የኢራን ከፍተኛ መሪዎችን ዒላማ ያደረጉት ጥቃቶች

ጠቅላይ መሪው ሃሜኒ እና ፕሬዝዳንቱ ፔዜሽኪያን
የምስሉ መግለጫ, የጥቃቶች ዋነኛ ዒላማ ሊሆኑ ይችላሉ የሚባሉት ጠቅላይ መሪው ሃሜኒ እና ፕሬዝዳንቱ ፔዜሽኪያን
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

የኢራን እስላማዊ ሪፐብሊክ ጠቅላይ መሪ አያቶላህ አሊ ኻሜኒ በእስራኤል እና በአሜሪካ በተከፈተው ጥቃት ዒላማ ከተደረጉት መካከል አንዱ መሆናቸውን ዘገባዎች እያመለከቱ ነው።

ከኢራን የሚወጡ ያልተረጋገጡ ዘገባዎች የተፈጸሙት ጥቃቶች በዋናነት ዒላማ ያደረጉት ጠቅላይ መሪውን ጨምሮ ሌሎች የአገሪቱ ከፍተኛ ፖለቲካዊ እና ወደታራዊ አዛዦች ላይ መሆኑን አመልክተዋል።

ጥቃቶቹ በአወዛጋቢዎቹ ወታደራዊ ተቋማት ላይ ሳይሆን በዋናነት በዋና ከተማዋ ቴህራን ማዕከላዊ ክፍሎች ውስጥ በሚገኙ ስፍራዎች ላይ ሲሆን፣ በሌሎች ከተሞችም ላይ ተፈጽሟል።

የኢራን መገናኛ ብዙኃን በአገሪቱ ፕሬዝዳንት ማሱድ ፔዜሽኪያን ጽህፈት ቤት ላይ ጥቃት መፈጸሙን አረጋግጠው፣ ፕሬዝዳንቱ ላይ ጉዳት አለመድረሱን ዘግበዋል።

የኢራን እስላማዊ ሪፐብሊክ የበላይ መሪ አያቶላህ አሊ ኻሜኒ ጥቃቱ ሲፈጸም ቴህራን ውስጥ እንዳልነበሩ እና ለደኅንነታቸው አስተማማኝ ከሆነ ስፍራ እንደሚገኙ አንድ ባለሥልጣን ለሮይተርስ ዜና ወኪል ተናግረዋል።

አሜሪካ በኢራን ላይ ወታደራዊ እርምጃ ለመውሰድ እየተዘጋጀች ባለበት በአሁኑ ሰዓት ጠቅላይ መሪው አያቶላህ አሊ ኻሜኒ እና ልጃቸው ዋነኛ ዒላማ ሊሆኑ እንደሚችሉ ተነግሯል።

አሜሪካ እና ኢራን ባካሄዷቸው ድርድሮች ከስምምነት አለማድረሳቸውን ተከትሎ አሜሪካ ወታደራዊ አማራጮችን እያጤነች መሆኑ በተነገረበት ባለፈው ሳምንት በተለያየ መጠን ጥቃት ለመፈጸም እየተዘጋጀች መሆኑ ተነግሮ ነበር።

የአየር ጥቃት በኢራን ላይ የሚፈጸም ከሆነ የአገሪቱ ከፍተኛ አመራሮች በተናጠል እና ቁልፍ ወታደራዊ ተቋማትን ዒላማ በማድረግ የመንግሥት ለውጥን ለማካሄድ ዕቅድ መውጣቱን የአሜሪካ ባለሥልጣናት ለሮይተርስ ተናግረው ነበር።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

አክሲዮስ የተባለው የአሜሪካ የዜና ድረገጽ እንደዘገበው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከመከላከያ ሚኒስቴር፣ ፔንታጎን አማካሪዎች የተለያዩ አማራጮች ቀርበውላቸዋል። ከእነዚህም መካከል የኢራን ጠቅላይ መሪን እና በዙሪያቸው ያሉ ቁልፍ ሰዎችን ዒላማ ማድረግ አንዱ እንደሆነ አመልክቷል።

አንድ አማካሪ ለድረ ገጹ እንደተናገሩት አንደኛው አማራጭ "አያቶላውን እና ወንድ ልጃቸውን እንዲሁም በዙሪያቸው ያሉ አመራሮችን ማስወገድ" ነው። የኻሜኒ ልጅ ሞጅታባ ዒላማ የሆነው የመሪነቱን ቦታ ሊረከብ የሚችል ቀጥተኛ ወራሽ ይሆናል ተብሎ ስለሚታሰብ ነው።

ሌላ ምንጭ በተመሳሳይ ለአክሲዮስ እንዳረጋገጠው ይህ አያቶላህ አሊ ኻሜኒን እና ልጃቸውን ዒላማ የማድረግ ሃሳብ ከበርካታ ሳምንታት በፊት አንስቶ የቀረበ ነው።

አንድ የፕሬዝዳንት ትራምፕ ከፍተኛ አማካሪ "ትራምፕ ያሉትን አማራጮች ክፍት አድርገዋቸዋል። በየትኛውም ሰዓት ጥቃት እንዲፈጸም ውሳኔ ሊያሳልፉ ይችላሉ" ሲሉ ተናግረዋል።

በአሁኑ ጥቃት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ዒላማ መደረጋቸው እየተነገረ ቢሆንም እስካሁን ስለደረሰው ጉዳት ከኢራን መንግሥት የተገለጸ ነገር የለም።

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት እና የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ባደረጉት ንግግር በኢራን ላይ የሚፈጸመው ጥቃት ለተከታታይ ቀናት የሚዘልቅ መሆኑን እያመለከቱ ነው።

ፕሬዝዳንት ትራምፕ ከዚህ በፊት ሲደጋግሙት እንደነበረው ኢራናውያን መሪዎቻቸውን በማስወገድ የመንግሥት ለውጥ እንዲያካሂዱ ጥሪ አቅርበዋል።

ባለፉት ዓመታት በአሜሪካ እና በእስራኤል የተፈጸሙ ጥቃቶች ከኒውክሌር እና ከሚሳዔል ማዕከላት ባሻገር የኢራን የኒውክርሌር ሳይንቲስቶች፣ ወደታራዊ እና ፖለቲካዊ መሪዎች ላይ የተነጣጠሩ ነበሩ።

ሰኔ ወር ላይ በተካሄደው የእስራኤል እና የኢራን የ12 ቀናት ጦርነት ጥቂት የማይባሉ ወታደራዊ እና ፖለቲካዊ ባለሥልጣናት መገደላቸው ይታወሳል።

አሜሪካም ሆነች እስራኤል ኢራን ውስጥ እግረኛ ወታደሮችን አሰማርተው መዋጋት እንደማይፈልጉ በተደጋጋሚ ከገለጹ በኋላ ዋነኛ ዒላማቸው የኢራን ሥርዓት የዕዝ ሰንሰለት መሆኑ ሲነገር ቆይቷል።

በዚህም የአየር እና የሚሳዔል ጥቃቶችን በመፈጸም የመንግሥቱን ቁልፍ አመራሮች በመምታት በኢራናውያን በራሳቸው ከውስጥ ለውጥ እንዲመጣ ዓላማ አላቸው።

ሃምሳ ዓመታት ለሚጠጋ ጊዜ ከኢራን እና ከአሜሪካ ጋር በጠላትነት የቆየው የኢራን እስላማዊ ሪፐብሊክ መሪዎች እና መንግሥት እንደ ከዚህ ቀደሞቹ አሁን የተከፈተባቸውን ዘመቻ ያልፉት ይሆን?