737 ማክስ 8 አውሮፕላን በአደገኛ ሁኔታ ከተናጠ በኋላ በአሜሪካ ቦይንግ ላይ ምርመራ ተከፈተበት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የደኅንነት ጥያቄ ሲነሳበት የቆየው ቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላን በረራ ላይ ሳለ በአደገኛ ሁኔታ ወደ ግራ እና ቀኝ ከተናጠ በኋላ የአሜሪካ የአቪዬሽን ባለሥልጣናት አውሮፕላን አምራቹ ላይ ምርመራ ከፈቱ።
ንብረትነቱ የሳውዝዌስት አየር መንገድ የሆነው አውሮፕላን በዘርፉ ‘ደች ሮል’ ተብሎ የሚጠረው ወደ ግራ እና ቀን የመላጋት ችግር ሲገጥመው በተሳፋሪዎች ላይ የደረሰ ጉዳት ባይኖርም፣ አውሮፕላኑ ግን ከፍተኛ ጉዳት ደርሶበት “ለበረራ ብቁ” እንዳይሆን አድርጎታል ተብሏል።
የአሜሪካ አቪዬሽን አስተዳደር ግንቦት 17/2016 ዓ.ም. ያጋጠመው ክስተት ከፊኒክስ አሪዞና ወደ ኦክላንድ ካሊፎርኒያ እየበረረ በነበረ አውሮፕላን ላይ መሆኑን ገልጿል።
ይህ ወደ ግራ እና ቀኝ ከፍተኛ መናጥ የገጠመው አውሮፕላን ከጥቂት ዓመታት በፊት በኢትዮጵያ እና በኢንዶኔዢያ ተከስክሰው 346 ሰዎች ሕይወታቸውን ካሳጠው አውሮፕላን ጋር ተመሳሳይ ነው።
እነዚህን አደጋዎች ተከትሎ በመላው ዓለም ከ18 ወራት በላይ ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላኖች ከበረራ ታግደው መቆየታቸው ይታወሳል።
ከእነዚህ አደጋዎች በኋላ ቦይንግ በተለይ የማክስ ዝርያ ካላቸው አውሮፕላኖቹ ጋር በተያያዘ የተለያዩ ምርመራዎች ተከፍተውበት በአሜሪካ የአቪዬሽን ባለሥልጣናት ክትትል እየተደረገበት ይገኛል።
ሚያዝያ ወር ውስጥ 2016 ዓ.ም. የሳውዝዌስት አየር መንገድ ቦይንግ 737-800 አውሮፕላን ለበረራ እየተነሳ ሳለ የሞተሩ ሽፋኑ ተገንጥሎ ከወደቀ በኋላ ምርመራ እየተደረገ ነው።
ከዚህ በተጨማሪም ከጥቂት ወራት በፊት የአላስካ አየር መንገድ 737 ማክስ 9 አውሮፕላን አየር ላይ ሳለ የአደጋ ጊዜ መውጫ በሩ ተገንጥሎ መውደቁ መነጋገሪያ ሆኖ ነበር።
የአሜሪካ የኢቪዬሽን አስተዳደር ግንቦት 17 አውሮፕላኑ ከፍተኛ መናጥ ካጋጠመው በኋላ አብራሪዎች አውሮፕላኑን መልሰው መቆጣጠር በመቻላቸው በሰላም አርፏል ብለዋል።
ይሁን እንጂ አገልግሎት መስጠት ከጀመረ የሁለት ዓመት ብቻ የሆነው የአውሮፕላኑ የኋላ ክፍል በክስተቱ ትልቅ ጉዳት ደርሶበታል ሲሉ ባለሥልጣናት አስታውቀዋል።
በቅርቡ የአየር ጉዞ ደኅንነት ተከታታዮች ቦይንግ በአውሮፕላን ምርት ሂደቱ ለጥራት ከፍተኛ ትኩረት እየሰጠ አይደለም ሲሉ እየከሰሱ ነው።
ቦይንግ የማክስ ዝርያ የሆኑ አውሮፕላን ምርቶቹን በመቀነስ እየተነሱ ያሉ ችግሮችን መቅረፍ ያስችለኛል ያለውን ተግባራዊ ዕቅድ ለአቪዬሽን ባለሥልጣናት አቅርቧል።












