የኢራን መንግሥት እጣ ፈንታ ምን ይሆናል? አሜሪካ እና እስራኤልስ ለምን አሁን ጥቃት ሰነዘሩ?

የፎቶው ባለመብት, EPA
የኢራን መንግሥት ሕልውናው አደጋ ውስጥ መውደቁን ተንታኞች ይናገራሉ። አሜሪካ እና እስራኤል የከፈቱት የተቀናጀ ወታደራዊ ጥቃት የኢራንን መንግሥት የመለወጥ አላማ አንግቧል።
ከስድስት ወራት በፊት ኢራን እና እስራኤል ለ12 ቀናት ተዋግተው ነበር። አሁን ላይ እስራኤል እና አሜሪካ የኢራን ወታደራዊ መቀመጫዎችን ዒላማ በማድረግ ጥቃት አድርሰዋል።
ኢራን በእስራኤል ላይ የአጸፋ እርምጃ ወስዳለች። የእስራኤል መከላከያ እንዳለው፤ የአሜሪካ ወይም አጋሮቿ ወታደራዊ መቀመጫ በሚገኝባቸው ከተሞች ማለትም በዱባይ፣ ዶሀ፣ ባሕሬን እና ኩዌት ላይም ኢራን ጥቃት ፈጽማለች።
ለምን አሁን?
በዩሮፒያን ካውንስል ኦን ፎሬን ሪሌሽንስ ከፍተኛ ተመራማሪ የሆኑት ኤሊ ገርናማያህ እንደሚሉት፤ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አሁን ላይ ለምን ጥቃት ሰነዘሩ? ከሚለው ጥያቄ ጀርባ ፖለቲካዊ ምክንያት ማስቀመጥ ይቻላል።
"የትራምፕ ግብ የኢራንን መንግሥት መለወጥ መሆኑ ግልጽ ነው። ለኢራን መንግሥት እጅ መስጠት አይፈልጉም" ይላሉ።
ትራምፕ በትሩዝ ሶሻል ማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት፤ የኢራን ወታደሮች እጃቸውን ካልሰጡ "ሞት ይጠብቃቸዋል" ብለዋል።
"ኢራናውያን መንግሥታችሁን ለመቀየር በዚህ ትውልድ አንዴ ብቻ የሚመጣ ዕድል አላችሁ" ሲሉም አክለዋል።
ተመራማሪዋ ኤሊ እንደሚናገሩት፤ አሜሪካ በኢራን ላይ ወታደራዊ እርምጃ መውሰዷ "ለቀጣናው ቀውስ በር የከፈተ" ነው። ኢራን አጸፋዊ ምላሽ መስጠቷም አይቀርም።
ሮያል ዩናይትድ ሰርቪስስ ኢንስቲትዩት በተባለው የዩናይትድ ኪንግደም ቲንክ ታንክ ተመራማሪ የሆኑት ኤች ኤ ሀይለር "ጥቃቱ የተፈጸመው [ኢራን] ጥቃት እንዳታደርስ አስቀድሞ ለመከላከል አይደለም" ይላሉ።
"ድርድር እየተካሄደ ሳለ ነው ጥቃቱ የተፈጸመው። የቀጣናው አሸማጋዮች ትኩረት ድርድሩ ላይ እንዲሆን ከተደረገ በኋላ ጥቃቱ ደርሷል" በማለትም ያስረዳሉ።
ከአደራዳሪዎቹ አንዱ የሆኑት የኦማን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፤ የኢራን እና አሜሪካ ንግግር ላይ ጉልህ መሻሻል መታየቱን በገለጹ በሰዓታት ውስጥ ነው ጥቃት የተፈጸመው።
የኦማን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር "የሰላም ስምምነት ላይ ለመድረስ ተቃርበናል። እዚያ ነጥብ ላይ ለመድረስ ለዲፕሎማሲ ዕድል መስጠት አለብን" ሲሉ ለሲቢኤስ ተናግረዋል።
ጥቃቱ ከተፈጸመ በኋላ ሚኒስትሩ "በጣም ደንግጫለሁ" ሲሉ በኤክስ ገጻቸው ጽፈዋል።
"ጥሩ እየሄደ የነበረው ድርድር ከስሟል። በዚህ ጥቃት አሜሪካም ዓለምም አይጠቀምም። በጥቃቱ ለሚጎዱ ንጹኃን እፀልያለሁ። አሜሪካ ከዚህ በላይ በጥቃቱ መቀጠል የለባትም። ጦርነቱ የአሜሪካ አይደለም" በማለትም ተናግረዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ቴህራን ያለችበት ሁኔታ
በኢራን ላይ የተሰረነዘው ጥቃት የአገሪቱ መሪዎች "የሕልውና አደጋ" ውስጥ እንዲወድቁ ያደረገ ነው።
ተመራማሪዋ ኤሊ እንደሚናገሩት፤ የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ የደኅንነት አደጋ ተደቅኖበታል። የሚያራምደው ዕሳቤ ቀጣይነትም አጠያያቂ ሆኗል።
የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ፤ የአገሪቱን ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ "ባለው ወታደራዊ አቅም" ራሳቸውን እንደሚከላከሉ ገልጸዋል።
ቴህራን ራሷን ለመከላከል የምታደርገው ጥረት "ከፍተኛ የኃይል እርምጃ እንድትወስድ" የሚያነሳሳ መሆኑን ኤሊ ያስረዳሉ።
ሌላኛው ተንታኝ ሀይለር በበኩላቸው "ኢራን እርምጃ የወሰደችበት ፍጥነት የተጋረጠባትን አደጋ ትልቅነት ያሳያል" ይላሉ።
ኢራን በአፋጣኝ የተቀናጀ እርምጃ በመውሰድ ራሷን በመከላከል ላይ ትገኛለች።
በአፋጣኝ እርምጃ መውሰድ ሁለት ጥቅም እንዳለው ባለሙያው ያስረዳሉ። አንደኛው ጦርነቱን ቀጣናዊ በማድረግ የአሜሪካን ወታደራዊ ሰፈሮች መጉዳት ነው።
ሁለተኛው ደግሞ አሜሪካ እና እስራኤል ላይ ጉዳት በማድረስ ጥቃት ከመፈጸም እንዲቆጠቡ ጫና ማሳደር ነው። ይህም የኢራን መንግሥት እንዳይወድቅ ሊያግዝ ይችላል።
በቻተም ሀውስ ቲንክ ታንክ የመካከለኛው ምሥራቅ እና ሰሜን አፍሪካ ጥናት ክፍል ዳይሬክተር ሳናም ቫኪል እንደሚሉት፤ የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ ራሱን ከውድቀት ለመታደግ እየሞከረ ነው።
"ራሱን በፍጥነት ከውድቀት ማዳን የሚችለው ጦርነቱን ቀጣናዊ በማድረግ ነው። ብዙ አገሮች መረጋጋት ሲርቃቸው ጦርነቱ በአጠቃላይ የመካከለኛው ምሥራቅ ይሆናል" ይላሉ አጥኚዋ።
'አክሲስ ኦፍ ሬዚስታንስ' በሚል የሚታወቁት የኢራን አጋሮች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተደጋጋሚ የጥቃት ሰለባ ቢሆኑም አቅማቸውን ማደራጀት እንደሚችሉ ተንታኞቹ ያስረዳሉ።
በእስራኤሉ ኢንስቲትዩት ፎር ናሽናል ሰኪውሪቲ ስተዲስ የሚሠሩት የኢራን ተመራማሪ ዳን ሲትኖዊዝ እንደሚሉት፤ በኢራን ላይ የሚርሰው ጥቃት በተራዘመ ቁጥር በቀጣናው ያሉ ታጣቂዎችም እርምጃ መውሰድ ይቀጥላሉ።
አሜሪካ እና እስራኤል አሁን ላይ ጥቃት ለመሰንዘር የወሰኑት የኢራን መንግሥት "ደካማ" ነው ብለው በማመናቸው እንደሆነ ያስረዳሉ።
የሁለቱ አገራት የተቀናጀ ጥቃት የኢራንን አስተዳደር በማዳከም የመንግሥት ለውጥ እንደሚያመጣም ያምናሉ።
የአሜሪካ እና እስራኤል ስሌት የተሳሳተ ከሆነ ግን ከፍተኛ ቀውስ እንደሚከተል ይገልጻሉ።
"አሁን እየተፈጸመ ያለው ጥቃት የኢራን መንግሥት እጅ እንዲሰጥ የሚያደርግ ላይሆን ይችላል። ከዚህ በኋላ የዲፕሎማሲ መንገድ መከተልም የሚቻል አይመስልም። ታዲያ እንዴት ስኬታማ መሆን ይችላል?" ይላሉ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ግጭቱ እንዴት ይቆማል?
ተንታኞቹ የሚስማሙበት ነጥብ የኢራን መንግሥት አጣብቂኝ ውስጥ መግባቱን ነው።
"ይህ ለአሜሪካ እና መካከለኛው ምሥራቅ የተራዘመ ጦርነት መነሻ ሊሆን ይችላል" ይላሉ ኤሊ።
"ትራምፕ የመንግሥት ለውጥ ለማምጣት የገቡበት ቢሆንም ረዥም እና ፈታኝ ጉዞ ይጠብቃቸዋል። ነገሮች የበለጠ ውስብስብ የሚሆኑበት ዕድል ሰፊ ነው።"
ሀይለር በበኩላቸው "ግጭቱ ለቀናት ወይም ሳምንታት ይቀጥላል። ኢራን የአጸፋ ምላሽ መስጠት ስትቀጥል የአገሪቱ መንግሥት ቀውስ ውስጥ መውደቁ አይቀርም" ሲሉ ያስረዳሉ።
ኢራውያን የመንግሥት ለውጥን "አዎንታዊ ውጤት" አድርገው ሊወስዱት ቢችሉም አገሪቱ ነውጥ ውስጥ ልትገባም ትችላለች።
ተንታኞቹ እንደሚሉት "ደም መፋሰሱ እንዲገታ" ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ኢራን እና አሜሪካ ወደ ዲፕሎማሲ እንዲመለሱ ጫና ማሳደሩን መቀጠል አለበት።













