሯል።
ካርድ የመንግሥት ኃይሎች እንዲሁም ከመንግሥት ጋር እየተዋጋ ያለው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት በጉጂ ሁለት ዞኖች በሚገኙ ነዋሪዎች ላይ ከሕግ ወጪ ግድያ፣ ጾታን መሠረት ያደረገ ጥቃት፣ የጅምላ እስር፣ ሰውን መሰወር፣ ድብደባ፣ ኢሰብዓዊ አያያዝ፣ ማፈናቀል የንብረት ውድመት እና ዘረፋ እየፈጸሙ ነው ብሏል።
ማዕከሉ በጉጂ እና በምዕራብ ጉጂ ዞኖች በመንግሥት እና በታጣቂዎች መካከል የቀጠለው ግጭት “ንፁሃን ዜጎች ላይ ከፍተኛ ስቃይ እና ዘርፈ ብዙ ዘግናኝ ድርጊቶችን አስከትሏል” ብሏል።
ካርድ በሁለቱ ኃይሎች በሰላማዊ ዜጎች ላይ ለደረሰው አስከፊ እና ከባድ ሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ፍትሕ ለመስጠት ተገቢው የማጣራት ሥራ አለመሠራቱን እንዲሁም ጥቃት አድራሾችን በሕግ ተጠያቂ ለማድረግ የተደረገ ጥረት የለም ብሏል።
የመንግሥት ኃይሎችም ሆኑ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ሰዎችን ከታጣቂዎች ወይም ከመንግሥት ጋር “አብራችኋል ወይም ግንኙነት አላችሁ” በሚል ግድያ መፈጸማቸውን የካርድ ሪፖርት ያሳያል።
በሪፖርቱ የሕግ ወጥ ግድያዎች ማሳያ ሆነው ከቀረቡት ማሳያዎች መካከል አንዱ በጉጂ ዞን ሳባ ቦሩ ወረዳ የተፈጸመው የጀምላ ግድያ ተጠቃሽ ነው።
ካርድ ጥር 2016 ዓ.ም. የዞኑ ነዋሪ የነበሩት የ52 ዓመቱ አዱላ ሳኒ እና ባለቤታቸውን ጨምሮ 10 ሰዎች በኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት መገደላቸውን ገልጿል።
ኅዳር 16/2016 ዓ.ም. ደግሞ በጉጂ ዞን ዋዳራ ወረዳ በመንግሥት እና በታጣቂዎች መካከል የተደረገ ውጊያን ተከትሎ የመንግሥት ኃይሎች ከኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ጋር ግንኙነት አላቸው ብለው የጠረጥሯቸውን ሦስት ሰላማዊ ዜጎች ከሕግ ውጪ ገድለዋል።
ፆታን መሠረት ያደረጉ ጥሰቶች
ካርድ ግጭቱ በተለይ ደግሞ ተጋላጭ በሆኑ የማኅበረሰቡ ክፍል ላይ አስከፊ መዘዝ አስከትሏል ብሏል።
ሪፖርቱ እንደሚያሳየው የሁለቱም ወገኖች ተዋጊዎች በሴቶች እና ልጃገረዶች ላይ ፆታን መሠረት ያደረጉ መብት ጥስት ፈጽመዋል።
እንደ ማሳያም በመልካ ሶዳ ወረዳ ዳዳ ጭምአ ገፋርሳ ቀበሌ ፍየል እየጠበቀች የነበረች የስምንት ዓመት ታዳጊ ነሐሴ 16/ 2015 ዓ.ም. “በአምስት የመንግሥት ወታደሮች ተደፍራለች” ብሏል።
ሪፖርቱ “የመንግሥት ወታደሮቹ ልጅቷን ቀኑን ሙሉ ያለማቋረጥ ደፍረዋታል። ራሷን በሳትች ጊዜ ወደ ጫካ ጥለዋት ሄዱ። በኋላ ቤተሰቦቿ ጫካ ውስጥ አግኝተዋት ወደ መልካ ሶዳ ሆስፒታል ወሰዷት”
በሳባ ቦሩ ወረዳ ሳቢቹ ቀበሌ ደግሞ አንዲት የ12 ዓመት ታዳጊ ታኅሣሥ 27/2014 ዓ.ም. ከብት እየጠበቀች ሳለ “በሁለት የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት አባላት መደፈሯ” በሪፖርቱ ተመላክቷል።
ታዳጊዋ “በሕይወት ከምኖር ቢገድሉኝ ይሻለኝ ነበር.... ከዚህ በኋላ በሕይወት አልኖርም....ምንም ሊያጽናናኝ አይችልም...ደስታን የሚያመጣልኝ ምንም ነገር የለም” በማለት ለጥናት ቡድን ስለመናገሯ በሪፖርቱ ተጠቅሷል።
የጅምላ እስርን በተመለከተ ባለሥልጣናት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ሰዎችን ያለ በቂ ምክንያት እና ክስ ሳይመሰርቱባቸው ለእስራት ዳርገው እንደሚገኙ ሪፖርቱ አመልክቷል።
በሁለቱ የኦሮሚያ ዞኖች በሁለቱ ተዋጊ ኃይሎች የተፈጸሙት ከሕግ አግባብ ውጪ ግድያ፣ የጅምላ እስር፣ የፆታ ጥቃት እና የንብረት ውድመትን የሚጨምሩ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ለቤተሰብ መፍረስ፣ ለጤና ችግር እና ከማኅብረሰብ የመገለል ችግር አስከትሏል።
ከተለያዩ የመረጃ ምንጮችን ዋቢ በማድረግ፤ በዴስክ ጥናት እንዲሁም የመስክ ጉብኝቶችን እና ከዋና ባለድርሻ አካላት ጋር የተደረጉ ቃለ ምልልሶችን በመጠቀም ሪፖርቱን ያጠናቀረው የመብቶች እና ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከል (ካርድ)፤ በዜጎች ላይ እየደረሰውን ስቃይ ለመግታት ተዋጊ ኃይሎች ግጭት እንዲያቆሙ እና ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ሕግጋትን እና የሰብዓዊ መብት መስፈርቶችን እንዲያከብሩ ጠይቋል።
ማዕከሉ የደረሱ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እና ረገጣዎች በገለልተኛ አካል ተመርምረው ወንጀለኞቹን በመለየት ለፍትሕ እንዲቀርቡ ጨምሮ ጠይቋል።












