ወጣት ወንዶችን ከተለያዩ አገራት እያጠመደች ለሩሲያ እንዲዋጉ የምታደርገው ሴት

አዛርኒክ ለጦርነት ከተመለመሉ ወጣቶች ጋር በሲቪል ልብስ የተነሳችው ፎቶ

የፎቶው ባለመብት, Telegram

የምስሉ መግለጫ, አዛርኒክ ከአዲስ ተመልማዮች ጋር ፎቶ እየተነሳች ትለጥፋለች

የኦማር ፓስፖርት ጠርዙ በእሳት እየተቃጠለ ነው። ተንቀሳቃሽ ምሥሉ ውስጥ "በጣም ይቀጣጠላል" ስትል አንዲት ፊቷ የማይታይ ሴት በሩሲያኛ ታወራለች።

የ26 ዓመቱ ሶሪያዊ ኦማር የግንባታ ሠራተኛ ነው። ለዘጠኝ ወራት ያህል ከሩሲያ ጦር ጋር ሆኖ በዩክሬን ሲዋጋ ቆይቷል። ቪድዮው የደረሰው ይሄኔ ነው።

የሴትየዋን ድምፅ ያውቀዋል። ፖሊና አሌክሳንድሮቭና አዛርኒክ ትባላለች። ዜግነት ይሰጥሀል፣ ሥራም ታገኛለህ በሚል ለሩሲያ እንዲዋጋ ያገዘችው እሷ እንደሆነች ይናገራል። አሁን ቁጭት እያንገበገበው ነው።

ለደኅንነቱ በመስጋት ስሙን የቀየረው ኦማር ከዩክሬን ሆኖ በተከታታይ የድምፅ መልዕክት ይልካል። እንዴት ሳያስበው የሚያስፈራ የጦርነት አዘቅት ውስጥ እንደገባ ያስረዳል።

እሱ እንደሚለው አዛርኒክ 3 ሺህ ዶላር ከከፈልከኝ ጦርነት የሌለበት ቦታ እልክሀለሁ ስልት ቃል ገብታለታለች። ነገር ግን የ10 ቀናት ሥልጠና ከወሰደ በኋላ ከለየለት ጦርነት መካከል ገባ። ገንዘቡን አልከፍልም ሲላት ነው ፖስፖርቱን ያቃጠለችበት።

በጦርነቱ ላይ አልሳተፍም ባለ ጊዜ አዛዦቹ ሊገድሉት አሊያም ሊያስሩት እንደሚችሉ እንዳስጠነቀቁት ይናገራል።

"ተጭበርብረናል. . . ይህች ሴት አጭበርባሪ ናት። ዋሾ ናት" ይላል ኦማር።

የቢቢሲ አይ የምርመራ ዘገባ የ40 ዓመቷ የቀድሞ አስተማሪ አዛርኒክ እንዴት የቴሌግራም ቡድን ተጠቅማ ከደሀ አገራት የመጡ ወጣት ወንዶችን በማታለል ለሩሲያ ጦር እንደምትመለምል ተመልክቷል።

በፈገግታ የምትቀርፃቸው ቪድዮዎች እና ልጥፎች "የአንድ ዓመት ኮንትራት ለወታደራዊ አገልግሎት" ይላሉ።

ቢቢሲ ያረጋገጣቸው 500 የሚደርሱ "ጥሪዎች" (ኢንቪቴሽን) የተባሉ ወረቀቶችን ያገኙ ሰዎች እንዴት ወደ ሩሲያ እንዲገቡና ጦር ኃይሉን እንዲቀላቀሉ እንደሚፈቀድላቸው ይገልጻል። አብዛኞቹ ከሶሪያ፣ ከግብፅ እና ከየመን የመጡ ወጣት ወንዶች ናቸው። ስማቸውን ለማስመዝገብ የፖስፖርት ዝርዝር መረጃቸውን ለእሷ ልከዋል።

ነገር ግን ተመልማዮቹ እና ቤተሰቦቻቸው ለቢቢሲ እንደተናገሩት ወጣቶቹ ጦርነት ላይ እንደማይሳተፉ ቃል ከመግባቷ ባለፈ እስከ አንድ ዓመት ድረስ መውጣት እንደማይችሉ በግልፅ አላሳወቀችም። በተጨማሪ አሻፈረኝ የሚሉ ወጣቶችን ታስፈራራለች።

ቢቢሲ ግለሰቧን አግኝቶ ጥያቄዎች ቢያቀርብላትም ወቀሳዎቹን አስተባብላለች።

ቢቢሲ ያናገራቸው አስራ ሁለት ቤተሰቦች በእሷ ተመልምለው የሄዱ ወጣቶች ያሉበት አይታወቅም አሊያም ሞተዋል ይላሉ።

አዛርኒክ ካሜራ እያየች ቅስቀሳ ስታደርግ ከለጠፈችው ቪድዮ የተነሳ ፎቶ

የፎቶው ባለመብት, Telegram

የምስሉ መግለጫ, አዛርኒክ ወጣቶች የሩሲያን ጦርን እንዲቀላቀሉ የሚያነሳሱ ቪድዮዎች ትለጥፋለች

ሩሲያ በአገሯ ውስጥ ለውትድርና የምትመዘግባቸው ሰዎች ቁጥር ጨምሯል። እስር ቤት ያሉ ሰዎችም ተመልምለዋል። አልፎም ለምዝገባ የሚሰጠው ገንዘብ ዳጎስ እንዲል አድርጋለች። ይህ የሆነው በዩክሬን ለምታካሂደው ጦርነት ቢሆንም የሞቱባት ሰዎች ቁጥር ቀላል የሚባል አይደለም።

የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃልኪዳን ድርጅት (ኔቶ) እንደሚለው ጦርነቱ ከተጀመረበት የአውሮፓውያኑ 2022 ጀምሮ ከአንድ ሚሊዮን በላይ የሩሲያ ወታደሮች ተገድለዋል አሊያም ቆስለዋል። በ2025 ታኅሣሥ ወር ብቻ 25 ሺህ መገደላቸውን ኔቶ ይገልጻል።

የቢቢሲ ሩሲያ ቋንቋ አገልግሎት ከሟቾች ታሪክ እና ለሕዝብ ይፋ ከሆኑ መረጃዎች አሰባስቦ ያሰናዳው ዘገባ እንደሚያሳየው ባለፈው የአውሮፓውያኑ ዓመት በርካታ የሩሲያ ወታደሮች ዩክሬን ውስጥ ተገድለዋል።

የሩሲያን ጦር የተቀላቀሉ የውጭ አገር ዜጎች ምን ያህል እንደሆኑ በትክክል ማጣራት አስቸጋሪ ቢሆንም የቢቢሲ ሩሲያ ትንታኔ ከኩባ፣ ኔፓል እና ሰሜን ኮሪያ ጨምሮ ከሌሎች አካባቢዎች የመጡ ሰዎች ቁጥር 20 ሺህ ገደማ ይደርሳል ይላል።

ዩክሬንም በጦርነቱ ቀላል የማይባል ወታደር የሞተባት ሲሆን፣ በርካታ የውጭ አገር ዜጎችን ለውትድርና መዝግባለች።

'በየቦታው ሬሳ'

ኦማር አዛርኒክን ለመጀመሪያ ጊዜ ያናገራት ከሌሎች 14 ሶሪያዊያን ጋር ሞስኮው አየር ማረፊያ ውስጥ ሳሉ ነበር።

ሶሪያ ውስጥ ሥራ ማግኘት አስቸጋሪ ከመሆኑም በላይ ክፍያው እጅግ ዝቅ ያለ ነው። ኦማር እንደሚለው መጀመሪያ የቀረበላቸው የሥራ አማራጭ ሩሲያ ውስጥ የሚገኙ የነዳጅ ማምረቻን መጠበቅ ነው። ወደ ሞስኮው ካመሩ በኋላ ነው እንደተጭበረበሩ የገባቸው።

አማራጭ አጥተው ኢንተርኔት እያሰሱ ሳለ አንዱ የአዛርኒክን የቴሌግራም ቡድን አግኝቶ የፅሑፍ መልዕክት ላከላት።

አየር ማረፊያ ሳሉ በአጭር ሰዓታት ጊዜ ውስጥ መጥታ አገኘቻቸው። ቀጥሎ በባቡር ወደ ምዕራብ ሩሲያዋ ብራያንስክ ከተማ እንደወሰደቻቸው ይናገራል።

እዚያ ከደረሱ በኋላ የሩሲያን ጦር ለአንድ ዓመት ለመቀላቀል 5 ሺህ ዶላር፣ በየወሩ ደግሞ 2500 ዶላር እንደሚሰጣቸው ቃል ገባችላቸው። ይህ ገንዘብ ፍፁም ያልገመቱት ነበር።

ኦማር እንደሚለው የኮንትራት ውሉ በሩሲያ ቋንቋ የተፃፈ ነው። ከመሐከላቸው ቋንቋውን የሚችል የለም። ቀጥላ የሩሲያ ዜግነት ታገኛላችሁ በማለት ፓስፖርታቸውን ወሰደች።

ለምዝገባ ከተከፈላቸው ገንዘብ ላይ 3 ሺህ ዶላር ለእሷ ከሰጧት ደግሞ ግንባር ከመሄድ ልታድናቸው እንደምትችል ቃል እንደገባችላቸው ይናገራል።

የዩክሬን ታንክ ሲተኩስ የሚያሳይ ፎቶ

የፎቶው ባለመብት, Roman Chop/Global Images Ukraine via Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ኦማር በጦር ግንባር ያየውን በጣም የሚያስፈራ እንደሆነ ይናገራል

ነገር ግን እሱ እንደሚለው በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ራሱን የጦርነት ግንባር ላይ አገኘው። የወሰደው ሥልጠና የ10 ቀናት ነው። የጦርነት ልምድም የለውም።

"እዚህ መሞታችን መቶ በመቶ አይቀሬ ነው" ይላል ለቢቢሲ ምርመራ ቡድን የላከው የድምፅ መልዕክት።

"በጣም በርካቶች ተጎድተዋል፣ ፍንዳታ ከዚህም ከዚያም ይሰማል። ጥይት ይጮሀል። በፍንዳታው ባትሞት እንኳ በፍንጣሪው ተመትተህ መሞትህ የማይቀር ነው" ይላል ግንቦት 2024 የላከው መልዕክት።

"በየቦታው ሬሳ ይታያል። ሬሳ ተረማምጄ አልፍያለሁ። ፈጣሪ ይቅር ይበለኝ" ይላል በሚቀጥለው ወር የላከው ድምፅ።

"አንድ ሰው ሲሞት በቆሻሻ መጣያ ፌስታል አስረው ዛፍ ሥር ሲጥሉት በዓይኔ በብረቱ አይቻለሁ" ሲል ያክላል።

አንድ ዓመት ሊሞላው ሲቃረብ ጦር ኃይሉ የወታደሮችን ውል እስከ ጦርነቱ ፍፃሜ ማራዘም እንደሚችል የሚያትት በ2022 ሩሲያ ያወጣቸው መመሪያን አገኘ። አዛርኒክ ይህን አልነገረችውም።

"ውሌን ካራዘሙት አለቀልኝ - የፈጣሪ ያለህ" ይላል።

ውሉ ተራዘመ።

ከዩኒቨርሲቲ የተመለመለ

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የአዛርኒክ የቴሌግራም ቻነል 21 ሺህ ተከታዮቸ አሉት። የሩሲያን ጦር መቀላቀል የሚሹ ፓስፖርታቸውን 'ስካን' አድርገው እንዲልኩ በቻነሏ ለጥፋለች። አንዳንድ ጊዜ የተመዝጋቢዎች ስም ዝርዝር ያለበት የጥሪ ወረቀት ትለጥፋለች።

ቢቢሲ ያጣራቸው ከ490 በላይ የሚሆኑ የጥሪ ወረቀቶች እንደሚያሳዩት ከየመን፣ ከሶሪያ፣ ከግብፅ፣ ከሞሮኮ፣ ከኢራቅ፣ ከአይቮሪ ኮስት እና ከናይጄሪያ የተመለመሉ ወጣቶችን ስም ዝርዝር ይዟል።

ምልመላው "ዓለም አቀፍ ንዑስ ባታሊዮንን" ለመቀላቀል እንደሆነ ትጽፋለች። በሕገ-ወጥ መንገድ ወደ ሩሲያ የገቡና የቪዛቸው ቀን ያለፈበት ሰዎችም መመዝገብ እንደሚችሉ ትናገራለች።

ኦማርን ጨምሮ በእሷ የተመለመሉ 8 የውጭ አገር ተዋጊዎችን አናግረናል። 12 የተገደሉ አሊያም ያሉበት የማይታወቅ ተዋጊዎችን ቤተሰቦችም አግኝተናል።

ብዙዎቹ እንደሚሉት አዛርኒክ ተመልማዮቹን አጭበርብራለች አሊያም የተሳሳተ መረጃ ሰጥታለች። ያናገርናቸው ሰዎች እንደሚሉት ወጣቶቹ ወደ ጦርነት እንደሚገቡ ቢያውቁም ግንባር ላይ እንሳተፋለን ብለው አላሰቡም።

ኦማርን ጨምሮ አብዛኛዎቹ በቂ ልምድ እንደሌላቸው እንዲሁም ከአንድ ዓመት በኋላ መውጣቱ እንደሚችሉ ነው የሚያውቁት።

ስሙ ለዚህ ፅሑፍ ሲባል የተቀየረው ግብፃዊው ዩሴፍ እንደሚለው ወንድሙ ሞሐመድ በሩሲያ የካተርሪንበርግ ትምህርት ለመማር ያቀናው በ2022 ነው።

ነገር ግን ክፍያ መክፈል አለመቻሉን እና ፖሊና የምትባል ሴት እርዳታ እያደረገችለት እንደሆነ ለቤተሰቦቹ እንደተናገረ ዩሴፍ ያስረዳል። ግለሰቧ በሩሲያ ጦር ውስጥ ካገለገለ የዩኒቨርሲቲ ትምህርቱን መቀጠል እንደሚችል ቃል ገባችለት።

"መኖሪያ ቤት እና ዜግነት እንደሚያገኝ ቃል ገባችለት. . . ወርሀዊ ክፍያን ጨምሮ" ይላል። "ድንገት ወደ ዩክሬን ተላከ። ራሱን ጦርነት ውስጥ አገኘው" ሲል ያክላል ዩሴፍ።

ለመጨረሻ ጊዜ ስልክ የደወለው ጥር 2024 ነበር። ከአንድ ዓመት በኋላ ከሩሲያ ቁጥር በቴሌግራም የተላከ መልዕክት የሞሐመድ አስከሬንን የሚያሳይ ፎቶ ያዘለ ነበር። ቤተሰቡ ሞሐመድ ከአንድ ዓመት በፊት እንደተገደለ ያወቀው ይሄኔ ነው።

'ያበዱም አሉ'

በሩሲያ ጦር ውስጥ ያገለገለው ሶሪያዊው ሀቢብ "አዛርኒክ ለሩሲያ ጦር ከሚመልመሉ ዋና ዋና ሰዎች መካከል አንዷ ናት" ይላል። በቪድዮ ለመቅረብ ባያመነታም ትክክለኛ ስሙ እንዲታወቅ ግን አልፈለገም።

ሀቢብ እንደሚለው "ከአዛርኒክ ጋር ለሦስት ዓመታት ያህል ወደ ሩሲያ የሚጋብዝ የጥሪ ወረቀት በማዘጋጀት" ሠርቷል። ተጨማሪ መረጃ ከመስጠት የተቆጠበ ሲሆን፣ እኛም የነበረውን ሚና በትክክል ማጣራት አልቻልንም። በ2024 የተነሳ ፎቶ ላይ አጠገቡ አዛርኒክ ትታያለች።

ከደቡብ ምዕራቧ የሩሲያ ግዛት ቮሮኔዥ የመጣችው አዛርኒክ ከቴሌግራም ገጿ በፊት በፌስቡክ ከአረብ አገራት ለሚመጡ ተማሪዎች እርዳታ ታደርግ ነበር።

በሩሲያ ጦር ያገለገለው ሶሪያዊው ሀቢብ
የምስሉ መግለጫ, ሀቢብ "ፖሊና ወጣቶች እንደሚሞቱ እያወቀች ነው የምትመለምላቸው" ሲል ለቢቢሲ ይናገራል

ሀቢብ እንደሚለው አብዛኞቹ የውጭ ተመልማዮች የሚመጡት የጥበቃ ሥራ ለመሥራት በማሰብ ነው። "የሚመጡት አረቦች ወዲያው ነው የሚሞቱት። ያበዱም አሉ። ሬሳ ለማየት እንኳ ከባድ ነው" ይላል።

ሀቢብ እንደ ኦማርን በወታደራዊ ማሠልጠኛ ተቋም እንዳገኛቸው ይናገራል። "ዜግነት እና ጥሩ ደመወዝ እንዲሁም ደኅንነታቸው እንደሚጠበቅ ቃል ገብታለች። ነገር ግን አንድ ጊዜ ውሉ ከተፈረመ የምትወጣበት አማራጭ የለም።

"መሣሪያ እንዴት መጠቀም እንዳለባቸው አያውቁም። ቢመቱ እንኳ መልሰው መተኮስ አይችሉም። ካልተኮስክ ትገደላለህ። ፖሊና ወጣቶች እንደሚሞቱ እያወቀች ነው የምትመለምላቸው።"

እሱ እንደሚለው "ለምትመለምለው ወታደር በነብስ ወከፍ 300 ዶላር ይሰጣታል።" ቢቢሲን ይህን መረጃ ማጣራት ባይችልም ሌሎች ተመልማዮች ገንዘብ እንደሚከፈላት እንደሚያምኑ ነግረውናል።

'ምንም በነፃ የሚሆን ነገር የለም'

በ2024 አጋማሽ አዛርኒክ የለጠፋቻቸው መልዕክቶች ተመልማዮች "በጦርነት እንደሚሳተፉ" እና በውጊያ ወቅት የውጭ አገር ዜጎች መሞታቸውን መጠቆም ጀመሩ።

ጥቅምት 2024 በለጠፈችው ተንቀሳቃሽ ምሥል "ሁላችሁም ወደ ጦርነት እንደምትሄዱ መቸም ትረዳላችሁ። ምንም ሳትሰሩ፣ አምስት ኮከብ ሆቴል እያረፋችሁ የሩሲያ ፓስፖርት እንደምታገኙ ታስባለችሁ? ምንም በነፃ የሚሆን ነገር የለም" ይላል።

በ2024 አዛርኒክ ለአንዲት ልጇ ወደ ጦርነት ለሄደ እናት የላከችውን የድምፅ መልዕክት ቢቢሲ አግኝቷል።

አዛርኒክ "ስለ ሩሲያ ጦር ክፉ ተናግረሻል" በሚል በአስፀያፊ ቃላት የተሞላ ማስፈራሪያ ልካለች። የልጇ ሕይወት አደጋ ላይ እንደሚወድቅም ታስፈራራለች።

ቢቢሲ በተደጋጋሚ አዛርኒክን ለማግኘት ሞክሯል። መጀመሪያ ወደ ሩሲያ ከመጣን ቃለ-ምልልስ ለመስጠት ፈቃደኛ መሆኗን ተናገረች።

ነገር ግን ቢቢሲ በደኅንነት ስጋት ምክንያት ይህን ጥያቄዋን ውድቅ አድርጓል። ቀጥሎ ስልክ ደውለን ተመልማዮች ጦር ግንባር እንደማይሄዱ ተነግሯቸዋል ብለን ስንጠይቃት ስልኩን ዘጋችው።

በመቀጠል በላከቻቸው የድምፅ መልዕክቶች ሥራችን "ፕሮፌሽናል" አይደለም በማለት በስም ማጥፋት እንደምትከስ ተናገረች። "የተከበሩ አረቦች ወቀሳዎቻቸውን አሽቀንጥረው መጣል ይችላሉ" አለች።

ቢቢሲ የሩሲያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና መከላከያ ሚኒስቴርን ለማናገር ቢሞክርም ምላሽ አላገኘም።

ሀቢብ፣ አዛርኒክ ከሌሎች የወታደር ልብ ከለበሱ ሰዎች ጋር የተነሱት ፎቶ

የፎቶው ባለመብት, Telegram

የምስሉ መግለጫ, በአዛርኒክ ቴሌግራም ገፅ ጥር 2024 የተለጠፈ ፎቶ ሀቢብ አጠጓብ ቆሞ ያሳያል

ፕሬዝደንት ፑቲን በመጋቢት 2022 ከመካከለኛው ምሥራቅ ለመዋጋት የሚመጡ ሰዎች በርዕዮተ ዓለም እንጂ በገንዘብ ተነሳስተው እንዳልሆነ ተናግረዋል።

ቢቢሲ ሌሎች ሁለት የቴሌግራም ቻነሎች በአረብኛ ቋንቋ ተመሳሳይ ምልመላ እንደሚያደርጉ ደርሶበታል። አንደኛው የጥሪ ወረቀት የሚለጥፍ ሲሆን ሌላኛው ደግሞ የሩሲያ ጦርን ለመቀላቀል ጠርቀም ያለ ገንዘብ ቃል ይገባል።

ባለፈው መስከረም የኬንያ ፖሊስ ዜጎችን ሥራ እንሰጣለን በማለት ወደ ዩክሬን ጦርነት የሚወስዱ ናቸው ያላቸውን "ቡድኖች" ሰንሰለት መበጠሱን አስታውቋል።

የጦርነት ጥናት ተቋም ተመራማሪ የሆኑት ካቴሪና ስቴፓኔንኮ አንዳንድ የሩሲያ ግዛቶች ሩሲያዊያን እና የውጭ አገር ዜጎችን ለሚመለምሉ ሰዎች 4 ሺህ ዶላር ይሰጡ ነበር ይላሉ።

ከዚህ ቀደም የሩሲያ መንግሥት እንደ ቫግነር ቡድን ያሉ የግል ቅጥረኞችን እንደሚጠቀም እና ታራሚዎችን ከእስር ቤት ይመለምል እንደነበርም ይናገራሉ።

ሀቢብ ለበርካታ አዛዦች ጉቦ ሰጥቶ አሁን ወደ ሩሲያ እንደተመለሰ ይናገራል። ኦማርም የሩሲያ ዜግነት እንዳገኘ እና አሁን ሩሲያ ውስጥ እንዳለ ነግሮናል። ከእሱ ጋር የዘመቱ ሁለት ሶሪያዊያን መሞታቸውን ቤተሰቦቻቸው ነግረውናል።

አዛርኒክ "እንደ ቁጥር አሊያም እንደ ገንዘብ ነው የምታየን። የሰው ልጅ አንመስላትም" ይላል። "ላደረገችን ነገር ይቅር አንላትም።"