ከእስራኤል ጥቃት ቀደም ብለው ወደ ኢራን ሰርገው የገቡት የሞሳድ ሰላዮች ምን አደረጉ?

ላፕቶፕ ላይ የሳተላይም ምሥል የሚመለከት ሰው እና የእስራኤል ሰንደቅ ዓላማ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ከሳምንት በፊት እስራኤል በሌሊት ጥቃት በመፈጸም የጀመረችው ግጭት በቀላሉ የሚቋጭ አይመስልም። ሁለተኛ ሳምንቱን የያዘው የሁለቱ አገራት አገር አቋራጭ መጠቃቃት ጋብ ሳይል ቀጥሏል።

እስራኤል ከመጀመሪያው የኒውክሌር ማዕከላትን እና ወታደራዊ ተቋማትን ዒላማ በማድረግ ጥቃት እንደምትፈጽም ስትገልጽ፣ ኢራንም በረጅም ርቀት ሚሳዔሎች እና ድሮኖች በእስራኤል ላይ የአጸፋ ጥቃት እኣካሄድች ነው።

እስራኤል ከመሬት በታች የሚገኙ የኢራን የኒውክሌር ተቋማትን ለማውደም የአሜሪካንን ድጋፍ ስትጠይቅ ቆይታ እሁድ ማለዳ ላይ አሜሪካ ኢራን ውስጥ ጥቃት በመፈጸም ከእስራኤል ጎን መቆሟን በይፋ አሳውቃለች።

አሁን ቀጥሎ የሚከሰተው ከመካከለኛው ምሥራቅ እና ከባሕረ ሰላጤው ባሻገር ከፍተኛ ተጽእኖ የሚኖረው ቀውስ ምን ሊያስከትል ይችላል? የሚለውን ለማወቅ ዓለም በስጋት ጉዳዩን እየተከታተለ ነው።

ይህ እየተጠናከረ እና መልኩን እየቀየረ የመጣው የእስራኤል-ኢራን ግጭት ሰኔ 6/2017 ዓ.ም. ሲጀምር የእስራኤል የስለላ ተቋም ሞሳድ ሚናው ምን ነበር? ከጥቃቱ በፊትስ ኢራን ውስጥ ምን ሲያደርግ ነበር?

ኢራን ውስጥ የሰነበተው ሞሳድ

የኢራን ሕዝብ 90 ሚሊዮን ነው። የእስራኤል ሕዝብ 10 ሚሊዮን አይሞላም። በቆዳ ስፋትም እንዲሁ ናቸው። በወታደራዊ አቅም ምናልባት ተመጣጣኝ ሊባሉ ይችላሉ።

ያልተመጣጠኑት በስለላ ነው። ሞሳድ ልቆ ተገኝቷል። ዱካ የለውም፤ ጥላ ነው። ከኢራን ሳይንቲስቶች ጋር አብሮ ይራመዳል። ግን አይጨበጥም።

ከኢራን ጄነራሎች ጋር አብሮ ይታደማል፤ ግን አይተኮስበትም። ለኢራኖች መንፈስ ሆኖባቸዋል። አንዳንድ የኢራን ከፍተኛ ባለሥልጣናት የሌላቸው መረጃ ሞሳድ ሊኖረው ይችላል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ሞሳዶች የጦርነቱ መባቻ ላይ ወይም የግጭቱ ዋዜማ አይደለም የገቡት። ኢራን ነው የከረሙት። 'ሰርገው ገቡ' የሚለው አገላለጽም ልክ የሚኾነው በከፊል ነው።

ምክንያቱም ሞሳድ ዜግነት አለው እንዴ? የአገሬው ሰው መልምሎ ነው የራሱ የሚያደርገው። ምናልባት የአንድ አገር ምክትል መከላከያ ሚኒስትር የሞሳድ መኮንን ሊኾን ይችላል።

ምናልባት የኢራን ከፍተኛ የደኅንነት ኃላፊ የሞሳድ ተከፋይ ሊሆን ይችላል። ምሥጢሩ የሚወጣው ከዓመታት በኋላ ነው። ተቀብሮ ሊቀርም ይችላል።

የሞሳድ ሰላዮች ኢራን በስቅላት ቀጥታ የምትጨርሳቸው አይደሉም። ረቂቅ ናቸው።

በሮቦት ይታገዛሉ። ከእስራኤል ከለላ ያገኛሉ።

በቴህራን ታላቅ ሳይንቲስት በጠራራ ፀሐይ መኪና መንገድ ላይ ተገድሎ ሊገኝ ይችላል። ገድሎ የሚሸሽ የሞሳድ ሰላይ ግን አይታይም።

ድምጽም፣ ጠረንም፣ ዱካም የለም። ይህን ምን ይሉታል?

የሐማሱ የፖለቲካ መሪ ኢስማኤል ሐኒያ ለእርሱ በተዘጋጀለት ዘወትር በሚያርፍበት፣ ጥበቃው በተጠናከረበት እንግዳ ማረፊያው ውስጥ ሳለ ነበር ቴህራን ውስጥ የተገደለው።

ማን ገደለው? ዛሬም እንቆቅልሽ ነው።

እሱን ጨምሮ ጎምቱ የኢራን ሳይንቲስቶች ከዚህ ቀደም በተጠና መንገድ በሞሳድ ተገድለዋል።

ሞሳድ ቤቱ ቴላቪቭ አይደለም። ቤቱ ቴህራን ነው።

የሞሳድ መናኸሪያ ከቴል አቪቭ ይልቅ ቴህራን ነው።

ኢራን የሞሳድን ዋና መሥሪያ ቤት በቴል አቪቭ ከምትደበድብ ራሷን ብትደበድብ-ጉያዋን ብታጸዳ ይሻል ነበር የተባለው ለዚያ ይሆን?

ለመሆኑ ሞሳዶች በዚህ ግጭት የመጀመሪያ ቀናት ምን አሳኩ?

በአጭር ቀናት አስገራሚ ሥራ ሠርተዋል፤ ጥበባቸው ሲታይ ደራሲ ማሞ ውድነህ አላጋነኑም ያስብላል።

በሁለት ቀን ደርዘን የኒውክሌር ሳንቲስት እና ሌላ ሁለት ደርዘን ጄኔራል መግደል የትኛውም አገር የሚያሳካው ነገር አይደለም። በዓለም ጦርነቶች እንኳ ተሰምቶ አያውቅም።

የሞሳድ የስለላ መኮንኖች ሁለት ቁልፍ ተልዕኮ ነበር የተሰጣቸው።

የኒውክሌር እና ሚሳኤል ቀጠናዎችን መሰለል አንዱ ነው። የኢራን ከፍተኛ ወታደራዊ እና የኒውክሌር ሳንቲስቶችን ማምከን ሌላው ተልዕኮ ነው።

ሁለቱም ተሳክቶላቸዋል።

በኢራን ዋና ከተማ ቴህራን ውስጥ እስራኤል ጥቃት በፈጸመችበት ጊዜ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በኢራን ዋና ከተማ ቴህራን ውስጥ እስራኤል ጥቃት በፈጸመችበት ጊዜ

ለወራት የተደረገው ዝግጅት

ኔታንያሁ እንዳመኑት የኢራንን የኒውክሌር እና የሚሳኤል ፕሮግራሞችን አፈር ለማድረግ የወራት ዝግጀት ተደርጓል። ሰፊ ልምምድ ሲደረጉ ነበር።

በተለይም በመጨረሻዎቹ ሳምንታት ዝግጅቱ ወደ ከፍተኛ ደረጃ አድጎ ነበር። የሚጠበቀው ዶናልድ ትራምፕ እስኪፈቅዱት ብቻ ነበር።

ትራምፕ ኢራንን በ60 ቀናት ስምምነት ካልደረሳችሁ 'ውርድ ከራሴ' ሲሉ ቆይተዋል። 61ኛው ቀን ኔታንያሁ የልባቸው ሳይደርስ አልቀረም።

የቋመጡለትን ነገር ለማሳካት ከፍተኛ ጉጉት ነበራቸው። ኢራን ምናልባት ስምምነት ላይ ከደረሰች ትራምፕን ማሳመን ፈተና ይሆንባቸው ነበር።

ኢራን በዚህ ጊዜ 6ኛውን ዙር ድርድር ለማድረግ ዝግጅት ላይ ነበረች።

የኢራን አመራር በፍጹም በኦማን የሚደረገው ድርድር ሳይለይለት ኔታንያሁ ይደፍሩናል አላለም። ከፍተኛ መዘናጋት ነበር፤ ከአያቶላህ ጀምሮ፤ አማካሪዎቻቸውን ጨምሮ።

ትንሽ ድንጋጤ የገባቸው አሜሪካ ከባህሬን እና ከኩዌት የዲፕሎማት ቤተሰቦቻችን ማስወጣት ስትጀምር ነው።

አሜሪካ እና እስራኤል በነገታው ኢራን ላይ ስለሚደርሰው መብረቃዊ ጥቃት ሁሉን ጨርሰው ነበር።

የእስራኤል ፓይለች እና ሰላዮች በጥንቃቄ ያደረጉት ዝግጅት እና ለወራት የዘለቀው ልምምድ ፍሬ አፈራ። ኢራን ምንም ምልክት ማየት ያልቻለችውም ለዚሁ ነው።

በመጨረሻው ሰዓት ታዲያ የኢራን ከፍተኛ ጄነራሎች እሰራኤል ጥቃት ልትሰነዝር ትችላለች የሚለው ነገር አሳስቧቸው ስብሰባ ጠሩ።

የኢስላማዊ አብዮታዊ ዘብ የአየር ኃይል ጄነራሎች ናቸው።

ሁልጊዜም እንደሚያደርጉት 'የእስራኤል ነገር አይታወቅም' ብለው ከመሬት ሥር በተዘጋጀ የምድር ቤት መሰብሰቢያ አዳራሽ ገቡ።

ሞሳድ ግን ይህን ያውቅ ነበር። ቁልፍ ስብሰባዎች እዚህ ምድር ቤት እንደሚደረጉ መረጃ ነበረው።

ሁሉም ኮማንደሮች በአንድ ጊዜ ተገደሉ። የአየር እና የድሮን ስምሪት ዋና አዛዥ ይገኙበታል።

አንድ የኢራን ከፍተኛ መኮንን ለቢቢሲ ሲናገሩ "ሁሉም በአንዴ መገደላቸው ኢራን ፈጥኖ ምላሽ ለመስጠት አልቻለችም፤ ትዕዛዝ ማን ይስጥ? የዕዝ ሰንሰለቱ ከላይ ተቀነጠሰ'' ብለዋል።

እነዚህ ጄነራሎች በአንድ የምድር ቤት ቢሮ ለስብሰባ በተቀመጡበት መገደላቸው ነው ልዩ የሚያደርገው። ሌሎች ኮማንደሮች ደግሞ በቤታቸው ተገድለዋል።

ከቤተሰባቸው ጋር አገር ሰላም ብለው በተኙበት ተገድለዋል።

የኢራን አብዮታዊ ዘብ ዋና አዛዥ፣ የኢራን የአስቸኳይ ጊዜ ወታደራዊ አዛዥ እንዲሁም የእነዚህ ማዘዣ ዋና መሥሪያ ቤቶች ሁሉ በተቀናጀ ሁኔታ ከጥቅም ውጪ ተደርገዋል።

ከዚህ በኋላ ዋናው ተልዕኮ የኢራንን የአየር መቃወሚያ እና ራዳር ማምከን ነበር።

የእስራኤል ስለላ መሥሪያ ቤት እነዚህ መቃወሚያዎች የት እንደሚገኙ አጥንቶ ጨርሷል። ይህ መረጃ ለእስራኤል አየር ኃይል ተላልፎ ተሰጠ። ገና ከመነሻው እንዳልነበረ አደረጉት።

በዚህ የተነሳ ነበር የእስራኤል መከላከያ በኢራን ሰማይ ላይ እንዳሻው መምነሽነሽ የቻለው።

ከመሬት በታች ያለ የሚሳዔል ማከማቻ

የፎቶው ባለመብት, Tansim

የምስሉ መግለጫ, ኢራን በርካታ የኒውክሌር እና የሚሳዔል ማዕከላት ከመሬት በታች በተገነቡ ስፍራዎች እንዳሏት ይነገራል

የሞሳድ ቡድን በኢራን

የእሰራኤል አየር ኃይል ይህን ዘመቻ በሚፈጽምበት ቅጽበት የእሰራኤል ሰላዮች በሌላ ተግባር ተጠምደው ቆዩ። ይህም የቦሊስቲክ ሚሳዔል ማስተኮሻዎችን በጥንቃቄ ከጥቅም ውጪ ማድረግ ነበር።

ይህን ለማሳካት በመቶዎች የሚቆጠሩ የሞሳድ መኮንኖች ግማሾቹ በኢራን ቀሪዎቹ በቴል አቪቭ ቢሮ፣ የተቀናጀ ተሳትፎ አድርገዋል። በዚህ ተግባር ላይ በተለይ ለሞሳድ የሚሠሩ ኢራናዊያንን ብቻ የያዘች አንዲት የስለላ ቡድን ተሳትፋለች።

በማዕከላዊ ኢራን አንዲት የሞሳድ ኮማንዶ ጓድ ራሷን አሰናዳች። በዚህች ጓድ ሥር የሚገኙ የሞሳድ ኮማንዶዎች ኢራን ውስጥ በራሳቸው የሚመሩ የጦር መሳሪያዎችን ከምድር ወደ አየር የሚወነጨፉ የኢራን ሚሳዔሎች በተጠመዱባቸው ማስተኮሻዎች አቅራቢያ ተክለው ነበር።

ሞሳድ ከዚህ ሌላ ወደ ኢራን አስርጎ ያስገባቸው እና የርቀት መቆጣጠሪያ የተበጀላቸው ድሮኖችን ጠምዶ ሲጠባበቅ ነበር። ድሮኖቹ የገቡት ከዚህ ጦርነት በጣም ቀደም ብሎ ነው።

ጊዜውን በትክክል ለመናገር ከጉዳዩ ስሱነት የተነሳ የእሰራኤል የመረጃ ምንጮች ፍቃደኛ አይደሉም።

እነዚህን ድሮኖች ያጠመደበት መለስተኛ የዕዝ ጣቢያም ከፍቶ ነበር። አሜሪካ ሠራሽ ጄቶች ከዚህ ማዘዣ እየታገዙ በቀላሉ ዒላማቸውን መምታት ቻሉ።

ከሰማይ ተመትተን እንጣላለን የሚል ስጋት ሽው ሳይልባቸው ማለት ነው።

የኢራን አብዛኞቹ የአየር መቃወሚያዎች የተመቱት በጥቅምቱ ጥቃት ጊዜ ነው። በረዥም ርቀት ተመዘግዛጊ ሚሳዔሎች። የኢራን ኤስ 300 ሚሳዔል ሥርዓት ከጥቅም ውጪ የተደረገው ያኔ ነው።

በቅርብ ቀናት የእስራኤል አየር ኃይል ትኩረት ያደረገው ከመሬት በሚተከሉ ራዳር እና ማስተኮሻ (ላውንቸርስ) ላይ ነው።

ጥቃቱ ከመጀመሩ ቀደም ብሎ እስራኤል ይህን ሥርዓት ሽባ የሚያደርጉ የስለላ መኮንኖች አሰናድታ ነበር።

የሞሳድ መኮንኖች የተቀረውን የኢራን የሚሳኤል ሥርዓት ለማፍረክረክ ቀደም ብለው አስርገው ያስገቧቸው ድሮኖችን በጥቅም ላይ አውለዋል።

እስራኤል ጥቃት ስትጀምር፣ ድሮኖቹ ሥራቸውን እንዲጀምሩ እና ቴህራን አቅራቢያ ኢስፋጃባድ ወታደራዊ ጦር ሠፈር ወደሚገኙት ከምድር ወደ ምድር የሚወነጨፉ ሚሳዔሎች ወደተጠመዱባቸው ማስተኮሻዎች መወርወር ጀመሩ።

በዚህ ጥቃትም፣ ድሮኖቹ የኢራን ባልስቲክ ሚሳዔሎች ወደ እስራኤል ከመተኮሳቸው በፊት ሊያወድሟቸው ችለዋል። የእስራኤል መከላከያ ዝግጅት ያደረገው የከፋ ነገር ከኢራን ይገጥመኛል ብሎ ነው።

ምናልባት ኢራን ከ300 እስከ 500 ባለስቲክ ሚሳዔሎችን ልትተኩስ ትችላለች በሚል ነው ስሌቱ የተሠራው። ይህን አድርጋ ቢሆን ኢራን እስራኤል ላይ ተሰምቶ የማይታወቅ ጉዳት ታደርስ ነበር።

የሆነው ግን በተቃራነው ነው።

ኢራን በፍጥነት ምላሽ ለመስጠት አቅም አጣች። በብዙ ጥረት እና መደናበር ያውም ከሰዓታት በኋላ መቶ ድሮኖችን ወደ እስራኤል ተኮሰች። በቀላሉ ተመከቱ።

ከመጀመሪያው ጥቃት በኋላም የእስራኤል ጦር የኢራን ባለስቲክ ሚሳዔሎችን መደብደቡን ቀጠለበት። ይህም ኢራን አገግማ ጥቃት እንዳትሰነዝር አቅሟን ለማሽመድመድ ነበር።

"በርካታ ማስተኮሻዎች፣ ከምድር ወደ ምድር ተመዘግዛጊ ሚሳዔል ማከማቻዎች.፣ ተጨማሪ የወታደራዊ ቁሳቁሶች አውድመናል፤ በምዕራብ ኢራን አንድ የተለየ ማስተኮሻ በኮንቴይነር ውስጥ ተደብቆ አግኝተን አውድመነዋል" ብሏል የእስራኤል መከላከያ በሰጠው መግለጫ።

የኢራኑ ጠቅላይ መሪ አያቶላህ አሊ ኻሜኒ 'እስራኤል ዋጋዋን ታገኛለች' ብለው ለበቀል ዝተዋል።

ኢራን በእስራኤል ጥቃት ከተከፈተባት ዕለት አንስቶ በእስራኤል ላይ የአጸፋ ጥቃት እየፈጸመች ሲሆን፣ አሁን ደግሞ አሜሪካ በጥቃቱ ውስጥ መሳተፏ አገሪቱ መረር ወዳለ እርምጃ እንድትገባ ሊገፋት ይችላል ተብሎ ተሰግቷል።